የስፖርት ዘገባ | ስፖርት | DW | 21.03.2011
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ስፖርት

የስፖርት ዘገባ

ሰንበቱን ስፓኝ-ፑንታ ኡምብሪያ ውስጥ ተካሂዶ በነበረው የዓለም አገር አቋራጭ ሩጫ ውድድር የኢትዮጵያና የኬንያ አትሌቶች ፉክክር በኋላኛው የበላይነት ተፈጽሟል።

default

ዓለምአቀፍ የአትሌቲክስ

ስፓኝ ውስጥ ሰንበቱን ተካሂዶ በነበረው የዓለም አገር አቋረጭ ሩጫ ውድድር የኬንያ አትሌቶች ከስምንት ስድሥቱን የወርቅ ሜዳሊያዎች በማግኘት ፍጹም የበላይነት አሳይተዋል። ኬንያውያኑ ይሁንና በወንዶች በቀለጠፈ አሯሯጥ ውድድሩን በድል የፈጸመውን የኢትዮጵያን ድንቅ አትሌት ኢማኔ መርጋን ሊገቱ አልቻሉም። ይህም ሆኖ ኬንያውያኑ ራጮች ደቡብ ኮሪያ-ዴጉ ላይ በፊታችን ነሐሴ ወር በሚካሄደው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና እጅግ ጠንካራ ቡድን ለማሰለፍ እንደሚችሉ ነው የስፓኙ ውድድር ያመለከተው።

በትናንቱ አገር አቋራጭ ሩጫ ኢማኔ መርጋን ተከትለው ከሁለት እስከ አምሥተኛው ቦታ በመከታተል የገቡት የኬንያ አትሌቶች ነበሩ። የኡጋንዳው ስቴፈን ኪፕሮቲች ስድሥተኛ ሲወጣ ሁነኛው መሥፍን ደግሞ ሩጫውን በስምንተኝነት በመፈጸም ከቀደምቱ አሥር አትሌቶች አንዱ ሊሆን በቅቷል። በሴቶቹ ውድድርም ኬንያውያን ሲያመዝኑ ሩጫው የቪቪያን ቼሩዮትና የሊኔት ማሣይ ሆኖ ነው ያለፈው። ሁለቱ ጠንካራ አትሌቶች በርሊን ላይ በ 2009 ተካሂዶ በነበረው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና የአምሥት ሺህና የአሥር ሺህ ሜትር አሸናፊ እንደነበሩ የሚታወስ ነው።

የስፓኙ ውድድር በዴጉው የዓለም ሻምፒዮና ለመሳተፍ በኬንያ ሴት አትሌቶች መካከል የሚደረገው ፉክክር ቀላል እንደማይሆንም አመልክቷል። በትናንቱ ሩጫ ቼሩዮትና ማሣይ በቀደምትነት ተከታትለው ሲገቡ ለሶሥተኝነት የበቃችው ብቸኛዋ የምዕራቡ ዓለም አትሌት አሜሪካዊቱ ሻሌን ፍላናጋን ነበረች። በተቀረው ከአንድ እስከ አሥር ተዋረድ ላይ ሶሥት ኬንያውያት ሲመዘገቡ ከኢትዮጵያም መሰለች መልካሙ አራተኛ፣ ውዴ አያሌው ስድሥተኛ፤ ገንዘቤ ዲባባ ዘጠነኛ፤ እንዲሁም በላይነሽ ኦልጂራ አሥረኛ ሆነዋል።

ኬንያ በወጣት ሯጮቿም ቀደምት ለመሆን ችላለች። በወንዶች ጄፍሪይ ኪፕሣንግ የኡጋንዳውን ቶማስ ዬኮንና የአገሩን ልጅ ፓትሪክ ምዊክያን አስከትሎ ሲያሸነፍ በሴቶች ደግሞ ፌይት ኪፕዬጎን ለአንደኝነት በቅታለች። የኢትዮጵያ አትሌቶችም ገነት አያሌው ሁለተኛ፤ አዝመራ ገብሩ ሶሥተኛ፤ እንዲሁም ዋጋነሽ መካሻ አራተኛ ለመሆን ችለዋል። በአጠቃላይ በቡድን በወንዶች ኬንያ አንደኛ፣ ኢትዮጵያ ሁለተኛና ኡጉንዳ ሶሥተኛ ሲወጡ በሴቶችም እንዲሁ ኬንያ አንደኛ፤ ኢትዮጵያ ሁለተኛ፤ እንዲሁም ዩ.ኤስ.አሜሪካ ሶሥተኛ ሆነዋል።

በትናንትናው ዕለት ኢጣሊያ ውስጥ ተካሂዶ በነበረው የሮማ ማራቶን ሩጫ ደግሞ ኬንያና ኢትዮጵያ ድሉን ለመከፋፈል ችለዋል። በወንዶች ዲክሰን ቹምባ ሁለት ኢትዮጵያውያንን አስከትሎ ሲያሸንፍ በሴቶች ድሉ ከአንድ እስከ ሶሥት የኢትዮጵያ ሆኗል። በጥሩ ጊዜ በአንደኝነት ያሸነፈችው ፍሬሕይወት ዳዶ ነበረች። በሶውል ዓለምአቀፍ ማራቶንም እንዲሁ ሮቤ ጉታ ለአንደኝነት ስትበቃ በወንዶች የሞሮኮው አብደርራሂም ጉምሪ አሸንፏል።
በወንዶቹ ውድድር የኮሪያው ጄኦንግ-ጂን-ሂዩንክ ሁለተኛ፤ የሩሢያው ኦሌግ ኩልኮቭ ሶሥተኛ ሲወጡ ወጋየሁ ግርማና ደረጀ አበራም ተከታዮቹ ሆነዋል። በሴቶች ሮቤ ጉቱ ስታሸንፍ ቻይናዊቱ ያናን ዋይ ሁለተኛ፤ የኮሪያዋ ጄዮንግ-ዩን-ሄም ሶሥተኛ ወጥታለች። በኒውዮርክ ግማሽ ማራቶን ሩጫ ደግሞ ከሶማሊያ የመነጨው የብሪታኒያ አትሌት ሞ ፋራህ የኢትዮጵያ ተፎካካሪውን ገቤ ገብረማርያምን በሁለት ሤኮንዶች ልዩነት በማስከተል አሸንፏል። በሴቶቹ ሩጫ ኬንያዊቱ ካሮሊን ሮቲች ቀዳሚ ሆናለች።

Fußball Champions League Olympique Marseille Manchester United

የአውሮፓ ሊጋዎች የእግር ኳስ ሻምፒዮና

በኢጣሊያ ሤሪያ-አ ኢንተርና ናፖሊ በዚህ ሰንበት ድንገት ያፈተለከ የመሰለውን የኤ.ሢ.ሚላንን ጠረን ለማሽተት ሲቃረቡ በዚህ በጀርመን ቡንደሊጋም የዶርትሙንድ የ 12 ነጥቦች ልዩነት አመራር ወደ ሰባት እስከመጥበብ ነው የደረሰው። በአንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ እንጀምርና የማንቼስተር ዩናይትድ አመራር የቅርብ ተፎካካሪው አርሰናል ከአልቢዮን ሁለት-ለሁለት በመለያየቱ ወደ አምሥት ነጥቦች ልዩነት ሊሰፋ ችሏል።
አርሰናል ዝቅተኛውን ክለብ ባለማሸነፉ ቢቆጭም በሌላ በኩል ሁለት-ለዜሮ ከተመራ በኋላ እኩል-ለእኩል በመውጣቱም ዕድለኛ ነው ሊባል ,ይችላል። ዕድልን ካነሣን ማንቼስተር ዩናይትድም ቦልተን ወንደረርስን ያሸነፈው ቡልጋሪያዊ ኮከቡ ዲሚታር ቤርባቶቭ ጨዋታው ሊያበቃ ሁለት ደቂቃዎች ብቻ ሲቀሩ ባስቆጠራት አንዲት ጎል ነበር። ቼልሢይ በበኩሉ በዚህ ሰንበት ሶሥተኛውን ማንቼስተር ሢቲይን ሁለት-ለባዶ በማሸነፍ በቦታው ተተክቷል። ከማንቼስተር ሢቲይ ቀጥሎ ቶተንሃም ሆትስፐር አምሥተኛ ሲሆን ሊቨርፑል ስድሥተኛ ነው።

በስፓኝ’ ፕሪሜራ ዲቪዚዮን ለሻምፒዮንነቱ የሚፎካከሩት ሁለት ክለቦች ባርሤሎናና ሬያል ማድሪድ የየበኩላቸውን ግጥሚያ በማሸነፋቸው ባርሣ በአምሥት ነጥቦች ብልጫ መምራቱን እንደቀጠለ ነው። ሬያል የከተማ ተፎካካሪውን አትሌቲኮ ማድሪድን 2-1 ሲረታ ባርሤሎናም ጌታፌን በተመሳሳይ ውጤት ነበር ያሸነፈው። ቫሌንሢያ በሤቪያ 1-0 ተሸንፎ ከሶሥት ወደ አራተኛው ቦታ ሲያቆለቁል ቪላርሬያል በአንጻሩ ቢልባኦን በተመሳሳይ ውጤት በመርታት በቦታው ተተክቷል። ሆኖም በሶሥተኛውና በአንደኛው መካከል የ 24 ነጥቦች ልዩነት በመኖሩ ቪላርሬያል እንደ ባርሣ ወይም እንደ ማድሪድ ስለ ሻምፒዮንነት ሊያልም አይችልም።

Deutschland Fußball Bundesliga Trainerwechsel Bayer Leverkusen Jupp Heynckes

የጀርመን ቡንደስሊጋ

በጀርመን ቡንደስሊጋ ውድድር በዶርትሙንድ የለየለት አመራር ከወዲሁ ያለቀለት መስሎ የቆየው ሻምፒዮና ከትናንት ወዲህ የሁለት ክለቦች ፉክክር የሰፈነበት ሊሆን እንደሚችል አዝማሚያ እየታየበት ነው። እስከ ቅርቡ 12 ነጥብ ይደርስ የነበረው የዶርትሙንድ አመራር ቀስ በቀስ እየቀነሰ ሲመጣ በአጭር ጊዜ ውስጥ ወደ ሰባት አቆልቁሏል። ዶርትሙንድ ባለፈው ቅዳሜ ከማይንስ ባደረገው ግጥሚያ በገዛ ሜዳው 1-1 ሲለያይ ሁለተኛው ሌቨርኩዝን ትናንት በበኩሉ ጨዋታ ሻልከን 2-0 በማሸነፍ አጋጣሚውን በሚገባ ነው የተጠቀመው። አሠልጣኙን ዩፕ ሃይንከስን በተለይም ያስደሰተው የቡድኑ የአጨዋወት ብስለት ጭምር ነበር።

“አስፈላጊው ሞራል አለን። ለነገሩ ተጫዋቾቹ ጥሩ ባህርይ ያላቸውና እርስበርስም የሚጣጣሙ ናቸው። በዛሬው ጨዋታ የመጀመሪያው አጋማሽ በተለይ ግሩም ነበር። በሁለተኛው አጋማሽም ቢሆን 45ቱን ደቂቃዎች ያሳለፍነው በበሰለ አጨዋወት ነው”

ሌቨርኩዝን ምናልባትም ባልጠበቀው ሻምፒዮንነት ላይ ማለም ሲጀምር በሌላ በኩል ለመጪው የአውሮፓ ሻምፒዮና ሊጋ ውድድር ማጣሪያ ለሚያበቃው ሶሥተኛ ቦታ በሚደረገው ፉክክር ሃኖቨርና ባየርን ሙንሺን የየበኩላቸውን ዕርምጃ አድርገዋል። በወቅቱ ሃኖቨር ሶሥተኛ ሲሆን ባየርን በሁለት ነጥቦች ዝቅ ብሎ አራተኛ ነው። የቡንደስሊጋው የውድድር ወቅት ሊጠቃለል ከእንግዲህ የቀሩት ሰባት ግጥሚያዎች ሲሆኑ 18 ክለቦችን ካቀፈው አንደኛ ሊጋ ወደታች ላለመከለስ በርከት ባሉ ክለቦች መካከል የሚደረገው ፉክክርም በጣሙን ተጠናክሯል። ለግንዛቤ ያህል ዘጠነኛውን ክለብ ከ 18ኛው የሚለዩት ስድሥት ነጥቦች ብቻ ናቸው።

በኢጣሊያው ሤሪያ-አ ቀደምቱ ኤ.ሢ.ሚላን በፓሌርሞ 1-0 ሲረታ ይሄም አመራሩ እንዲጠብ ምክንያት ነው የሆነው። ዘንድሮ በጅምሩ ዕድል የከዳው መስሎ የታየው ኢንተር ሚላን ድንገት ወደ ላይ በማንሰራራት የከተማ ተፎካካሪውን ኤ.ሢ..ሚላንን በሁለት ነጥብ ልዩነት ብቻ ሲቃረብ ናፖሊም አንዲት ነጥብ ወረድ ብሎ ሶሥተኛ ነው። የኢጣሊያው ሻምፒዮና እንግዲህ ስምንት መጪ ግጥሚያዎች ቀርተው ገና ምኑም አልለየለትም።

በፈረንሣይ ሊጋ ከ 57 ዓመታት ወዲህ ሻምፒዮን መሆኑ ያልተሳካለት ሊል ዘንድሮ ሕልሙን ለማሳካት ወደፊት እየገሰገሰ ነው። ማርሤይን በአራት ነጥቦች ልዩነት አስከትሎ ይመራል። በኔዘርላንድም አይንድሆፈን በአንዲት ነጥብ ብልጫ ኤንሼዴን እያሰተለ ሲሆን በፖርቱጋል ሻምፒዮና ደግሞ የፖርቶ አመራር ወደ 16 ነጥቦች ከፍ ብሏል። በግሪክ ሱፐር-ካፕ ፍጻሜ ግጥሚያ ኦሊምፒያኮስ ፒሬውስ ኤ.ኢ.ኬ.አቴንን 6-0 በማሸነፍ ለ 38ኛ ጊዜ ዋንጫውን ወስዷል። ክለቡ በሊጋው ሻምፒዮና ደግሞ ሶስት ጨዋታዎች ብቻ ቀርተው በአሥር ነጥቦች እየመራ ነው።

Caroline Wozniacki Tennis Dänemark U.S. Open Flash-Galerie

ዓለምአቀፍ ቡጢና ቴኒስ

የኡክራኒያው ተወላጅ ቪታሊ ክሊችኮ በዓለም የቡጢ ካውንስል የከባድ ሚዛን ግጥሚያ ኩባዊውን ኦድላነር ሶሊስን በመጀመሪያው ዙር ሶሥት ደቂቃዎች ውስጥ በመዘረር ማዕረጉን ለማስከበር ችሏል። የ 2004 ዓ.ም. የኦሎምፒክ ሻምፒዮን ሶሊስ በኮሎኝ ከተማ በተካሄደው ግጥሚያ ሲሽነፍ ለመጀመሪያ ጊዜ መሆኑ ነበር። በአጭሩ የተቀጨውን ግጥሚያ ለአንድ አፍታም ቢሆን 11 ሚሊዮን ጀርመናውያን በቴሌቪዥን ተከታትለዋል። ካናዳ ውስጥ የሚኖረው የሩሜኒያ ተወላጅ ሉሢያን ቡትም የሰሜን አየርላንዱን ብራያን ሜጊን በአሥረኛው ዙር ላይ በበቃኝ በማሸነፍ የዓለም ቡጡ ፌደሬሺን ልዩ የመካከለኛ ክብደት ማዕረጉን ለሰባተኛ ጊዜ አስከብሯል።

በቴኒስ ደግሞ በካሊፎርኒያ-የኢንዲያን ዌልስ ዓለምአቀፍ ውድድር ኖቫክ ጆኮቪች ትናንት ግንባር ቀደሙን ራፋኤል ናዳልን በለየለት ሁኔታ 4-6, 6-3, 6-2 በሆነ ውጤት በማሸነፍ ዘንድሮ በቀላሉ የማይበገር መሆኑን አስመስክሯል። የሰርቢያው ተወላጅ በያዝነው 2011 ዓ.ም. በተከታታይ ለ 18ኛ ድሉ መብቃቱ ነው። በሴቶች በዓለም የማዕረግ ተዋረድ ላይ አንደኛ የሆነችው የዴንማርኳ ካሮሊን ቮዝኒያችኪ እንደተጠበቀው ፈረንሣዊቱን ማሪዮን ባርቶሊን 6-1, 2-6, 6-3 ረትታለች።

መሥፍን መኮንን
አርያም ተክሌ