የስፖርት ዘገባ | ስፖርት | DW | 26.07.2010
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ስፖርት

የስፖርት ዘገባ

ሣምንቱ በአትሌቲክሱ የስፖርት መድረክ ሞናኮ ላይ የዲያመንድ ሊግ ውድድር የተካሄደበት ነበር። ካናዳ-ሞንክተን ላይ ሲካሄድ የሰነበተው የዓለም አትሌቲክስ ፌደሬሺኖች ማሕበር የወጣቶች ሻምፒዮናም ባለፈው ምሽት ተጠናቋል።

default

ከዚህ በተጨማሪ በቱር-ዴ-ፍራንስ የቢስክሌትና በፎርሙላ-አንድ የአውቶሞቢል እሽቅድድሞች፤ እንዲሁም በቴኒስ ላይም የምናተኩር ሲሆን በአትሌቲክስ እንጀምርና ባለፈው ሐሙስ ሞናኮ ላይ በተካሄደው የዲያመንድ ሊግ ውድድር አሜሪካዊው ታይሰን ጌይ በሁለት መቶ ሜትር ሩጫ ሲያሸንፍ በሴቶች አንድ መቶ ሜትርም እንዲሁ የአገሩ ልጅ ካሜሊታ ጄተር ቀድማ ከግቧ ደርሳለች። ሁለቱም አሜሪካውያን ያሸነፉት ጠንካራ የጃማይካ ተፎካካሪዎቻቸውን በማስከተል ነው።
በሌላ በኩል በወንዶች አራት መቶ ሜትር ሩጫ ጃማይካውያኑ ጀርሜይን ጎንዛለስና ሪካርዶ ቼምበርስ በመከታተል ሲያሸንፉ በ 800 ሜትር የሱዳኑ ተወዳዳሪ አቡባከር ካኪ ኬንያዊ ተፎካካሪውን ቦአዝ ኪፕላጋትን ከኋላው በማስቀረት ልዕልናውን እንደገና አስመስክሯል። ሌላው ኬንያዊ የመካከለኛ ርቀት ሯጭ ሢላስ ኪፕላጋት በአንጻሩ በ 1,500 ሜትር የሞሮኮና የኬንያ ተፎካካሪዎቹን ጥሎ ከግቡ በመድረስ ለድል በቅቷል። የአሜሪካ ወንድ አትሌቶች በ 110 እና 400 ሜትር መሰናክል ሩጫም አሸናፊ ሲሆኑ በከፍታ ዝላይ ደግሞ የሩሢያ አትሌቶች ኢቫን ኡኮቭና አንድሬ ሲልኖቭ አንደኛና ሁለተኛ ወጥተዋል።

ዩ,ኤስ.አሜሪካ በሴቶችም ጠንክራ ስትታይ ሎላ ጆንስ በ 110 ሜትር መሰናክልና አሊሢያ ጆንሰንም በ 800 ሜትር ሩጫ አሸንፈዋል። ለኢትዮጵያ ስንታየሁ እጅጉ በሶሥት ሺህ ሜትር ሩጫ ስታሸንፍ ማርያም ዩሱፍ ጀማል ከባሕሬይን ሁለተኛ፤ ሼኒን ሮውበሪይ ከአሜሪካ ሶሥተኛ፤ ሚሚ በለጠ ለባህሬይን አራተኛ፤ እንዲሁም ሢልቪያ ኪቤት ከኬንያ አምሥተኛ በመሆን ሩጫውን ፈጽመዋል። በላይነሽ’ ኦልጂራ ደግሞ ሰባተኛ ሆናለች። በአትሌቲክሱ መድረክ ዛሬ የአውሮፓ አትሌቲክስ ሻምፒዮና ስፓኝ-ባርሤሎና ላይ በስነ ስርዓት የሚከፈት ሲሆን ውድድሩ ከነገ አንስቶ ዓለም የሚከታተለው ነው።

ኬንያ ደግሞ በሚቀጥለው ሣምንት የሚከፈተው የአፍሪቃ አትሌቲክስ ሻምፒዮና አዘጋጅ ስትሆን ፖሊስ ማንኛውንም ጥቃት ለመከላከል በአገሪቱ እስካሁን ያልታየ የደህንነት ጥበቃን ለማስፈን እየተዘጋጀ ነው። የደህንነት ጥበቃው ዕቅድ አውጭ ቡድን ስፖርተኞቹ በሆቴሎች፣ በስታዲዮምና በመንገድ ላይም ብርቱ ጥበቃ የሚደረግላቸው መሆኑን አስታውቋል። ኬንያ ከዚህ ቀደም የዓለም አገር አቋራጭ ሩጫና የመላው አፍሪቃ ጨዋታን አዘጋጅታ አስተናግዳለች።

ሣምንቱ በካናዳ-ሞንክተን ከተማ 13ኛው የዓለም ታዳጊ ወጣቶች የአትሌቲክስ ሻምፒዮና የተካሄደበትም ነበር። ሰባት ቀናት በፈጀው ውድድር ከ 170 ሃገራት የተውጣጡ 1,400 አትሌቶች ሲሳተፉ በመጨረሻ ኬንያ የበላይቷን ለማረጋገጥ ችላለች። የኢትዮጵያ አትሌቶችም ተሳትፏቸውን በሰባተኝነት ሲያበቁ በስፍራው የተገኘው አንዳርጋቸው ታምር ውድድሩ ባለፈው ምሽት ሊጠቃለል ጥቂት ሰዓታት ሲቀሩት ዘገባ ልኮልናል።

Tour de France 2010 20. und letzte Etappe Alberto Contador

ቱር-ዴ-ፍራንስ

በዓለም ላይ ታላቅ ከሚባሉት የቢስክሌት እሽቅድድሞች የአንዱ የቱር-ዴ-ፍራንስ የዘንድሮ ውድድር ትናንት በስፓኙ ተወላጅ በአልቤርቶ ኮንታዶር ድል ተፈጽሟል። ለኮንታዶር የትናንቱ ድል በቱር-ዴ-ፍራንስ ሶሥተኛው መሆኑ ነው። በአንጻሩ የሰባት ጊዜው ሻምፒዮን አሜሪካዊው ላንስ አርምስትሮንግ በ 38 ዓመት ዕድሜው ተመልሶ እንደገና ጠንካሮቹን ተወዳዳሪዎች በማሸነፍ ለመሰናበት የነበረው ሕልም ዕውን ሳይሆንለት ቀርቷል።
ኮንታዶር ሶሥት ሣምንታት በፈጀው ውድድር ትናንት በመጨረሻው ደረጃ እሽቅድድም ያሽነፈውን የብሪታኒያ ተወዳዳሪ ማርክ ካቨንዲሽን ለመቅደም ባይችልም አጠቃላይ ድሉን ሊነጠቅ አልቻለም። በአጠቃላይ ነጥብ የሉክሰምቡርጉ ኤንዲይ ሽሌክ ሁለተኛ ሲሆን የሩሢያው ዴኒስ ሜንቾቭ ደግሞ ሶሥተኛ ወጥቷል። ላንስ አርምስትሮንግ ከእሽቅድድሙ ዓለም ለመጨረሻው ሲሰናበት በገናና ዘመኑ የተከለከሉ አካል አጎልባች መድሃኒቶችን ወስዷል ሲል እየተጠናከረ በመጣው ጥርጣሬ የተነሣ መጪው ጊዜ ቀላል የሚሆንለት አይመስልም። ጉዳዩ ጭብጥ ከሆነ ለወህኒቤት ሊያበቃው የሚችልም ነው።

ፎርሙላ-አንድ እሽቅድድም

Formel 1 Rennen in Hockenheim Deutschland

በዚህ በጀርመን ትናንት የተካሄደው የፎርሙላ-አንድ አውቶሞቢል እሽቅድድም ደግሞ ለአገሪቱ ተወዳዳሪዎች ለክሪስቲያን ፌትል ሆነ ለኒኮ ሮዝበርግ ወይም ለሚሻኤል ሹማኸር የተሣካ ሣይሆን አልፏል። እሽቅድድሙን በቀደምትነት የፈጸሙት ሁለቱ የፌራሪ ዘዋሪዎች የስፓኙ ተወላጅ ፌርናንዶ አሎንሶና ብራዚላዊው ፌሊፔ ማሣ ናቸው። ዜባስቲያን ፌትል ምንም እንኳ እሽቅድድሙን ከአንደኛው ቦታ ቢጀምርም በአገሩ ለማሸነፍ ያገኘውን አመቺ ዕድል ሊጠቀምበት አልቻለም።
በመጨረሻ የተቀሩት ጀርመናውያን ሮዝበርግ ስምንተኛ፤ እንዲሁም ሚሻኤል ሹማኸር ደግሞ ዘጠነኛ በመሆን ተወስነዋል። ከትናንቱ እሽቅድድም ወዲህ የብሪታኒያው ሉዊስ ሃሚልተን በ 157 አጠቃላይ ነጥቦች አንደኛ ሲሆን ሌላው ብሪታኒያዊ ያለፈው ዓመት ሻምፒዮን ጄሰን ባተን በ 143 ነጥቦች ሁለተኛ ነው። የአውስትራሊያው ማርክ ዌበርና የጀርመኑ ዜባስቲያን ፌትል ደግሞ እኩል 136 ነጥብ ይዘው ይከተላሉ።

የቴኒስ ዓለምአቀፍ ግጥሚያዎች

የትናንቱ ሰንበት በዓለም ዙሪያ የተለያዩ የቴኒስ ፍጻሜ ግጥሚያዎች የተካሄዱበትም ነበር። አሜሪካ ውስጥ በአትላንታው የቴኒስ ሻምፒዮና ማርዲይ ፊሽ ጆን ኢስነርን በሶሥት ምድብ ጨዋታ 2-1 በማሸነፍ በድል ጉዞው ቀጥሏል። ለፊሽ የትናንቱ ድል በተከታታይ አሥረኛው ሲሆን በዘንድሮው የውድድር ወቅትም አከታትሎ ሁለተኛው መሆኑ ነው። አሜሪካዊው ፊሽ በዚህ ከቀጠለ በዓለምአቀፉ የማዕረግ ተዋረድ ላይ ደረጃውን በጣሙን እንደሚያሻሽል ጨርሶ አያጠራጥርም።

በቪየና የዓለም ቴኒስ ማሕበር ፍጻሜ ግጥሚያ ጀርመናዊቱ ዩሊያ ጎርግስ የስዊስ ተጋጣሚዋን ቲሜያ ባሺንስኪን በሁለት ምድብ ጨዋታ በለየነት ሁኔታ በማሽነፍ ለታላቅ ድል በቅታለች። ድሉ በዓለምአቀፉ የማዕረግ ተዋረድ ላይ ከ 65ኛ ወደ 50ኛው ቦታ ከፍ የሚያደርጋት ነው። ስሎቬኒያ ውስጥ በተካሄደ ውድድር ደግሞ ቀድሞ በዓለም ላይ አንደኛ የነበረችው አና ቻክቬዳትሴ ከሁለት ዓመታት ቆይታ በኋላ ለመጀመሪያ የፍጻሜ ድሏ በቅታለች። የ 23 ዓመቷ ሩሢያዊት ከቁንጮነት ወደ 103ኛው ቦታ ማቆልቆሏ የሚታወቅ ነው።

በጀርመን ሰሜናዊት ከተማ የሃምቡርግ ኤቲፒ ፍጻሜ ግጥሚያም የካዛክስታኑ አንድሬይ ጎሉቤቭ የአውስትሪያ ተጋጣሚውን ዩርገን ሜልሰርን በሁለት ምድብ ጨዋታ አሸንፏል። ጎሉቤቭ በአንድ ዓለምአቀፍ ውድድር ላይ ለፍጻሜ ድል ሲበቃ የትናንት የመጀመሪያ መሆኑ ነበር።

መሥፍን መኮንን

ሂሩት መለሰ