የስፖርት ዘገባ | ስፖርት | DW | 11.04.2011
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ስፖርት

የስፖርት ዘገባ

በአውሮፓ ቀደምት የእግር ኳስ ክለቦች ብሄራዊ ሻምፒዮና የውድድሩ ወቅት ሊጠናቀቅ እየተቃረበ ነው።

default

በእንግሊዝም ሆነ በስፓኝ ወይም በኢጣሊያ አመራሩን የያዙት ቡድኖች ሰንበቱን አንዳች ድክመት አልታየባቸውም። ነገና ከነገ ወዲያም የአውሮፓ ሻምፒዮና ሊጋ የሩብ ፍጻሜ የመልስ ግጥሚያዎች ይካሄዳሉ። በአትሌቲክሱ መድረክ ኬንያውያን ከፓሪስ እስከ ሮተርዳም የማራቶን ባለድል ሲሆኑ በማሌይዚያ የፎርሙላ-አንድ እሽቅድድም ደግሞ ጀርመናዊው ዘዋሪ ዜባስቲያን ፌትል ለሁለተኛ ድሉ በቅቷል።

በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ ውድድር በዚህ ሰንበት ቀደምቱ ክለቦች ማንቼስተር ዩናይትድ አርሰናል፣ ቼልሢይና ቶተንሃም ሆትስፐር ሁሉም በማሸነፋቸው በአመራሩ ላይ ብዙም የተለወጠ ነገር የለም። ማኒዩ ዲሚታር ቤርባቶቭና አንቶኒዮ ቫሌንሢያ ከእረፍት በፊት ባስቆጠሯቸው ሁለት ጎሎች ፉልሃምን በሜዳው ሲያሸንፍ አርሰናልም ከሶሥት እኩል ለእኩል ውጤቶች በኋላ ትናንት ብላክፑልን 3-1 ረትቷል። ቼልሢይ ዊጋን አትሌቲክን 1-0 በማሸነፍ ወደ ሶሥተኛው ቦታ ከፍ ሲል በወቅቱ አራተኛ የሆነው ማንቼስተር ሢቲይ ከሊቨርፑል የሚጋጠመው ገና በዛሬው ምሽት ነው።

በጥቅሉ ማንቼስተር ዩናይትድ በ 69 ነጥቦች የሚመራ ሲሆን አርሰናል አንድ ግጥሚያ ጎሎት በ 62 ነጥቦች ሁለተኛ ነው። ማንቼስተር ሢቲይ በዛሬው ምሽት ካሸነፈ ቼልሢይን ከሶሥተኛው ቦታ መልሶ ሊፈነቅል ይችላል። በጎል አግቢነት የማንቼስተሩ ቡልጋሪያዊ አጥቂ ዲሚታር ቤርባቶቭ 21 አስቆጥሮ የሚመራ ሲሆን በ 19  ጎሎች ሁለተኛው የማንቼስተር ሢቲይ አርጄንቲናዊ ኮከብ ካርሎስ ቴቬዝ ነው።

በስፓኝ ፕሪሜራ ዲቪዚዮን ኤፍ.ሢ.ባርሤሎና እንደተጠበቀው የመጨረሻውን አልሜሪያን 3-1 በማሸነፍ በስምንት ነጥቦች ልዩነት መምራቱን ቀጥሏል። በዚሁ ግጥሚያ የቡድኑ አርጄንቲናዊ ኮከብ ሊዮኔል ሜሢ ከሶሥት ሁለቱን ጎሎች ሲያስገባ በጠቅላላው 29 አስቆጥሮ ሊጋውን ለብቻው እየመራም ነው። የሬያል ማድሪዱ ክሪስቲያኖ ሮናልዶ በአንዲት ጎል ዝቅ ብሎ ይከተለዋል። ሬያልን ካነሣን የማድሪዱ ንጉሣዊ ክለብ ሰንበቱን ያሳለፈው በበኩሉ ግጥሚያ ቢልባዎን 3-0 በመሸኘት ነበር። ባርሤሎና ውድድሩ ሊያበቃ ሰባት ግጥሚያዎች ቀርተው ሳለ በ 84 ነጥቦች የሚመራ ሲሆን ሬያል ማድሪድ በ 76 ነጥቦች ይከተላል፤ ሶሥተኛው ቪላርሬያልን 5-0 ያሸነፈው ቫሌንሢያ ነው።

Fußball Bundesliga Hamburg Dortmund Flash-Galerie

የጀርመን ቡንደስሊጋ

በጀርመን ቡንደስሊጋ ውድድር ዘንድሮ ብዙዎችን ያስደነቀው ክለብ ቦሩሢያ ዶርትሙንድ አመራሩን ጠብቆ ሻምፒዮን ለመሆን መታገሉን እንደቀጠ ቢሆንም ከ 12 ነጥቦች ይበልጥ የነበረ አመራሩ ቀስ በቀስ አሁን ወደ አምሥት አቆልቁሏል። ዶርትሙንድ በሰንበቱ ግጥሚያው ከሃምቡርግ ጋር ለዚያውም በመጨረሻ በተገኘች ጎል 1-1 ሲለያይ ሁኔታው ሁለተኛው ሌቨርኩዝን የሻምፒዮንነት ሕልም ማለም እንዲጀምር ነው ያደረገው። ይሁን እንጂ የዶርትሙንዱ አሠልጣኝ ዩርገን ክሎፕ እኩል ለእኩሉን ውጤት የድል ያህል አድርጎ መመልከቱ አልቀረም።

“የውድድሩ ወቅት በመገባደድ ላይ ሳለ ይሄ ላለመሸነፍ ያደረግነው ትግል በጣሙን የሚደነቅ ነው። የተጫዋቾቹን ትግል ግሩም አድርጌ ነው የተመለከትሁት። ለነገሩ ብናሸንፍም በተገባን ነበር። ሆኖም አንድ ነጥብ ይዘን መመለሳችንም በቂ ነው”

ታላቁ የቡንደስሊጋ ክለብ ባየርን ሙንሺን በአንጻሩ ባለፈው ቅዳሜ ከኑርንበርግ 1-1 ተለያይቶ ሶሥተኛ ቦታውን ለሃኖቨር ሲያስረክብ በደረሰበት ክስረት ሆላንዳዊ አሠልጣኙን ሉዊስ-ፋን-ኸልን አቧሯል። የባየርኑ ፕሬዚደንት ኡሊ ሄነስ ፋን-ኻል አምሥት ግጥሚያዎች ቀርተው ሳለ ከወዲሁ መሰናበታቸው ግድ እንደነበረ ነው ትናንት ለጋዜጠኞች የገለጸው።

“የትናንቱ ዕለት ሰንሰለቱ መጨረሻ ጫፍ ላይ የተደረሰበት ነበር። እናም የክለቡ አመራር አንድ ውሣኔ ማድረግ ነበረበት። ምክንያቱም ሁኔታው ባለበት ሊቀጥል አልቻለም። ስለዚህም ውሣኔው መቶ በመቶ ትክክለኛ ነው”

በተቀሩት ግጥሚያዎች ፍራይቡርግ ሆፈንሃይም 3-2፤ ሃኖቨር ማይንስ 2-0፤ ሻልከ ቮልፍስቡርግ 1-0፤ ካይዘርስላውተርን ሽቱታርት 4-2፤ እንዲሁም ፍራንክፉርት ከብሬመን 1-1 ሲለያዩ ከሁሉም ያስደነቀው የመጨረሻው ግላድባህ ትናንት ኮሎኝን በሜዳው 5-1 መቅጣቱ ነበር። በጎል አግቢነት ሃያ አስቆጥሮ የሚመራው የፍራይቡርጉ ሤኔጋላዊ ተጫዋች ፓፒስ ሢሤ ነው። በተቀረ በኢጣሊያ ኢንተር ሚላን፣ በፈረንሣይ ሊል፤ በኔዘርላንድ ትዌንቴ ኤንሼዴ በየፊናቸው መምራታቸውን ሲቀጥሉ የፖርቱጋሉ ፖርቶ ባለፈው ሣምንት ሻምፒዮንነቱን ቀድሞ ማረጋገጡ አይዘነጋም።  

BdT Magdeburg Marathon

አትሌቲክስ

በትናንትናው ዕለት ፈረንሣይ ውስጥ ተካሂዶ በነበረው የፓሪስ ማራቶን ሩጫ ኬንያዊውያኑ ቤንጃሚን ኪፕቶና በርናርድ ኪፕየጎ አንደኛና ሁለተኛ ሲወጡ ኢትዮጵያዊው ተወዳዳሪ እሸቱ ወንድሙ ደግሞ ሶሥተኛ ሆኗል። የሁለቱ የረጅም ርቀት ሩጫ ሃያላን ሃገራት አትሌቶች እስከ ዘጠነኛው ቦታ ሲከታተሉ ከነዚሁ መካከልም ሩጫውን በአምሥተኝነት የፈጸመው አሰፋ ግርማ አንዱ ነው። በሴቶችም እንዲሁ ኬንያውያት ከአንድ እስከ ሁለት ሲከታተሉ የኢትዮጵያ ተወካዮች ኮረን ያልና ኢየሩሣሌም ኩማ ሶሥተኛና አራተኛ ወጥተዋል።

በ 31ኛው የሮተርዳም ማራቶንም ቢሆን ሁኔታው የተለየ አልነበረም። ኬንያዊው ዊልሰን ቼቤት የአገሩን ልጅ ቪንሤንት ኪፕሩቶን ቀድሞ ለድል ሲበቃ ኢትዮጵያዊው ጫላ ደቼሣ ሶሥተኛ ሆኗል። በሴቶችም ያሸነፈችው ለማራቶኑ ውድድር አዲስ የሆነችው ኬንያዊት ፊልስ ኦንጎሪ ነበረች። በሰንበቱ የሚላኖ ማራቶንም እንዲሁ ድሉ የኬንያና የኢጣሊያ ሆኖ አልፏል። በወንዶች ሶሎሞን ናይባይ ሲያሸንፍ በሴቶች ባለድል የሆነችው ማርቼላ ማንቺኒ ነበረች።                                                      
በደቡብ አፍሪቃ የአትሌቲክስ ሻምፒዮና ደግሞ በጾታ ባሕርይዋ አከራካሪ የነበረችው ካስተር ሤሜንያ በ 800 እና በ 1,500 ሜትር ሩጫ በማሸነፍ ዓለምአቀፍ ትኩረትን ለመሳብ በቅታለች። በተለይም የኋለኛውን ሩጫ በግሩም ጊዜ ነው የፈጸመችው። ሤሜንያ ከሁለት ዓመታት ገደማ በፊት በበርሊን ተካሂዶ በነበረው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ውድድር በ 800 ሜትር የወርቅ ሜዳሊያ ማሽነፏ የሚታወስ ነው። አትሌቷ ቀስ በቀስ ወደ ዓለምአቀፉ መድረክ እየተመለሰች ሲሆን ወደፊት በዓለም የዲያመንድ ሊግ ውድድሮች ላይ እንደምትሳተፍ ይጠበቃል።

BdT Sebastian Vettel Formel 1 Sieg in Malaysia

የፎርሙላ-አንድ እሽቅድድም

ባለፈው ሌሊት ማሌይዚያ ላይ ተካሂዶ በነበረው በዘንድሮው የፎርሙላ-አንድ አውቶሞቢል እሽቅድድም ጀርመናዊው ዜባስቲያን ፌትል አሸናፊ ሆኗል። ፌትል ካለፈው ሣምንት የሜልበርን ድሉ በኋላ በሁለተኛ ውድድሩም የበላይነቱን ማረጋገጡ ነው። እርግጥ የማሌይዚያው እሽቅድድም በአየሩ ሙቀት የተነሣ ለፌትልም ቢሆን ቀላል ነገር አልነበረም። በመሆኑም ሁለተኛውን የብሪታኒያ ዘዋሪ ጄሰን ባተንን የቀደመው በሶሥት ሤኮንዶች ብቻ ነው።

“እሽቅድድሙ ቀላል አልነበረም። የጎማዎቹ ሁኔታ ወሣኝነት ነበረው። እናም በጎማዎቹ መበላት የተነሣ ላጥቃ አላጥቃ፣ በምን ጥንካሪ ልግፋ፤ ይሄ ሁሉ ግምት ውስጥ መግባት የነበረበት ነገር ነው። የሆነው ሆኖ በጥቅሉ ሲታይ አካሄዳችን መጥፎ አልነበረም”

ፌትል ከማሌይዚያው ውድድር በኋላ በአጠቃላይ 50 ነጥቦች የሚመራ ሲሆን ሁለቱ የብሪታኒያ ዘዋሪዎች ጄሰን ባተን በ 26፤ እንዲሁም ሉዊስ ሃሚልተን በ 22  ይከተሉታል። በቡድን ደግሞ ሬድ-ቡል-ሬኖ 72፤ ማክላረን ሜርሤደስ 48፤ እንዲሁም ፌራሪ 36  ነጥብ አላቸው። የሚቀጥለው እሽቅድድም የሚካሄደው በፊታችን ሰንበት ቻይና-ሻንግሃይ ላይ ነው።

Caroline Wozniacki Tennis Dänemark U.S. Open Flash-Galerie

ቴኒስ

በዓለም የሴቶች ቴኒስ የማዕረግ ተዋረድ ላይ አንደኛ የሆነችው ካሮሊን ቮዝኒያችኪ በዩ.ኤስ.አሜሪካ-ቻርልስተን ትናንት የሩሢያ ተጋጣሚዋን ኤሌና ቬስኒናን 6-2, 6-3 በመርታት በዘንድሮው የውድድር ወቅት በአሽዋ ሜዳ ላይ ለሶሥተኛ ድሏ በቅታለች። የዴንማርኳ ዜጋ ቀደም ሲል በተመሳሳይ ሁኔታ በዱባይና በካሊፎርኒያ-ኢንዲያን ዌልስ አሸንፋ ነበር። በማዕረግ ተዋረዱ ላይ ሁለተኛ የሆነችው የቤልጂጓ ኪም ክላይስተርስ ደግሞ በአካል ጉዳት የተነሣ በሚቀጥለው ወር በታላቁ የፈረንሣይ-ኦፕን ውድድር መሳተፏን አጠያያቂ አድርጋለች።                                                                       
ክላይስተርስ ከዚህ ቀደም በሮላንድ ጋሮሽ ሁለቴ ለፍጻሜ መድረሷ የሚታወስ ነው። በሂውስተን ቴክሣስ አሜሪካዊው ራያን ስዊቲንግ በመጀመሪያ የፍጻሜ ግጥሚያው የጃፓኑን ካይ ኒሺኮሪን 2-1 አሸንፏል። የሞንቴ ካርሎ ማስተርስ ደግሞ ከትናንት ጀምሮ እየተካሄደ ነው።

ዘገባችንን በእግር ኳስ ለማጠቃለል በአውሮፓ ክለቦች ሻምፒዮና ሊጋ ውድድር በዚህ ሣምንት የሩብ ፍጻሜው የመልስ ግጥሚያዎች ይካሄዳሉ። በነገው ምሽት ማንቼስተር ዩናይትድ የቼልሢይ አስተናጋጅ ሲሆን ባርሤሎና የሚጫወተው ደግሞ በኡክራኒያ ከሻህታር ዶኔትስክ ጋር ነው። በማግሥቱ ረቡዕ ቶተንሃም ሆትስፐር ከሬያል ማድሪድ፤ ሻልከ ከኢንተር ሚላን ይጋጠማሉ። ሁለቱ የስፓኝ ክለቦች ባርሤሎናና ሬያል የመጀመሪያ ግጥሚያቸውን 5-1 እና 4-0 በሆነ ሰፊ ውጤት ማሸነፋቸው ሲታወስ ወደ ግማሽ ፍጻሜው ከማለፍ ይሰናከላሉ ብሎ የሚያስብ የለም።                                                             
የጀርመኑ ክለብ ሻልከም ቢሆን ኢንተርን የሚቀበለው በመጀመሪያው ግጥሚያ ባልተጠበቀ 5-2 ውጤት አሸንፎ ከተመለሰ በኋላ ነው። በሌላ በኩል በእንግሊዙ ክለቦች ቀጥተኛ ፉክክር ማንቼስተር ዩናይትድ 1-0 ቢያሸንፍም ቼልሢይ ከወዲሁ አልቆለታል ለማለት አይቻልም። በአጠቃላይ ሁለቱ የስፓኝ ክለቦች ባርሣና ሬያል ማድሪድ ከሻልከና ምናልባትም ከማኒዩ ጋር ወደ ግማሽ ፍጻሜው የሚያልፉ ነው የሚመስለው። እርግጥ ተጨባጩን ውጤት ከፊታችን ረቡዕ ግጥሚያዎች በኋላ እንደርስበታለን።

መሥፍን መኮንን          ሽዋዮ ለገሰ