የስፖርት ዘገባ | ስፖርት | DW | 07.02.2011
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ስፖርት

የስፖርት ዘገባ

ባለፈው ሰንበት በዓለምአቀፍ ደረጃ በርካታ የአዳራሽ ውስጥ የአትሌቲክስ ውድድሮች ሲካሄዱ የኢትዮጵያ አትሌቶችም በየቦታው ግሩም ተሳትፎዋል።

default

ወጣቱ አትሌት የኔው አላምረው በዚህ በጀርመን-በሽቱትጋርት አዲስ ክብረ-ወስን ማስመዝገቡ ለምሳሌ አንዱ አስደሳች ውጤት ነው። የአውሮፓ ቀደምት ክለቦች የእግር ኳስ ሻምፒዮናም ድንቅ ጨዋታዎች በታዩበት ሁኔታ ሲቀጥል የያዝነው ሣምንት ደግሞ በዓለምአቀፍ ደረጃ በርካታ የወዳጅነት ግጥሚያዎች የሚካሄዱበትም ነው።
የአዳራሽ’ ውስጥ አትሌቲክስ ውድድሮች

በዚህ በጀርመን ሽቱትጋርት ከተማ ውስጥ በተካሄደው በዘንድሮው ዓለምአቀፍ የአዳራሽ ውስጥ ውድድር የኔው አላምረው በአስደናቂ ውጤት ብቸኛው የኢትዮጵያ አሸናፊ አትሌት ለመሆን በቅቷል። የኔው አላምረው ትናንት በሶሥት ሺህ ሜትር ሩጫ ሲያሸንፍ ውድድሩን የፈጸመውም በዚህ ርቀት ለረጅም ጊዜ ጸንቶ የቀየውን የኬንያዊውን አትሌት የዳኒየል ኮሜንን የዓለም ክብረ-ወሰን በማሻሻል ነበር። የሃያ ዓመት ወጣቱ አትሌት ስምና ዝና ያላቸውን አትሌቶች ጥሎ በመሄድ ሩጫውን በሰባት ደቂቃ ከ 27.80 ሤኮንድ ጊዜ ሲፈጽም በዚህም የእስካሁኑን ሶሥተኛ ፈጣን ሰዓት ማስመዝገቡ ነው።
በዚሁ ሩጫ ሁለተኛና ሶሥተኛ የወጡት ኬንያውያኑ አውጉስቲን ቾጌና ኤሊዩድ ኪፕቾጌ ናቸው። የኬንያ ወንድ አትሌቶች በሌላ በኩል በ 1,500 ሜትር ሩጫ አንደኛና ሁለተኛ በመሆን የበላይነቱን ሲይዙ በሴቶች ሶሥት ሺህ ሜትርም በሜርሢይ እንጆሮጌ አማካይነት አሸናፊ ሆነዋል። የአፍሪቃን አትሌቶች በተመለከተ በወንዶች 800 ሜትር ለድል የበቃው ደግሞ ሱዳናዊው አቡባከር ካኪ ነበር። በተቀሩት የስፖርት ዓይነቶች በአጭር ርቀት ሩጫ፣ ዝላይና ውርወራ እንደተለመደው አውሮፓውያኑ አይለው ታይተዋል።

ሰንበቱን አሜሪካ ውስጥ በተካሄደው የቦስተን የአዳራሽ ውስጥ አትሌቲክስ ውድድርም የሶሥት ሺው ሜትር ሩጫ ድል የኢትዮጵያ ነበር። የ 21 ዓመቱ ወጣት አትሌት ደጀን ገ/መስቀል ምንም እንኳ መሮጥ እንደጀመረ ብዙ ሳይቆይ አንድ ጫዋው ወልቆ ቢቀርበትም አስቸጋሪው ሁኔታ ሳይበግረው አሸናፊ ለመሆን ችሏል። ደጀን ለዚህ አስደናቂ ድል የበቃው ከሶማሊያ የመነጨውን የብሪታኒያ ቀደምት አትሌት ሞ ፋራህን ከኋላው በማስቀረት ነው። ወጣቱ ኢትዮጵያው በአንድ ጫማ መሮጡ ቀላል ነገር እንደነበረ ሩጫውን ከፈጸመ በኋላ አስረድቷል።

በሴቶች ሶሥት ሺህ ሜትር ሩጫ ግን የ 1.500 ሜትር የዓለም ሻምፒዮን የሆነችው ኢትዮጵያዊት አትሌት ቃልኪዳን ገዛኸኝ ያሰበችው አልሆነላትም። ቃልኪዳን ሩጫውን የፈጸመችው በአራተኝነት ነው። በዚሁ ሩጫ ኬንያዊቱ ሣሊይ ኪፕየጎ ስታሸንፍ አሜሪካዊቱ ጄኒይ ሲምሰን ሁለተኛ፤ እንዲሁም ሜጋን ራይት ከካናዳ ሶሥተኛ ወጥታለች። በተቀረ የአሜሪካ አትሌቶች ከ 60 ሜትር እስከ ማይል ቀደምቱ ሲሆኑ በማይሉ ሩጫ ሄኖክ ለገሰም አራተኛ ሆኗል።

ሩሢያዊቱ የምርኩዝ ዝላይ የኦሎምፒክ ሻምፒዮንና የዓለም ክብረ-ወሰን ባለቤት የለና ኢዚንባየቫ በአስደናቂ ሁኔታ ለድል በመብቃት ከ 11 ወራት መተጓጎል በኋላ ወደ ውድድሩ መድረክ በስኬት ለመመለስ ችላለች። ኢዚንባየቫ ለዚህ ስኬት የበቃችው ትናንት በሩሢያው ዓመታዊ የክረምት የአዳራሽ ውስጥ ውድድር 4,81 ሜትር ከፍታን በመዝለል ነው። ሩሢያዊቱ አትሌት እስካሁን በዚህ የስፖርት ዓይነት 27 የዓለም ክብረ-ወሰኖችን ያስመዘገበች ሲሆን በዕውነትም አድናቂዎቿ እንደሚጠሯት የምርኩዝ ዝላይ ንግሥት ናት።

በተረፈ አሜሪካዊው ኤሽተን ኢተን ኤስቶኒያ ውስጥ በተካሄደ የአዳራሽ ውስጥ ውድድር በቅይጥ ስፖርት የራሱን የዓለም ክብረ-ወሰን በ 69 ነጥቦች ሲያሻሽል በጃፓን የኦይታ ማራቶን ደግሞ የሞሮኮው አትሌት አሕመድ ባዳይ ኬንያዊውን ዳኒየል እንጄንጋን በሁለተኝነት በማስከተል አሸንፏል። በነገራችን ላይ ከወዲሁ ለማስታወስ ያህል የዓለም የአዳራሽ ውስጥ የ 1.500 ሜትር ሻምፒዮን ደረሰ መኮንንና ቃልኪዳን ገዛኸኝ በፊታችን የካቲት 12 ቀን በእንግሊዝ-በርሚንግሃም ግራንድ-ፕሪ ውድድርም ይሳተፋሉ።

1. Fußball Bundesliga - 1. FC Köln gegen FC Bayern München

የአውሮፓ እግር ኳስ ሊጋና የወዳጅነት ግጥሚያዎች

በስፓኝ ፕሪሜራ ዲቪዚዮን የባርሤሎና የወደፊት ግስጋሤ ሳይገታ ቀጥሏል። ባርሣ አትሌቲኮ ማድሪድን 3-0 ሲረታ ይህም ያለማቋረጥ 15ኛ የሊጋ ድሉ መሆኑ ነው። የቡድኑ ኮከብ ያለፈው ዓመት የዓለም ድንቅ ተጫዋች ሊዮኔል ሜሢም በሰንበቱ ጨዋታ 23ኛና 24ኛ ጎሎቹን በማስቆጠር ከሬያል ማድሪዱ ኮከብ ከክሪስቲያኖ ሮናልዶ ሊስተካከል በቅቷል። ሬያል ማድሪድም ሬያል ሶሲየዳድን 4-1 አሸንፏል። እስካሁን ከተካሄዱት 22 ግጥሚያዎች በኋላ ባርሤሎና በ 61 ነጥቦች ሊጋውን በአንደኝነት የሚመራ ሲሆን ሬያል ሰባት ነጥቦች ዝቅ ብሎ ሁለተኛ ነው፤ ሶሥተኛው ቪላርሬያል ደግሞ በሌቫንቴ 1-0 በመረታቱ ከሬያል ማድሪድ ያለው ልዩነት ወደ ዘጠኝ ነጥቦች ሰፍቷል።

በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ ሰንበቱ በተለይም የሊቨርፑል ነበር ለማለት ይቻላል። በዘንድሮው ውድድር ጅማሮው ያልቀናው ታዋቂ ክለብ ቀስ በቀስ እየተነሣ ሲሆን ትናንት በቼልሢይ ሜዳ 1-0 በማሸነፍ በደጋፊዎቹ ዘንድ የቀድሞ ትውስትን ነበር የቀሰቀሰው። በሌላ በኩል ከሊቨርፑል ወደ ቼልሢይ የተሻገረው የስፓኝ አጥቂ ፌርናንዶ ቶሬስ በአዲሱ ክለብ ያደረገው ጅማሮ የቀና አልሆነም። ማንቼስተር ዩናይትድ የሰንበት ግጥሚያውን 2-1 በማሸነፍ በአመራሩ ሲቀጥል ሁለተኛው አርሰናል በአንጻሩ ከኒውካስል ዩናይትድ 4-4 ብቻ በመለያየቱ የሁለቱ ልዩነት ወደ አራት ነጥቦች ሰፍቷል። ማንቼስተር ሢቲይ ከአርሰናል አንዲት ነጥብ ዝቅ ብሎ ሶሥተኛ ሲሆን አራተኛው ቼልሢይ ነው።

በጀርመን ቡንደስሊጋ ውድድር ቀደምቱ ቦሩሢያ ዶርትሙንድ ምንም እንኳ ከሻልከ ባዶ-ለባዶ ቢለያይም ተከታዮቹ ክለቦች በመሽነፋቸው አመራሩን ወደ 12 ነጥቦች ማስፋቱ ሆኖለታል። ዶርትሙንድ በዚህ ሰንበትም እንደተለመደው ጠንካራ ጨዋታ ሲያሳይ ድሉ ያመለጠው በተለይም በሻልከው በረኛ በማኑዌል ኖየር ጥንካሬ ነው። የሆነው ሆኖ የሻልከው በረኛ ማኑዌል ኖየር እንዳለው በምሽቱ እንደ ጀግና ከመወደሱ ይልቅ ቡድኑ ማሸነፉን በመረጠ ነበር።

“አሸንፈን ቢሆን ኖሮ ለጀግንነት በበቃሁ ነበር። እርግጥ ከጎል አግቢው ጋር በአንድነት! ግን በጨዋታው ዶርትሙንድ እንጂ እኛ ብዙ የጎል ዕድል አልነበረንም። እናም አንዲት ነጥብ ይዘን መሄዳችንን ራሱን እንደ ስኬት ነው የምቆጥረው። በተቀረ ከዚሁ ትምሕርት በመቅሰም የበለጠ ነጥብ ለማግኘት እንደምንጥር ተሥፋ አደርጋለሁ”
ሁለተኛው ሌቨርኩዝን በኑርንበርግ 1-0 ሲረታ ሰንበቱን ከሁሉም በላይ ያስደነቀው ታላቁ ባየርን ሙንሺን ኮሎኝን 2-0 እየመራ ካረፈ በኋላ በመጨረሻ 3-2 መሽነፉ ነው። በዚሁም ለሻምፒዮንነት የነበረው ተሥፋ ጨርሶ ሳያከትምለት አልቀረም። ለኮሎኝ በአንጻሩ አሠልጣኙ ፍራንክ ሼፈር እንዳለው ዕለቱ የፌስታ ነበር።

“ማንኛውንም ድላችንን ከቡድኑ ጋር ሆኜ በተለየ ደስታ ነው የማጣጥነው። ምክንያቱም በጀርመን ቡንደስሊጋ ውስጥ ሶሥት ነጥቦች ማግኘት ሁሌም የተለየ ነገር ነው። ሁሌም ፌስታ ነው ማለት ነው። በተለይ ይህን መሰሉ ጨዋታ ከባየርን ሙንሺን ጋር ሲሆን ደግሞ የበለጠ ትርጉም ይኖረዋል”

በኢጣሊያ ሤሪያ-አ ቀደምቱ ኤ.ሢ.ሚላን ከጄኖዋ 1-1 ብቻ ሲለያይ አመራሩ ወደ ሶሥት ነጥቦች ብልጫ ዝቅ ብሏል። ናፖሊ ቼሴናን 2-0 በመርታት የሚከተለው ሲሆን ኢንተር ሚላን አንድ ጨዋታ ጎሎት ሶሥተኛ ነው። ከዚሁ ሌላ በፈረንሣይ አንደኛ ዲቪዚዮን ሊል፣ በኔዘርላንድ ሻምፒዮና አይንድሆፈንና በፓርቱጋል ሊጋም ፖርቶ ቀደምቶቹ ናቸው።

በተረፈ በአግር ኳሱ ዓለም በዚህ በያዝነው ሣምንት አጋማሽ በርካታ የወዳጅነት ግጥሚያዎችም ይካሄዳሉ። ከነዚሁ መካከልም ቢቀር በስም እጅግ ማራኪና ታላላቅ ጨዋታዎች የሚገኙበት ሲሆን ዋነኞቹም ለምሳሌ ፈረንሣይ ከብራዚል፤ ጀርመን ከኢጣሊያ፤ አርጄንቲና ከፖርቱጋል፤ እንዲሁም የዓለም ዋንጫ ባለቤት ስፓኝ ከኮሉምቢያ ናቸው።

Formel 1 Jenson Button Robert Kubica Felipe Massa

ቴኒስ ዴቪስ-ካፕ / ፎርሙላ-አንድ

በዓለምአቀፉ የቴኒስ ፌደሬሺን ካፕ ውድድር ወደ ግማሽ ፍጻሜ ለማለፍ በተደረጉ ግጥሚያዎች ሩሢያ ፈረንሣይን ከኋላ ተነስታ 3-2 ስታሸንፍ በተለይም አናስታዚያ ፓቭሉቼንኮቫ ከታዋቂዋ ከማሪያ ሻራፖቫ ይልቅ የድሉ ዋስትና ነበረች። ኢጣሊያ ደግሞ አውስትሪያን 4-1 ስታሸንፍ ቤልጂግም አሜሪካን በተመሳሳይ ውጤት አሰናብታለች። ከዚሁ ሌላ ቼክ ሬፑብሊክ ስሎቫኪያን 3-2 ስትረታ ግማሽ ፍጻሜ ግጥሚያዎቹ የሚካሄዱት የፊታችን ሰንበት ሣምንት ነው።

የፎርሙላ-አንዱ ዘዋሪ የሮበርት ኩቢትሣ ትናንት በከባድ አደጋ መጎዳት ዓለም የዚህን ስፖርት አደገኝነት መልሶ እንዲያጤን አዲስ መነሻ ሆኗል። ኩቢትሣ በከባድ ግጭት የተነሣ ቀኝ ክንዱ ላይ ሃያል ጉዳት የደረሰበት በአዲሱ የፎርሙላ-አንድ የዓለም ሻምፒዮና ውድድር ወቅት ዋዜማ ኢጣሊያ ውስጥ በተካሄደ እሽቅድድም ከግምብ ጋር ከተጋጨ በኋላ ነው።
የፖላንዱ ተወላጅ ሰባት ሰዓታት የፈጀ ቀዶ ጥገና ሲደረግለት ቀደም ሲል ቀኝ ዕጁን እንዳያጣ ተፈርቶ ነበር። ሆኖም ኢጣሊያዊው ሃኪም ፕሮፌሰር ማሪዮ ሮዜሎ ቀዶ ጥገናው ከባድ እንደነበር ሲጠቅሱ መሳካቱንም አያይዘው አስረድተዋል። የ 26 ዓመቱ የሬኖ ዘዋሪ ውድድሩ ቢቀርበት ጤንነቱን መልሶ እንደሚያገኝ ተሥፋ እናደርጋለን።

መሥፍን መኮንን

አርያም ተክሌ