የስፖርት ዘገባ | ስፖርት | DW | 23.05.2011
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ስፖርት

የስፖርት ዘገባ

የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌደሬሺን ለአገሪቱ ብሄራዊ ቡድን የቤልጂግ ዜጋ የሆነ አዲስ ዋና አሠልጣኝ ሰይሟል።

default

በአትሌቲክስ እንጀምርና ሰንበቱን በጀርመን ሰሜናዊት ከተማ በሃምቡርግ በተካሄደው 26ኛ የማራቶን ሩጫ የኢትዮጵያ አትሌቶች ለድርብ ድል በቅተዋል። በወንዶች ሸንተማ ጉዲሣ በሁለት ሰዓት ከ 11 ደቂቃ ሶሥት ሤኮንድ ጊዜ ሲያሽንፍ ሁለተኛና ሶሥተኛ በመሆን ተከትለውት የገቡት ኬንያውያን ነበሩ። ያለፈው ዓመት አሸናፊ የኬንያው ዊልፍሪድ ኪገን በ 25ኛው ኪሎሜትር ላይ ከአመራሩ ጋር የነበረውን ግንኙነት ሲያጣ ውጤቱን አብሮ የመወሰን አንዳች ተጽዕኖ ሳይኖረው ቀርቷል። በሴቶች ደግሞ የ 19 ዓመቷ ወጣት ኢትዮጵያዊት ፋጡማ ደጎ ለዚያውም በመጀመሪያ ተሳትፎዋ ለታላቅ ድል በቅታለች። ሩጫዋን የፈጸመችውም ግሩም በሆነ ሁለት ሰዓት ከ 28 ደቂቃ ከሰላሣ ሤኮንድ ጊዜ ነበር። በዚሁ ሩጫ ሌላዋ የኢትዮጵያ ተወዳዳሪ ሃሊማ በሪሶ ሁለተኛ ስትሆን ሶሥተኛ የወጣችው ኬንያዊቱ ጆይስ ካንዲ ናት።

በዚህ በጀርመን ባለፈው ቅዳሜ ሃለ ከተማ ላይ በተካሄደ የአትሌቲክስ ውድድር ደግሞ በዲስክ ውርወራ የአውሮፓ ሻምፒዮን የሆነችው ጀርመናዊቱ ቤቲይ ሃይድለር አዲስ ክብረ-ወሰን ለማስመዝገብ በቅታለች። ሃይድለር ዲስኩን 72,42 ሜትር ስትወረውር ያሻሻለችው ባለፈው ዓመት የፖላንዷ አኒታ ቭሎዳርቺክ አስመዝግባ የነበረውን 78,30 ሜትር የዓለም ክብረ-ወሰን ነው። ጀርመናዊቱ አትሌት ከሰንበቱ ውጤት በኋላ በቅርቡ ደቡብ ኮሪያ ዴጉ ላይ በሚካሄደው ዓለምአቀፍ የአትሌቲክስ ውድድር የዓለም ሻምፒዮንነቷን ለማስመለስ ታላቅ ተሥፋ ጥላለች።

እግር ኳስ

በአውሮፓ ቀደምት የእግር ኳስ ሊጋዎች ውስጥ ሲካሄድ የቆየው ሻምፒዮና በአብዛኛው ቀደም ብሎ ሲለይለት ፉክክሩ የጠበበ ሆኖ በቆየበት በፈረንሣይ አንደኛ ዲቪዚዮን ደግሞ ሊል ከ 57 ዓመታት ወዲህ እንደገና ሻምፒዮን ሊሆን በቅቷል። ሊል ሻምፒዮን ሊሆን የቻለው በመጨረሻ ግጥሚያው ከፓሪስ-ሣንት-ዠረማን 2-2 ከተለያየ በኋላ ነው። ሰንበቱ ወደ ሁለተኛው ዲቪዚዮን ላለመከለስ በየቦታው ነርቭ የሚጨርሱ ግጥሚያዎች የተካሄዱበትም ነበር። ከብዙ በጥቂቱ ለመጥቀስ ያህል በስፓኝ ላ-ሊጋ የ 2000 ዓ.ም. ሻምፒዮን ዴፖርቲቮ ኮሩኛ፤ በእንግሊዝም የሊጋ ዋንጫ አሸናፊ የነበረው በርሚንግሃም ሢቲይ ባልተጠበቀ ሁኔታ ወደታች ከተከለሱት ክለቦች መካከል ዋነኞቹ ሆነዋል።

Flash-Galerie DFB-Pokalfinale 2011 MSV Duisburg - FC Schalke 04

ውድድሩ ቀደም ብሎ በተፈጸመበት በዚህ በጀርመን ሰንበቱ የፌደሬሺን ዋንጫ ፍጻሜ ግጥሚያ የተካሄደበት ነበር። በዘንድሮው ፍጻሜ ሻልከና የሁለተኛው ዲቪዚዮን ክለብ ዲዩስቡርግ ሲገናኙ ሻልከ ከፍተኛ በሆነ 5-0 ውጤት አሸናፊ ሊሆን በቅቷል። ሻልከ የፌደሬሺኑን ዋንጫ ሲወስድ የአሁኑ ለአምሥኛ ጊዜ ሲሆን ድሉ በመጪው ወቅት በአውሮፓ ሊጋ ውድድር ለመሳተፍም የሚያበቃው ነው። በተቀረ በዝነኛው ዌምብሌይ ስታዲዮም በፊታችን ቅዳሜ የሚካሄደው የአውሮፓ ሻምፒዮና ሊጋ ፍጻሜ ግጥሚያ በዓለም ዙሪያ በሚገኙ የእግር ኳስ አፍቃሪዎች ዘንድ በታላቅ ጉጉት ነው የሚጠበቀው። ተጋጣሚዎቹ በዝነኛ ከዋክብት የተሞሉት ማንቼስተር ዩናይትድና ባርሤሎና ሲሆኑ ጨዋታው ግሩም እንደሚሆን ጨርሶ አያጠራጥርም።

ከአውሮፓ ወደ አፍሪቃ እንሻገርና የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌደሬሺን በስነ-ምግባር ብልሹነት ምክንያት ያሰናበተውን የቀድሞ አሠልጣኝ አይፊይ ኦኑራን ለመተካት ባለፈው ሣምንት አዲስ ዋና አሠልጣኝ መሰየሙ አይዘነጋም። ስለ አሠልጣኙ ማንነት፣ የስራ ልምድ፣ የአመራረጥ ሁኔታና የመጀመሪያ ተግባር ዛሬ የፌደሬሺኑን የግንኙነት ጉዳይ ሃላፊ አቶ መላኩ አየለን አነጋግሬ ነበር። ያድምጡ!

Sebastian Vettel beim Großen Preis von Spanien

በመጨረሻም በአውቶሞቢል እሽቅድድም በቴኒስ ላይ እናተኩርና ትናንት ባርሤሎና ውስጥ በተካሄደው የስፓኝ ግራንድ-ፕሪ የፎርሙላ-አንድ አውቶሞቢል እሽቅድድም ጀርመናዊው ዜባስቲይ ፌትል አሸናፊ ሆኗል። ለ 23 ዓመቱ ወጣት ዘዋሪ ድሉ እስካሁን በተካሄዱት አምሥት እሽቅድድሞች አራተኛው መሆኑ ነው። የብሪታኒያ ዘዋሪዎች ሉዊስ ሃሚልተንና ጄሰን ባተን ሁለተኛና ሶሥተኛ ሲሆኑ የአውስትራሊያው ማርክ ዌበር አራተኛ ወጥቷል። ፌትል በአጠቃላይ 118 ነጥቦች ሉዊስ ሃሚልተንን በ 77 በማስከተል በሰፊ ልዩነት እየመራ ነው። በቴኒስ ደግሞ የዘንድሮው የፍሬንች-ኦፕን ውድድር ተከፍቶ እየተካሄደ ነው። በሂደቱ ብዙ አስደናቂ ግጥሚያዎች የሚጠበቁ ሲሆን ዋናው ጥያቄ ዓመቱን እስካሁን የዘለቀው የሰርቢያው ኮከብ የኖቫክ ጆኮቪች የድል ጉዞ ይገታል አይገታም ወይ ነው። ለማንኛውም በዚሁ አጋጣሚ ዛሬ የወጣ የሴቶች የማዕረግ ተዋረድ ዝርዝር የዴንማርኳ ካሮሊን ቮዝኒያችኪ በአንደኝነት መቀጠሏን አመልክቷል። ሁለተኛ የቤልጂጓ ኪም ክላይስተርስ ስትሆን ሶሥተኛዋ ደግሞ ሩሢያዊቱ ቬራ ዝቮናሬቫ ናት።

መሥፍን መኮንን

Audios and videos on the topic