1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የስፖርት ዘገባ

ሰኞ፣ ሐምሌ 11 2003

በዚህ በጀርመን ለሶሥት ሣምንታት ሲካሄድ የሰነበተው የሴቶች የዓለም እግር ኳስ ዋንጫ ፍጻሜ ውድድር ባለፈው ምሽት በጃፓን አሸናፊነት ተፈጽሟል።

https://p.dw.com/p/RaU4
ምስል dapd

“በስታዲዮሞች ውስጥ የነበረው መንፈስ ግሩም ነበር። በቴሌቪዥንና በመገናኛ ዘዴዎች ዘንድ ከጠበቅነው በላይ ትኩረት አግኝተናል። ሁሉም ግሩም ግምት የሚሰጠው ነው”

የጀርመን የዓለም ዋንጫ አዘጋጅ ኮሚቴ ፕሬዚደንት ሽቴፊ ጆንስ ነበረች።

ስድሥተኛው የሴቶች የዓለም እግር ኳስ ዋንጫ ፍጻሜ ውድድር ባለፈው ምሽት ፍራንክፉርት ከተማ ውስጥ በጃፓንና በዩ.ኤስ.አሜሪካ መካከል በተካሄደ ግሩም የፍጻሜ ግጥሚያ ተጠናቋል። ሃምሣ ሺህ ገደማ የሚጠጋ ተመልካች በተገኘበት ስታዲዮም በሰዓት ጭማሪና ከዚያም ከ 120 ደቂቃዎች በኋላ በፍጹም ቅጣት ምት በለየለት ግጥሚያ ጃፓን 5-3 ስታሸንፍ አገሪቱ ለዓለም ዋንጫ ባለቤትነት ስትበቃም ለመጀመሪያ ጊዜ መሆኑ ነው። ታዲያ ጃፓንን ሊነጋጋ ሲል ያጥለቀለቀው ደስታ በአገሪቱ ለአንድ አፍታም ቢሆን በነውጽና በማዕበል የደረሰው ጥፋት እንዲረሳ ማድረጉ አልቀረም። አትሞ ...
የጃፓን ብሄራዊ ቡድን ለፍጻሜ የደረሰው በሩብ ፍጻሜው አስተናጋጇን ጀርመንንና በግማሽ ፍጻሜውም ጠንካራውን የስዊድንን ቡድን በማሸነፍ እንደነበር ይታወሣል። ከባድ መሰናክሎችን ማለፍ ነበረበት። በመሆኑም የቡድኑ አምበል ሆማሬ ሣዋ ከትናንቱ የፍጻሜ ጨዋታ በኋላ እንዲህ ነበር ደስታዋን የገለጸችው።

“ሁላችንም እስከመጨረሻው በራሳችን በመተማመን ነበር የታገልነው። በዚህም በጣም ደስተኞች ነን። እናም አሁን የዓለም አንደኛ ለመሆን በቅተናል”

ወደ ጨዋታው ልመለስና ጃፓንና አሜሪካ መደበኛውን ዘጠና ደቂቃ 1-1 ሲጨርሱ አሜሪካ በተጨማሪው ሰዓት የመጀመሪያ አጋማሽ 2-1 በማድረግ ለድል የቀረበች መስላ ታይታ ነበር። ሆኖም በቴክኒክ የረቀቁት የጃፓን ተጫዋቾች ተሥፋ ሳይቆርጡ በመታገል በ 117ኛው ደቂቃ ላይ ውጤቱን መልሰው ያስተካክላሉ። እንዲህ እያለ ነበር ወደ ፍጹም ቅጣት ምት ውሣኔ የተደረሰው። የዶቼ ቬለ የጀርመንኛ ፕሮግራም የስፖርት ክፍል ባልደረባ ስቴፋን ኔስትለር እንደገለጸው በጥቅሉ ምንም እንኳ የአሜሪካ ቡድን ይበልጥ የጠነከረው ቢሆንም ጃፓን ደግሞ ካሳየችው የጨዋታ ብቃት አንጻር ዋንጫውን ማግኘቱ የሚገባት ነው።

“ጃፓን የዓለም ሻምፒዮን ለመሆን መብቃቷ ይገባታል። በታክቲክና በዲሲፕሊን የሰከነ፤ በቴክኒክም እንዲሁ ጠንካራ የሆነ ቡድን ነው ያየነው። ዕውነቱን ለመናገር በሌላ በኩል የፍጻሜውን ግጥሚያ 120 ደቂቃዎች መለስ ብለን ከተመለከትን የአሜሪካ ቡድን የተሻለው ነበር። ሆኖም ተጫዋቾቹ በጊዜው ጎል ማግባቱን ዘንግተውታል። ጃፓኖች በአንጻሩ በሚያስደንቅ ሞራል በመታገል እስከ ፍጹም ቅጣት ምቱ ሲደርሱ እዚያም ቢሆን የተሻለ ነርቭ ነው ያሣዩት”

የጃፓን ብሄራዊ ቡድን በተለይ በአጭር ቅብብል አጨዋወት ብቃቱ ብዙዎች የስፓኝን ወይም የብራዚልን የወንዶች አጨዋወት እንዲያስታውሱ ነው ያደረገው። እርግጥ የአሜሪካ ቡድን ነበር የዋንጫ ባለቤት ይሆናል የሚል የላቀ ዕድል ተሰጥቶት ሜዳ የገባው። ግን እንደታሰበው አልሆነለትም። በመጀመሪያዎቹ 15 ደቂቃዎች ብቻ እንኳ ምናልባትም ወሣኝ የነበሩ ብዙ ጎሎች ተስተዋል።

“አንድ ቡድን በጣም ሃያል ሆኖ ሳለ ጎሎች ማግባቱን ከረሣ አብዛኛውን ጊዜ በጥፋቱ መቀጣቱ ያለ ነው። ከኋላ ተከላካዮቹ ጥቂት ስህተት ከሰሩ ድንገት ጎል ይቆጠርብታል። የሆነውም በትክክል ይሄው ነው። የጃፓን ተጫዋቾች ለረጅም ጊዜ ተቆጥበው ከቆዩ በኋላ ጥቂት ዕድላቸውን በመጠቀም በአስፈላጊው ወቅት ጎል ማስቆጠር ችለዋል። ቀደምት ቡድኖች የሚጫወቱት እንግዲህ እንዲህ ነው”

በዘንድሮው የዓለም ዋንጫ ውድድር ቀድሞ ከሩብ ፍጻሜ አልፋ የማታውቀው ጃፓን ለዋንጫ ትበቃለች ብሎ ያሰበ ማንም አልነበረም። ሃያልነታቸው በሰፊው የተነገረላቸውና ለፍጻሜ ድል የተጠበቁት አስተናጋጇ ጀርመን፣ ብራዚል፣ ኖርዌይ ወይም ስዊድን ነበሩ። ግን የመጀመሪያዎቹ ሶሥቱ ከሩብ ፍጻሜው ባሻገር እንኳ ሊዘልቁ አልቻሉም። ጃፓን ለምሳሌ በሩብ ፍጻሜው የሁለት ጊዜዋን የዋንጫ ባለቤት ጀርመንን፤ በግማሽ ፍጻሜውም ስዊድንን በማስወጣት ነበር መንገዷን ያመቻቸችው። የሃይል ሚዛኑ መቀያየር ሲታይ ምናልባትም የሴቶች እግር ኳስ ከአውሮፓና ከአሜሪካ ውጭ በሌሎች አካባቢዎች እያደገ መምጣቱ ሣይሆን አልቀረም። ይህ የዶቼ ቬለው የስፖርት ፕሮግራም ባለደረባ የስቴፋን ኔስትለርም ዕምነት ነው።

ዓለም በሴቶች እግር ኳስ ዕርምጃም በጣሙን እየተቀራረበ ያለ ይመስለኛል። ይህ ደግሞ የዋንጫ ተሥፋ የተጣለባቸው አገሮች በሩብ ፍጻሜው ቀድመው በመሰናበታቸው ብቻ አይደለም። በመጀመሪያው የምድብ ዙርም ለምሳሌ ኤኩዋቶሪያል ጊኒን ወይም ኮሉምቢያን የመሳሰሉትን ብንመለከት ቀድመው ወደ አገር ይመለሱ እንጂ ግሩም የአግር ኳስ አጨዋወት ነው ያሳዩት። እንዲያው እንደቀድሞው በቀላሉ 5-0 ወይም 6-0 የሚሸኙ አልነበሩም። በአቅም እየተቀራረቡ መምጣታቸው የሚታይ ነው። እንግዲህ ያለ ብዙ ትግል በቀላሉ የዓለም ሻምፒዮን የሚኮንበት ጊዜ አልፏል”

ለማንኛውም ጀርመን ለሶሥተኛ ጊዜ በአገር ውስጥ የዓለም ዋንጫ ባለቤት መሆኑ ባይሳካላትም ዝግጅትና መስተንግዶዋ ግን “የዓለም ሻምፒዮን” የሚያሰኛት ነው ቢባል ማጋነን አይሆንም። በስምንት ስታዲዮሞች ሲካሄዱ የቆዩት ግጥሚያዎች በጥሩ ሁኔታ ሲጎበኙ ትናንት በፍጻሜው ግጥሚያ 50 ሺህ ገደማ የሚጠጋ ተመልካች በስታዲዮም መገኘቱም ትልቅ ዕርምጃ ነው። ታዲያ ይህ በቅርብ ለሴቶች እግር ኳስ ዝና ማደግ አስተዋጽኦ ያደርግ ይሆን?

“እኔ በመጠኑም ቢሆን እጠራጠራለሁ። በዚህ በጀርመን እርግጥ የሴቶቹ ብሄራዊ ቡድን ጥሩ ዝና አለው። በሚጫወትበት ጊዜ ስታዲዮሞች በተመልካች ይሞላሉ። ግን ችግሩ የሚታየው አሁን መደበኛው የሴቶች ቡንደስሊጋ ውድድር ሲጀምር ነው። ባለፈው ዓመት በአማካይ ጨዋታዎችን ለማየት ስታዲዮም የሚገባው ተመልካች ከ 800 አይበልጥም ነበር። ይህ ደግሞ በጣም ዝቅተኛ ነው። እንግዲህ በዚህ ረገድ ዕድገት መኖሩ እያደር የሚታይ ይሆናል። በበኩሌ ግን ሃቁን ለመናገር ለውጥ በመኖሩ ተጠራጣሪ ነኝ። እርግጠኛ አይደለሁም”

ያም ሆነ ይህ ስድሥተኛው የሴቶች የዓለም እግር ኳስ ዋንጫ ውድድር የደመቀና በዝግጅት ረገድም የተሳካ ሆኖ አልፏል። በነገራችን ላይ ባለፈው ቅዳሜ ለሶሥተኝ’ነት በተካሄደው ግጥሚያ ስዊድን ፈረንሣይን 2-1 በመርታት የናስ ሜዳሊያ ተሸላሚ ለመሆን በቅታ ነበር።

በእግር ኳሱ ዓለም እንቀጥልና በላቲን አሜሪካ ዋንጫ ኮፓ-አሜሪካ ውድድር ደግሞ የተለመደው የሃይል አሰላለፍ ከባድ ዝቤት ደርሶበታል። አስተናጋጇ አርጄንቲና ባለፈው ቅዳሜ ከኡሩጉዋይ ጋር ባደረገችው ግጥሚያ በሩብ ፍጻሜው ተሸንፋ ከውድድሩ ስትወጣ ብራዚልም ትናንት ተመሳሳይ ጽዋ ገጥሟታል። ብራዚልና አርጄንቲና ባለፉት ሁለት ዓመታት በተከታታይ በኮፓ-አሜሪካ ፍጻሜ ሲገናኙ ብራዚል ባለድሏ እንደነበረች ይታወሣል። ይህ አሁን ታሪክ ሲሆን ብራዚል በፓራጉዋይ 2-0 ተሸንፋ የወጣችው በፍጹም ቅጣት ምት ንጽጽር ነው። ቬኔዙዌላም ቺሌን 2-1 ረትታለች። በግማሽ ፍጻሜ ኡሩጉዋይ ከፔሩ የምትገናኝ ሲሆን ፓራጉዋይ ደግሞ የቬኔዙዌላ ተጋጣሚ ናት።

አትሌቲክስ

ናይሮቢ ላይ ሰንበቱን የተካሄደው ብሄራዊ የአትሌቲክስ ሻምፒዮና ውድድር አገሪቱ በፊታችን ነሐሴ ወር ደቡብ ኮሪያ-ዴጉ ላይ ለሚካሄደው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ተወዳሪዎቿን እንድትመርጥ መለኪያ ሆኗል። በመካከለኛና ረጅም ርቀት ለኢትዮጵያ አትሌቶች ብርቱ ተፎካካሪ እንደሚሆኑ የሚጠበቁት ሴቶችና ወንድ ተወዳዳሪዎች ከሞላ ጎደል በሙሉ ማጣሪያውን አልፈዋል። በወንዶች በአምሥት ሺህ ሜትር ኢሣያክ ኮች ሲያሸንፍ በአሥር ሺህ ሜትር ደግሞ ፒተር ኪሩዊ ቀዳሚ ሆኗል። በሶሥት ሺህ ሜትር መሰናክል ብሪሚን ኪፕሩቶ ሲያሸንፍ በዓለም ሻምፒዮናው በነዚህ ርቀቶች አገሪቱን እንዲወክሉ በጠቅላላው 11 አትሌቶች ተሰይመዋል። በሴቶችም በተመሳሳይ ርቀቶች ከሚሳተፉት መካከል ቪቪያን ቼሩዮት፣ ሊኔት ማሣይ፣ ሜርሢይ ቼሮኖና ሤሊይ ኪፕየጎ ጥቂቶቹ ናቸው።

ቴኒስ

በትናንትናው ዕለት በዚህ በጀርመን በሽቱትጋርት ከተማ በተካሄደ ዓለምአቀፍ የቴኒስ ግጥሚያ የቀድሞው የዓለም አንደኛ የስፓኙ ተወላጅ ሁዋን-ካርሎስ-ፌሬሮ የአገሩን ልጅ ፓብሎ አንዱሃርን 6-4, 6-0 በማሸነፍ ለድል በቅቷል። ፌሬሮ በጉልበት ጉዳት የተነሣ በማዕረግ ማቆልቆሉ የሚታወቅ ነው። በኢጣሊያ-ፓሌርሞ ፍጻሜ ግጥሚያም የስፓኟ አናቤል ሜዲና የስሎቬኒያ ተጋጣሚዋን ፖሎና ሄርሲግን 6-3, 6-2 በመርታት ለአምሥተኛ ድሏ በቅታለች። በስዊድን-ኦፕን ደግሞ የአገሩ ተወላጅ ሮቢን ሶደርሊንግ የስፓኙን ዴቪድ ፌሬርን በቀላሉ 6-2, 6-2 አሸንፋል። ከዚሁ ሌላ ትናንት ጃፓን ውስጥ የመጪው 2012 ዓ.ም. የቴኒስ ፌደሬሺን-ካፕ የመጀመሪያ ዙር ዕጣ ሲወጣ ዋና ዋናዎቹ ሩሢያ ከስፓኝ’፤ ጀርመን ከቼክ ሬፑብሊክ፤ ቤልጂግ ከሰርቢያ፤ እንዲሁም ዩ.ኤስ.አሜሪካ ከቤላሩስ ናቸው።

መሥፍን መኮንን

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ