የስፖርት ዘገባ | ስፖርት | DW | 05.04.2011
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ስፖርት

የስፖርት ዘገባ

በአውሮፓ ቀደምት ሊጋዎች የእግር ኳስ ውድድር የፖርቱጋሉ ክከብ ፖርቶ ትናንት ቤንፊካ ሊዝበንን በማሸነፍ የውድድሩ ወቅት ከመጠናቀቁ በፊት ቀድሞ ለ 25ኛ ጊዜ የአገሪቱ ሻምፒዮን ሆኗል።

default

ሣምንቱ በአፍሪቃና በአውሮፓም የክለቦች ሻምፒዮና ግጥሚያዎች የተካሄዱበትና የሚካሄዱበትም ነው። በአትሌቲክሱ ዓለም በበርሊን የግማሽ ማራቶን ሩጫ ኬንያውያን አይለው ሲታዩ በካሊፎርኒያ-የካርልስባድ አምሥት ሺህ ሜትር ሩጫም የኢትዮጵያ አትሌቶች ለድርብ ድል በቅተዋል። በዓለምአቀፉ ቴኒስ ደግሞ የሰርቢያውን ኮከብ የኖቫክ ጆኮቪችን የድል ጉዞ የሚያስቆም አሁንም አልተገኘም።

በእግር ኳስ እንጀምርና በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ ማንቼስተር ዩናይትድ አጥቂው ዌይን ሩኒይ ባስቆጠራቸው ሶሥት ጎሎች በመደገፍ አመራሩን ወደ ሰባት ነጥቦች ሊያሰፋ በቅቷል። ማኒዩ ዌስትሃም-ዩናይትድን 4-2 ያሸነፈው ለዚያውም ሁለት-ለባዶ ከተመራ በኋላ እንደገና ተመልሶ ነበር። ማንቼስተር ዩናይትድ ለ 19ኛ ጊዜ የእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ ሻምፒዮን ለመሆን በያዘው ትግል እርግጥ በተከታዩ በአርሰናል ድክመት መታገዙም አልቀረም። አርሰናል በገዛ ሜዳው ከብላክበርን ሮቨርስ የተለያየው ባዶ-ለባዶ ብቻ ነው።

ሌላው የሰንበቱ ተጠቃሚ የማኒዩ ጎረቤት የሆነው ማንቼስተር ሢቲይ ነበር። ክለቡ ሰንደርላንድን 5-0 አከናንቦ በመሸኘት ከስቶክ ሢቲይ 1-1 የተለያየውን ቼልሢይን ከሶሥተኛው ቦታ መፈንቀሉ ተሳክቶለታል። በጥቅሉ ማንቼስተር ዩናይትድ በ 31  ግጥሚያዎች 66 ነጥቦችን በመሰብሰብ አንደኛ ሲሆን አርሰናል አንድ ጨዋታ ጎሎች በ 59 ነጥቦች ሁለተኛ ነው። ማንቼስተር ሢቲይ ሶሥተኛ፣ ቼልሢይ አራተኛ፣ ቶተንሃም ሆትስፐር አምሥተኛ በመሆን ይከተላሉ።

በስፓኝ ፕሪሜራ ዲቪዚዮን ላ-ሊጋም ሁኔታው ከእንግሊዙ የሚመሳሰል ነው። ሬያል ማድሪድ በገዛ ሜዳው በስፖርቲንግ ጊዮን 1-0 በመረታቱ የባርሤሎናን የሁለት ዓመታት የበላይነት ለማብቃት ያለው ዕድል ጥቂት ሳይከብድ አልቀረም። ሬያል ማድሪድ በዘንድሮው የውድድር ወቅት ከ 14 ግጥሚያዎች ድል በኋላ በሜዳው ሲሸነፍ ለመጀመሪያ ጊዜ መሆኑም ነው። ባርሤሎና በአንጻሩ ቪላርሬያልን ተከላካዩ ዤራርድ ፒኬ ባስቆጠራት ጎል 1-0 በመርታት ውድድሩ ሊያበቃ ስምንት ግጥሚያዎች ቀርተው በስምንት ነጥቦች ይመራል።

Bundesliga 28. Spieltag Borussia Dortmund vs. Hannover 96 FLASH Galerie

የጀርመን ቡንደስሊጋ

በጀርመን ቡንደስሊጋ የዘንድሮው አስደናቂ ቡድን ቦሩሢያ ዶርትሙንድ ሃኖቨርን ድንቅ በሆነ አጨዋወት 4-1 በማሸነፍ ዘንድሮ ሻምፒዮንነቱን ከዕጁ የማያስወጣ መሆኑን በሚገባ አስመስክሯል። ወጣቱ ቡድን በቀለጠፈ ጨዋታ አራቱን ጎሎች ያስቆጠረው ለዚያውም ቀድሞ በአንዲት ጎል ከተመራ በኋላ ነበር። ዶርትሙንድ የሊጋው ውድድር ሊያበቃ ስድሥት ግጥሚያዎች ቀርተው ሳለ በሰባት ነጥቦች ልዩነት የሚመራ ሲሆን ቢቀር 80 ሺህ ተመልካቾቹ ከወዲሁ ፌስታውን ጀምረዋል። ከተጫዋቾቹ አንዱ ማትስ ሁመልስም ዶርትሙንድ ዘንድሮ በትግልና በራስ መተማመን መንፈስ የተመላ መሆኑን ነው ያመለከተው።

“እርግጥ ነው በመጀመሪያ ደረጃ ጨዋታው ጥንቃቄ የሰፈነበት ነበር። ከሃኖቨርም በኩል እንዲሁ! የሃኖቨር ተጫዋቾች 1-0 መምራታቸው እንድንነሣ ነው ያደረገን። እናም ተገቢውን ምላሽ ለመስጠት ችለናል”

ሌቨርኩዝን ካይዘርስላውተርንን 1-0 በማሸነፍ በሁለተኝነቱ ሲቀጥል በመሠረቱ አሁንም ሻምፒዮን የመሆን ዕድሉን እንደጠበቀ ነው። እርግጥ ዶርትሙንድ ከፈቀደ! በሌላ በኩል የካይዘርስላውተርን አሠልጣኝ ማርኮ ኩርስ የሌቬርኩዝንን የበላይነት አምኖ ነው የተቀበለው።

“እንደማስበው ከሁለቱም በኩል በመሠረቱ ከባድ የሆነ ጨዋታ ነው ያየነው። ዛሬ ሙቀቱም ጠንከር ያለ ነበር። ለነገሩ በመጀመሪያው አጋማሽ በርካታ ዕድሎች ነበሩን። ግን በሁለተኛው አጋማሽ በተከሰተው የግል ችሎታ ጉድለት ለመሸነፍ በቅተናል”                                              
ለማንኛውም ካይዘርስላውተርን በአንደኛው ዲቪዚዮን ውስጥ ለመቆየት ብርቱ ትግል የሚጠብቀው ሲሆን በሌላ በኩል የብዙ ጊዜው ሻምፒዮን ባየርን ሙንሺን  የመጨረሻውን ግላድባህን 1-0 በመርታት ለአውሮፓ የክለቦች ሻምፒዮና ሊጋ ውድድር ማጣሪያ ወደሚያበቃው ወደ ሶሥተኛው ቦታ ከፍ ብሏል። በነገራችን ላይ ባየርን ሙንሺን ከዘንድሮው የአውሮፓ ሻምፒዮና ሊጋ ውድድር ለሩብ ፍጻሜ እንኳ ሳይደርስ በቅርቡ በኢንተር ሚላን ተሸንፎ መውጣቱ አይዘነጋም።                                            
ሃኖቨር ከሶሥት ወደ አራተኛው ቦታ ሲያቆለቁል የሣንት ፓውሊና የሻልከ ግጥሚያ ደግሞ ሻልከ እየመራ ሳለ በ 88ኛው ደቂቃ ላይ መቋረጥ ነበረበት። ለዚሁም ምክንያቱ አንድ ተመልካች ወደ ሜዳ በወረወረው የመጠጥ ኩባያ የመሥመር ዳኛው መመታቱ ነበር። የፌደሬሺኑ የዲሢፕሊን ኮሚሢዮን የሻልከን ድል እንደሚያጸድቅ የሚጠበቅ ሲሆን በሌላ በኩል አስተናጋጁ ክለብ ሣንት ፓውሊ ግን ከባድ ቅጣት የሚጠብቀው ነው የሚመስለው። 

በኢጣሊያ ሤሪያ-አ ኤ.ሢ.ሚላን የከተማ ተፎካካሪውን ኢንተር ሚላንን 3-0 በማሸነፍ አመራሩን ሲያጠናክር ኢንተር በተከታታይ ለስድሥተኛ ጊዜ ሻምፒዮን ለመሆን ያለውን ዕድልም ሳያጨልመው አልቀረም። ኢንተር በሽንፈቱ ከአመራሩ በአምሥት ነጥቦች በመውረድ ወደ ሶሥተኛው ቦታ ሲያቆለቁል ናፖሊ ላሢዮን 4-3 በመርታት ወደ ሁለተኛው ቦታ ከፍ ብሏል። በፈረንሣይ ሊጋ ቀደምቱ ሊል ኬንን 3-1 ሲያሸንፍ የሁለት የቅርብ ተፎካካሪዎቹ የኦላምፒክ ሊዮንና የሬንስ በእኩል-ለእኩል ውጤት መወሰን በጣሙን ነው የጠቀመው።                                                         
ሊል ከሰንበቱ ግጥሚያዎች በኋላ ማርሤይን በሁለተኝነት አስከትሎ በአራት ነጥቦች ልዩነት የሚመራ ሲሆን በኔዘርላንድ ደግሞ የትዌንቴ ኤንሼዴ፣ የአይንድሆፈንና የአያክስ አምስተርዳም ፉክክር እንደቀጠለ ነው። ሶሥቱም ሻምፒዮን የመሆን ዕድል አላቸው። በፖርቱጋል ሊጋ ኤፍ.ሢ.ፖርቶ አንዴም ሳይሽነፍ ለ 19ኛ ጊዜ የአገሪቱ ሻምፒዮን ሊሆን በቅቷል። ፖርቶ ገና አምሥት ግጥሚያዎች ቀርተው ሳለ ለዚህ ክብር የበቃው ከትናንት በስቲያ ሁለተኛውንና ብርቱ ተፎካካሪውን ቤንፊካ ሊዝበንን 2-1 ካሸነፈ በኋላ ነበር። በነገራችን ላይ ቤንፊካ የፖርቱጋልን ሻምፒዮና 32  ጊዜ በማሸነፍ ከሁሉም ቀደምቱ ክለብ ነው።

Trendreiseziel Berlin Flash-Galerie Berlin Marathon

አትሌቲክስ፤ በርሊን/ካሊፎርኒያ

በካሊፎርኒያ-ካርልስባድ ትናንት ተካሂዶ በነበረ የአምሥት ሺህ ሜትር ሩጫ ውድድር በወንዶችና በሴቶችም ኢትዮጵያውያን አሸናፊ ሆነዋል። ደጀን ገብረመስቀል ያለፈውን ሻምፒዮን ኬንያዊውን ኤሊዩድ ኪፕቾጌን በመቅደም በታሪክ አራተኛውን ፈጣን ጊዜ ሲያስመዘግብ አሄዛ ኪሮስም ኬንያዊቱን ፓውሊን ኮሪክዊያንግን በማስከተል አሸንፋለች።

በዚህ በጀርመን ሰንበቱን በተካሄደው 31ኛ የበርሊን ግማሽ ማራቶን ሩጫ ውድድር ደግሞ ኬንያውያን የበኩላቸውን ልዕልና አሳይተዋል። በወንዶች ጆፍሪይ ኪፕሣንግ አሸናፊ ሲሆን እስከ አምሥተኛው ቦታ ተከትለውት የገቡትም በሙሉ ኬንያውያን ነበሩ። መገርሧ ባቻ ከኢትዮጵያ ስድሥተኛ ወጥቷል። በሴቶችም ኬንያዊቱ ቫሌንቲን  ኪፕኬቴር ስታሸንፍ ፋጤ ቶላ ከኢትዮጵያ ሁለተኛ ሆናለች። ሶሥተኛ ሶኒያ ሣሙኤልስ ከብሪታኒያ!

Serbien Tennis Novak Djokovic

ቴኒስ፤ ጆኮቪች የሚበገር አልሆነም

በዓለምአቀፉ የቴኒስ ውድድሮች በያዝነው ዓመት ረቺ ያጣውን የሰርቢያውን ኮከብ ኖቫክ ጆኮቪችን የሚገታ አሁንም እንደጠፋ ነው። ጆኮቪች ትናንት በማያሚ ፍጻሜ ግጥሚያም በዓለም የማዕረግ ተዋረድ ላይ አንደኛ ሆኖ የቆየውን የስፓኙን ተወላጅ ራፋኤል ናዳልን 3-1 በሆነ የምድብ ውጤት ረትቷል። ጆኮቪች በዚሁ 24  ምድብ ጨዋታዎችን ያለማቋረጥ ማሸነፉ ነው። ካለፈው ዓመት ሕዳር ወር ወዲህ አንዴም አልተደፈረም። ናዳል በአንጻሩ ካለፈው ጥቅምት የቶኪዮ ድሉ ወዲህ ስኬት አጥቶ ነው የሚገኘው። በሴቶች ደግሞ የቤላሩሧ ቪክቶሪያ አዛሬንካ ሩሢያዊቱን ማሪያ ሻራፖቫን 6-1, 6-4 ለማሽነፍ በቅታለች። ይህም አስደናቂ ድል ነው።

በእግር ኳስ ለማጠቃለል በአውሮፓ ሻምፒዮና ሊጋ የሩብ ፍጻሜ የመጀመሪያ ግጥሚያዎች በነገው ምሽት ሬያል ማድሪድ ከቶተንሃም ሆትስፐር፤ እንዲሁም ኢንተር ሚላን ከጀርመኑ ክለብ ከሻልከ ይገናኛሉ። በማግሥቱም የሁለቱ የእንግሊዝ ክለቦች የቼልሢይና የማንቼስተር ዩናይትድ የእርስበርስ ግጥሚያ በጉጉት እየተጠበቀ ሲሆን ባርሤሎና የሚጫወተው ደግሞ ከኡክራኒያው ሻክታር ዶኔትስክ ጋር ነው። በአፍሪቃ ሻምፒዮና ሊጋም የሁለተኛው ዙር የመልስ ግጥሚያዎች ሲካሄዱ ኤኒምባ ከናይጄሪያ፣ ሙሉዲያ ከአልጄሪያ፣ አል-ሂላል ከሱዳንና ያለፈው ሻምፒዮን ማዜምቤ ወደፊት ካለፉት መካከል ከፊሉ ናቸው።                                                                   
የግብጹ ታዋቂ ክለብ አል-አህሊም እንዲሁ ወደ ተከታዩ ዙር ሲሻገር በሌላ በኩል በዛማሌክ ግጥሚያ ወቅት ካይሮ ላይ የታየው የስታዲዮም ወረራ ሕዝብን አሳፍሯል። የዛማሌክ ደጋፊዎች ቡድናችን ጎል ተከለከለ በሚል ጨዋታው ሊያበቃ ጥቂት ሲቀር በቁጣ ሜዳውን ሲወሩ ግጥሚያው መቋረጡ ግድ ነበር የሆነው። ተጫዎቾቹ በበኩላቸው የቱኒዚያ አፍሪኬን ክለብ ተጋጣሚዎቻቸውን ከጥቃት ለመጠበቅ ሲሞክሩ ታይተዋል። የግብጽ ጊዜያዊ ወታደራዊ መሪዎችም ድርጊቱን በመኮነን ለቱኒዚያ ይቅርታ ጠይቀዋል።

መሥፍን መኮንን ሂሩት መለሰ