የስፖርት ዘገባ | ስፖርት | DW | 20.06.2011
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ስፖርት

የስፖርት ዘገባ

የዓለም እግር ኳስ ፌደሬሺኖች ማሕበር የፊፋ የሴቶች የዓለም ዋንጫ ውድድር በዚህ በጀርመን በፊታችን ዕሑድ ይከፈታል።

default

የፊፋ የሴቶች የዓለም ዋንጫ ውድድር በሴቶች እግር ኳስ ስፖርት ውስጥ ታላቅ ዕውቅና የሚሰጠው ዋናው ውድድር ነው። በየአራት ዓመቱ አንዴ የሚካሄደው የፊፋ የሴቶች የዓለም ዋንጫ ለመጀመሪያ ጊዜ የተካሄደው እ.ጎ.አ. በ 1991 ከሃያ ዓመታት በፊት ነበር። ይህም ለንጽጽር ያህል የወንዶች የዓለም ዋንጫ ከተጀመረ ከ 60 ዓመታት በኋላ መሆኑ ነው። የሴቶቹ የዓለም ዋንጫ ውድድር ምንም እንኳ የወንዶቹን ያህል ሰፊ ተመልካች ባይስብም ሃሣቡን የጸነሱት የጊዜው የፊፋ ፕሬዚደንት ጆአኦ ሃቫላንዥ ነበሩ። የመጀመሪያው ውድድር ቻይና ውስጥ ሲካሄድ ዩ.ኤስ.አሜሪካ ኖርዌይን በፍጻሜው ግጥሚያ 2-1 አሸንፋ ዋንጫውን ትወስዳለች። ሁለተኛው ውድድር ደግሞ እንደ ቻይናው ሁሉ 12 ቡድኖች በተሳተፉበት በ 1995 ስዊድን ውስጥ ሲካሄድ የዋንጫ ባለቤት ለመሆን የበቃችው ኖርዌይ ነበረች።

ዩ.ኤስ.አሜሪካ አራት ዓመታት ዘግየት ብላ ሶሥተኛውን ውድድር ስታዘጋጅ ዋንጫውንም በዚያው ለማስቀረት ትበቃለች። ቀጣዩ የ 2003 የሴቶች የዓለም ዋንጫ ውድድርም በቻይና የሣርስ በሽታ መስፋፋቱ ባስከተለው ስጋት የተነሣ ወደ አሜሪካ እንዲሸጋሸግ ይደረጋል። ዋንጫውን የወሰደችው ግን ጀርመን ነበረች። ቻይና የዛሬ አራት ዓመት በ 2007 ያለፈውን የዓለም ዋንጫ ውድድር ስታስተናግድ አሁንም ጀርመን ለሁለተኛ ጊዜ የዋንጫ ባለቤት ትሆናለች። የጀርመን የሴቶች ብሄራዊ ቡድን ብራዚልን፣ ኖርዌይንና አሜሪካን ከመሳሰሉት ጠንካራ ቡድኖች አንዱ ሲሆን እንደ አስተናጋጅ አገር ለሶሥተኛ ጊዜ የዋንጫ ባለሬት ለመሆን የተጣለው ተሥፋ እጅግ ከፍተኛ ነው።
ቡድኑ በዕውነትም የዘንድሮው የዓለም ዋንጫ ውድድር ሊከፈት አሥር ቀናት ሲቀሩት ባለፈው ሐሙስ ከኖርዌይ ጋር ባካሄደው ግጥሚያ እንደታየው ከሆነ ከግቡ ሊደርስ የማይችልበት ምን ምክንያት አይኖርም። የጀርመኑ ብሄራዊ ቡድን ግሩም ተጫዋቾቹ ዚሞነ ላውዴርና አሌክሣንድራ ፖፕ ባስቆጠሯቸው ጎሎች ኖርዌይን 3-0 ሲያሸንፍ ውጤቱ በትክክለኛው ሰዓት ትክክለኛው ማበረታቻ ነው የሆነው። እርግጥ የቡድኑ አንጋፋ ኮከብ ቢርጊት ፕሪንስ እንዳለችው ጨዋታው እስከ 79ኛው ደቂቃ ያላንዳች ጎል መቀጠሉ ሲታሰብ ኖርዌይም ቀላል ተጋጣሚ አልነበረም።

“እስከመጨረሻው ድረስ በፍጥነት መጫወት እንደምንችል ሁሉም ያየ ይመስለኛል። ያለማቋረጥ የምናጠቃ ሲሆን በተወሰነ ጊዜ ጎል ለማግባት መቻላችን ወይም በጨዋታችን መካሣችን የማይቀር ነው። ግን ዛሬ ዚሞነ የመጀመሪያዋን ጎል እስካስገባችበት ጊዜ ድረስ ሁኔታው እጅግ ከባድ ነበር”

ለማንኛውም ግጥሚያው ለሁለቱም ታላላቅ ቡድኖች አቅጣጫ ጠቋሚ ሣይሆን አልቀረም። ስለ ሴቶች እግር ኳስ አንዳንድ ተጨማሪ መረጃዎችን ለመጠቃቀስ ያህል የሴቶቹም እግር ኳስ እንደ ወንዶቹ ሁሉ የራሱ ከዋክብት አሉት። በዓለም ዋንጫው ታሪክ ውስጥ በተለይም ጠንካራ ከሚባሉት አንዷ የብራዚሏ ማርታ ናት። በብዙዎች ዕምነት በዓለም ላይ ድንቋ የሆነችው ሴት ተጫዋች ማርታ ባለፈው 2007 የዓለም ዋንጫ የውድድሩ ግሩም ተጫዋች ተብላ ስትመረጥ በጎል አግቢነት የወርቅ ጫማና በአጠቃላይ የአጨዋወት ብቃቷም የወርቅ ኳስ ተሽላሚ ነበረች።
የጀርመኗ ቢርጊት ፕሪንስም በሴቶች የዓለም ዋንጫ ታሪክ ውስጥ 14 በማስቆጠር በጎል አግቢነት የምትመራ ሲሆን በ 2003 ዓ.ም. የወርቅ ጫማና ኳስም ተሸላሚ ሆናለች። ዩ.ኤስ.አሜሪካ ደግሞ በዓለምአቀፍ ውድድሮች ከመቶ በላይ ጎሎችን ያስቆጠረችው ድንቅ ተጫዋች ኤቢይ ዋምባህ አለቻት። ሌሎች ዛሬ የውድድር ዘመናቸውን የፈጸሙ ማያ ሃምን፣ ክሪስቲን ሊሊንና ሰን ዌንን የመሳሰሉ ተጫዋቾችም በአንድ አሠርተ-ዓመት ድንቅ አስተዋጽኧቸው ሊታወሱ የሚገባቸው ናቸው። ታሪኩን በዚሁ ተወት እናድርግና ስድሥተኛው የወቅቱ የሴቶች የዓለም ዋንጫ ውድድር በፊታችን ዕሑድ ዚንስሃይም ላይ በምድብ-አንድ በናይጄሪያና በፈረንሣይ ግጥሚያ ይከፈታል። በዚሁ ምድብ አስተናጋጇ ጀርመንም በዚያው ዕለት ምሽት ከካናዳ የምትገናኝ ሲሆን ጨዋታው የሚካሄደው ዋና ከተማይቱ በርሊን ላይ ነው። በአራት ምድቦች ተከፍሎ የሚጀምረው ውድድር ፍጻሜ ግጥሚያ የሚካሄደው ደግሞ ሐምሌ 10 ቀን ፍራንክፈርት ከተማ ላይ ይሆናል።

Haile Gebrselassie Äthiopien gewinnt am Sonntag den 36. Berlin - Marathon

አትሌቲክስ

ስዊድን ርዕሰ-ከተማ ስቶክሆልም ላይ ሰንበቱን የተካሄደው የአውሮፓ የአትሌቲክስ የቡድን ሻምፒዮና ፍጻሜ ትናንት በሩሢያ የበላይነት ተጠናቋል። የሩሢያ አትሌቶች በጠቅላላው 385 ነጥቦች ሲያስመዘግቡ ሁለቱንም የውድድር ቀናት ሃያላኑ ነበሩ። ሩሢያ ባለፈው ዓመትም ኖርዌይ-በርገን ላይ በተመሳሳይ ውድድር አሸናፊ እንደነበረች ይታወሣል። ጀርመን በ 331,5 ሁለተኛ ስትሆን 304 ነጥቦች በማግኘት ሶሥተኛውን ቦታ የያዘችው ደግሞ ኡክራኒያ ናት። ብሪታኒያ ከተል ብላ አራተኛ ስትወጣ፣ ፈረንሣይም አምሥተኛ ሆናለች።

የፈረንሣዩ ወጣት የአጭር ርቀት ኮከብ ክሪስቶፍ ሌሜትር በመቶና ሁለት መቶ ሜትር ሩጫ የውድድሩን አዲስ ክብረ-ወሰን ሲያስመዘግብ ደመቅ ብለው ከታዩት አትሌቶች መካከል አንዱ ነበር። ሩሢያ በወንዶችና በሴቶች በአራት ጊዜ አራት መቶ ሜትር የዱላ ቅብብል፣ በሴቶች መቶ ሜትር፣ በሴቶችና በወንዶች የርዝመት ዝላይ፣ በወንዶች አራት መቶ ሜትር፣ እንዲሁም በሴቶች ስምንት መቶና ሶሥት ሺህ ሜትር ቀደምት ለመሆን በቅታለች። ስፓኝ በመካከለኛ ርቀት በወንዶች ሶሥት ሺህ፣ በአምሥት ሺህ ሜትር እንዲያውም በወንዶችና በሴቶች ለድል በቅታለች። በተረፈ በጥቅሉ ሲታይ የብሪታኒያ፣ የፖላንድ፣ የቤላሩስና የቼክ ሬፑብሊክ አትሌቶችም መልካም ውጤት አስመዝግበዋል።

በኦሎምፒክ ማራቶን ላይ እናተኩርና ሃይሌ ገ/ስላሤ ዘንድሮም በዚህ በጀርመን የዓለም ክብረ-ወሰን ባስመዘገበባት በበርሊን ማራቶን ሩጫ እንደሚሳተፍ ከውድድሩ አዘጋጆች በኩል ሰሞኑን ተጠቅሷል። ሃይሌ በፊታችን መስከረም የበርሊን ማራቶን የሚወዳደረው ለሚቀጥለው 2012 ዓ.ም. የለንደን ኦሎምፒክ ተሳትፎ የሚያበቃውን ጊዜ ለማረጋገጥ ነው። የ 38 ዓመቱ ሃይሌ ባለፈው ወር የማንቼስተርን የአሥር ኪሎሜትር ሩጫ ለአራተኛ ጊዜ ካሸነፈ በኋላ ትኩረቱ ለኦሎምፒክ ማራቶን የሚያበቃ ጊዜ ለመሮጥ መዘጋጀት እንደሆነ መግለጹ አይዘነጋም። ሃይሌ በሚወደው የበርሊን ማራቶን ለመጀመሪያ ጊዜ ሁለት ሰዓት ከአራት ደቂቃ በታች በመሮጥ ያስመዘገበው የዓለም ክብረ-ወሰን እስካሁን በማንም አልተደፈረም። በከባድ የአየር ሁኔታ ሳቢያ በቤይጂንግ ኦሎምፒክ ከመሳተፍ የተቆጠበው አትሌት ለለንደን ተሳትፎው እንዲበቃ ምኞታችን ከፍተኛ ነው።

Logo CONCACAF

እግር ኳስ ኮንካካፍና ኤውሮ ከ 21 በታች

በሰሜን፣ ማዕከላዊ አሜሪካና ካራይብ የእግር ኳስ ማሕበራት ኮንፌደሬሺን የኮንካካፍ ወርቃማ ዋንጫ ውድድር የሩብ ፍጻሜው ግጥሚያዎች ትናንት ተፈጽመዋል። ዩ.ኤ.አሜሪካ ጃሜይካን 2-0 አሸንፋ ወደ ግማሽ ፍጻሜው ስታልፍ ጎሎቹ በሙሉ የተቆጠሩት ከእረፍት በኋላ ነበር። በመጀመሪያው ዙር አንድም ጎል ያልገባበት የጃሜይካ ቡድን ለሽንፈት የበቃው በተለይም አንድ ተጫዋቹ ቀይ ካርድ ተሰጥቶት ከሜዳ በመውጣቱ ነው። ዩ.ኤስ.አሜሪካ በበኩሏ እስካሁን በተካሄዱት ስድሥት ውድድሮች በሙሉ ለግማሽ ፍጻሜ መድረሷ ነው። በምድቡ ዙር ባልተጠበቀ ሁኔታ አሜሪካን አሸንፋ የነበረችው ፓናማም ከበድ ባለ ሁኔታም ቢሆን ለግማሽ ፍጻሜው ለመድረስ በቅታለች። ፓናማ ከኤል ሣልቫዶር ጋር ባደረገችው የሩብ ፍጻሜ ግጥሚያ እየተመራች ቆይታ በዘጠናኛዋ ደቂቃ ላይ ቀንቷት 1-1 ስታደርግ በሰዓት ጭማሪና ከዚያም በኋላ በፍጹም ቅጣት ምት 5-3 በማሸነፍ ነው ለማለፍ የቻለችው።

አሜሪካና ፓናማ በግማሽ ፍጻሜው እርስበርስ ይገናኛሉ። ሌሎቹ የግማሽ ፍጻሜ ተጋጣሚዎች ሜክሢኮና ሆንዱራስ ሲሆኑ ሜክሢኮ ያለፈችው ጉዋቴማላን በሩብ ፍጻሜው 2-1 በመርታት ነው። ድንቅ አጥቂዋ ሃቪየር ሄርናንዴዝ በዚሁ ግጥሚያ ስድሥተኛ የውድድር ጎሉን ለማስቆጠር በቅቷል። ሆንዱራስ ደግሞ ለግማሽ ፍጻሜው የደረሰችው ከኮስታ ሪካ ጋር በመደበኛ ጨዋታ 1-1 ከተለያየች በኋላ በፍጹም ቅጣት ምት በማሸነፍ ነው። በነገራችን ላይ የዋንጫው አሸናፊ በ 2013 ዓ.ም. ብራዚል ውስጥ በሚካሄደው የኮንፌደሬሺን ዋንጫ ውድድር ሰሜን፣ ማዕከላዊ አሜሪካንና ካራይብን ወክሎ ይሳተፋል።

ዴንማርክ ውስጥ በመካሄድ ላይ ባለው ከ 21 ዓመት በታች ወጣቶች የአውሮፓ እግር ኳስ ሻምፒዮና ሰንበቱን በተከሄዱ ግጥሚያዎች በምድብ አንድ አስተናጋጇ አገር በአይስላንድ ባልተጠበቀ ሁኔታ 3-1 ተረታለች። ሶሥቱም ጎሎች የተቆጠሩት በሁለተኛው አጋማሽ ውስጥ ነበር። በዚሁ ምድብ ሌላ ግጥሚያ ደግሞ ስዊትዘርላንድ ቤላሩስን 3-0 አሸንፋለች። በምድብ ሁለት ግጥሚያዎች ስፓኝ ኡክራኒያን 3-0 ስትረታ እንግሊዝ በቼክ ሬፑብሊክ 2-1 ተሸንፋለች። በሌላ የእግር ኳስ ዜና ኢራን ኢራቅን በለንደን ኦሎምፒክ ማጣሪያ ሁለተኛ ዙር ግጥሚያ 1-0 ስታሸንፍ በዓለም ላይ ጠንካራው የሆነው ክለብ ባርሤሎና ደግሞ የቺሌውን የክንፍ ተጫዋች አሌክሢስ ሣንቼዝን በመግዛት ቡድኑን አጠናክሯል። ባርሣ ተጫዋቹን ከኢጣሊያው ክለብ ከኡዲኔዘ ለመግዛት 54 ሚሊዮን ዶላር ገደማ ነው የከፈለው።

በተቀረ 125ኛው የእንግሊዝ ዊምብልደን የቴኒስ ውድድር በዛሬው ዕለት ይጀምራል። በወንዶች ከታዋቂዎቹ መካከል ራፋኤል ናዳል ዛሬ በመጀመሪያ ከአሜሪካዊው ከማይክል ራስል የሚጋጠም ሲሆን የብሪታኒያዊው የኤንዲይ መሪይ ተጋጣሚ ደግሞ የስፓኙ ዳኒየል ትራቬር ነው። ከዚህ በተጨማሪ አሜሪካዊው ኤንዲይ ሮዲክ ከጀርመናዊው ከአንድሬያስ ቤክ ይጋጠማል። በሴቶችም ካሮሊን ቮዝኒያችኪ ከአራንቻ ፓራ፤ ማሪያ ሻራፖቫ ከአና ቻክቬላድሤ፤ ጥቂቶቹ ማራኪ መክፈቻ ግጥሚያዎች ናቸው። በሌላ በኩል ዛሬ በወጡ የዓለም የቴኒስ የማዕረግ ተዋረዶች መሠረት በወንዶች የስፓኙ ራፋኤል ናዳልና በሴቶችም የዴንማርኳ ካሮሊን ቮዝኒያችኪ ቀደምት እንደሆኑ ቀጥለዋል። በወንዶች የሰርቢያው ኖቫክ ጆኮቪች ሁለተኛ ሲሆን ሶሥተኛው የስዊሱ ሮጀር ፌደረር ነው። በሴቶች ሁለተኛ የቤልጂጓ ኪም ክላይስተርስ፣ ሶሥተኛ ሩሢያዊቱ ቬራ ዝቮናሬቫ እንዲሁም ያስደንቃል ቻይናዊቱ ሊ ና አራተኛውን ቦታ ይዛለች።

መሥፍን መኮንን

Audios and videos on the topic