የስፖርት ዘገባ | ስፖርት | DW | 01.06.2010
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ስፖርት

የስፖርት ዘገባ

የደቡብ አፍሪቃ የዓለም እግር ኳስ ዋንጫ ፍጻሜ ውድድር የፊታችን አርብ ሣምንት ይከፈታል። ታላቁ ፌስታ በሽብርተኞች ጥቃት ሊታወክ ይችል ይሆን?

የስፖርት ዘገባ

የአሜሪካ የፖለቲካ ኢንስቲቲዩት ሃላፊ ሮናልድ ሣንዲ በብሄራዊው ሸንጎ ፊት በሰጡት ቃል ከፍተኛ የጥቃት አደጋ አለ ሲሉ ማስጠንቀቃቸው ጥቂትም ቢሆን ማሳሰቡ አልቀረም። በሌላ በኩል ተወዳዳሪዎቹ ቡድኖች ቀስ በቀስ ደቡብ አፍሪቃ መግባት ሲጀምሩ ሣምንቱ በርካታ የአቅም ፍተሻ ግጥሚያዎች የተካሄዱበትም ነበር።

በአፍሪቃ ምድር የመጀመሪያውና ከሰባ ዓመታት በሚበልጥ ዕድሜው 19ኛው የሆነው የዓለም አግር ኳስ ዋንጫ ፍጻሜ ውድድር በትክክል ከአሥር ቀናት በኋላ ይከፈታል። መሰናዶው ሁሉ በተጠበቀው መጠን እየተጠናቀቀ ሲሆን በጅምሩ ደከም ብሎ የታየው የቲኬት ሽያጭም ስኬት እየታየበት ነው። የብሄራዊው አዘጋጅ ኮሚቴ ሊቀ-መንበር ኢርቪን ኮዛ ሰንበቱን እንደገለጹት በጠቅላላው ለ 64 ግጥሚያዎች ከተመደቡት 2,9 ሚሊዮን ቲኬቶች 97 በመቶው ከወዲሁ ተሽጠዋል።
ይህም ደቡብ አፍሪቃን ካለፈው የ 2006 ዓ.ም. አዘጋጅ ከጀርመን የሚያስተካክል ሲሆን ኮዛ እንዳሉት በተቀሩት ቀናት ከዚህም ሊያልፍ የሚችል ነው። ይህ አስደሳቹ ዜና ሲሆን በሌላ በኩል ታላቁ ውድድር የሽብርተኞች የጥቃት ዒላማ እንዳይሆን ከዚህም ከዚያም የሚሰማው ማስጠንቀቂያ በሰንበቱ መጠናከር ይበልጥ ትኩረትን መሳቡ አልቀረም። ለዚህም እርግጥ ምክንያት አልታጣም።
የኢራቅ ባለሥልጣናት በቅርቡ በዓለም ዋንጫው ሂደት ደቡበ አፍሪቃ ውስጥ ጥቃት ለማድረስ ያቀደ አብዱላህ-አል-ቃህታኒ የተሰኘ የአል-ቃኢዳ ተከታይን ማሰራቸውና አሁን ደግሞ አደጋው 80 በመቶ ሊደርስ እንደሚችል ከአሜሪካ መነገሩ ብዙ የሚያሳስብ ነው። ይሁንና የደቡብ አፍሪቃ ባለሥልጣናት በውድድሩ ወቅት ጸጥታን ለማስከበር የተቻላቸውን ሁሉ እየጣሩ ሲሆን በነርሱ አባባል እስካሁን ለተባለው አደጋ የተገኘ ጭብጥ ፍንጭ የለም።
የአገሪቱ ፖሊስም ጸጥታን ለማስከበር አስፈላጊው ዝግጅት ተደርጓል ባይ ነው። ሰለዚሁ የጸጥታ ጉዳይና አስተናጋጇን አገር ጨምሮ የአፍሪቃ ታሳታፊ አገሮች በውድድሩ ስለሚኖራቸው ተሥፋ ዛሬ ሶዌታን የተሰኘውን ዮሶዌቶን ቀደምት ጋዜጣ ምክትል አዘጋጅ ሞጎሞትሲ ሴሌቢን በስልክ አነጋግረን ነበር፤ መንግሥት ጸጥታን እንደሚያረጋግጥ ዋስትና መስጠቱን ነው በመጀመሪያ የገለጸልን።

“ልገልጽልህ የምችለው ቢኖር ትልልቅ ክንውኖች ከመካሄዳቸው በፊት ምንጊዜም ስጋት ይኖራል። የተለየ ነገር የለም። እያንዳንዱ ነገር በጥንቃቄ እየታየ እንደሆነ ከጸጥታ ክፍሉ መተማመኛ አግኝተናል። ከሣምንታት በፊት በአረንጓዴው ጎዳና ላይ የቦምብ ጥቃት ሊፈጸም ነው የሚል ነገር ተነስቶ ነበር። ግን ሃሰት ነው። እንዲህ ዓይነት ማስፈራራት ይኖራል። በአገሪቱ ያለውን ሁኔታ ስናይ ሁሉም ሰው ደህንነቱ የተረጋገጠ ነው። ባለፈው ዓመት የዓለም የኮንፌደሬሺን ዋንጫ ውድድርን አስተናግደናል። ምንም የተፈጠረ ችግር አልነበረም። ሰዎች አል-ቃኢዳ ይህን ሊያደርግ ነው፤ አል-ቃኢዳ ያንን ሊያደርግ ነው የሚሉት ለምን እንደሆነ አይገባኝም”

የደቡብ አፍሪቃ ብሄራዊ ቡድን ዝግጅትስ እስከምን ነው? ወደ ተከታዩ ዙር የማለፍ ዕድል አለው?

“ቡድናችን ጥሩ ይጫወታል። ብዙ የወዳጅነት ጨዋታዎች አድርጓል። በቅርቡ ከኮሉምቢያ ብሄራዊ ቡድን ጋር ተጋጥሞ 2-1 አሸንፎ ነበር። ደጋፊዎቹ የውድድሩን ጥሩ መሆን ነው የሚጠብቁት። እናም፤ አዎ! ጥሩ ነገር ይሰራል። ቡድኑ ወደሚቀጥለው ዙር እንደሚያልፍ አምናለሁ”

የተቀሩት የአፍሪቃ አገሮች ጥንካሬስ ምን ያህል ነው?

“አይቮሪ ኮስት እንዲሁም ማይክል ኤሢየንን የያዘችው ጋና ካባድ ቡድኖች ናቸው። ግን፤ አይቮሪ ኮስት የተሻለው ነው እላለሉ። በርግጥ ናይጄሪያም የአፍሪቃ እግር ኳስ ሃያል መሪ እንደነበረች ይታወቃል። ነገር ግን አሁን ጠንካራ አድርጌ የማያቸው አይቮሪ ኮስትንና ጋናን ነው”

Südafrika Füßball südafrikanische Fans Südafrika gegen Namibia

ወደ እግር ኳሱ ጨዋታ መለስ እንበልና አብዛኞቹ የዓለም ዋንጫው ፍጻሜ ተሳታፊ አገሮች በወቅቱ በያዙት የመጨረሻ ዝግጅት የአቅም ፍተሻ ግጥሚያዎችንም እያካሄዱ ነው። ባለፈው ሣምንትና ሰንበቱን በተደረጉ ግጥሚያዎች’ ካሜሩን ከስሎቫኪያ 1-1 ስትለያይ ሰርቢያ ባልተጠበቀ ሁኔታ በኒውዚላንድ 1-0 ተሸንፋለች። ዩናይትድ ስቴትስ ቱርክን 2-1 ስትረታ ጀርመን ደግሞ ሁንጋሪያን ልዕልና በተመላበት ሁኔታ 3-0 ሸኝታለች። ዩናይትድ ስቴትስ ለስኬት የበቃችው ቀደም ሲል ባለፈው ማክሰኞ ዘንድሮ ለዓለም ዋንጫ ውድድር ባልደረሰችው በቼክ ሬፑብሊክ 4-2 ከተሽነፈች በኋላ ነበር።

የቺሌ ብሄራዊ ቡድን በሣምንቱ ሰሜን አየርላንድን 3-0 ከዚያም እሥራኤልን 1-0 በመርታት ራሱን ሲያሟሙቅ ፈረንሣይ ደግሞ ቀደም ሲል ኮስታ ሪካን 2-1 ካሽነፈች በኋላ ትናንት ግን ከቱኒዚያ በ 1-1 ውጤት ተወስናለች። ከዚሁ ሌላ ናይጄሪያ ከኮሉምቢያ 1-1፤ ፓራጉዋይ ከአይቮሪ ኮስት 2-2፤ ሁለቱም እኩል ለእኩል ሲወጡ በፊታችን አርብ ሣምንት የደቡብ አፍሪቃ የመክፈቻ ተጋጣሚ የሆነችው ሜክሢኮ ጋምቢያን 5-1 በመርታት በጥሩ ሁኔታ ላይ መሆኗን አሳይታለች። ውጤቱ ለደቡብ አፍሪቃ ማስጠንቀቂያ የሚሆን ነው።

የዓለም ዋንጫው ውድድር እግር ኳስ እጅግ ተወዳጅ በሆነባት በኢትዮጵያስ በስፖርቱ አፍቃሪዎች ዘንድ ምን ስሜትን ነው የሚቀሰቅሰው? የኢትዮጵያ የእግር ኳስ ስፖርት ለታላቅ ድል የበቃበት ሶሥተኛው የአፍሪቃ ዋንጫ ውድድር ዛሬ የረጅም ጊዜ ትውስት ነው። ቢቀር ባለፉት ሶሥት አሠርተ-ዓመታት ምናልባት ማቆልቆል እንጂ የዕድገት ዕርምጃ አልታየም። ታዲያ በተለይም ዛሬ ታላቁ የዓለም ዋንጫ ውድድር በክፍለ-ዓለማችን፤ በቅርባችን ሲካሄድ አገሪቱ የዳር ተመልካች እንደሆነች መቀጠሏ ያሳዝናል። ቀሪው ቁጭት ነው፤ ከአዲስ አበባ፤ የታደሰ እንግዳውን ዘገባ ያድምጡ!

መሥፍን መኮንን

ተክሌ የኋላ