የስፖርት ዘገባ | ስፖርት | DW | 16.05.2011
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ስፖርት

የስፖርት ዘገባ

በአውሮፓ ቀደምት ሊጋዎች ውስጥ ሲካሄድ የቆየው የ 2010-11 ዓ.ም. የእግር ኳስ ውድድር ባለፈው ሣምንት በሰፊው ለይቶለታል።

default

በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ ማንቼስተር ዩናይትድ ለ 19ኛ ድሉ ሲበቃ በኔዘርላንድ አንደኛ ዲቪዚዮንም አያክስ አምስተርዳም ለ 30ኛ ጊዜ የዳች ሻምፒዮን ሆኗል። በጀርመን ቡንድሊጋም የውድድሩ ወቅት ባለፈው ቅዳሜ ሲጠቃለል አንደኝነቱን ቀድሞ ያረጋገጠው የዶርትሙንድ ፌስታ እጅግ የደመቀ ነበር። ቡንደስሊጋን ካነሣን ዘንድሮ ድንቅ ሆኖ የተገኘው አፍሪቃዊ ጎል አግቢ ፓፒስ-ዴምባ-ሢሴም ማተኮሪያችን ነው። ዘገባችን በተረፈ አትሌቲክስን ቴኒስንና የቢስክሌት እሽቅድድምንም ይጠቀልላል።

በእግር ኳስ እንጀምርና በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ ማንቼስተር ዩናይትድ ከብላክበርን ሮቨርስ 1-1 በመለያየት ሬኮርድ 19ኛ የዋንጫ ድሉን ሊያረጋግጥ በቅቷል። ክለቡ ለሻምፒዮንነት የጎደለችውን አንዲት ነጥብ ያሟላው አጥቂው ዌይን ሩኒይ በፍጹም ቅጣት ምት ባስቆጠራት ጎል ነው። ማኒዩ ዘንድሮ በአውሮፓ ሻምፒዮና ሊጋ ውድድርም ለፍጻሜ ሲደርስ ለተጨማሪ ዋንጫ ገና ዕድል አለው። ጎረቤቱ ማንቼስተር ሢቲይ ደግሞ በእንግሊዝ ፌደሬሺን በ FA Cup ፍጻሜ ግጥሚያ ስቶክ ሢቲይን 1-0 በመርታት ከ 35 ዓመታት በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ለዋንጫ ባለቤትነት በቅቷል። ያለፈው ዓመት ሻምፒዮን ቼልሢይ በበኩሉ ሁለተኝነቱን ሲያረጋግጥ ሶሥተኛው አርሰናል ነው። ዌስት ሃም ዩናይትድ ደግሞ ከወዲሁ ከፕሬሚየም ሊጉ ሲከለስ በፊታችን ቅዳሜ ሌሎች ሁለት ክለቦች ተመሳሳይ ዕጣ ይጠብቃቸዋል።

በስፓኝ ፕሪሜራ ዲቪዚዮን ባርሤሎና ባለፈው ሣምንት አጋማሽ ላይ በተከታታይ ለሶሥተኛ ጊዜ ሻምፒዮንነቱን ሲያረጋግጥ ቫሌንሢያ ደግሞ ከጎረቤቱ ከሌቫንቴ ባዶ-ለባዶ ብቻ ቢለያይም በሶሥተኝነት ለመጪው የአውሮፓ ክለቦች ሻምፒዮና ሊጋ ውድድር ቀጥተኛ ተሳትፎ በቅቷል። ሁለተኛው ሬያል ማድሪድም ቪላርሬያልን 3-1 ሲረታ ስፓኝን በአውሮፓ ሻምፒዮና ሊጋ ከሚወክሉት ቀደምት ክለቦች አንዱ ነው። አራተኛው ቪላርሬያል ግን ለዚህ ለመብቃት መጀመሪያ ማጣሪያውን ማለፍ ይኖርበታል።

Deutschland Fußball Bundesliga Borussia Dortmund gegen Eintracht Frankfurt Gruppenfoto Meisterschale

የጀርመን ቡንደስሊጋና የዶርትሙንድ ፌስታ

የጀርመን ቡንደስሊጋ ውድድር ባለፈው ቅዳሜ ሲጠቃለል በተለይም ትልቁን ትኩረት የሳበው ወደታች ላለመውረድ የተደረገው ፉክክር ነበር። ሻምፒዮንነቱን ሁለት ሣምንታት ቀደም ብሎ ያረጋገጠው ዶርትሙንድ በበኩሉ በሜዳው ባካሄደው በመጨረሻ ግጥሚያው ፍራንክፉርትን 3-1 በማሸነፍ ከተመልካቹ ጋር የደመቀ ፌስታ አድርጓል።

“ማነው የጀርመን ሻምፒዮን? ቦሩሢያ ዶርትሙንድ!!!”

ለፍራንክፉርት በአንጻሩ ሽንፈቱ እንደ ሣንት ፓውሊ ሁሉ ወደ ሁለተኛው ዲቪዚዮን መከለስ ነው የሆነው። ቮልፍስቡርግ በፊናው ሆፈንሃይምን 3-1 በማሸነፍ በመጨረሻው ቀን ለጥቂት ራሱን ከውድቀት ሲያተርፍ ከሃምቡርግ 1-1 የተለያየው ግላድባህ ሶሥተኛው ተከላሽ እንዳይሆን ከሁለተኛው ዲቪዚዮን ሶሥተኛ ከቦሁም ጋር በሚያደርገው ተከታይ ግጥሚያ የግድ ማሸነፍ ይጠበቅበታል። በተረፈ ሌቬርኩዝን ሁለተኝነቱን አስከብሮ ለሻምፒዮናው ሊጋ ውድድር በቀጥታ ሲያልፍ ባየርን ሙንሺንም በሶሥተኝነት በማጣሪያ ግጥሚያ ወደዚያው የማለፍ ዕድል አለው። በዘንድሮው የቡንደስሊጋ ውድድር በተለይ አስደናቂው ነገር በአንድ በኩል ባልተጠበቀ ሁኔታ የቀደምቱ ክለቦች የብሬመን ወይም የሻልከ እጅግ ማቆልቆልና በሌላ በኩል ደግሞ ሃኖቨርን፣ ማይንስን፣ ኑርንበርግንና ፍራይቡርግን የመሳሰሉት ለወትሮው ደካማ ተብዬ ቡድኖች ጠንክሮ መገኘት ነው። አራተኛ፣ አምሥተኛ፣ ስድሥተኛና ዘጠነኛ በመሆን ነው ውድድሩን የፈጸሙት።

ፍራይቡርግን ካነሣን አይቀር የዚህ ክለብ የስኬት ዋስትና በተለይም አፍሪቃዊ አጥቂና ጎል አግቢው ፓፒስ-ዴምባ-ሢሴ ነበር። ሢሴ በተገባደደው የውድድር ወቅት 22 ጎሎችን በማስቆጠር በቡንደስሊጋው ታሪክ ውስጥ አቻ ያልታየለት የአፍሪቃ ጎል አግቢ ሊሆን በቅቷል። ለ 25 ዓመቱ ሤኔጋላዊ ብዙዎች የአፍሪቃ ተጫዋቾች በታላቁ የእግር ኳስ መድረክ ላይ ሃያል ሆነው ለመገኘት የሚያልሙት ሕልም ዘንድሮ ዕውን ነው የሆነለት። ግን እንዲህም ሆኖ ጨዋነትና ጭምትነቱ አሁንም አልተለየውም።

“በስኬቴ በጣም ነው የምደሰተው። በጣሙንም እኮራበታለሁ። ግን ገና መሻሻል የምችል ይመስለኛል። በጨዋታ ላይ ሁሌም እስከ መጨረሻዋ ደቂቃ ድረስ የምታገል ሲሆን ስራዬን በሚገባ ለማከናወን ነው የምጥረው። ይሄውም ጎል ማግባት ነው”

በዕውነትም ሢሤ ዘጠና ደቂቃ ሙሉ የሚሮጥ ታታሪ ተጫዋች ሲሆን ይህም በክለቡ በፍራይቡርግ በጣም ሳያስወድደው አልቀረም። ዘንድሮ በጎል አግቢነት የቡንደስሊጋው ሁለተኛ ሊሆን መብቃቱም በዚሁ ባልተቆጠበ ጥረቱ እንጂ በሌላ አይደለም። በነገራችን ላይ 28 ጎሎችን በማስቆጠር አንደኝነቱን የያዘው የባየርን ሙንሺን አጥቂ ማሪዮ ጎሜስ ነው። ወደ ሢሴ መለስ እንበልና የእግር ኳስ ታሪኩ የጀመረው በሤኔጋል ዋና ከተማ በዳካር ነበር።

“ሤኔጋል ውስጥ እንደሌሎች ሁሉ እግር ኳስ ጨዋታን የተማርኩት መንገድ ላይ ነው። ማለት ሁሉንም ነገር ራስህን ማስተማር አለብህ። የመንገድ እግር ኳስ አቅድ የለውም። እና የምታደርገው በመንፈስህ የመጣልህን ነው”

አፍሪቃ ውስጥ አብዛኛው ሕጻናት ኳስ የሚጫወቱት በባዶ አግራቸው ነው። የእግር ኳስ ጫማን ከቴሌቪዥን ስዕሎች ነው የሚያውቁት ቢባል ሙሉ በሙሉ ስህተት አይሆንም። ከዚህ አንጻር ታዲያ የዚህ የጨዋታ መሣሪያ ባለቤት መሆን ምንኛ እንደሚያስደስት መገመት አያዳግትም። የፓፒስ-ዴምባ-ሢሴም ታሪክ በዚሁ አቅጣጫ ነው የተራመደው። አንድ ቀን የብርቅየዋ ጫማ ባለቤትም ይሆናል።

“አጎቴ ነበር የመጀመሪያ የእግር ኳስ ጫማዬን የገዛልኝ። ደስታዬ ወደር አልነበረውም። በጊዜው የ 16 ዓመት ልጅ ስሆን እስከዚያው ዕውነተኛ የእግር ኳስ ጫማ ኖሮኝ አያውቅም ነበር። ታዲያ አጎቴን እስከዛሬ ድረስ በጣም ነው የማመሰግነው”

ሢሴ ወደ ጀርመኑ ቡንደስሊጋ የተሻገረው በፈረንሣይ ሊጋ ሁለተኛ ዲቪዚዮን ለሜትስ ጥቂት ከተጫወተ በኋላ ነበር። በጊዜው በዝቅተኛ 1,5 ሚሊዮን ኤውሮ ግዢ ወደ ፍራይቡርግ የመጣው ኮከብ ዛሬ እጅግ ታዋቂ ሲሆን የገበያ ዋጋውም በብዙ ዕጅ ከፍ ብሏል። ገና ከዛሬው ሊገዙት ካተኮሩበት ቀደምት የአውሮፓ ክለቦች መካከል አርሰናልና ሊፐርፑል እንደ ምሳሌ የሚጠቀሱት ናቸው።

በተቀሩት የአውሮፓ ሊጋዎች ውድድሮች ፖርቶ አንዴም ሳይሸነፍ የፖርቱጋልን ሻምፒዮና በመፈጸም ከ 33 ዓመታት ወዲህ የመጀመሪያው የአገሩ ክለብ ሆኗል። ባለፈው ወር ቀደም ብሎ ለ 25ኛ ጊዜ የፖርቱጋል ሻምፒዮን ለመሆን የበቃው ፖርቶ የውድድሩን ወቅት የፈጸመው 27 ጊዜ በማሸነፍና ሶሥቴ ደግሞ እኩል-ለእኩል በመውጣት ነው። ፖርቶ ዘንድሮ በሁለት የፖርቱጋል ክለቦች መካከል በሚካሄደው የአውሮፓ ሊጋ ፍጻሜ ግጥሚያም በቅርቡ ከብራጋ ጋር ይገናኛል። በስኮትላንድ ግላስጎው ሬንጀርስ ለሶሥተኛ ተከታታይ ሻምፒዮንነቱ በቅቷል።
በፈረንሣይ ሊጋ ደግሞ ሊል የአገሪቱን የጥሎ ማለፍ ዋንጫ ሲያገኝ በፊታችን ረቡዕ የሊጋው ሻምፒዮን በመሆን ለድርብ ድል የመብቃት ዕድል አለው። በኢጣሊያ ሤሪያ-አ ኤ.ሢላን ሰንበቱን ካልጋሪን 4-1 በማሸነፍ የውድድሩን ወቅት በአንደኝነት ሲዘጋ ሣምፕዶሪያ ብሬሺያና ባሪ ደግሞ ተከልሰዋል። በኔዘርላንድ የክብር ዲቪዚዮን አያክስ አምስተርዳም በመጨረሻዋ ቀን ነው ሻምፒዮንነቱን ያረጋገጠው። ካለፈው ወቅት ሻምፒዮን ከኤንሼዴ ጋር ያደረገው የጦፈ ፉክክር በመጨረሻ ሰምሮለታል።

London Marathon

አትሌቲክስ

በአትሌቲክሱ ዓለም ዛሬ ታላቁና አስደንጋጩ ዜና የኬንያው የኦሎምፒክ ማራቶን ሻምፒዮን የሣሙዔል ዋንጂሩ ከፎቅ ቤቱ በረንዳ ላይ ወድቆ መሞቱ ነው። የኬንያ ፖሊስ የአትሌቱን ሞት ከማረጋገጥ አልፎ እስካሁን ዋንጂሩ ከፎቁ ዘሎ ራሱን ይግደል ወይም ሌላ ምክንያት ይኑር ለመግለጽ አልቻለም። የ 24 ዓመቱ ወጣት ዋንጂሩ በቤይጂንግ ኦሎምፒክ በማሸነፍ አገሩን ለመጀመሪያ ጊዜ ለኦሎምፒክ የማራቶን ወርቅ ያበቃ አትሌት ነበር። ኬንያዊው አትሌት በቺካጎና በለንደን ማራቶን ሩጫዎችም አሸናፊ እንደነበር ይታወሣል። በሣሙዔል ዋንጂሩ ሞት ኬንያ ብቻ ሣትሆን መላው ዓለም ነው ድንቅ አትሌቱን ያጣው። ወደ ውድድሩ ዓለም መለስ እንበልና የማራቶኑ የዓለም ክብረ-ወሰን ባለቤት ሃይሌ ገ/ስላሤ በበኩሉ ትናንት እንግሊዝ ውስጥ በተካሄደው የማንቼስተር የእሥር ኪሎሜትር ሩጫ ለአራተኛ ጊዜ አሸናፊ ሆኗል።
ሃይሌ ገ/ስላሤ በወቅቱ የሚያተኩረው ለሚቀጥለው ዓመት የለንደን ኦሎምፒክ ተሳትፎ የሚያበቃ ፈጣን የማራቶን ሰዓት በማስመዝገቡ ላይ እንደሆነ ከውድድሩ በኋላ ገልጿል። በሴቶች አንደኛ የሆነችው የብሪታኒያዋ ሄለን ክሊቴሮ ነበረች። በሻንግሃይ የዲያመንድ ሊግ ውድድር በአጭር ርቀት እንደተለመደው የአሜሪካና የጃሜይካ አትሌቶች ሲያይሉ በመካከለኛና ረጅም ርቀት ደግሞ ኬንያውያን ጠንከር ብለው ታይተዋል። በወንዶች 1,500 ሜትር ኬንያውያን አንደኛና ሁለተኛ ሲወጡ መኮንን ገ/መድህን ሩጫውን በሶሥተኝነት ፈጽሟል። በሶሥት ሺህ ሜትር መሰናክል ከአንድ እስከ አምሥት ተከታትለው የገቡት በሙሉ ኬንያውያን ነበሩ። በሴቶች አምሥት ሺህ ሜትር ደግሞ ኬንያዊቱ ቪቪያን ቼሩዮት ስታሸንፍ ስንታየሁ እጅጉ ሁለተኛ ሆናለች።

Serbien Tennis Novak Djokovic

ቴኒስ

በሮም ማስተርስ የቴኒስ ውድድር በወንዶች ፍጻሜ የሰርቢያው ኮከብ ኖቫክ ጆኮቪች ትናንት የስፓኙን ራፋኤል ናዳልን እንደገና በለየለት 6-4, 6-4 ውጤት በማሽነፍ ለአንደኝነቱ ማዕረግ ተጨማሪ ዕርምጃ አድርጓል። በዓለም የማዕረግ ተዋረድ ላይ በአሁኑ ጊዜ ሁለተኛ የሆነው ጆኮቪች የያዝነውን ዓመት ሙሉ ከድል ወደ ድል እየተሸጋገረ ሲመጣ የትናንቱም በማከታተል 37ኛው መሆኑ ነበር። በወቅቱ አያያዝ ማን እንደሚያቆመው አይታወቅም። በሴቶች ደግሞ ሩሢያዊቱ ማሪያ ሻራፖቫ የአውስትራሊያ ተጋጣሚዋን ሣማንታ ስቶሱርን በተለየ ጥንካሬ 6-2, 6-4 አሸንፋለች። የቀድሞይቱ የዓለም አንደኛ ሻራፖቫ የትናንቱን የሮም ድሏን አዲስ ጅማሮ ብላዋለች። በተቀረ የዚህ ዓመቱ ዢሮ-ዴ-ኢታሊያ የቢስክሌት ውድድር አሽናፊ የስፓኙ አልቤርቶ ኮንታዶር ሆኗል። ኮንታዶር በአጠቃላይ ነጥብም ቀደምቱ ነው።

መሥፍን መኮንን

Audios and videos on the topic

ተዛማጅ ዘገባዎች