የስፖርት ዘገባ | ስፖርት | DW | 10.01.2011
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ስፖርት

የስፖርት ዘገባ

የዓለም አግር ኳስ ፌደሬሺኖች ማሕበር ፊፋ ዛሬ ማምሻውን በስዊትዘርላንድ መቀመጫው በዙሪክ በሚካሄድ ታላቅ ፌስታ ከአሥር ቀናት በፊት የተገባደደውን የ 2010 ዓ.ም.ን ኮከብ ተጫዋቾችና አሠልጣኝ መርጦ ይሸልማል።

default

የወንዶቹ አሸናፊ በዕጩነት ከቀረቡት የባርሤሎና ሶሥት ተጫዎቾች አንዱ እንደሚሆን ከሞላ ጎደል ከወዲሁ የተረጋገጠ ጉዳይ ነው። ጀርመንም ቢቀር በሴቶች ንጽጽር ተሸላሚ የመሆን ዕድል አላት።

የዓለም አግር ኳስ ፌደሬሺኖች ማሕበር ፊፋ በዛሬው ምሽት የዓመቱን ወንድና ሴት ድንቅ ተጫዋቾችና አሠልጣኝ መርጦ ይሸልማል። በወንዶች ለማሸነፍ ዕድል ያላቸው ሶሥቱም ተጫዋቾች ዘንድሮ የመነጩት ከስፓኙ ቀደምት ክለብ ከኤፍ.ሢ.ባርሤሎና ሲሆን እነርሱም ያለፈው ወቅት ተመራጭ አርጄንቲናዊው ሊዮኔል ሜሢ፤ እንዲሁም ሁለቱ ድንቅ የስፓኝ ተጫዎቾች ሻቢና አንድሬስ ኢኒየስታ ናቸው። በነገራች’ን ላይ በሽልማቱ ታሪክ ለፍጻሜ የደረሱት ዕጩዎች ከአንድ ክለብ የመነጩ ሲሆኑ የአሁኑ ለሶሥተኛ ጊዜ መሆኑ ነው።
ከዚህ ቀደም እ.ጎ.አ. በ 1988 እና 1989 ዓ.ም. የኤ.ሢ.ሚላን ተጫዋቾች ለፍጻሜ ደርሰው ሁለቱንም ጊዜ የኔዘርላንዱ ማርኮ-ፋን-ባስተን አሸናፊ መሆኑ ይታወሣል። እርግጥ ደቡብ አፍሪቃ ውስጥ በተካሄደው የዓለም ዋንጫ ውድድርም ሆነ ሌሎች አጋጣሚዎች ከሶሥቱ የባርሣ ኮከቦች ውጭ ለምሳሌ የጀርመኑን ሜሱት ኡዚልን ወይም የኡሩጉዋዩን ዲየጎ ፎርላንን የመሳሰሉ ሌሎች ድንቅ ተጫዋቾች መታየታቸውም አልቀረም። ከሆነ ታዲያ የእንድ ክለብ ተጫዋቾች ብቻ ለፍጻሜ መድረሳቸው ምክንያቱ ምንድነው? የዶቼ ቬለ የስፖርት ፕሮግራም ክፍል ባልደረባ ቮልፍጋንግ ፋን ካን እንደሚለው በእርግጥም የዓለም ዋንጫው ውድድር ሂደት ድርሻ ሳይኖረው አልቀረም።

“ምን ምክንያቶች ወሣኝ እንደነበሩ እርግጥ እንዲህ ብሎ መናገሩ ከባድ ነው። የዕጩዎቹ ዝርዝር የሚጠናቀረው በብሄራዊ አሠልጣኞች፣ በብሄራዊ ቡድን አምበሎችና በጋዜጠኞች መሆኑ ይታወቃል። እና እዚህ ላይ ታላላቅ ውድድሮች ለምሳሌ የአውሮፓ ሻምፒዮና ሊጋና እንዲሁም የደቡብ አፍሪቃው የ 2010 የዓለም ዋንጫ ፍጻሜ ውድድር ታላቅ ሚና እንደነበራቸው አያጠራጥርም። ለነገሩ ስፓኝ ለዓመታት በብሄራዊ ቡድን ደረጃ በጣም ግሩም አቀራረብ ነው የነበራት። ከዚህ አንጻር እንግዲህ ሁለት የስፓኝ’ ተጫዋቾች ከመጨረሻዎቹ ዕጩዎች መካከል መሆናቸው ጨርሶ አያስደንቅም። እርግጥ ሜሢ በዓለም ላይ አንዱ ግሩም ተጫዋች ለመሆኑ ጥርጥር የለውም። እናም የርሱም መኖር የሚያስገርም አይደለም”
የዛሬው ምሽት ተሸላሚዎች ማንነት በሚስጥር የተያዘ ጉዳይ ሲሆን ለአንዱ ወይም ለሌላው የሚደረግ ቅስቀሣ ግን ከያቅጣጫው መሰማቱ አልቀረም። እንደ ኢጣሊያው ዕለታዊ የስፖርት ጋዜጣ “ጋዜታ-ዴሎ-ስፖርት” ዘገባ ከሆነ ድሎ የኢኒየስታ ነው የሚሆነው። በሌላ በኩል የአውሮፓ የእግር ኳስ ፌደሬሺኖች ማሕበር የዩኤፋ ፕሬዚደንት ፈረንሣዊው ሚሼል ፕላቲኒ ደግሞ ሻቪ ይመረጣል ባይ ነው። ለማንኛውም ሽልማቱ በዚህም ቢዚያም ወደ ስፓኝ የሚሄድ ይመስላል።

“በመሠረቱ በዓለም ዋንጫው ውድድር ዓመት የዓመቱ ተጫዋች ከዋንጫው ባለቤት ቡድን የሚመረጥ መሆኑ የተለመደ ነገር ነው። ስለዚህም ሁለቱ የስፓኝ ተጫዋቾች ሻቪና ኢኒየስታ በእርግጥ ከሜሢ የላቀ ዕድል ይኖራቸዋል። ኢኒየስታ ደግሞ በዓለም ዋንጫው ፍጻሜ ግጥሚያ ወሣኟን ግብ በማስቆጠሩ በብዙዎች ዘንድ ይበልጡን አሸናፊ ሆኖ ነው የሚታየው”

በሴቶች ንጽጽር ደግሞ ለመጨረሻ ፉክክር ተውጣጥተው የቀረቡት የብራዚልና የጀርመን ዕጩዎች ሲሆኑ ቮልፍጋንግ ፋን ካን የሚገምተው ምርጫው እጅግ ከባድ እንደሚሆን ነው።

“ቢርጊት ፕሪንስ ብቻ ሣትሆን ፋትሚረ ባይራማይም እንደ ጀርመን ብሄራዊ ቡድን ተጫዋች ከዕጩዎቹ መካከል አለችበት። ማለት ሁለቱ ጀርመናውያንና የብራዚሏ ማርታ ናቸው ለምርጫ የቀረቡት። እና ማን አሸናፊ ይሆናል፤ አሁን መናገሩ ከባድ ነው። ማርታ ምንም እንኳ በዓመቱ ከብሄራዊ ቡድኗ ጋር አስደናቂ ጨዋታ ባታሳይም በዓለምአቀፍ ደረጃ ብዙ ደጋፊዎች ነው ያሏት። ችላ የምትባል አይደለችም። ውሣኔው እንግዲህ ቀላል አይሆንም”

ያም ሆነ ይህ ከዚህ ቀደም ለሶሥት ጊዜ ተመራጭ ለነበረችው ለ 33 ዓመቷ ለቢርጊት ፕሪንስ ጊዜው የስንብት ሲሆን ዕውቅናውን መልሶ ማግኘቱ ታላቅ ትርጉም እንደሚኖረው አንድና ሁለት የለውም። የ 22 ዓመቷ ወጣት የጀርመን ተጫዋችባይራማይ ከተመረጠች እርግጥ አስደናቂና ብዙ ያልተጠበቀ ውጤት ነው የሚሆነው። ለማንኛውም ሁሉንም ማምሻውን እንደርስበታለን።

በሣምንቱ የአውሮፓ ቀደምት ሊጋዎች ውድድር ላይ እናተኩርና በስፓኝ ፕሪሜራ ዲቪዚዮን እንደታየው እንደ ሰንበቱ አጨዋወት ከሆነ ሊዮኔል ሜሢ ከተፎካካሪዎቹ ሁሉ የበላዩ ነበር። ባርሤሎና ዴፖርቲቮ-ላ-ኮሩኛን 4-0 ሲረታ ሜሢ በቅጣት ምት አንዷን ጎል በማስቆጠርና ሁለቱን ደግሞ በማዘጋጀት ለድሉ ወሣኝ አስተዋጽኦ አድርጓል። ባርሣ ከ 18 ግጥሚያዎች በኋላ በ 49 ነጥቦች አመራሩን እንደያዘ ሲቀጥል ሬያል ማድሪድም በበኩሉ ግጥሚያ ቪላርሬያልን 4-2 በማሸነፍ በ 47 ነጥቦች በሁለተኝነቱ እንደረጋ ነው።
ክሪስቲያኖ ሮናልዶ ሶሥት ጎሎች በማስቆጠር እንደገና ግሩም ጨዋታ ሲያሳይ ብራዚላዊው ካካም በአካል ጉዳት ለረጅም ጊዜ ከረፈ በኋላ እንደገና ተሥፋ ሰጭ ጅማሮ ለማድረግ ችሏል። ቪላርሬያል በ 36 ነጥቦች ሶሥተኛ ሲሆን ሊጋውን በጎል አግቢነት በአራት ግብ ብልጫ የሚመራው 22 ያስቆጠረው የፖርቱጋሉ ኮከብ ክሪስቲያኖ ሮናልዶ ነው። በኢጣሊያ ሤሪያ-አ ኤ.ሢ.ሚላን ከኡዲኔዘ 4-4 ቢለያይም ተዝናንቶ መምራቱን እንደቀጠለ ነው። ከተከታዩ ከናፖሊ አራት ነጥብ ብልጫ አለው።
ላሢዮ በበኩሉ ግጥሚያ በሌቼ 2-1 በመረታቱ አመራሩን ለመቃረብ የነበረውን ዕድል ሳይጠቀምበት ቀርቷል፤ እንዲያውም ቦታውን ለናፖሊ አስረክቦ ወደ ሶሥተኛ ስፍራ ነው ያቆለቆለው። ሮማ አራተኛ! በፖርቱጋል ሻምፒዮና ፖርቶ ማሪቲሞን 4-1 በማሸነፍ ሊጋውን በስምንት ነጥቦች ልዩነት እየመራ ሲሆን ቤንፊካ ሊዝበን በሁለተኝነት ይከተላል። በግሪክ ሻምፒዮና ደግሞ ኦሊምፒያኮስ ፒሬውስ ሰንበቱን ኬርኪይራን 2-0 በመርታት በአምሥት ነጥቦች ልዩነት እንደመራ ነው።

Schnee im Stadion - Winterzeit in der Bundesliga

በዚህ በጀርመን የቡንደስሊጋው የመልስ ዙር ከክረምቱ ዕረፍት በኋላ በፊታችን ቅዳሜ ይጀምራል። ታዲያ በመጀመሪያው ዙር አንዲት ጨዋታ ብቻ ተሸንፎ ግሩም በሆነ ሁኔታ የበልጉ ሻምፒዮን የነበረው ዶርትሙንድ በድል ጉዞው ይቀጥል ይሆን? የብዙ ጊዜው ሻምፒዮን የባየርን ሙንሺን ወደ ላይ ከፍ የማለት ዕድልስ ምን ያህል ነው? የሌቨርኩዝን ሚናና የብሬመን ዕጣስ? የዶቼ ቨ የስፖርት ፕሮግራም ባልደረባ ቮልፍጋንግ ፋን ካን ዶርትሙንድ ጥሩ የመልስ ጅማሮ ካደረገ ያማረ የሻምፒዮንነት ዕድል እንዳለው ነው የሚገምተው።

“ባየርን እርግጥ ወደ አመራሩ እንደሚቃረብ ጥርጥር የለኝም። በተለይም አሁን ለረጅም ጊዜ ቆስሎ የነበረው አርየን ሮበን በመመለሱ! ሪቤሪም እንዲሁ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እየተጫወተ ነው። እናም ባየርን በሁለተኛው ዙር የተሻለ እንደሚሆን አምናለሁ። ዶርትሙንድን በተመለከተ ወሣኙ ነገር ቡድኑ የመልሱን ዙር የሚጀምርበት ሁኔታ ይሆናል። አሁን ሣምንት ከሌቨርኩዝን ጋር ከባድ ግጥሚያ ነው ያለው። እና ተጫዋቾቹ የድል ጉዟችን አበቃ የሚል ስሜት እንዳያድርባቸው ቢያንስ እኩል ለእኩል መውጣት መቻል ይኖርባቸዋል። ማለት የመጀመሪያው የመልስ ግጥሚያ ለዶርትሙንድ በጣሙን ወሣኝ ነው”

በተረፈ ለወትሮው ከቀደምቶቹ አንዱ የሆነው ብሬመን ከእረፍት የሚመለሰው ከባድ ፈተና ላይ እንደወደቀ ነው። ቡድኑን ወደ ሁለተኛ ዲቪዚዮን ከሚያወርደው ከ 16ኛው ቦታ የሚለዩት አራት ነጥቦች ብቻ ሲሆኑ በሚቀጥሉት ሣምንታትና ምናልባትም ወራት ብርቱ ግፊት እንደሚጠብቀው አንድና ሁለት የለውም።

ዶሃ ላይ በመካሄድ ላይ ባለው በእሢያ ዋንጫ ውድድር በምድብ-ሁለት የመጀመሪያ ግጥሚያ የሚከተሉት ውጤቶች ተመዝግበዋል። ጃፓን ከዮርዳኖስ 1-1 ስትለያይ ሳውዲት አረቢያ ደግሞ በሶሪያ 2-1 ተሸንፋለች። ከምድቡ ሁለቱ ጠንካራ ቡድኖች ወደ ሩብ ፍጻሜው የሚያልፉ ሲሆን በነገው ዕለት ዮርዳኖስ ከሳውዲት አረቢያ፤ እንዲሁም ሶሪያ ከጃፓን ይጋጠማሉ።

በምድብ-አንድ ቻይና በመክፈቻው ግጥሚያ ኩዌይትን 2-0 ስትረታ ኡስቤኪስታንም አስተናጋጇን ካታርን በተመሳሳይ ውጤት አሸንፋለች። በነገራችን ላይ ስታዲዮም የሚገባው ተመልካች ቁጥር እጅግ ዝቅተኛ ሆኖ ተገኝቷል።

መሥፍን መኮንን

ተክሌ የኋላ