የስፖርት ዘገባ | ስፖርት | DW | 29.03.2010
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ስፖርት

የስፖርት ዘገባ

የጀርመን ቡንደስሊጋ ውድድር በሶሥት ክለቦች የበላይነት ፉክክር ሲቀጥል ሻልከ በዚህ ሰንበት አመራሩን ይዟል።

default

በትናንትናው ሰንበት ፖላንድ ውስጥ የተካሄደው የዓለም አገር-አቋራች ሩጫ ውድድር በግልም ሆነ በቡድን በኬንያ የተሟላ ድል ተፈጽሟል። ኬንያውያኑ በሁሉም ስምንት ውድድሮች ሲያሸንፉ በተለይ ለኢትዮጵያ አትሌቶች ዕለቱ የቀና አልነበረም። በአውሮፓ ቀደምት የእግር ኳስ ሊጋዎች የውድድሩ መጠቃለያ ወቅት እየተቃረበ በሄደ ቁጥር በዋና ዋናዎቹ ክለቦች መካከል ለሻምፒዮንነት የሚደረገው ፉክክርም ይበልጥ እየጠነከረ እንደቀጠለ ነው። ትናንት አወስትራሊያ ውስጥ የተካሄደው የፎርሙላ-አንድ አውቶሞቢል እሽቅድድም አሸናፊ ደግሞ ጄሰን ባተን ሆኗል።

ዓለምአቀፍ የአገር-አቋራጭ ሩጫ ውድድር

ፖላንድ-ቢጎሽች ላይ ትናንት ተካሂዶ በነበረው የዓለም አገር-አቋራጭ ሩጫ ሻምፒዮና የኬንያ አትሌቶች በመላው ስምንት ውድድሮች በማሸነፍ ፍጹም የበላይነት ለማሣየት በቅተዋል። በወንዶች 12 ኪሎሜትር ሩጫ የ 22  ዓመቱ ወጣት ኬንያዊ ጆዜፍ ኤቡያ በ 33 ደቂቃዎች ሲያሸንፍ ኤርትራዊው ተክለማርያም መድህን ስድሥት ሤኮንዶች ዘግየት ብሎ በመግባት ሁለተኛ ሆኗል። የኡጋንዳው ሞሰስ እንዲየማ ሶሥተኛ ሲወጣ ሩጫውን በተመሳሳይ ጊዜ በአራተኝነት የፈጸመው የኬንያው ሌዎናርድ ኮሜን ነው።                                                                                   
በተቀረ ኤርትራዊው ሣሙዔል ጸጋይ፣ የባሕሬይኑ ሃሣን ማሕቡብ፣ ኬንያውያኑ ሪቻርድ ማቴሎንግና ፓውል ታኑዊ ከአምሥት እስከ ዘጠኝ ሲከታተሉ ያለፈው ሻምፒዮን ኢትዮጵያዊው ገ/እግዚአብሄር ገ/ማርያም በአሥረኝነት ተወስኖ ቀርቷል። ኬንያዊው ኤቡያ በወንዶች 12 ኪሎሜትር ሲያሸንፍ አገሪቱ ዝነኛው ፓውል ቴርጋት ለመጨረሻ አምሥተኛ ድሉ ከበቃ ከ 11  ዓመታት ወዲህ ለመጀመሪያ ጊዜ መሆኑ ነው። ኤቡያ በቅርቡ በኤደንበርግ አገር-አቋራጭ ሩጫ ቀነኒሣ በቀለን ያህል ታላቅ አትሌት ማሸነፉ ይታወሣል።                                                   
በሴቶች 8  ኪሎሜትር ሩጫም ኬንያውያኑ አትሌቶች ሃያላኑ ነበሩ። ኤሚሊይ ቼቤትና ሊኔት ማሣይ አንደኛና ሁለተና ሲወጡ መሰለች መልካሙ ሩጫውን በሶሥተኝነት ፈጽማለች። ታዛቢዎችን ከሁሉም በላይ ያስደነቀው የሶሥት ጊዜዋ የዓለም ሻምፒዮን ጥሩነሽ ዲባባ በአራተኝነት ተወስና መቅረቷ ነው። ሌሎቹ ኬንያውያት ሊኔት ቼፕኩሩዊና ማርግሬት ሙሪኡኩ ደግሞ ሶሥት የኢትዮጵያ ተፎካካሪዎቻቸው’ን በማስከተል አምሥተኛና ስድሥተኛ ሆነዋል።

የኬንያ አትሌቶች ድል በዚህ ብቻ አላበቃም። የወጣቶቹ ውድድርም በካሌብ እንዲኩና በሜርሢይ ቼሬኖ መሪነት በወንዶችና በሴቶችም ከአንድ እስከ ሶሥት በመከታተል ነው የተፈጸመው። እናም ኬንያውያን በዓለም አገር-አቋራጭ ሻምፒዮና በወንዶችና በሴቶች ድርብ ድል ሲጎናጸፉ የትናንቱ ከ 16  ዓመታት በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ መሆኑ ነበር። በመሆኑም የቀድሞው ሻምፒዮን ፓውል ቴርጋት ዕለቱን ለኬንያውያን ታላቅ ቀን ሲል ነው የአገሩን አትሌቶች ድል ያወደሰው። በጥቅሉ በቡድን ደረጃ በወንዶች ኬንያ አንደኛ፣ ኤርትራ ሁለተኛና ኢትዮጵያ ሶሥተኛ ሲወጡ በሴቶችም ኬንያ ኢትዮጵያንና ዩ.ኤስ.አሜሪካን በማስከተል ቀደምቷ ሆናለች።

እግር ኳስ፤ የአውሮፓ ሊጋዎችና ሻምፒዮና ሊጋ

Fußball Bundesliga München Stuttgart Flash-Galerie

የባየርን ሽንፈትና የአሠልጣኑ የሉዊስ-ፋን-ኸል ራስ ምታት

በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ ውስጥ ለሻምፒዮንነት በሚደረገው የሶሥት ክለቦች የጠበቀ ፉክክር ማንቼስተር ዩናይትድና ቼልሢይ የሰንበት ግጥሚያዎቻቸውን በአስተማማኝ ድል ሲወጡ አርሰናል ብቻ ከበርሚንግሃም-ሢቲይ 1-1 በመለያየቱ ሁለት ጠቃሚ ነጥቦችን ማጣቱ ግድ ሆኖበታል። ማንቼስተር ዩናይትድ ዎንደረርስን 4-0 ሲያሸንፍ በተለይ የሣምንቱን ታላቅ ድል የተጎናጸፈው ኤስተን ቪላን 7-1 የሸኘው ቼልሢይ ነበር። ቼልሢይ በተለይ በሁለተኛው አጋማሽ አይሎ ሲታይ የክለቡ ምክትል ሃላፊ ሬይ ዊልኪንስ የተጫዋቾቹን የትግል መንፈስና ጥንካሬ እጅግ ነው ያወደሰው።

“አዎን በሣምንቱ ግሩም ነው የተጫወትነው። ወድግጥሚያው የገባነውም በጥሩ መንፈስ ነው። በተለይ በሁለተኛው አጋማሽ ያሳየነው ጨዋታ ግሩም ነበር። ተጫዋቾቹ በአካል ጠንካሮች ናቸው። በትጋትም ነው የሚለማመዱት። ሰባት ጎሎች አስቆጥረው እንኳ ስምንተኛ ለማግባት ነበር የሚታገሉት። የማሸነፍ ፍላጎታቸው ታላቅ ነው። እናም ሻምፒዮናው ክፍት እንደሆነ ይቀጥላል።

ቼልሢይ ከአውሮፓ ሻምፒዮና ሊጋ በኢንተር ሚላን ተሸንፎ በመውጣቱ የፕሬሚየር ሊጉን ሻምፒዮንነት ዘንድሮ ከመቼውም ይልቅ ይፈልገዋል። ለዚህም ነው በሣምንቱ አጋማሽ ፖርትማውዝን 5-0፤ አሁን ደግሞ ቪላን 7-1 በማሸነፍ ቁርጠኛ ትግል የያዘው። ከሰባት አራቱን ጎል ያስቆጠረው ግሩም ተጫዋቹ ፍራንክ ላምፓርድም ሻምፒዮን ለመሆን በሣምንቱ የታየው ጥንካሬ ቀጣይነት ሊኖረው ይገባል ባይ ነው።

“አዎን ግሩም ነገር ነው። ግን የውድድሩን ወቅት በሙሉ ጠንክሮ መገኘት ያስፈልጋል። እኔ ዛሬ ከጨዋው በፊት ግሩም ስሜት ነው የነነበረኝ። ሁሉም ነገር የሰመረ ነበር። እና ድሉ ተገቢ ነበር ለማለት እችላለሁ”

ፍራንክ ላምፓርድ በአራት ግቦቹ በጠቅላላ ያስቆጠራቸውን ጎሎች ወደ 151 ከፍ በማድረግ በክለቡ ታሪክ ውስጥ ሶሥተኛው አነጣጣሪ ሊሆን በቅቷል።                                                                        
ከሰንበቱ ግጥሚያዎች በኋላ ማንቼስተር ዩናይትድ በ 72  ነጥቦች በአንደኝነት የሚመራ ሲሆን ቼልሢይ አንዲት ነጥብ ብቻ ዝቅ ብሎ በ 71 ሁለተኛ ነው። አርሰናል ደግሞ 68  ነጥቦች አሉት። ሣምንት የቼልሢይ ጉዞ ወደ ማንቼስተር ዩናይትድ ኦልድ-ትሬፎርድ ስታዲዮም ሲሆን ግጥሚያው ምናልባት ለሁለቱም ክለቦች ወሣኝነት ሊኖረው የሚችል ነው።

በስፓኝ ላ-ሊጋ ሁለቱም ሃያል ክለቦች በማሸነፋቸው ቢቀር በነጥብ እኩል እንደሆኑ ቀጥለዋል። ሬያል ማድሪድ የከተማ ተፎካካሪውን አትሌቲኮ ማድሪድን 3-2  ሲረታ ባርሤሎናም ማዮርካን 1-0 አሸንፏል። ሁለቱም ክለቦች በየፊናቸው 74 ነጥቦች ሲኖሯቸው ሬያል የሚመራው በጥቂት ጎሎች ብልጫ ብቻ ነው። ሶሥተኛው ቫሌንሢያ በሣራጎሣ 3-0 በመሸነፉ ከሁለቱ ቀደምት ክለቦች የሚለየው ነጥብ እንዲያውም ወደ 21 ከፍ ሊል በቅቷል። ክለቡ ለሚቀጥለው የአውሮፓ ሻምፒዮና ሊጋ ውድድር ተሳትፎ ለሚያበቃ ቦታ ከመታገል የበለጠ ዕድል የለውም።

የሶሥት ክለቦች የበላይነት ፉክክር ሰፍኖ በቆየበት በጀርመን ቡንደስሊጋ የባየርን ሙንሺንና የሌቨርኩዝን በሣምንቱ ግጥሚያዎች መሸነፍ የበጀው ለረጅም ጊዜ ከኋላ ሲከተል ለቆየው ለሻልከ ነው። ባየርን በገዛ ሜዳው በሽቱትጋርት 2-1 ሲሸነፍ ሻልከ አመራሩን ሊይዝ የበቃው ሌቨርኩዝንን በጠንካራ አጨዋወት 2-0 በመርታት ነው። ሁለቱንም ጎሎች በማስቆጠር የጨዋታው’ን ሂደት የወሰነው ደግሞ ድንቁ አጥቂው ኬቪን ኩራኒ ነበር።

“በጣም ደስ የሚል ነገር ነው። አሁን በመጨረሻው እሽቅድድም ላይ ስንሆን በዚሁ ለመግፋትና የሚቀጥሉትን ግጥሚያዎች በስኬት ለመወጣት ነው የምንፈልገው። እኔ የበኩሌን አስተዋጽኦ ለማድረግ ዝግጁ ነኝ። ለቡድኔ ስኬት የተቻለኝን ሁሉ አደርጋለሁ”

በዕውነትም ሻልከ በተለይ በፊታችን ሰንበት የኩራኒን ጎሎች በጣሙን ይፈልጋል። ምክንያቱም የሚያስተናግደው መጪ ተጋጣሚው በሁለት ነጥቦች ዝቅ ብሎ በ 56  የሚከተለው ባየርን ሙንሺን ነው። ሻልከ አመራሩን ከማስከበር ባሻገር ባለፈው ሣምንት አጋማሽ ከጀርመን ፌደሬሺን ዋንጫ ውድድር ለጥቂት ላስወጣው ለባየርን ምላሽ ለመስጠትም መፈለጉም የሚቀር አይመስልም። ባየርን በተጨማሪ ሰዓት ለጥቂት 1-0 ሲያሸንፍ የሻልከ በረኛ ቁጭቱን እንዲህ ነበር የገለጸው።

“በተጨማሪ ሰዓት ሁለተኛው አጋማሽ ላይ ሆነን ጨዋታውን እየተቆጣጠርን ሳለ ጎል በመግባቱ በጣም ነው ያዘንነው። ከኋላ ምንም ድክመት አላሳየንም። ጨዋታው በእድ ግለሰብ ችሎታ ነው የተወሰነው። ይሄ ደግሞ ያሳዝናል”                

ለማንኛውም እንደ እንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ ሁሉ እዚህም በመጪው ሰንበት ከፍጻሜው የቀደመ ፍጻሜ ግጥሚያ የሚካሄድ ነው የሚመስለው። ሶሥተኛው ሌቨርኩዝን 53 ነጥቦች ሲኖሩት ባለፉት ሣምንታት ድክመቱ ከቀጠለ ለአውሮፓ ሻምፒዮና ሊጋ የሚያበቃውን ቦታ እንዳያጣ በጣሙን ያሰጋዋል። ዶርትሙንድና ብሬመን በሚቀጥሉት ሣምንታት የቅርብ ተፎካካሪዎቹ ናቸው።

በተረፈ በኢጣሊያ ሤሪያ-አ ሮማ ኢንተር ሚላንን 2-1 በማሸነፍ ከቀደምቱ ክለብ ጋር ያለውን ልዩነት በአንዲት ነጥብ ሲያጠብ ኤ.ሢ.ሚላን ከላሢዮ በ 1-1 ውጤት በመወሰኑ ወደ ሶሥተኛው ቦታ አቆልቁሏል። ከ 31 ግጥሚያዎች በኋላ ኢንተር 63፤ ሮማ 62፤ ኤ.ሢሚላን 60 ነጥቦች ሲኖሯቸው የሻምፒዮናው ፉክክር የሚቀጥለው በነዚሁ ሶሥት ክለቦች መካከል ነው። በተረፈ በኔዘርላንድ አንደኛ ዲቪዚዮን ትዌንቴ-ኤንሼዴ፤ በፈረንሣይ ቦርዶና በፓርቱጋል ቤንፊካ ሊዝበን በአመራራቸው ቀጥለዋል።

ፎርሙላ-አንድ የአውቶሞቢል እሽቅድድም

Formel 1 Jenson Button Robert Kubica Felipe Massa

ጄሰን ባተን በድል ሰዓት

ትናንት አውስትራሊያ ውስጥ የተካሄደው የዘንድሮው ሁለተኛ የፎርሙላ-አንድ አውቶሞቢል እሽቅድድም አሸናፊ ብሪታኒያዊው ያለፈው ዓመት ሻምፒዮን ጄሰን ባተን ሆኗል። ዕለቱ በተለይ ለጀርመናውያኑ ዘዋሪዎች ለዜባስቲያን ፌትልና ለሚሻኤል ሹማኸር የቀና አልነበረም። ፌትል በፍሬን ብልሽት የተነሣ አመራሩን ለቆ ከውድድሩ ሲወጣ ሁኔታው በሚቀጥለው ሣምንት ማሌይዚያ ላይ ለሚካሄደው ውድድር ተሥፋን የሚያዳብር አልነበረም። ሆኖም ወጣቱ አብራሪ ራሱን ማጽናናቱን ነው የመረጠው።

“በእንደዚህ ዓይነት ወቅት ወደ ቤቴ ብመለስ ነበር የምመርጠው። ነገር ግን ሕይወት ይቀጥላል። በበኩሌ ከነበረው አስቸጋሪ ሁኔታ አንጻር፤ ማለት እስከ ብልሽቱ ወቅት ድረስ ሁሉንም ነገር ትክክል ነው ያደረግኩት”

ለሰባት ጊዜው የዓለም ሻምፒዮን ለሚሻኤል ሹማሸር ደግሞ ውድድሩ ከባተንና ከአሎንሶ ጋር በደረሰ ግጭት ገና በጥቂት ሤኮንዶች ነበር የተሰናከለው። እናም በመጨረሻ በአሥረኝነት መወሰኑ ግድ ሆኖበታል። ምንም ሊለውጠው የሚችለው ነገር አልነበረም።

ቢስክሌት/የበረዶ ስፖርት

በሌላ የስፖርት መድረክ ዴንማርክ ውስጥ ትናንት በተካሄደ የዓለም የቢስክሌት ውድድር በወንዶች እንግሊዛዊው የኦሎምፒኩ ሻምፒዮን ኤድ ክላንሢይ ሲያሸንፍ አውስትራሊያዊው ሌይህ ሃዋርድ ሁለተኛ፤ እንዲሁም አሜሪካዊው ቴይለር ፊኒይ ሶሥተኛ ሆኗል። የኦሎምፒኳ ሻምፒዮን ቪክቶሪያ ፔንደልተን ባለፈው ቅዳሜ በስፕሪንት ለአራተኛ ተከታታይ ድሏ ስትበቃ ትናንት ደግሞ በካይሪን የብር ሜዳሊያ ተሸላሚ ሆናለች። ሁለተኛና ሶሥተኛ የወጡት የሊቱዋኒያና የአውስትራሊያ ተወዳዳሪዎች ናቸው። በቡድን ስፕሪንት ጀርመን በወንዶች እንዲሁም አውስትራሊያ በሴቶች አሸናፊ ሆነዋል።

ኢጣሊያ-ቶሪኖ ላይ በተካሄደው የበረዶ ዳንስ ውድደር “ፊገር-ስኬቲንግ” ጃፓናዊቱ  ማኦ አሣዳ የደቡብ ኮሪያ ተፎካካሪዋን ኪም ዩናን በማሸነፍ ባለፈው ቅዳሜ የዓለም ሻምፒዮንነቷን አረጋግታለች። አሣዳ በነጻው ትርዒት ደግሞ ኪምን ተከትላ ሁለተኛ ስትወጣ የፊንላንዷ ላውራ ሌፒስቶ ሶሥተኛ ሆናለች። በአጠቃላይ አውሮፓውያን በአራቱም የውድድር ዓይነቶች አንድ ወርቅ እንኳ ሳያገኙ ቀርተዋል። ቀደም ሲል በሣምንቱ በጥንድ ዲሲፕሊን ቻይናውያኑ ፓንግ ኪንግና ቶንግ ጂያን ለወርቅ ሲበቁ በበረዶ ዳንስ ትርዒት ደግሞ የካናዳ የኦሎምፒክ ሻምፒዮኖች ቴሣ ቨርቺዩና ስኮት ሞይር አሸናፊ ሆነው ነበር።

ዘገባችንን በእግር ኳስ ለማጠቃለል ሣምንቱ በአውሮፓ ሻምፒዮና ሊጋ ማራኪ የሩብ ፍጻሜ ግጥሚያዎች የሚካሄዱበት ነው። ነገ የጀርመኑ ባየርን ሙንሺን ማንቼስተር ዩናይትድን የመሰለ ሃያል ቡድን የሚያስተናግድ ሲሆን ሁለቱ ቀደምት የፈረንሣይ ክለቦች ኦላምፒክ ሊዮንና ዢሮንዲን ቦርዶው ዕጣ ሆኖ እርስበርሳቸው ነው የሚገናኙት። በማግሥቱ ረቡዕ ምሽትም አርሰናል ካለፈው ሻምፒዮን ከባርሤሎና፤ እንዲሁም ኢንተር ሚላን ከ ሢ.ስ.ኬ.ኤ ሞስኮ ይጋጠማሉ። በተረፈ የአንዴው የእንግሊዝ ብሄራዊ ቡድን አሠልጣኝ ስዊድናዊው ስቬን-ጎራን-ኤሪክሰን ትናንት የአይቮሪ ኮስት አሠልጣኝ ሆነው ተሰይመዋል። ታዋቂው አሠልጣን ቡድኑን ለዓለም ዋንጫው ፍጻሜ ውድድር በሚገባ ማዘጋጀቱ እንደሚሳካላቸው ተሥፋ እናደርጋለን።                                
/DW/RTR/AFPMM/HM