የስፖርት ዘገባ | ስፖርት | DW | 24.01.2011
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ስፖርት

የስፖርት ዘገባ

በአውሮፓ ቀደምት ሊጋዎች የእግር ኳስ ሻምፒዮና የስፓኙ ክለብ ባርሤሎናና የኢጣሊያው ኤ.ሢ.ሚላን የየበኩላቸውን የሰንበት ግጥሚያዎች በመሸነፍ መምራታቸውን ቀጥለዋል።

default

ለስፓኙ ክለብ የቅዳሜው ድል በተከታታይ 14ኛው መሆኑ ነበር። በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ ደግሞ ሰንበቱ በተለይም ለማንቼስተር ዩናይትድና ለአርሰናል ኮከብ አጥቂዎች የሰመረ ሆኖ አልፏል። የአውሮፓ ቀደምት ሊጋዎች ሻምፒዮናና ካታር ላይ የሚካሄደው የእሢያ ዋንጫ ውድድር ዛሬ በእግር ኳሱ መድረክ ዋነኞቹ ማተኮሪያዎቻችን ናቸው። ከዚሁ በተጨማሪም በቴኒስና በዕጅ ኳስ ላይ ሰብሰብ ያለ ዘገባ ይኖረናል።

የአውሮፓ ቀደምት ክለቦች የእግር ኳስ ሻምፒዮና

በአውሮፓ ቀደምት ክለቦች የእግር ኳስ ሻምፒዮና እንጀምርና በስፓኝ ፕሪሜራ ዲቪዚዮን ኤፍ-ሢ.ባርሤሎና በዚህ ሰንበት ሣንታንዴርን 3-0 በመርታት በተከታታይ ለ 14ኛ የሊጋ ድሉ በቅቷል። ቡድኑ በዚሁ ከአምሥት ዓመታት በፊት በድርብ የስፓኝና የአውሮፓ የክለብ ሻምፒዮና ድሉ ወቅት አስመዝግቦት የነበረውን ክብረ-ወሰን ለሁለተኛ ጊዜ መልሶ ማስፈኑ ነው። ለባርሣ ሶሥቱን ጎሎች ያስቆጠሩት ፔድሮ፣ የቡድኑ መንኮራኩር ሊዮኔል ሜሢና ኢኒየስታ ነበሩ።

ተቀናቃኙ ሬያል ማድሪድም ትናንት ማዮርካን 1-0 በሆነች ጠባብ ውጤት በማሸነፍ በአራት ነጥቦች ልዩነት ሁለተኛ ሆኖ መከተሉን ቀጥሏል። ለሬያል ብቸኛዋን ጎል ያስቆጠረውም የፈረንሣዩ ብሄራዊ ተጫዋች ካሪም ቤንዜማ ነበር። ከኢጣሊያ ወደ ስፓኝ የተሻገረው ቤንዜማ ምንም እንኳ ታላቅ ተሥፋ ተጥሎበት ቢገዛም እስካሁን እንደተጠበቀው አልሆነም። የትናንቷ ግቡ ለሬያል ገና ሁለተኛዋ መሆኗ ነው። ኢጣሊያን ካነሣን ሰንበቱን ለቪላርሬያል ሁለት ጎሎችን በማስቆጠር ቡድኑ በሶሥተኝነቱ ጸንቶ እንዲቀጥል ያደረገው ኢጣሊያዊው አጥቂ ጁሴፔ ሮሢ ነበር። ቪላርሬያል ሬያል ሶሢየዳድን 2-1 ለማሸነፍ በቅቷል።

ከሰንበቱ የፕሪሜራ ዲቪዚዮኑ ግጥሚያዎች በኋላ ባርሤሎና በ 55 ነጥቦች የሚመራ ሲሆን ሬያል ማድሪድ በ 51 ሁለተኛ ነው። ቪላርሬያል ዘጠኝ ነጥቦች ወረድ ብሎ ሶሥተኛው ሲሆን ሻምፒዮናው ምናልባት በባርሣና በሬያል ማድሪድ መካከል የሚለይለት ነው የሚመስለው። በጎል አግቢነት የሬያል ማድሪዱ ክሪስቲያኖ ሮናልዶ 22 በማስቆጠር የባርሣ ተፎካካሪውን ሜሢን በአራት ግቦች በመብለጥ ይመራል፤ ሶሥተኛው ዴቪድ ቪያ ነው።

በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ ሣምንቱ በተለይም የቡልጋሪያዊው አጥቂ የዲሚታር ቤርባቶቭና የኔዘርላንዱ ኮከብ የሮቢን-ፋን-ፐርዚ ነበር ለማለት ይቻላል። ማንቼስተር ዩናይትድና አርሰናል ሁለቱ ኮከቦች በየፊናቸው ባስቆጠሯቸው ሶሥት ሶሥት ጎሎች ለሻምፒዮናው ራሳቸውን ሲያጠናክሩ ብርቱ ተፎካካሪያቸው ማንቼስተር ሢቲይ በአንጻሩ በኤስተን ቪላ 1-0 ተሸንፎ ጠቃሚ ነጥቦችን አጥቷል። ማንቼስተር ዩናይትድ በርሚንግሃም ሢቲይን 5-0 ሲቀጣ አጥቂው ቤርባቶቭም በአንድ ጨዋታ ሶሥት ጎሎችን ሲያስቆጥር በዘንድሮው ውድድር ለሶሥተኛ ጊዜ መሆኑ ነው። ለማኒዩ የተቀሩትን ጎሎች ያስቆጠሩት ራያን ጊግስና የፖርቱጋሉ ናኒ ነበሩ።

አርሰናል ደግሞ ዊጋን አትሌቲክን 3-0 ሸኝቷል። በወቅቱ ማንቼስተር ዩናይትድ ከ 22 ግጥሚያዎች በኋላ በ 48 ነጥቦች ፕሬሚየር ሊጉን የሚመራ ሲሆን አርሰናል በ 46 ሁለተኛ ነው። ሆኖም ከማኒዩ የአንድ ጨዋታ ብልጫ አለው። ማንቼስተር ሢቲይ ሶሥተኛ፤ ቼልሢይ አራተኛ፣ ቶተንሃም ሆትስፐር አምሥተኛ! በነገራችን ላይ ቼልሢይ የሣምንቱን ግጥሚያውን ከቦልተን ወንደረርስ የሚያካሂደው ገና በዛሬው ምሽት ነው። እናም ካሸነፈ ማንቼስተር ሢቲይን እስከ ሁለት ነጥብ ልዩነት የመቃረብ ዕድል ይኖረዋል።

Mario Goetze Bundesliga Borussia Dortmund gegen VfB Stuttgart

በጀርመን ቡንደስሊጋ ቀደምቱ ቦሩሢያ ዶርትሙንድ ከሚፈራው ተጋጣሚው ከሽቱትጋርት ጋር 1-1 ብቻ በመለያየቱ አመራሩ ከ 13 ወደ 11 ነጥቦች ወረድ ብሏል። በዚሁ የ 11 ነጥቦች ልዩነት ሁለተኛነቱን ሊይዝ የቻለው ትናንት የሊጋውን መጨረሻ መንሸን ግላድባህን የረታው ሌቨርኩዝን ነው። የዶርትሙንድ መገታት ለጊዜው ገና የድንጋጤ ምክንያት ሊሆን ባይችልም በሌላ በኩል አሠልጣኙን ዩርገን ክሎፕን ጥቂትም ቢሆን መከንከኑ አልቀረም።

“በተፋጠነ የምላሽ ጥቃት የገባብን ጎል በተወሰነ መጠንም ቢሆን የአጨዋወት ስልታችንን ምንነት ያመለክታል። እስከመጨረሻ ወደፊት ነው የምንጫወተው። ይህ የማጥቃት አጨዋወታችን ደግሞ እርግጥ በዘንድሮው ውድድር ሂደት ስድሥት ወይም ሰባት ጊዜ ነጥብ እንድናስቆጥር ረድቶናል። ዛሬ ግን አልጠቀመንም። ሆኖም ትግሉ ባለበት ይቀጥላል”

በሣምንቱ ከሁሉም ይልቅ ጠቃሚ እመርታ ያደረገው ወደ አራተኛው ቦታ ከፍ ለማለት የቻለው ባየርን ሙንሺን ነው። ባየርን ካይዘርስላውተርንን 5-1 ሲቀጣ ቀደምቱ ክለብ በሻምፒዮናው ላይ መልሶ ዓይን ማሳረፉ አልቀረም። ዶርትሙንድና ሌቨትኩዝን በሚቀጥሉት ሣምንታት ብርክ ከያዛቸው በእርግጥም ባየርን ወዳይ ሊዘልቅ የሚችል ነው። ይህን ደግሞ ባለፉት ዓመታት በተደጋጋሚ አሳይቷል።

ለማንኛውም ወደ ኢጣሊያ ሤሪያ-አ ሻገር እንበልና ቀደምቱ ኤ.ሢ.ሚላን ቼሤናን 2-0 በማሸነፍ አመራሩን ሳያስነካ ቀጥሏል። ናፖሊም ባሪን በተመሳሳይ ውጤት ሲረታ አራት ነጥቦች ወረድ ብሎ ሁለተኛ ነው። ሮማ ካልጋሪን 3-0 አሸንፎ ሶሥተኛ ሲሆን ላሢዮ በአንጻሩ በቦሎኛ 3-1 ተረትቶ ወደ አራተኛው ቦታ አቆልቁሏል። በተቀረ ሰንበቱ ላለፉት ዓመታት የኢጣሊያ ሻምፒዮን ለኢንተር ሚላን የቀና አልነበረም። ቡድኑ በኡዲኔዘ 3-1 ተሸንፎ ከአመራሩ መራቁን ቀጥሏል።

በፈረንሣይ ሣምንቱ የብሄራዊው ዋንጫ ጥሎ ማለፍ ግጥሚያዎች የተካሄዱበት ነበር። በዚሁ ውድድር አስደናቂው ነገርም የአምሥተኛው ዲቪዚዮን ክለብ ቻምቤሪይ የአንደኛውን ዲቪዚዮን ቡድን ብሬስትን በፍጹም ቅጣት ምት ከውድድሩ አስወጥቶ ከመጨረሻዎቹ 16 ቡድኖች አንዱ ለመሆን መብቃቱ ነው። በጥቅሉ ወደ ሩብ ፍጻሜው ከተሻገሩት 16 ክለቦች ከአንደኛው ዲቪዚዮን የመነጩት ሰባቱ ብቻ ሲሆኑ ቀጣዩ ግጥሚያዎች ከሣምንት በኋላ ይካሄዳሉ። በተቀረ በኔዘርላንድ አንደኛ ዲቪዚዮን አይንድሆፈን፤ እንዲሁም በፖርቱጋል ሻምፒዮና ፖርቶ በአመራቸው ቀጥለዋል።

ካታር ውስጥ በመካሄድ ላይ ባለው የእሢያ የእግር ኳስ ዋንጫ ውድድር ለግማሽ ፍጻሜው የደረሱት አገሮች ማንነት ትናንት ለይቶለታል። አውስትራሊያና ኡዝቤኪስታን በፊታችን ማክሰኞ የመጀመሪያዎቹ የግማሽ ፍጻሜ ተጋጣሚዎች ሲሆኑ ሁለተኛው የግማሽ ፍጻሜ ጨዋታ የሚካሄደው በጃፓንና በደቡብ ኮሪያ መካከል ነው። በተለይም ይሄው በሶሥት ጊዜዋ የዋንጫ ባለቤት በጃፓንና በደቡብ ኮሪያ መካከል የሚካሄደው ግጥሚያ ጠንካራው እንደሚሆን ይጠበቃል። በሌላ የአካባቢ ውድድር በማዕከላዊ አሜሪካ ዋንጫ ደግሞ ሁንዱራስ ኮስታ ሪካን 2-1 በመርታት ባለድል ሆናለች። ለሆንዱራስ የትናንቱ ድል ሶሥተኛው መሆኑ ነው።

Handball WM Schweden 2011 Logo

የዕጅ ኳስ የዓለም ሻምፒዮና በስዊድን

ስዊድን ውስጥ በሚካሄደው የዓለም ዕጅ ኳስ ሻምፒዮና ዴንማርክና አስተናጋጇ አገር ወደ ግማሽ ፍጻሜው ዙር ለመሻገር በቅተዋል። ዴንማርክ ትናንት በዋነኛው ዙር ሁለተኛ ግጥሚያዋ ማልመ ውስጥ አርጄንቲናን 31-24 ስትረታ አንድም ጨዋታ ሳትሸነፍ ስዊድንን በማስከተል የምድቡን ዙር አጠናቃለች። የአውሮፓ ሻምፒዮን የሆነችው ስዊድን ደግሞ ለግማሽ ፍጻሜ ያለፈችው ክሮኤሺያን 29-24 ካሸነፈች በኋላ ነው። በዚሁ ምድብ-ሁለት ውስጥ ለማለፍ የሚያበቃውን ሶሥተኛ ቦታ ለመያዝ ደግሞ የዓለም ሻምፒዮና ሁለተኛና ሶሥተኛ የነበሩት ክሮኤሺያና ፖላንድ ነገ ይጋጠማሉ።

በምድብ-አንድ ውስጥ የዓለም ሻምፒዮናዋ ፈረንሣይና ስፓኝ ቀደምቱ ሲሆኑ አይስላንድ፣ ጀርመንና ሁንጋሪያም ገና ወደ ግማሽ ፍጻሜ የማለፍ የተወሰነ ዕድላቸውን እንደጠበቁ ነው። በዛሬው ዕለት አይስላንድ ከስፓኝ፤ ጀርመንም ከሁንጋሪያ ይጋጠማሉ። ሁንጋሪያ በዋናው ዙር የመጀመሪያ ግጥሚያዋ በፈረንሣይ እንዳልነበር ሆና ብትሸነፍም ከጀርመን በኩል ስኬት ለማግኘት ትልቅ ትኩረት ማስፈለጉ ግግ እንደሆነ ነው ከተጫዋቾቹ አንድኡ ያኮብ ሃይነር የተነገረው።

“ጥሩ ቀን ሊገጥማቸውና ማንኛውንም ቡድን ለማሸነፍም ይችላሉ። ግን በበኩላችን በሙሉ ትኩረት ከፊትም ከኋላም ጠንክረን ከቀረብን ልናሸንፋቸው እንችላለን”

ጀርመን በውድድሩ ወደፊት ባትገፋ እንኳ ቢቀር ለኦሎምፒክ ጨዋታ ለማለፍ አምሥተኛውን ቦታ ማረጋገጥ ይኖርባታል። ቡድኑ ወደ ውድድሩ የገባው ይህን አነስተኛ ግብ ግዴታ በማድረግም ነው።

David Nalbandian Tennis Schläger Flash-Galerie

ቴኒስ፤ አውስትራሊያን-ኦፕን

በአውስትራሊያን-ኦፕን የቴኒስ ውድድር በሴቶች የቼኳ ፔትራ ክቪቶቫ ኢጣሊያዊቱን ፍላቪያ ፓኔታን 2-1 ስታሸንፍ፤ ሩሢያዊቱ ቬራ ዝቮናሬቫ የቼኳን ኢቬታ ቤኔሶቫን 2-0፤ እንዲሁም የፖላንዷ አግኒየትስካ ራድቫንስካ ደግሞ የቻይና ተጋጣሚዋን ፔንግ ሹዋይን 2-1 ረትታለች። ከሁሉም የሚያሰንቀው ጀርመናዊቱ አንድሬያ ፔትኮቪች ሩሢያዊቱን ጠናካራ ተጫዋች ማሪያ ሻራፖቫን በሁለት ምድብ ጨዋታ 6-3, 6-2 በማሸነፍ ከወዲሁ ማሰናበቷ ነበር።
በወንዶች በዓለም ላይ አንደኛ የሆነው ራፋኤል ናዳል እስካሁን አንዲት ምድብ እንኳ ሳይሽነፍ ወደ ሩብ ፍጻሜው አልፏል። ናዳል ማሪን ቺሊችን 3-0 ሲያሸንፍ የፊታችን ረቡዕ ተጋጣሚው የአገሩ ልጅ ዴቪድ ፌሬር ነው። ዴቪድ ፌሬር በበኩሉ ሚሎሽ ራኦኒችን 3-1 ሲያሸንፍ ከዚሁ ሌላ የኡክራኒያው አሌክሣንድር ዶልጎፖሎቭ ሮቢን ሶደርሊንግን 3-1፤ ኤንዲይ መሪይም ዩርገን ሜልሰርን 3-0 አሰናብቷል። በነገው ዕለት የስዊሱ ሮጀር ፌደረር ከአገሩ ልጅ ከስታኒስላቭ ቫብሪንካ፤ አንድሬያ ፔትኮቪች ከሊ-ና እና ካሮሎን ቮዝኒያችኪ ደግሞ ከፍራንቼስካ ሺቮኔ ይጋጠማሉ።

መሥፍን መኮንን

ሸዋዬ ለገሠ