የስፖርት ዘገባ | ስፖርት | DW | 22.11.2010
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ስፖርት

የስፖርት ዘገባ

በአውሮፓ ቀደምት የእግር ኳስ ሊጋዎች ውስጥ የሚካሄደው ውድድር በአብዛኛው ወደ መጀመሪያው ዙር ሁለተኛ አጋማሽ ሲሸጋገር ፉክክሩም እየጠነከረ መሄዱን ቀጥሏል።

default

የያዝነው ሣምንት አጋማሽም በአውሮፓ ክለቦች ሻምፒዮና ሊጋ ውድድር ወደ ጥሎ ማለፉ ዙር ለማለፍ በሚደረገው ፉክክር የብዙዎቹ ዕጣ የሚለይበት ነው። በአውሮፓ ቀደምት ሊጋዎች የእግር ኳስ ውድድር እንጀምርና በዚህ በጀርመን ቡንደስሊጋ ቦሩሢያ ዶርትሙንድ በውጭ ሜዳ ሰባተኛ ተከታታይ ግጥሚያውን በማሸነፍ የማይበገር እንደሆነ ቀጥሏል። ዶርትሙንድ በሰንበቱ ግጥሚያው ፍራይቡርግን ከኋላ ተነስቶ እርግጥ ከዕድል ጋር 2-1 ሲረታ የሰባት ነጥብ ልዩነት አመራሩን አሁንም እንደጠበቀ ነው። ለዘንድሮው አስደናቂ ክለብ የሰንበቱ ድል ከ 13 ግጥሚያዎች 11 ኛው ሲሆን አሠልጣኙ ዩርገን ክሎፕ ይሁንና የሻምፒዮናው ጉዞ ገና ረጅም መሆኑን ነው ያስገነዘበው።

“እኔ በበኩሌ የሊጋውን አመራር መያዙን በተመለከተ ብዙም ልምድ የለኝም። ሆኖም ግን ማንም ከሚያስበው በላይ እርጋታዬን እንደጠበቅኩ ነው። ይህን ለመገመት እችላለሁ። እርግጥ ነው 13 ግጥሚያዎች አድርገን 34 ነጥቦችን አግኝተናል። ይህ ደግሞ አስደናቂ ነገር ነው። ግን ሃቁን በትክክል መመልከት እንዳለብንም እናውቃለን”
ሊጋውን በመጀመሪያዎቹ ሰባት ግጥሚያዎች በበላይነት ይመራ የነበረው ማይንስ ደግሞ ደከም ካለ በኋላ እንደገና በማንሰራራት የመጨረሻውን መንሸን ግላድባህን 3-2 ሲያሸንፍ ወደ ሁለተኛው ቦታ ለመመለስ በቅቷል። የብዙ ጊዜው የጀርመን ሻምፒዮን ባየርን ሙንሺን በአንጻሩ ባለፉት ሁለት ሣምንታት የመጠናከር አዝማሚያ ካሣየ በኋላ በዚህ ሰንበት ከሌቨርኩዝን 1-1 በሆነ ውጤት ብቻ በመለያየት ከስድሥት ወደ ዘጠነኛው ቦታ መልሶ አቆልቁሏል። ሌቨርኩዝን በአንጻሩ ሶሥተኛ ነው።

Flash-Galerie Bundesliga 12. Spieltag Bayern Nürnberg 2010

የጀርመን ቡንደስሊጋ የዘንድሮ ሂደት ታላላቆቹ ወደታች፤ ታናናሾቹ ወደ ላይ ያሉበት አስደናቂ ሂደት ሲሆን በተለይ ማይንስ፣ ሃኖቨር፣ ፍራይቡርግ ወይም ፍራንክፈርት ከመጀመሪያዎቹ ሰባት ክለቦች መካከል ይሆናሉ ብሎ የጠበቀ ብዙ አልነበረም። በአንጻሩ ብሬመን፣ ሻልከና ሽቱትጋርት ከታች ወደ ላይ ተመልካች ሆነው እንደቀጠሉ ሲሆን በተለይም የብሬመን የዘንድሮ ክስረት በዓመታት ታሪኩ አቻ የማይገኝለት እየሆነ ነው። ቡድኑ ባለፉት ሣምንታት ድክመቱ ከቀጠለ ወደ ሁለተኛው ዲቪዚዮን እንዳይንሸራተት በጣሙን የሚያሰጋው ነው።

በዚህ መሰሉ ሁኔታ ላይ ከሚገኙት ክለቦች አንዱ የሆነው ኤፍ.ሢ.ኮሎኝም ሣምንቱን የመጨረሻውን ቦታ ይዞ ካሳለፈ በኋላ ትናንት ሽቱትጋርትን 1-0 በማሸነፍ ቦታውን ለግላድባህ አስረክቧል። ብቸኛዋንና አከራካሪ የሆነችውን የፍጹም ቅጣት ምት ጎል በ 82ኛዋ ደቂቃ ላይ ያስቆጠረው የብሄራዊው ቡድን አጥቂ ሉካስ ፖዶልስኪ ነበር። ከጥቂት ዕድል ጋር የተገኘው ድል በደጋፊዎች ቁጣ ሳቢያ ነውጽ ላይ ለሚገኘው ክለብ ጊዜያዊ ዕፎይታን ቢሰጥም ዘላቂ መሻሻል መታየቱ ግን ገና እርግጠኛ አይደለም። ለማንኛውም በአሻሚ ፍጹም ቅጣት ምት የለየለት ግጥሚያ ለሽቱትጋርት ደግሞ የመሃል ሜዳ ተጫዋቹ ቲሞ ጌብሃርት እንዳለው መሪር ነው የሆነው።

“መሪር ነገር ነው። እኔ በዕውነት ፍጹም ቅጣት እንደነበር አላውቅም። ያልነበረ መስሎ ነው የታየኝ። በመጨረሻው ደቂቃ ላይ እንዲያውም ራሴ ተመትቻለሁ። እና ይህን መሰሉ ፍጹም ቅጣት ምት ከተሰጠ ዳኛው እዚህም ዕርምጃ ሊወስድ በተገባው ነበር። ለማንኛውም በጨዋታው ብዙ ዕድል አግኝተን ነበር። ግን ጎል አላገባንም። እናም ትግሉ ይቀጥላል”

በስፓኝ ፕሪሜራ ዲቪዚዮን የሁለቱ ቀደምት ክለቦች ከዋክብት ክሪስቲያኖ ሮናልዶና ሊዮኔል ሜሢ በየፊናቸው ሶሥት ጎሎች በማስቆጠር ለየክለቦቻቸው ሰፊ ድል ታላቅ አስተዋጽኦ አድርገዋል። ሰንበቱ ሬያል ማድሪድ ቢልባኦን 5-1 የረታበት ባርሤሎናም አልሜይራን 8-0 ቀጥቶ የተመለሰበት ነበር። ሬያል አሁን ከ 12 ግጥሚያዎች በኋላ በአንዲት ነጥብ ብልጫ የሚመራ ሲሆን ባርሣ ሁለተኛ ነው፤ ቫልሬያል ሰባት ነጥቦች ዝቅ ብሎ በሶሥተኝነት ይከተላል።
ሣምንት ሁለቱ ክለቦች ሬያልና ባርሤሎና በባርሣው ኖው-ካምፕ ስታዲዮም እርስበርስ የሚገናኙ ሲሆን ግጥሚያው ምናልባት በወደፊቱ ሂደት ላይ ወሣኝ ሊሆን የሚችል ነው። በሌላ በኩል በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ ደግሞ የቼልሢይ በተከታታይ ለሁለተኛ ጊዜ መሽነፍ ቢያንስ በአራት ክለቦች መካከል የተያዘውን የቁንጮነት ፉክክር የበለጠ አጠናክሮታል። ዝርዝሩን የለንደን ወኪላችን ሃና ደምሤ!

በኢጣሊያ ሤሪያ-አ የኢንተር ሚላን ማቆልቆል ባለበት ቀጥሏል። ቀደምቱ ክለብ በቺየቮ 2-1 ሲረታ ከአንደኛው ከኤ.ሢ.ሚላን ዘጠኝ ነጥቦች ዝቅ ብሎ ስድሥተኛ ነው። ላሢዮ ምንም እንኳ ከፓርማ 1-1 ቢለያይም ሶሥተኛ ሆኖ እንደቀጠለ ሲሆን ናፖሊም በአራተኝነቱ ረግቷል። በተቀረ በፈረንሣይ ሻምፒዮና ሊል ሞናኮን 2-1 በማሸነፍ አመራሩን ሲይዝ በኔዘርላንድ ሊጋም አይንድሆፈን አመራሩን ወደ ሶሥት ነጥቦች ለማስፋት ችሏል።

በአውሮፓ ክለቦች ሻምፒዮና ሊጋ ውድድር ወደ ጥሎ ማለፉ ዙር ለማለፍ ወይም ከ 16ቱ ቀጣይ ክለቦች መካከል አንዱ ለመሆን በሚደረገው ውድድር ነገና ከነገ በስቲያ ምሽት በርካታ ግጥሚያዎች ይካሄዳሉ። ከነዚሁ ጥቂቶቹም አያክስ አምስተርዳም ከሬያል ማድሪድ፤ ሮማ ከባየርን ሙንሺን፤ ብራጋ ከአርሰናል፤ እንዲሁም ኢንተር ሚላን ከኤን’ሼዴና ፓናቴናኢኮስ አቴን ከባርሤሎና ናቸው።

Commonwealth Games David Lekuta Rudisha

ዓለምአቀፉ አትሌቲክስ ፌደሬሺኖች ማሕበር በወንዶች የ 800 ሜትር የዓለም ክብረ-ወሰን ባለቤት የሆነውን ኬንያዊ ዴቪድ ሩዲሻንና በሴቶችም የክሮኤሺያዋን የከፍታ ዝላይ ንግሥት ብላንካ ቭላዚችን የዓመቱ አትሌቶች ብሎ ሰይሟል። ውጤቱ ይፋ የሆነው ትናንት ሞናኮ ላይ በተካሄደ የማሕበሩ የግብዣ ስነ-ስርዓት ላይ ነው። የ 21 ዓመቱ ሩዲሻ ለዚህ ታላቅ ክብር ሲበቃ ወጣቱና የመጀመሪያው የኬንያ አትሌትም ሆኗል።

በአሜሪካ-አትላንቲክ ሢቲይ በዓለም ቡጡ ካውንስል የመካከለኛ ክብደት ግጥሚያ የአርጄንቲናው ሤርጆ ማርቲኔዝ አሜሪካዊ ተጋጣሚውን ፖውል ዊሊያምስን በሁለተኛው ዙር ላይ በከባድ ምት በመዘረር እንደገና ማዕረጉን ለማስመለስ በቅቷል። ማርቲኔዝ በዚሁ አሜሪካዊ ተሸንፎ ማዕረጉን የተነጠቀው ባለፈው ታሕሣስ ወር ነበር።
ዘገባችንን በእግር ኳስ ለማጠቃለል ባለፈው ሣምንት አጋማሽ ላይ በዓለም ዙሪያ የዓመቱ መጠቃለያ ሆነው የታዩ ከሰላሣ የሚበልጡ የወዳጅነት ግጥሚያዎች ተካሂደው ነበር። በደቡብ አፍሪቃው የዓለም ዋንጫ ዓመት መገባደጃ ላይ ታዲያ በተለይም ሻምፒዮኑ የስፓኝ ብሄራዊ ቡድን በፖርቱጋል 4-0 መሸነፉ ብዙ ሳያስገርም አልቀረም። ከብዙ በጥቂቱ ለማስታወስ አርጄንቲና ብራዚልን 1-0፤ ፈረንሣይ እንግሊዝን 2-1፤ ኔዘርላንድ ቱርክን 1-0፤ እንዲሁም ግብጽ አውስትራሊያን 3-0 ሲያሸንፉ፤ ስዊድንና ጀርመን ደግሞ ባዶ-ለባዶ ተለያይተዋል።

መሥፍን መኮንን

ተክሌ የኋላ