የስፖርት ዘገባ | ስፖርት | DW | 29.11.2010
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ስፖርት

የስፖርት ዘገባ

ቻይና-ጉዋንግሹ ላይ ሲካሄድ የቆየው አሢያድ በመባል የሚታወቀው 16ኛው የእሢያ ጨዋታ የአስተናጋጇ አገር ልዕልና በሰፈበት ሁኔታ ተጠናቋል።

default

ዝግጅቱ ባለፈው ቅዳሜ የተጠቃለለው በርችትና በሕብረ-ቀለማት በደመቀ የመዝጊያ ፌስታ ለተሳታፊዎቹ ስፖርተኞችና ለተመልካቹ ሁሉ ምንጊዜም እንዳይረሣ ሆኖ ነው። ከዚሁ ሌላ የያዝነው ሣምንት በዓለም እግር ኳስ ፌደሬሺኖች ማሕበር በፊፋ ታሪክ ውስጥ ለመጀመሪያ ጊዜ የሁለት የዓለም ዋንጫ አዘጋጆች በአንድ ጊዜ የሚመረጡበት ነው። ትናንት ለንደን ላይ የተካሄደው የዓመቱ ማጠቃለያ ኤቲ.ፒ የቴኒስ ፍጻሜ ግጥሚያ ደግሞ ቀደምቱ ራፋኤል ናዳልና ሮጀር ፌደረር የተገናኙበት ነበር።
የቻይናው የአሢያድ ጨዋታ ፍጻሜ

ሕዝባዊት ቻይና በማበብ ላይ በምትገኘው የአገሪቱ ደቡባዊት ከተማ በግዋንግሹ ያስተናገደችው ታላቅ የስፖርት ውድድር፤ 16ኛው የኢሢያድ ጨዋታ ባለፈው ቅዳሜ በደመቀ ትርዒት ተፈጽሟል። ለቻይና በዝግጅቱ የፈሰሰው በቢሊዮን የሚቆጠር ገንዘብ ከንቱ ሆኖ አልቀረም። የእሢያ የኦሎምፒክ ም/ቤት ፕሬዚደንት ሼይክ-አሕመድ-አል-ሣባህ በመዝጊያው ስነ ስርዓት ላይ ባሰሙት ንግግር ያላንዳች ጥርጥር ድንቁ የእሢያ ጨዋታ እንደነበረ ነው ያረጋገጡት።
የቤይጂንጉን ኦሎምፒክና የሻንግሃዩን ኤክስፖ ተከትሎ የተካሄደው ሁለት ሣምንታት የፈጀ ጨዋታ አስደናቂነት እርግጥ እንደገና የቻይናን የተፋጠነ ዕድገትና ዕርምጃ የሚያንጸባርቅ ነው። የሕዝባዊት ቻይና ስኬት ደግሞ በዝግጅት ብቃት ብቻ ተወስኖ አልቀረም። አትሌቶቿ 199 ወርቅ ሜዳሊያዎችን በማግኘትም በአዲስ የአሢድስ ክብረ-ወሰን ቀደምቱ ሆነዋል። በውድድሩ ጃፓን ከብርቱ ተፎካካሪዋ ከደቡብ ኮሪያ ጋር ባደረገችው ፉክክር ስትበለጥ በ 48 ወርቅ ሜዳሊያዎች ተወስናለች።
መጪውን የ 2014 የእሢያ ጨዋታ የምታዘጋጀው ደቡብ ኮሪያ በአንጻሩ በ 76 ወርቅ ሜዳሊያዎች በግሩም ውጤት ነው የተሰናበተችው። በሌላ በኩል ባሕሬይንና ካታር ደግሞ ከአፍሪቃ በተለይም ከኬንያና ከኢትዮጵያ በመነጩ አትሌቶች ከአጭር እስከ ረጅም ርቀት ሩጫ ለብዙ ሜዳሊያዎች በቅተዋል። ካታር በ 200 እና በ 400 ሜትር ሩጫ ከናይጄሪያ በመነጩ አትሌቶች ስታሸንፍ በአምሥት ሺህ ሜትር ደግሞ በቀድሞ ኬንያውያን አማካይነት ብርና ናስ ሜዳሊያ አግኝታለች። ለባሕሬይን በ 1500 እና በ 5000 ሜትር ያሸነፉትም የኬንያ ተወላጅ አትሌቶች ነበሩ።

በዚህ ብቻ አያበቃም፤ ባሕሬይን በኬንያ አትሌቶች አማካይነት በሶሥት ሺህ ሜትር መሰናክል፣ በወንዶች ማራቶንም አሸናፊ ሆናለች። ከኢትዮጵያ ከመነጩት አትሌቶች በኩል ቢሊሱማ-ሹጊ-ገላሣ በወንዶች አሥር ሺህ ሜትር፤ በ 1500 ሜትር ዘነበች ቶላ፤ በአምሥት ሺህ ሜትር ሚሚ ገ/ጊዮርጊስና በሴቶች አሥር ሺህ ሜትር ሺታዬ ሃ/ገብርኤል ሁሉም ለባሕሬይን አሸንፈዋል። በነገራችን ላይ በሴቶች ማራቶን የቻይናዋ ሹ-ቹን-ቺ ያለፈ ድሏን ስታስከብር በወንዶች ደግሞ የደቡብ ኮሪያው ጂ-ያንግ-ጁን ቀዳሚ ሆኗል። ባሕሬይንና ካታር በጠቅላላው ስምንት ወርቅ ሜዳሊያዎች ሲያገኙ ይሄው በጠቅላላው ከአፍሪቃ በመነጩ አትሌቶች ላይ ጥገኞች መሆናቸውን የሚያመለክት ነው።

Symbolbild FIFA WM Vergabe 2012 und 2022 Freies Bildformat

ፊፋና የ 2018/22 የዓለም ዋንጫ ዕጣ

የዓለም እግር ኳስ ፌደሬሺኖች ማሕበር ፊፋ ከብራዚል በኋላ በ 2018 እና በ 2022 የዓለም ዋንጫ ፍጻሜ ውድድርን የሚያዘጋጁትን አገሮች መርጦ የሚሰይመው በዚህ ሣምንትንት ሂደት ነው። በመሆኑም ማመልከቻ ያስገቡት አገሮች ብቻ ሣይሆን ዓለም በሙሉ በፊታችን ሐሙስ በሚደረገው ምርጫ ላይ በጉጉት እንደሚያተኩር አንድና ሁለት የለውም። ድምጽ የሚሰጡት የፊፋ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ዓባላት ብቻ ሲሆኑ እስካሁን ብዙ ገና ከውሣኔ ያልደረሱ በመኖራቸው ዕድሉ ክፍት እንደሆነ ነው የሚነገረው። በዋዜማው ከ 24ቱ የኮሚቴው ዓባላት ሁለቱ በጉቦኝነት በመጠርጠር ሲወገዱ እነዚሁ በቀረው ጊዜ ውስጥ እንደሚተኩ ይጠበቃል።
እ,.ጎ.አ. ለ 2018 መስተንግዶ ለፉክክር የቀረቡት እንግሊዝና ሩሢያ በተናጠል፤ በጥንድ ደግሞ ስፓኝ/ከፖርቱጋል፤ እንዲሁም ኔዘርላንድ/ከቤልጂግ ጋር ናቸው። ከነዚሁ እንግሊዝና ሩሢያ የተሻለ ዕድል እንዳላቸው ነው የሚነገረው። እርግጥ እንግሊዝ እንደ እግር ኳስ እናት አገር ከ 1966 ወዲህ ሁለተኛውን የዓለም ዋንጫ ለማዘጋጀት እንደምትመረጥ ታላቅ ተሥፋ ጥላለች። ለቀጣዩ 2022 ዓ.ም. የዓለም ዋንጫ አዘጋጅነት ደግሞ አምሥት አገሮች ሲያመለክቱ እነዚሁም ዩናይትድ ስቴትስ፣ ጃፓን፣ ደቡብ ኮሪያ፣ ካታርና አውስትራሊያ ናቸው።
ከነዚሁ መካከል እስካሁን ሩሢያ፣ ፖርቱጋል፣ ኔዘርላንድ፣ ቤልጂግ፣ ካታርና አውስትራሊያ በውድድሩ አስተናጋጅ ሆነው አያውቁም። እናም የፊፋን መስፈርቶች ለማሟላት ከተቃረቡ ምናልባት ይሄው የመመረጥ ዕድላቸውን ሊያጠነክረው ይችል ይሆናል። ከነዚሁ ምናልባትም አውስትራሊያ የበለጠ የመመረጥ ተሥፋ እንዳላት ነው የሚታመነው። ሆኖም ፉክክሩ በአጠቃላይ ቀላል የሚሆን አይመስልም። በሌላ በኩል ዓለምን ለመሳብ ብዙ ገንዘብ ለማፍሰስ ዝግጁ የሆነችው ካታር ትንሽ አገር በመሆኗ ተሥፋ እንደሌላት የፊፋ ተቆጣጣሪ ሜይን ኒኮልስ ከወዲሁ ተናግረዋል። ለማንኛውም ሁሉንም ነገር በፊታችን ሐሙስ እንደርስበታለን።

የአውሮፓ እግር ኳስ ሊጋዎች በሰንበቱ

በአውሮፓ ሊጋዎች የእግር ኳስ ሻምፒዮና በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ ማንቼስተር ዩናይትድ ብላክበርን ሮቨርስን 7-1 በመቅጣት በዘንድሮው የውድድር ወቅት ለመጀመሪያ ጊዜ አመራሩን ሊይዝ በቅቷል። ከሰባት አምሥቱን ጎሎች በማስቆጠር ለአሥር ግጥሚያዎች ያህል ጸንቶ የቆየ ጥሙን ያበረደው የቡልጋሪያው ኮከብ ዲሚታር ቤርባቶቭ ነበር። ከሰንበቱ ግጥሚያዎች በኋላ ዩናይትድ በ 31 ነጥቦች አንደኛ ነው። ሻምፒዮናው ቼልሢይ በአንጻሩ በማቆልቆል ሂደቱ በመቀጠል ከኒውካስል ዩናይትድ 1-1 ሲለያይ ከማኑዩ ሁለት ነጥቦች ዝቅ ብሎ ሁለተኛ ሆኗል። በተመሳሳይ ነጥቦች ሶሥተኛው ኤስተን ቪላን 4-2 የሸኘው አርሰናል ነው።

በዚህ በጀርመን ቡንደስሊጋ ዶርትሙንድ የመጨረሻውን መንሺን ግላድባህን 4-1 በማሸነፍ በሰባት ነጥቦች ልዩነት መምራቱን ቀጥሏል። ከታላላቁ ቡድኖች መካከል ባየርን ሙንሺን ፍራንክፉርትን 4-1 በመርታት ወደ አምሥተኛው ቦታ ከፍ ሲል ብሬመንም ሣንት-ፓውሊን 3-0 በማሸነፍ ለጊዜውም ቢሆን ከባሰ ማቆልቆል ነው ራሱን ያተረፈው። ለሬኮርድ ሻምፒዮኑ ለባየርን ሙንሺን ሆላንዳዊ አሠልጣኝ ለሉዊስ-ፋን-ሃል የሰንበቱ ድል የገናው እረፍት እየተቃረበ ባለበት ወቅት ዕፎይ የሚያሰኝ ሣይሆን አልቀረም’።

“በጣም ደስ ብሎኛል። አሁን ከሶሥተኛው ቦታ የምንርቀው በሶሥት ነጥቦች ብቻ ነው። ይህ ደግሞ በዚህ ወቅት ልንደርስበት የሚገባ አነስተኛው ግባችን ነው። ግን በአውሮፓ ክለቦች ሻምፒዮናና በጀርመን ፌደሬሺን ዋንጫ ውድድር ውስጥም እንዳለንበት ሊታወቅ ይገባል። ብዙ ክለቦች ይህን ለማለት አይችሉም”

Fußball 1. Bundesliga 14. Spieltag FC Bayern München Eintracht Frankfurt Louis Van Gaal

ሉዊስ-ፋን-ሃል

በጀርመን ቡንደስሊጋ ውስጥ ባለፈው ሰንበት የከፋው ክስረት የደረሰበት እርግጥ ሻልከ ነበር። ቀደምቱ ክለብ ከሁለተኛ ዲቪዚዮን በመጣው በካይዘርስላውተርን 5-0 ሲቀጣ ከ 15ኛው ቦታ ወደ ላይ ፈቀቅ ማለት አቅቶት እንደቀጠለ ነው። አሠልጣኙ ፌሊክስ ማጋት በተጫዋቾቹ ግድ የለሸነት ሲቆጣ አንዳች ሳያመነታ የክረምት እረፍታቸውን እስከመሰረዝ ነው የደረሰው።

“በጣም ነው የተበሳጨሁት። ከበረኛው ከማኑዌል ኖየር፣ ከክሪስቶፍ ሜትሤልደርና ከጄፈርሰን ፋርፋን በስተቀር ከልብ ለመታገል የሞከረ አንድም ተጫዋች አላየሁም”

በኢጣሊያ ሊጋ ኤ.ሢ.ሚላን ከሣምንታት የድል ጉዞ በኋላ ከሣምፕዶሪያ በ 1-1 ውጤት ቢወሰንም በሶሥት ነጥቦች መምራቱን ሲቀጥል ውድድሩ እንደጠበበ በቀጠለበት በፈረንሣይ ሻምፒዮና ደግሞ ኦላምፒክ ማርሤይ አመራሩን ጨብጧል። ለግንዛቤ ያህል አንደኛውን ከስምንተኛው ከብሬስት የሚለዩት ሶሥት ነጥቦች ብቻ ናቸው። በኔዘርላንድ አንደኛ ዲቪዚዮን አይንድሆፈን ምንም እንኳ በብሬዳ 4-2 ቢሸነፍም መምራቱን ቀጥሏል፤ በፖርቱጋል ሻምፒዮናም ፖርቶ ከስፖርቲንግ ሊዝበን 1-1 ይለያይ እንጂ የማይደረስበት እንደሆነ ነው።

በስፓኝ ፕሪሜራ ዲቪዚዮን ታላቁ ግጥሚያ የሚካሄደው ገና በዛሬው ዕለት ነው። ማምሻውን በታላላቁ የዓለም ከዋክብት በክሪስቲያኖ ሮናልዶና በሊዮኔል ሜሢ የሚመሩት ሬያል ማድሪድና ባርሤሎና በኑው-ካምፕ ስታዲዮም ለ 167ኛ የእርስበርስ ግጥሞሚያቸው የሚገናኙ ሲሆን ጨዋታው በስፓኝ ብቻ ሣይወሰን በዓለም ዙሪያ በሁለት መቶ አገሮች በጉጉት የሚጠበቅ ነው። መቶ ሺህ ተመልካች በሚገኝበት ስታዲዮም የሚካሄደው ግጥሚያ በማጥቃት ላይ ያመዘነ ማራኪ ጨዋታ እንደሚሆን የቡድኖቹ የአሰላለፍ ታክቲክ ከወዲሁ ያመለክታል። በሁለቱ ክለቦች ውስጥ 14 የዓለም ዋንጫ ባለቤት ተጫዋቾች የሚገኙ ሲሆን ጨዋታውን መቶ ሚሊዮን ሕዝብ በቴሌቪዥን አማካማይነት እንደሚከታተል ነው የሚጠበቀው።

US OPen Tennis Championship Roger Federer Schweiz 2010 Flash-Galerie

የለንደን ኤ.ቲ.ፒ. ፍጻሜ ግጥሚያ

ትናንት ለንደን ላይ የተካሄደው የዓለም ኤ.ቲ.ፒ. ዙር ፍጻሜ ግጥሚያ አሸናፊ የስዊሱ ሮጀር ፌደረር ሆኗል። ፌደረር ለዓመቱ ማጠቃለያ ድል የበቃው የዓለም አንደኛ የሆነውን የስፓኝ ተጋጣሚውን ራፋኤል ናዳልን ግሩም በሆነ ጨዋታ 2-1 በማሸነፍ ነው። በዚህ ዓመት በፈረንሣይ፣ በዊምልደንንና በዩ.ኤስ.ኦፕን አሸናፊ በመሆን ሃያልነቱን ያስመሰከረው ናዳል ትናንት የተለመደ ጥንካሬውን ለማሳየት አልቻለም። የሁለቱ ከዋክብት ፉክክር በሚቀጥለው ዓመትም በቴኒሱ ስፖርት መድረክ ላይ ጎልቶ የሚቀጥል መሆኑን የሚጠራጠር የለም።

መሥፍን መኮንን