የስፖርት ዘገባ | ስፖርት | DW | 24.05.2010
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ስፖርት

የስፖርት ዘገባ

ሰንበቱ ኢንተር ሚላን የጀርመኑን ቀደምት ክለብ ባየርን ሙንሺንን በማሸነፍ የአውሮፓ ሻምፒዮና ሊጋ የዋንጫ ባለቤት የሆነበት ነበር።

default

ዲየጎ ሚሊቶ

በዓለምአቀፍ ከዋክብት የተመላው የኢጣሊያው ቀደምት ክለብ ኢንተር ሚላን ከሤሪያ-አ እና ከብሄራዊው ፌደሬሺን ዋንጫ ባሻገር ባለፈው ቅዳሜ ምሽት ባየርን ሙንሺንን 2-0 በመርታት ለውድድሩ ወቅት ሶሥተኛ ድሉ በቅቷል። በማድሪዱ ቤርናቤዎ ስታዲዮም በተካሄደው የፍጻሜ ግጥሚያ ሁለቱም ክለቦች የታክቲክና የቴክኒክ ስክነት ሲያሳዩ የጨዋታውን ውጤት የወሰነው እርግጥ ኢንተር ረቀቅ ያለው ቡድን ቢሆንም የግል ችሎታ ነበር ለማለት ይቻላል። ሁለቱንም ጎሎች በ 35ኛና በሰባኛዋ ደቂቃ ላይ ያስቆጠረው አርጄንቲናዊው ግሩም አጥቂ ዲየጎ ሚሊቶ ነበር። ሆኖም ግን ሚሊቶ ለስኬቱ ይበልጡን ድርሻ የሰጠው ለአሠልጣኙ ለሆሴ ሞሪኖ ነው።

“በዚህ ድል ከመጠን በላይ ነው የተደስትነው። ሕልማችን ዕውን ሊሆን ችሏል። ለዚህ ስኬት ደግሞ እርግጥ የአሠልጣኛችን ድርሻ እጅግ አስፈላጊ ነበር። በተለየ ትጋት በመሥራት እንደ ቡድን ሊያስተሳስረን በቅቷል”

ሚላኖ ውስጥ ከመቶ ሺህ የሚበልጡ የኢንተር ደጋፊዎች የከተማይቱን ማዕከል በርችትና በሰንደቅ ዓላማዎች ሲያደምቁ በድል የተመለሰው ቡድን ዋንጫውን በያዘው አርጄንቲናዊ አምበሉ በዛኔቲ አማካይነት ከስታዲዮሙ ሲገባ አርባ ሺህ ደጋፊዎቹ በታላቅ ስሜት ተቀብለውታል። የኢንተር ደጋፊዎች ምሽቱን ያሳለፉት ወደ ሬያል ማድሪድ የሚሄደውን የቡድኑን ፖልቱጋላዊ አሠልጣኝ ሆሴ ሞሪኖንም በማወደስና እንዲቆይ በመማጸን ነበር። የኢጣሊያ ጋዜጦች እንደዘገቡት የኢንተር ድል ለኢጣሊያ እግር ኳስ ከፍተኛ ትርጉም ያለው ነው።

ከብዙ በጥቂቱ ለመጥቀስ ላ ጋዜታ ስፖርቲቫ ሲያትት “የድንቁ አርጄንቲናዊ የዲየጎ ሚሊቶ ሁለት ጎሎች ታላቁን ኢንተርን ከ 45 ዓመታት በኋላ ወደ አውሮፓ ዙፋን መልሰዋል” ሲል “ኮሪየሬ ዴሎ ስፖርት” ደግሞ “ድሉ የሞሪኖ ነበር። ክለቡ ወደ ዓለምአቀፍ ቦታው እንዲመለስ ያደረገ የተለየ አሠልጣኝ ነው” በማለት አድናቆቱን ገልጿል። ለባየርን ሙንሺን በአንጻሩ ሽንፈቱ መሪር ቢሆንም ሆላንዳዊው አሠልጣኝ ሉዊስ ፋን ኸል የኢንተርን ልዕልና ላለመቀበል አላንገራገሩም።

“ኢንተር ሚላንን የመሰለ ቡድንን ለማሸነፍ በጥሩ ሁኔታ ላይ መሆን የግድ አስፈላጊ ነው። ዛሬ ይህ እንደሚፈለገው አልነበረም። ማጥቃት ደግሞ ከመከላከል ይልቅ ከባድ መሆኑ ግልጽ ነው”

የጀርመኑን ቀደምት ክለብ የሚያጽናና አንድ ነገር ቢኖር ፈረንሣዊ ግሩም ተጫዋቹ ፍራንክ ሪቤሪይ ከብዙ ውጣ ውረድ በኋላ ኮንትራቱን በአምሥት ዓመት ማራዘሙና ክለቡ በሚቀጥለው የአውሮፓ ሻምፒዮና ሊጋ ውድድርም የሚሳተፍ መሆኑ ነው።

Artikelbild Übersicht Maskottchen WM 2010 Fußball-Weltmeisterschaft

ደቡብ አፍሪቃ ውስጥ የሚካሄደው የዓለም እግር ኳስ ዋንጫ ፍጻሜ ውድድር እየቀረበ ሲሄድ በዝግጅቱ ላይ አፍጥጦ የቆየው ውይይትና ክርክር ቀስ በቀስ ወደ ተሳታፊዎቹ ቡድኖችና የውድድር ዕድላቸው እየተሻገረ ነው። በተለይ በአፍሪቃ ምድር ለመጀመሪያ ጊዜ በሚካሄደው ውድድር የአፍሪቃ ቡድኖች የስኬት ተሥፋ እስከምን ነው? ብዙዎችን ማነጋገሩ አልቀረም።
አስተናጋጇን አገር በተመለከተ ብራዚላዊው አሠልጣኝ ካርሎስ አልቤርቶ ፓሬይራ ሆዴ ውስጥ ጠለቅ ብሎ ጥሩ ስሜት ነው ያለኝ ብለዋል። ቡድኑ ከቀን ወደቀን እየተሻሻለ መምጣቱ ተሥፋ ሰጭ እንደሆነ ነው የሚናገሩት። ደቡብ አፍሪቃ ከፈረንሣይ፣ ከሜክሢኮና ከኡሩጉዋይ ጋር የተመደበች ሲሆን እርግጥ ቀደምቱ ጥረት የመጀመሪያውን ከባድ ዙር ማለፉ ይሆናል። እርግጥ ሌሎቹም አምሥት የአፍሪቃ አገሮች ወደሚታለመው ድል ለመዝለቅ ወይም ወደ ጆሃንስበርጉ ሶከር-ሢቲይ ስታዲዮም ፍጻሜ የሚያመራውን መንገድ በስኬት ለማቋረጥ ገና ከጅምሩ ብርቱ ፈተና ነው የሚጠብቃቸው።
ጋና ከጀርመን፣ ከሰርቢያና ከአውስትራሊያ ጋር ስትመደብ አይቮሪ ኮስት ደግሞ ይብሱን ከብራዚል፣ ከፖርቱጋልና ከሰሜን ኮሪያ ጋር እሣት ውስጥ ነው ያለችው። ከአልጄሪያና ከናይጄሪያ ብዙ አይጠበቅም፤ ምናልባት ካሜሩን በ 1990 ኢጣሊያ ውስጥ ያሳየችውን ተዓምር ትደግመው ይሆን? የማይቻል ነገር የለም። መንገዱ ጠባብ ይምሰል እንጂ!

ያለፈው ሣምንት ዓለምአቀፍ የአትሌቲክስ ውድድሮችም የተካሄዱበት ነበር። ብራዚል ውስጥ ትናንት ቤለም ላይ’ በተካሄደው ግራንድ-ፕሪ ውድድር የአሜሪካ አትሌቶች በመቶና ሁለት መቶ ሜትር አሸናፊ ሲሆኑ በ 800 ሜትር ለድል የበቃው ብራዚላዊው ዴቪድ ክሌበርሶን ነው። በአምሥት ሺህ ሜትር ኬንያውያን ከአንድ እስከ አምሥት ተከታትለው ሲያሽንፉ ጋሪ ሮባ ስድሥተኛ ወጥቷል። በሴቶች አጭር ሩጫ የጃማይካ አትሌቶች ሲያይሉ በሶሥት ሺህ ሜትር መሰናክል ደግሞ ድሉ የመቅደስ በቀለ ነበር። ብርቱካን አለሙም ሶሥተኛ ሆናለች።

በሣምንቱ የዲያመንድ-ሊግ ውድድር ደግሞ ጃማይካዊው የዓለም ኮከብ ዩሤይን ቦልት ባለፈው ረቡዕ ደቡብ ኮሪያ ዴጉ ውስጥ በመቶ ሜትር፤ ትናንትም በሻንግሃይ በሁለት መቶ ሜትር በማሸነፍ በግሩም ሁኔታ ወደ አትሌቲኩ መድረክ ተመልሷል። በሌላ በኩል ሁለቱም ውድድሮች በመካከለኛ ርዝመት ሩጫ ኬንያውያን ከኢትዮጵያ አትሌቶች ይልቅ አይለው የታዩባያቸው ነበሩ።

ለማጠቃለል በዚህ በጀርመን ሲካሄድ የሰነበተው የዓለም የበረዶ-ሆኪይ ሻምፒዮና ትናንት በቼክ ሬፑብሊክ አሸናፊነት ተፈጽሟል። ቼኮች ለዚህ ድል የበቁት የብዙ ጊዜዋን የዓለም ሻምፒዮን ሩሢያን ኮሎኝ ውስጥ በተካሄደው ፍጻሜ ግጥሚያ 2-1 በመርታት ነው። ጀርመን ደግሞ ለሶሥተኝነት በተካሄደው ግጥሚያ በስዊድን 3-1 በመሽነፍ ውድድሩን በአራተኝነት ፈጽማለች።

መስፍን መኮንን

አርያም ተክሌ