የስፖርት ዘገባ | ስፖርት | DW | 13.06.2011
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ስፖርት

የስፖርት ዘገባ

እግር ኳስ፣ አትሌቲክስ፣ ቴኒስና የአውቶሞቢል እሽቅድድም

default

በእግር ኳስ እንጀምርና የሰሜንና ማዕከላዊ አሜሪካ እንዲሁም የካራይብ የእግር ኳስ ማሕበራት ኮን-ፌደሬሺን የኮንካካፍ የወርቃማ ዋንጫ ውድድር ሰንበቱን ወደ ሩብ ፍጻሜው ዙር ተሸጋግሯል። በምድብ-አንድ ውስጥ ሜክሢኮ ትናንት ኮስታ ሪካን 4-1 ስታሸንፍ የመጀመሪያውን ዙር አንዲት ነጥብ ሳታስነካ በበላይነት ለመፈጸም በቅታለች። ሁለቱን ጎሎች አንድሬስ ጉዋርዳዶ ሲያስቆጥ የተቀሩትን ያስገቡት ደግሞ ራፋኤል ማርኬዝና ፓብሎ ባሬራ ነበሩ። ማርኮስ ኡሬና ደግሞ የኮስታሪካን ብቸኛ ጎል ለማስቆጠር በቅቷል። እርግጥ የሜክሢኮ ድል አምሥት ተጫዋቾቿ የተከለከለ የአካል ማዳበሪያ መድሃኒት ወስደዋል የሚል ጥርጣሬ የጋረደው ነበር።
ሜክሢኮ ግን ጥርጣሬውን የቀሰቀሰው የተመረዘ ምግብ ነው ትላለች። ለማንኛውም ሜክሢኮ በሩብ ፍጻሜው ዙር በሁለተኝነት ማለፍ ከቻለችው ከኮስታ ሪካ መልሳ ትገናኛለች። ኮስታ ሪካ አራት ነጥብ ኖሯት በጎል ልዩነት ስታልፍ በተመሳሳይ ነጥብ ሶሥተኛ የሆነችው ኤል-ሣልቫዶርም ከሁለቱ ጠንካራ ሶሥተኞች አንዷ ሆና የማለፍ ዕድሏን ገና እንደጠበቀች ነው። ኤል-ሣልቫዶር ቀደም ሲል በኩባ በለየለት ሁኔታ 6-1 ተቀጥታ ነበር። ሌላ አስደናቂ ነገር ቢኖር ዩ.ኤስ.አሜሪካ በፓናማ 2-1 መሸነፏ ነው። አሜሪካ ከዚህ ቀደም 12 ሃገራት በሚሳተፉበት የኮንካካፍ ወርቃማ ዋንጫ ውድድር በመጀመሪያው የምድብ ዙር የተሸነፈችበት ጊዜ የለም። እርግጥ አሜሪካ በፊታችን ማክሰኞ ጉዋደሎፕን በማሸነፍ ከቀጣዮቹ ስምንት ቡድኖች አንዷ እንደምትሆን የታዛቢዎች ጽኑ ዕምነት ነው።

በደቡብ አሜሪካ የአርጄንቲና ሊጋ ውድድር ቬሌዝ ሣርስፊልድ ትናንት የዘንድሮው የአገሪቱ ሻምፒዮን ሊሆን በቅቷል። ክለቡ ለዚህ ክብር የበቃው በመጨረሻ ግጥሚያው ሁራካንን 2-0 በማሸነፍ ነው። ሁለቱን የድል ጎሎች ያስቆጠሩት የኡሩጉዋዩ አጥቂ ሣንቲያጎ ሲልቫና ዴቪድ ራሚሬስ ነበሩ። በአርጅቲኖስ ጁኒዮርስ የተረታው ላኑስ ደግሞ ውድድሩን በሁለተኝነት ፈጽሟል። የብራዚል ሻምፒዮና ገና በጅምሩ ላይ ሲሆን ከአራት ግጥሚያዎች በኋላ ሣኦ ፓውሎና ኮሪንቲያንስ ቁንጮ ሆነው ይመራሉ። በሌላ በኩል በኡሩጉዋይ ናሢዮናል ቀደም ሲል ዴፌንሶርን 1-0 በማሸነፍ ሻምፒዮን ሲሆን ትናንት ደግሞ ኡኒቨርሲዳድ-ዴ-ቺሌ ከመጀመሪያ ግጥሚያ 2-0 ሽንፈቱ አገግሞ በመልሱ ጨዋታ ኡኒቨርሢዳር ካቶሊካን 4-1 በመርታት የቺሌ አፔርቱራ ዋንጫ ባለቤት ሆኗል።

ዴንማርክ ውስጥ ከትናንት በስቲያ በተከፈተው ከ 21 ዓመት በታች ወጣቶች የአውሮፓ የእግር ኳስ ሻምፒዮና ውድድር ስዊትዘርላንድ አስተናጋጇን ዴንማርክን 1-0 በማሸነፍ የተሳካ ጅማሮ ለማድረግ በቅታለች። የስዊስ የወደፊት ተሥፋ መሆኑ የተነገረለት የመሃል ሜዳ ተጫዋች ሤርዳን ሻኪሪ ብቸኛዋን ጎል ያስቆጠረው ከእረፍት በኋላ ነበር። ሻኪሪ ከሣምንት በፊት በአንጋፋው ቡድን የኤውሮ ማጣሪያ በዌምብሌይ ስታዲዮም ከእንግሊዝ ጋር በተደረገው ግጥሚያ በመሰለፍ አድናቆትን ማትረፉ አይዘነጋም። ጨዋታው የተፈጸመው 2-2 ነበር። ወደ ወቅቱ ውድድር ልመለስና ዴንማርክም በበኩሏ ክሪስቲያን ኤሪክሰንን የመሳሰሉ ወጣት ተሥፋዎቿን ብታሰልፍም በተለይ በጨዋታው መጨረሻ አካባቢ ብዙ ዕድሎችን ለመጠቀም አልቻለችም። በዚሁ ምድብ ሁለተኛ ግጥሚያ ቤላሩስ አይስላንድን 2-0 ስታሸንፍ አመራሩንም ለጊዜው በጎል ብላጫ ለመያዝ በቅታለች።

በሁለተኛው ምድብ ግጥሚያ እንግሊዝና ስፓኝ ሲገናኙ ጨዋታው 1-1 አቻ-ላቻ ተፈጽሟል። ስፓኝ በመጀመሪያው አጋማሽ የበላይነት ስታሳይ አንደር ሄሬራ የመጀመሪያዋን ጎል በአናቱ ያስቆጠረው ገና በ 14 ኛዋ ደቂቃ ላይ ነበር። ሆኖም የእንግሊዝ ቡድን በሁለተኛው አጋማሽ የተሻለው ሆኖ ሲቀርብ በማንቼስተር ዩናይትድ አጥቂ በዌልቤክ አማካይነት በ 88 ኛዋ ደቂቃ ላይ ውጤቱን ሊያስተካክል በቅቷል። በዚሁ ምድብ ውስጥ በቼክ ሬፑብሊክና በኡክራኒያ መካከል የተካሄደው መክፈቻ ግጥሚያም የተፈጸመው በተመሳሳይ እኩል-ለእኩል ውጤት ነው። ውድድሩ በሂደቱ ማራኪ እየሆነ እንደሚሄድ አንድና ሁለት የለውም። በነገራችን ላይ በአንድ የላቲን አሜሪካና አውሮፓ የወዳጅነት ግጥሚያ ደግሞ ፓራጉዋይ ሩሜኒያን 2-0 አሸንፋለች። በአሱንሢዮን ብሄራዊ ስታዲዮም በተካሄደው ግጥሚያ ለአስተናጋጇ አገር ጎሎቹን ያስቆጠሩት ሃኤዶና ሣንታ-ክሩስ ነበሩ።

EM Leichtathletik in Spanien

አትሌቲክስ

ሰንበቱን ኒውዮርክ ላይ በተካሄደው የዳያመንድ ሊግ አትሌቲክስ ውድድር በመቶ ሜትር ሩጫ አሜሪካዊው ታይሰን ጌይ ድሉን ለጃማይካዊው ለስቲቭ መሊንግስ መተዉ ግድ ሆኖበታል። ሁለቱ አትሌቶች ሩጫውን በተመሳሳይ 10,26 ሣኮንድ ጊዜ ሲፈጽሙ አሸናፊውን በዓይን መለየቱ ቀላል ነገር አልነበረም። በሌላ በኩል በአራት መቶ ሜትር ሩጫ አሜሪካዊው ጄረሚይ ዋሪነር የጃማይካ ተፎካካሪውን ጀርሜይን ጎንዛሌስን ከኋላው ማስቀረቱ ተሳክቶለታል። በስምንት መቶ ሜትር ሩጫ ኬንያዊው አልፍሬድ የጎ ሲያሸንፍ የደቡብ አፍሪቃው ተወዳዳሪ እምቡሌኒ ሙላውጂ ሁለተኛ ሆኗል። ሩጫውን በሶሥተኝነት የፈጸመው ኬንያዊው ቦዝ-ኪፕላጋት-ላላንግ ነበር። በ 1,500 ሜትር ሩጫ ደግሞ አሜሪካዊው ዴቪድ ቶረንስ የኒውዚላንዱን ኒኮላስ ዊሊስንና የኬንያውን ካሌብ እንዲኩን በማስከተል አሸናፊ ሆኗል።

በአምሥት ሺህ ሜትር ሩጫ እንደተለመደው የኢትዮጵያና የኬንያ ፉክክር ጎልቶ ሲታይ ደጀን ገ/መስቀል በመጨረሻ አንደኛ ሆኗል። ከኬንያ የመነጨው አሜሪካዊ በርናርድ ላጋት ሁለተኛ ሲወጣ ሩጫውን በሶሥተኝነት ያጠናቀቀው ደግሞ ታሪኩ በቀለ ነበር። ግሩም ውጤት ነው! በሴቶች ሁለት መቶ ሜትር ሩጫ የሶሥት ጊዜዋ የዓለም ሻምፒዮን አሊይሰን ፌሊክስ ስታሸንፍ የአሜሪካ አትሌቶች ከአንድ እስከ አራት ቀደምቱን ቦታዎች በሙሉ ተቆጣጥረዋል። በሴቶች አራት መቶ ሜትር ሁለት ጃማይካውያት ቀደምት ሲሆኑ በስምንት መቶ ሜትር ደግሞ ድሉ የአሜሪካ ነበር።

በ 1,500 ሜትር ሩጫ ጃማይካዊቱ ኬኒያ ሲንክሌር አሜሪካዊቱን ሞርጋን ኡቼኒን አስከትላ ስታሸንፍ ከኢትዮጵያ ቃልኪዳን ገዛኸኝ ሶሥተኛ አንዲሁም ገለቴ ቡርቃ አራተኛ ሆነዋል። በሶሥት ሺህ ሜትር መሰናክልም ኬንያዊቱ ሚካህ ቼኖስ ስታሸንፍ ሶፊያ አሰፋ ሁለተኛ ሆናለች። ሶሥተኛ የወጣችው ደግሞ ሩሢያዊቱ ጉልናራ ሣሚቶቫ ነበረች። በተቀረ በፈረንሣይ-ሽትራስቡርግ ላይ ትናንት በተካሄደ ዓለምአቀፍ የአትሌቲክስ ውድድር የጃማይካዊው የመቶ ሜትር የዓለም ሻምፒዮን የዩሤይን ቦልት የሥልጠና ባልደረቦች ዳኒየል ቤይሊይና ዮሃን ብሌክ ከአሥር ሤኮንድ በታች በመሮጥ ግሩም ጊዜ አስመዝግበዋል። የአንቲጉዋው ቤይሊይ ርቀቱን በ 9,97 ሤኮንድ ሲያቋርጥ ጃማይካዊ ተፎካካሪውን ቤይሊይን የቀደመው በአንዲት መቶኛ ሤኮንድ ነው። ቦልት ወደፊት ብርቱ ፉክክር ይጠብቃዋል።

Jenson Button siegt bei Formel 1 Rennen in Montreal Kanada

ፎርሙላ-አንድ

ባለፈው ሌሊት ካናዳ ውስጥ በተካሄደው የፎርሙላ-አንድ አውቶሞቢል እሽቅድድም የብሪታኒያው ተወዳዳሪ ጄሰን ባተን የዓለም ሻምፒዮኑን ዜባስቲያን ፌትልን በመጨረሻዋ ዙር በመደረብ ለአስደናቂ ድል በቅቷል። ፌትል ምንም እንኳ እሽቅድድሙን ከመጀመሪያው ረድፍ ቢጀምርም በሰባተኛው ውድድር ለስድሥተኛ ድል መብቃቱ እንዳለመው አልተሳካለትም። እሽቅድድሙ በዝናብ ምክንያት ለሁለት ሰዓታት ሲቋረጥ ከዚሁ ሌላ ብዙ ትርምስምስ በታየበት በአስቸጋሪ ሁኔታ ነበር የተካሄደው። ለባተን ድሉ መወዳደር ከጀመረ ወዲህ አሥረኛው መሆኑ ነው።
በካናዳው እሽቅድድም ከባተንና ከፌትል ቀጥሎ የአውስትራሲያው ማርክ ዌበር ሶሥተኛ ሲወጣ ጀርመናዊው የሰባት ጊዜ የዓለም ሻምፒዮን ሚሻኤል ሹማሸር ደግሞ ባለፈው የውድድር ወቅት ከተመለሰ ወዲህ ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ አራተኛ ቦታ ከፍ ሊል በቅቷል። ከሰባቱ እሽቅድድሞች በኋላ አሁንም በአጠቃላይ 161 ነጥብ የሚመራው ዜባስቲያን ፌትል ነው። ሁለተኛው ባተን ደግሞ 101 ነጥቦች አሉት።

Caroline Wozniacki Tennis Dänemark U.S. Open Flash-Galerie

ቴኒስ

በቴኒስ ለማጠቃለል በለንደን ኩዊንስ-ክለብ ትናንት በብሪታኒያው ተወላጅ በኤንዲይ መሪይና በፈረንሣዊው ጆ-ዊልፍሪድ-ሶንጋ መካከል ሊካሄድ ታቅዶ የነበረው የወንዶች ፍጻሜ ግጥሚያ በከባድ ዝናብ ሳቢያ ለዛሬ መሸጋሸግ ግድ ሆኖበታል። በግማሽ ፍጻሜው ግጥሚያ የአሜሪካ ተጋጣሚውን ኤንዲይ ሮዲክን በለየለት ሁኔታ ያሰናበተው በዓለም አራተኛው መሪይ ከሁለት ዓመታት ወዲህ እንደገና የኩዊንስ አሸናፊ እንደሚሆን አይጠራጠርም። በነገራችን ላይ ይህ ዘግይቶ የሚታይ ሲሆን ለዊምብልደን ማሟሟቂያ ሆኖ የሚታየው ውድድር በተመሳሳይ የአየር ሁኔታ ሲሽጋሸግ ከሰባና ከሰማንያዎቹ ዓመታት ወዲህ ለሶሥተኛ ጊዜ መሆኑ ነው።
አየርን ካነሣን ትናንት በርሚንግሃም ላይ በዳኒየላ ሃንቱቼቫና በዛቢነ ሊሢችኪ መካከል ሊካሄድ ታስቦ የነበረ የሴቶች ፍጻሜ ግጥሚያም ወደ ዛሬ መሸጋሸጉ ግድ ሆኖበት ነበር። በሌላ ትናንት ዴንማርክ ውስጥ በተካሄደ የሴቶች ፍጻሜ ግጥሚያ በዓለም የማዕረግ ተዋረድ ላይ ቀደምቷ የሆነችው የአገሪቱ ዜጋ ካሮሊን ቮዝኒያችኪ የቼክ ሬፑብሊክ ተጋጣሚዋን ሉሢ ሣፋሮቫን በለየለት 6-1, 6-4 ውጤት አሸንፋለች።

መሥፍን መኮንን

ነጋሽ መሐመድ

Audios and videos on the topic