የስፖርት ዘገባ | ስፖርት | DW | 28.03.2011
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ስፖርት

የስፖርት ዘገባ

የሚቀጥለው የጎርጎሮሣውያኑ 2012 ዓ.ም. የአፍሪቃና የእውሮፓ እግር ኳስ ዋንጫ ፍጻሜ ውድድሮች የሚካሄዱበት ነው።

default

የጀርመኑ ጎል አግቢ ሚሮስላቭ ክሎዘ

ለዚሁ በሚካሄደው ማጣሪያ ውድድርም ሰንበቱን በሁለቱም ክፍለ-ዓለማት በርካታ ግጥሚያዎች ተካሂደው ነበር። ከነዚሁ አንዱ በናይጄሪያና በኢትዮጵያ መካከል የተካሄደው ሲሆን የኢትዮጵያ ቡድን መሸነፍ የማለፍ ዕድሉን ከወዲሁ ሳይቀጨው የደከመ ሳያደርገው የቀረ አይመስልም። አዲሱ የፎርሙላ-አንድ አውቶሞቢል እሽቅድድም የውድድር ወቅትም ትናንት አውስትራሊያ ውስጥ ባለፈው ሻምፒዮን በዜባስቲያን ፌትል አሸናፊነት ተከፍቷል።

የአውሮፓ ዋንጫ ማጣሪያ

በሚቀጥለው ዓመት ኡክራኒያና ፖላንድ በጋራ ለሚያስተናግዱት የአውሮፓ እግር ኳስ ዋንጫ ውድድር ሰንበቱን በርካታ የምድብ ግጥሚያዎች ተካሂደዋል። በምድብ-አንድ ጀርመን ካዛክስታንን 4-0 በመቅጣት በአምሥተኛ ግጥሚያዋም በድል ለመቀጠል በቅታለች። እርግጥ የጀርመን ብሄራዊ ቡድን ለድል ቢበቃም በአጨዋወቱ ድክመት የተቆጡትና የፉጨት ናዳ ያወረዱት ተመልካቾች ጥቂቶች አልነበሩም። ቡድኑ በተለይም በሁለተኛው አጋማሽ የሚጠበቅበትን አለማሳየቱን አሠልጣኙ ዮአኺም ሉቭም ቢሆን አምኖ ነው የተቀበለው።
“በዚህ ጨዋታ በተጋጣሚያችን ሣይሆን በራሳችን መለካት እንደመበረብን ግልጽ የሆነ ነገር ነው። የመጀመሪያው አጋማሽ መልካም ነበር። ሶሥት ጎሎች ለማስገባትና ጥሩ ጨዋታ ለማሳየት ችለናል። እንግዲህ የመጀመሪያው አጋማሽ ተጋጣሚያችን በመከላከል የሚጫወት መሆኑ ሲታሰብ አርኪ ነበር ለማለት ይቻላል። በሁለተኛው አጋማሽ ግን ፍጥነታችን እየቀነሰና ኳስ ወዲያ ወዲህ መግፋቱ እየጎላ ሲሄድ ነው የታየው”

ያም ሆነ ይህ ምድብ-ሁለትን አየርላንድ፣ ሩሢያና ስሎቫኪያ በእኩል አሥር ነጥብ ተከታትለው የሚመሩ ሲሆን በምድብ-ሶሥት ኢጣሊያ የቅርብ ተፎካካሪዋን ስሎቬኒያን 1-0 በማሸነፍ የበላይነቱን ይዛለች። በተቀሩት ምድቦችም እንደተጠበቀው እንግሊዝ፣ ፈረንሣይ፣ ኔዘርላንድና ስፓኝም እንዲሁ ግንባር ቀደም እንደሆኑ ናቸው። በነገው ዕለትም በርካታ ተከታይ ግጥሚያዎች ይካሄዳሉ።

Fußball WM 2010 - Elfenbeinküste Didier Drogba

ዲዲየር ድሮግባ

የአፍሪቃ ዋንጫ ማጣሪያ ግጥሚያዎች

በአፍሪቃም በሚቀጥለው ዓመት በኤኩዋቶሪያል ጊኒና በጋቦን የጋራ አስተናጋጅነት ለሚካሄደው የአፍሪቃ ዋንጫ ፍጻሜ ዙር ለማለፍ በሚደረገው የምድቦች ማጣሪያ ውድድር አይቮሪ ኮስት በሶሥተኛ ግጥሚያዋ ለሶሥተኛ ድል በመብቃት የወደፊት ዕድሏን አጠናክራለች። አይቮሪ ኮስት ቤኒንን 2-1 ስትረታ ሁለቱንም ጎሎች በማስቆጠር ለቡድኑ የድል ዋስትና የሆነው የቼልሢው ዲዲየር ድሮግባ ነበር። በትናንቱ ግጥሚያዎች ጋና፣ ናይጄሪያና ዛምቢያም በየፊናቸው ሲያሸንፉ በሰሜን አፍሪቃ በጉጉት ሲጠበቅ በቆየው የማግሬብ ግጥሚያም አልጄሪያ በአንዲት የፍጹም ቅጣት ምት ጎል ሞሮኮን ለማሸነፍ ችላለች።

ከብዙ በጥቂቱ ለመጥቀስ ምድብ-ሁለትን ጊኒ ናይጄሪያን አስከትላ በአንደኝነት የምትመራ ሲሆን ሶሥተኛዋ ኢትዮጵያ ናት። ምድብ-አራትን ማዕከላዊት አፍሪቃ ሬፑብሊክ ምድብ-አምሥትን ደግሞ ሤኔጋል በቀደምትነት ይመራሉ። እንደ አይቮሪ ኮስት ሁሉ ከዋና ዋናዎቹ መካከል ደቡብ አፍሪቃና ጋናም የየምድባቸው ቁንጮዎች ናቸው። በምድብ-ስሥት ውስጥ የብዙ ጊዜዋ የዋንጫ ባለቤት ግብጽ ትናንት በደቡብ አፍሪቃ 1-0 ስትረታ የምድቧ መጨረሻ አራተኛ ናት። እንግዲህ የአገሪቱ የለውጥ እንቅስቃሴ በቡድኑ ዝግጅት ላይ ተጽዕኖ ማሳደሩ አልቀረም።
መለስ ብለን በኢትዮጵያ ላይ እናተኩርና የአገሪቱ ብሄራዊ ቡድን ትናንት አቡጃ ላይ በናይጄሪያ 4-0 ተሸንፎ ተመልሷል። ውጤቱ አይጠበቅም ባይባልም የሽንፈቱ መጠን ግን ብዙ የሚያጠያይቅ መሆኑ አልቀረም። ለመሆኑ ከዚህ አንጻር የቡድኑ ወደፊት የመዝለቅ ዕድል እስከምን ነው? በኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌደሬሺን ውስጥ የግንኙነት ጉዳይ ሃላፊ የሆኑትን አቶ መላኩ አየለን አነጋግረናል።

Sebastian Vettel 27.03.2011

ዜባስቲያን ፌትል

ፎርሙላ-አንድ እሽቅድድም

ትናንት አውስትራሊያ ውስጥ በተከፈተው አዲስ የፎርሙላ-አንድ አውቶሞቢል ውድድር ያለፈው ወቅት ሻምፒዮን ጀርመናዊው ዜባስቲያን ፌትል ከመጀመሪያ እስከ መጨረሻው በመምራት ለድል በቅቷል። የብሪታኒያው ሉዊስ ሃሚልተን ሁለተኛ ሲወጣ ሶሥተኛ የሆነው የሩሢያው ተወላጅ ቪታሊ ፔትሮቭ ነው። ባለፈው ዓመት ወደ ውድድሩ የተመለሰው የሰባት ጊዜው የዓለም ሻምፒዮን ሚሻኤል ሹማኸር ደግሞ ትናንትም ለስኬት ሳይበቃ ቀርቷል። 11ኛ ነው የሆነው።

በማያሚ የሶኒይ-ኤሪክሰን ቴኒስ ውድድር የሰርቢያው ኖቫክ ጆኮቪች የአሜሪካ ተጋጣሚውን ጀምስ ብሌክን በለየለት ሁኔታ 6-2, 6-0 በመርታት በአዲሱ ዓመት ሳይሸነፍ ቀጥሏል። በውድድሩ ወደ አራተኛው ዙር ያለፈው ጆኮቪች ከዚህ ቀደም ሃያላኑን ሮጀር ፌደረርንና ራፋኤል ናዳልን ጭምር ማሸነፉ የሚታወቅ ነው። በማያሚው ውድድር ሶሥተኛ ዙር አርጄንቲናዊው ሁዋን-ማርቲን-ዴል-ፖትሮ የስዊድኑን ሮቢን ሶደርሊንግን 6-3, 6-2 ሲረታ የአሜሪካው ማርዲይ ፊሽም የፈረንሣይ ተጋጣሚውን ሚሼል ሎድራን አሰናብቷል።
የስፓኙ ዴቪድ ፌሬርና አሜሪካዊው ጆን ኢስነርም ወደ አራተኛው ዙር ካለፉት መካከል ናቸው። በሴቶች ደግሞ ማሪዮን ባርቶሊ፣ ፍራንቼስካ ሺያቮኔ፣ አና ኢቫኖቫ፣ ኪም ክላይስተርስና ቬራ ዝቮናሬቫ ወዘተ ወደተከታዩ ዙር ተሻግረዋል።

መሥፍን መኮንን

ተክሌ የኋላ

ተዛማጅ ዘገባዎች