የስፖርት ዘገባ | ስፖርት | DW | 22.08.2011
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ስፖርት

የስፖርት ዘገባ

በሳምንቱ መጨረሻ ላይ የተከናወኑ ዓበይት ስፖርታዊ ውድድሮች ላይ ዳሰሳ እናደርጋለን። የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግና የጀርመን ቡንደስ ሊጋ የእግር ኳስ ውጤቶች ቀዳሚውን ስፍራ ይይዛሉ። የሜዳ ቴኒስ እና የቢስክሌት ውድድሮችንም ቃኝተናል። ዝውውር ነክ መረጃዎችንም እናካፍላችኋለን።

default

የባየርኑ ሮበን እና የሀምቡርጉ ሶን ሁንግ ሚን

በእንግሊዝ በተከናወኑ የፕሪሚየር ሊግ የእግር ኳስ ግጥሚያዎች መድፈኞቹ በሊቨርፑሎች መድፍ ተቀጥቅጠዋል። የመድፈኞቹ አሰልጣኝ «እንዲያም ሆኖ ሁሉም ነገር ጨለመብን ማለት አይደለም» ሲሉ ተደምጠዋል። ዝርዝር ዘገባውን ከሌሎች የፕሬሚየር ሊግ ውጤቶች ጋር አያይዘን እናቀርባለን። በመጀመሪያ ግን የምንሻገረው ወደ ጀርመኑ ቡንደስ ሊጋ ውጤት ነው።

በጀርመኑ ቡንደስ ሊጋ የእግር ኳስ ፍልሚያ፤ ሃያሉ ባየር ሙኒክ እና ቬርደር ብሬመን በጎል ተንበሽብሸው ነው ሳምንቱን ያሳረጉት። ባየር ሙኒክ ሰሜን ጀርመን የሚገኘውን የሀምቡርግ የእግር ኳስ ቡድን የጎል ጎተራ አድርጎ ነው የሸኘው። በእሁዱ ግጥሚያ ሀምቡርጎች በባየር ሙኒክ 5 ለ ዜሮ ነበር የተቀጡት።

ለሙኒክ በ13ኛው ደቂቃ ላይ ዳኒኤል ቫን ቡይቴን የመጀመሪያዋን ግብ ከመረብ ካሳረፈ በኋላ ሀምቡርጎች የተረፋቸው ነገር ቢኖር በተከታታይ የወረደባቸውን የግብ ውርጅብ ማስተናገድ ብቻ ነበር። 2ኛዋን ግብ ፍራንክ ሪቤሪ በ17ኛው ደቂቃ ላይ፣ 3ኛዋን ግብ አርያን ሮበን በ34ኛው ደቂቃ፣ 4ኛዋን ግብ ማሪዮ ጎሜዝ በ56ኛው ደቂቃ ላይ እንዲሁም የማሳረጊያዋን እና የመጨረሻዋን ግብ ኢቪቻ ኦሊች በ80ኛው ደቂቃ ላይ ከመረብ አሳርፈዋል። ሀምቡርግ በ69 ሺህ ተመልካቾች ፊት እንዲያ 5 ለባዶ በሆነ ከባድ ሽንፈት ሲቀጣ የባየር ሙኒክ ደጋፊዎች በደስታ ሰክረው ነበር። ለባየር ሙኒኩ አሰልጣኝ ዩፕ ሀይንከስ ግን የእሁዱ ውጤት እምብዛም አርኪ የነበረ አይመስልም።

«5 ለ0 ማሸነፍ እና በልጠን መገኘታችን ብቻ አልነበረም፤ በቀጥታ ግብ ሊሆኑ ይችሉ የነበሩ ሁለት ግቦችን ስተን በግብ የመንበሽበሽ ዕድላችንንም አምክነናል። ምንም እንኳን በሁለተኛው አጋማሽ በልጠን ብንጫወትም ግብ ሊሆኑ የሚችሉ ዕድሎችን አግኝተን ግን አልተጠቀምንባቸውም። እንዲያም ሆኖ ግን ውጤቱ ረቡዕ ዕለት ከፊታችን ለሚጠብቀን ግጥሚያ ተጨማሪ ርምጃ ነው።»

እሁድ ዕለት በተከናወነ ሌላ ጨዋታ እንደ ባየር ሙኒክ በግብ የተንበሸበሸው ቬርደር ብሬመን ነበር። በርግጥ ተቀናቃኙ ፍራይቡርግ እንደሙኒኩ ተቀናቃኝ ሀምቡርግ ዝም ብሎ እጁን አልሰጠም ነበር። በብሬመን 5 ግቦች ቢቆጠሩበትም ፍራይቡርግ አፀፋውን ብሬመን ላይ 3 ግቦችን አስቆጥሯል። ሆፈንሀይም አውስቡርግን 2ለ0፤ ባየር ሌቨርኩሰን ሽቱትጋርትን 1 ለምንም ሲያሸንፉ ኮሎኝ ከካይዘርላውተርን ጋር 1 ለ 1 አቻ ተለያይቷል።

ከዚያው ከቡንደስ ሊጋ የእግር ኳስ ፍልሚያ ሳንወጣ፤ ቅዳሜ ዕለት በተደረጉ ውድድሮች ሄርታ ቤርሊንም እንደዛው ሀኖቨር ጋር 1 ለ 1 ነጥብ ተጋርቶ ወጥቷል። በሁለት ግቦች ሲመራ ቆይቶ ማምሻውን በድል ያጠናቀቀው ደግሞ ሻልካ ነበር። ተቀናቃኙ ማይንስ በአምስት ደቂቃዎች ውስጥ ነበር ሻልካ ላይ ሁለት ተከታታይ ግቦችን ያስቆጠረው። ሆኖም ሻልካ ከኋላ ተነስቶ ተከታታይ 4 ግቦችን በማስገባት ማይንስን በባዶ ነጥብ ሸኝቷል። እሁድ ቦሪሲያ ዶርትሙንድ ኑረንበርግን 2 ለ 0 አሸንፏል። ቀድሞ በኑረንበርግ ይጫወት የነበረው የዶርትሙንዱ ኢልካይ ጉንዶዋን፥

«ወደፊት ገፍቶ ለመጫወት ከብዶን ነበር። መጀመሪያ አካባቢ ላይ ኳሷን በሚገባ ተቆጣጥረን አልተጫወትንም። ከዚያም ብዙ ረዣዥም ኳሶችን ተጫወትን። ቢሆንም እንደማስበው ሁለተኛው አጋማሽ የተሻለ ነበር። ኳሷን በበላይነት ተቆጣጥረን በፍጥነት በመጫወታችን ዕድላችንን ተጠቅመንበታል።»

Bundesliga Borussia Dortmund vs. TSG 1899 Hoffenheim FLASH Galerie

የዶርትሙንዱ ግብ ጠባቂ ሮማን ኳሷን ሲያድን

አርብ ዕለት በተከናወነ ግጥሚያ ደግሞ ቦሩሲያ ሞንሼንግላድባህ ዎልፍስቡርግን 4 ለ 1 በሆነ ሰፊ ልዩነት ረቷል። በዚህም መሰረት ሞንሼንግላድባህ በ7 ነጥብ ሊጋውን እየመራ ይገኛል። ሀኖቨር በተመሳሳይ 7 ነጥብ በግብ ክፍያ ተበልጦ ሞንሼንግላድባህን ይከተላል። ባየር ሙኒክ ከሀኖቨር በ አንድ ነጥብ ዝቅ ብሎ በሶስተኛነት ደረጃ ላይ ይገኛል። ሻልካ በተመሳሳይ 6 ነጥብ ግን ደግሞ በጎል ልዩነት ከሙኒክ ዝቅ ብሎ በ4ኛ ደረጃን ይዟል። አሁንም በተመሳሳይ 6 ነጥብ ግን በጎል ክፍያ ልዩነት ብሬመን 5ኛ ሲሆን፤ 6ኛውን ደረጃ የያዘው ደግሞ ቦሩሲያ ዶርትሙንድ ነው። ኮሎኝ በአንድ ነጥብና በ9 የግብ ዕዳ የደረጃ ሰንጠረዡ የመጨረሻ ጠርዝ ላይ ተንጠላጥሎ ይገኛል።

ቅዳሜ ለት በተከናወኑ የቡንደስ ሊጋ ግጥሚያዎች ብሬመን ካይዘርስላውተርንን፤ እንዲሁም ሀኖቨር ሆፈንሀይምን 2 ለ ባዶ ሲያሰናብቱ፣ ሽቱት ጋርት ሻልካን 3ለ ምንም አሸንፏል። በተመሳሳይ ውጤት ዎልፍስቡርግ የቦን ከተማ አጎራባች የሆነውን የኮሎኝ ከተማ ቡድን ኮሎኝን ረትቷል። አውግስቡርግና ፍራይቡርግ 2 ለ2 አቻ ሲለያዩ፣ ኑረንበርግ ቤርሊንን 1 ለ ምንም አሸንፏል።

ከዛው ከእግር ኳስ ሳንወጣ አሁን የምንሸጋገረው ወደ እንግሊዝ ይሆናል። በፕሬሚየር ሊጉ ማን ዩናይትድን ጨምሮ ከጥቂት ቡድኖች በስተቀር በርካታ ቡድኖች ሁለተኛ ግጥሚያቸውን አከናውነዋል። ከዋነኞቹ ተፎካካሪዎች መካከል ቅዳሜ ዕለት ሊቨርፑል እና ቸልሲ ድል ቀንቷቸዋል። በተለይ ሊቨርፑል አርሰናልን በሜዳው 2 ለባዶ በሆነ ውጤት አሳፍሮታል። የሊቨርፑሉ አሰልጣኝ ባሳለፍነው ሳምንት ነጥብ ተጋርተው ሲወጡ ለደጋፊዎቻቸው «ግድ የለም ትንሽ ታገሱኝ» ማለታቸው ይታወሳል። እንዳሉትም ሳምንት ሳያሳልፉ በዋነኛ ተቀናቃኛቸው አርሴናል ላይ ድልን ተቀዳጅተዋል።

የአርሰናሉ አሰልጣኝ አርሰን ቬንገር የቅዳሜውን ሽንፈት አስመልክቶ «እንዲያም ሆኖ ሁሉም ነገር ጨለመብን ማለት ግን አይደለም» ሲሉ ለደጋፊዎቻቸው በጋዜጠኞች በኩል የማፅናኛ ቃል ልከዋል። ሊቨርፑል የመጀመሪያዋን ግብ ያገኘው ኢግናሲ ሚኩዌል አወጣለሁ ብሎ የመታት ኳስ የአርሰናሉ አሮን ራምሴይ ደረት ላይ ነጥራ መረብ በመንካቷ ነበር። በዚያች ግብም 78ኛው ደቂቃ ላይ ቀያዮቹ መድፈኞቹን በሜዳቸው ኢሚሬትስ ስታዲየም ላይ ኩም አድርገዋቸዋል።

በነገራችን ላይ ግቧ የተቆጠረችው የአርሴናሉ የ19 ዓመቱ ወጣት በሁለት ቢጫ ካርድ ከሜዳ ከተባረረ ብዙም ሳይቆይ ነበር። ኢማኑኤል ፍሪምፖንግ በቀይ ከሜዳ ሲሰናበት አሰልጣኙ አርሴን ቬንገር ወደ መሬት አቀርቅረው ፀጉራቸውን በንዴት ሲያፍተለትሉ ታይተዋል። ሆኖም በቃለ-ምልልስ ወቅት ኢማኑኤል ልምድ ስለሌለው ነው በሚል ጥፋቱን ሳያከብዱ አልፈውታል። ለሊቨርፑል 2ኛዋን ግብ ያስቆጠረው ሉዊስ ሱዋሬዝ ነበር። ሊቨርፑሎች ሁለተኛዋን ግብ ውብ በሆነ ቅብብል በተረጋጋ መንፈስ ነበር ከመረብ ያሳረፏት። ሱዋሬዝ ከጨዋታ ውጪ ነው ሲሉ የአርሰናሉን አሰልጣን ጨምሮ በርካቶች ተከራክረዋል።

መድፈኞቹ በመጀመሪያዎቹ ሁለት ግጥሚያዎች ውጤት ማስጠበቅ ሲሳናቸው ይህ ከ42 ዓመታት በኋላ የመጀመሪያው መሆኑ ነው። ልክ የሊቢያው መሪ ሙዓመር ቃዛፊ ከ42 ዓመታት አምባገነናዊ አገዛዝ በኋላ ውጤት ማስጠበቅ እንደተሳናቸው ማለት ነው። ወጣም ወረደ ሊቨርፑል 3 ነጥብ ይዞ ወደ ቤቱ ሲመለስ፤ አርሰናል በሜዳው ነጥብ ሊጥል ግድ ሆኖበታል።

ቅዳሜ በተደረጉ ሌሎች ግጥሚያዎች አስቶን ቪላ ብላክ በርን ሮቨርስን 3 ለ 1፣ ቸልሲ ዌስት ብሮሚች አልቢዮንን 2 ለ 1፣ ሬንጀርስ ኤቨርተንን 1 ለዜሮ፣ ኒው ካስል ዩናይትድ ሰንደርላንድን 1 ለ ለባዶ አሸንፈዋል። ስዋንሲ ስሲቲ እና ዊጋን አትሌቲክ ባዶ ለባዶ ተለያይተዋል። እሁድ ዕለት በተደረጉ ጨዋታዎች ደግሞ፤ ማንቸስተር ሲቲ ቦልተን ዋንደረርስን 3 ለ 2 አሸንፏል። ዎልፈርሀምፕተን ፉልሀምን 2 ለ ዜሮ ሸኝቷል። ስቶክ ሲቲ ከኖርዊች ሲቲ 1 ለ 1 አቻ ተለያይተዋል።

የፕሬሚየር ሊግ የደረጃ ሰንጠረዡን ማንቸስተር ሲቲ በ6 ነጥብ እና በግብ ክፍያ ልዩነት ከዎልፈርሀምፕተን ዋንደረረስ በልጦ በ1ኛንት ይመራል። አስቶን ቪላ እና ሊቨርፑል ከዎልፈርሀምፕተን ዋንደረረስ በሁለት ነጥብ ዝቅ ብለው በ4 ነጥብ ሶስተኛ ደረጃ ላይ ይገኛሉ። ቼልሲ በተመሳሳይ 4 ነጥብ ግን በግብ ክፍያ ልዩነት ተበልጦ አምስተኛ ደረጃን ይዟል። አንድ ተስተካካይ ጨዋታ የሚቀረው ማንቸስተር ዩናይትድ ዛሬ ከቶትንሀም ሆትስፐር ጋር ይገጥማል። ማን ዩናይትድ ካሸነፈ ሊቨርፑልን እና አስቶን ቪላን በልጦ 3ኛ ደረጃን ይቀዳጃል። ከተሸነፈ ባለበት 8ኛ ደረጃ ላይ ይቆያል ማለት ነው። እንግዲህ የማን ዩናይትድ ደረጃ መደበኛው ስርጭታችን ዛሬ እንደተደመደመ በሚጀምረው ግጥሚያ የሚወሰን ይሆናል።

Tennis Wimbledon Novak Djokovic Petra Kvitova NO FLASH

ዝነኛው ኖቫክ ጃኮቪች እና ፔትራ ክቪቶቫ

በፕሬሚየር ሊጉና በቡንደስ ሊጋው የተሰሙ አንዳንድ ዝውውር ነክ ዜናዎችን ይዘናል ከቀጣዩ የቢስኪሌት እና የሜዳ ቴኒስ አጠር ያለ ውጤት በኋላ እናስደምጣለን።

ቴኒስ

ሩሲያዊቷ ማሪያ ሻራፖቫ ሰርቢያዊቷ ዬሌና ያንኮቪችን 7ለ6 እና 6ለ3 በሆነ ውጤት እሁድ ዕለት አሸንፋታለች። ተቀናቃኟ ያንኮቪች ከሶስቱ ዙር አንደኛውን ብቻ 6ለ4 ልታሸንፍ ችላለች፤ በጥቅል ውጤቱ ግን አሸናፊዋ ሩሲያዊቷ ሆናለች። በወንዶች የሜዳ ቴኒስ ውድድር የዓለማችን ቁጥር አንድ ኖቫክ ጆኮቪች በ71ኛው ደቂቃ ላይ ጨዋታውን መቀጠል ባለመቻሉ ሊያቋርጥ ተገዷል። በዚህም መሰረት አንዲ ሙራይ ኖቫክ ጆኮቪችን 6ለ4 እና ባልተጠናቀቀው 3 ለ0 ውጤት አሸንፏል። ጆኮቪች ጨዋታውን ሳይጨምር ከሜዳ የወጣው ትከሻው ላይ በደረሰበት ጉዳት እንደሆነ ገልጿል።

ቢስክሌት

ኖርዌጃዊው የ24 ዓመቱ ወጣት እሁድ ስፔን ላይ የተከናወነውን የኤኔኮ ቶር አሸነፈ። ኤድቫልድ ባሶን በሁለተኛነት ጀርመናዊውን ጌራልድ ሲዮሌክ ነበር ያስከተለው። ጌራልድ በኤድቫልድ ለጥቂት በመቀደሙ በብስጭት የቢስኪሌቱን መሪ ሲደበድብ በቴሌቪዥን በተላለፈው እሽቅድምድም ታይቷል። ጀርመናዊው ጌራልድ ከዛሬ 4 ዓመታት እና ሁለት ዓመታት በፊት በሰከንዶች ልዩነት ሶስተኛ ወጥቶ እንደነበር ይታወቃል። ጀርመን የዛሬ 10 ዓመታት ግድም በኢሪክ ዛቤል አሸናፊ ከሆነች ወዲህ የትናንቱ የጌራልድ ለጥቂት ሁለተኛ መውጣት ለዳግማዊ ድሉ ሊታጣ የማይገባው አጋጣሚ ተብሎ ተነግሮለታል።

አሁን ቀደም ሲል ቃል የገባነውን ዝውውር ነክ ዜና እናሰማለን። የስፔኑ ታላቅ ቡድን ቫሌንሺያ አጥቂው ጁዋን ማታን ለፕሬሚየር ሊጉ ቸልሲ ሊሸጥ እንደሆነ አስታወቀ። የ23 ዓመቱ ስፔናዊ አጥቂን በእጁ ለማስገባት ቼልሲ 28 ሚሊዮን ዩሮ ገደማ እንደሚያወጣ ተዘግቧል። በግራ በኩል አጥቂ የሆነው ማታ ከሪያል ማድሪድ ወደ ቫሌንሺያ የተዛወረው ከ4 ዓመታት በፊት ነበር። ጁዋን ማታ ባለፈው ዓመት ደቡብ አፍሪቃ ላይ የዓለም ዋንጫ ባለቤት የሆነው የስፔን ቡድን ውስጥ ተሰላፊ ነበር። ቫሌንሺያ በደረሰበት የገንዘብ ቀውስ በሁለት ዓመታት ውስጥ ብቻ ምርጥ ምርጥ ተጫዋቾቹን ለመሸጥ ሲገደድ ጁዋን ማታ አምስተኛው ተጫዋች ሆኖ ተመዝግቧል። እስካሁን ቡድኑ ራውል አልቢዮን፣ ካርሎስ ማርቼናን፣ ዳቪድ ሲልቫን እና ዳቪድ ቪላን ለመሸጥ ተገዷል። በእርግጥ ከነዚህ 5 ተቻዋቾች ቫሌንሺያ ከ100 ሚሊዮን ብር በላይ አፍሶበታል።

በሌላ የዝውውር ዜና ደግሞ በጀርመን ቡንደስ ሊጋ ውስጥ ለሻልካ የሚጫወተው ሌላኛው ስፔናዊ አጥቂ ራውል በሻልካ መቆየት እንደሚፈልግ ገለፀ። ራውል ልጄና ባለቤቴ ከጀርመን ማኋበረሰብ ጋር ከመላመድ አልፈው ስለተዋሀዱ ጀርመንን መልቀቅ ይከብደናል ብሏል። ራውል ወደ እንግሊዙ ፕሬሚየር ሊግ አቅንቶ ብላክ በርን ሮቨርስን ሊቀላቀል ነው የሚል ወሬ ሲናፈስ ቆይቷል።

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ነጋሽ መሀመድ

Audios and videos on the topic