የስፖርት ዘገባ | ስፖርት | DW | 15.03.2010
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ስፖርት

የስፖርት ዘገባ

በፎርሙላ-አንድ የአውቶሞቢል እሽቅድድም የሰባት ጊዜው የዓለም ሻምፒዮን የሚሻኤል ሹማኸር ወደ ውድድሩ መድረክ መመለስ ሰፊ ትኩረትን ነው የሳበው።

default

ባሕሬይን፤ የፎርሙላ-አንድ እሽቅድድም

የዘንድሮው የፎርሙላ-አንድ አውቶሞቢል እሽቅድድም የውድድር ወቅት ትናንት ባሕሬይን ላይ ለየት ያለ ትኩረት ተሰጥቶት ተጀምሯል። ዓመቱን የተለየ የሚያደርገው አዳዲስ ቡድኖችና ዘዋሪዎች ቀየርየር ብለው የቀረቡበት መሆኑ ብቻ አይደለም። በተለይ ማራኪ የሚያደርገው በውድድሩ ታሪክ ውስጥ በስኬቱ አቻ የማይገኝለት ጀርመናዊው የሰባት ጊዜ የዓለም ሻምፒዮን ሚሻኤል ሹማኸር ወደ ሞተሩ ስፖርት መድረክ መመለሱ ነው።

“ሁሉም ነገር ጥሩ ነው። ለእሽቅድድሙ በፊት ከወዲሁ ያለኝ ጉጉትም ትልቅ ነው” ሹማኸር በውድድሩ ዋዜማ!

ባብሕሬይኑ የመጀመሪያ እሽቅድድም ደጋፊዎቹ ሹሚ እያሉ በማቆላመጥ የሚጠሩት ሚሻኤል ሹማኸር ምንም እንኳ ቀድሞ እንደለመደውና አፍቃሪዎቹ እንደተመኙት ወዲያው ለድል ባይበቃም ውድድሩን ካለፈው ዓመት ሻምፒዮን ከብሪታኒያዊው ከጄሰን ባተን ቀድሞ በሥድሥተኝነት መፈጸሙ ትልቅ ነገር ነው። አንዴ የፍርሙላ-አንድ ንጉሥ የሚል ስያሜ ተሰጥቶት የነበረው ሹማሸር መወዳደሩን ካቆመ ከሶሥት ዓመታት በኋላ ተመልሶ ግሩም አጀማመር ማድረጉ በዕውነትም ሊደነቅ ይገባዋል።

Formel 1 Nico Rosberg Mercedes Dossier 1

በትናንቱ እሽቅድድም የስፓኙ ፌርናንዶ አሎንሶና የብራዚሉ ፌሊፔ ማሣ በአስደናቂ ሁኔታ የፌራሪን ድርብ ድል ሲያረጋግጡ እንግሊዛዊው ሉዊስ ሃሚልተን ሶሥተኛ፤ እንዲሁም በጢስ ማውጫ ብልሽት የታወከው ወጣቱ ጀርመናዊ ዜባስቲያን ፌትል አራተኛ ሆነዋል። አምሥተኛ ኒኮ ሮዝበርግ፣ ስድሥተኛ ሹማኸር፣ ሰባተኛ ጄሰን ባተን!
ዘንድሮ ለሜርሴደስ የሚወዳደረው የቀድሞው የፌራሪ ዘዋሪ ሚሻኤል ሹማኸር በበኩሉ የትናንቱን ውጤት ጅማሮ ብጫ አድርጎ ነው የሚመለከተው። ባለፈው ሣምንት ልምምዱ ምንም እንኳ የፈለገውን ያህል ባይፈጥንም በውድድሩ ሂደት ከጊዜ ወደ ጊዜ በመሻሻል ለሻምፒዮንነቱ ብርቱ ተፎካካሪ እንደሚሆን ጨርሶ እንደማይጠራጠር ነበር የገለጸው።

“ዛሬ እንደፈለግነው ወይም መሆን እንዳለብን ፈጣን አልነበርንም። ይሁን እንጂ በዚህ ዓመትም የሻምፒዮናው ተፎካካሪ የማንሆንበት ምንም ምክንያት አይኖርም”

ሹማኸር እንዲያውም የሜርሴደስ ተሽከርካሪው ቴክኒካዊ ብቃትና የርሱ ልምድ ተደምሮ ግቡ የዓለም ሻምፒዮንነት ብቻ እንደሆነ ዕምነቱ የጸና ነው። በዘንድሮው ፕሮግራም የደቡብ ኮሪያ የዮንጋምና የሞንትሬያል ግራን-ፕሪዎች ተጨምረው በጠቅላላው 19 እሽቅድድሞች የሚካሄዱ ሲሆን ፉክክሩ ይበልጥ ማራኪ እንደሚሆን አንድና ሁለት የለውም።

ዶሃ፤ የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና

ካታር ርዕሰ-ከተማ ዶሃ ላይ ሰንበቱን በተካሄደው የአዳራሽ ውስጥ የዓለም አትሌቲክስ ውድድር ኢትዮጵያ በሶሥት የወርቅና ሁለት የነሃስ ሜዳሊያዎች ከአሜሪካ ቀጥላ ሁለተኛ ለመሆን በቅታለች። በ 1,500 ሜትር ሩጫ ደረሰ መኮንን የሞሮኮና የኬንያ ተፎካካሪዎቹን አብዳላቲ ልጊደርንና ሃሮን ካይታኒን በመቅደም ሲያሸንፍ ገ/መድህን መኮንን ደግሞ አራተኛ ወጥቷል። በተመሳሳይ ርቀት በሴቶችም ኢትዮጵያዊቱ ቃልኪዳን ገዛኸኝ ስታሸንፍ ገለቴ ቡርቃ ደግሞ ሩጫውን በሶሥተኝነት ፈጽማለች። ከዚሁ ሌላ በሶሥት ሺህ ሜትር ሩጫ መሠረት ደፋር ኬንያዊቱን ቪቪያን ቼሩዮትን በማስከተል ቀዳሚ ስትሆን ስንታየሁ እጅጉ ሶሥተኛ ወጥታለች።

በዶሃው ውድድር ላይ በተለይ ጎልተው የታዩት የኩባው ከአዳራሽ ውጭ የመሰናክል ሩጫ የዓለም ክብረ-ወሰን ባለቤት ዴይሮን ሮብልስና ፈረንሣዊው ቴዲይ ታማንጎ ነበሩ። ሮብልስ በ 60 ሜትር መሰናክል በማሸነፍ ውጤቱን በዓለም ላይ ሶሥተኛው ከሆነው ፈጣን ጊዜ ሲያስተካክል ታማንጎ ደግሞ በሶሥቴ መወንጨፍ የርዝመት ዝላይ 17 ሜትር ከ 90 በመዝለል አዲስ የዓለም ክብረ-ወሰን ለማስመዝገብ በቅቷል።
ዝላይን ካነሣን አዲስ ክብረ-ወሰን ለማስመዝገብ ተሥፋ አድርጋ በውድድሩ የተሳተፈችው ሩሢያዊቱ የምርኩዝ ዝላይ ኮከብ የለና ኢዚምባየቫ በማይረባ ስህተት እንዳለፈው የዓለም ሻምፒዮና ሁሉ ለድል ሳትበቃ ቀርታለች። አራተኛ ነው የሆነችው። ሌላው ድንቅ ውጤት የአሜሪካው አትሌት በርናርድ ላጋት በሶሥት ሺህ ሜትር ሩጫ በማሸነፍ ያስመዘገበው ነበር። የቀድሞው ሻምፒዮን ታሪኩ በቀለ በዚሁ ሩጫ በአራተኝነት መወሰኑ ግድ ሲሆንበት ደጀን ገ/መስቀል ደግሞ አሥረኛ ሆኗል።
የዶሃው የሶሥት ቀናት ውድድር በአጠቃላይ ለቀደምቷ ለአሜሪካ ከ 17 ዓመታት ወዲህ አቻ ባልታየለት ስኬት ነው ያለፈው። በተቀረ በወንዶች 800 ሜትር የሱዳኑ አትሌት አቡባከር ካኪ ሲያሸንፍ ክሮኤሺያዊቱ የዓለም ሻምፒዮን ብላንካ ቭላዚች በከፍታ ዝላይ ለድል በቅታለች። በአጠቃላይ ውጤት አሜሪካ በስምንት ወርቅ ሜዳሊያ አንደኛ ስትሆን ኢትዮጵያ በሶሥት ወርቅ ሁለተኛ፤ ሩሢያ በሁለት ወርቅ ሶሥተኛ ወጥታለች። ለወትሮው የኢትዮጵያ ብሩቱ ተፎካካሪ የሆነችው ኬንያ በሁለት ብርና በሁለት ነሃስ በመወሰን ውድድሩን በ 16ኝነት ነው የፈጸመችው።


እግር ኳስ፤ የአውሮፓ ቀደምት ሊጋዎች

Bundesliga Spielszene vom Spiel Bayern - Freiburg 2:1 Flash-Galerie

ቡንደስሊጋ፤ አርየን ሩበን

በአውሮፓ ቀደምት ሊጋዎች የእግር ኳስ ሻምፒዮና በኢጣሊያ ሤሪያ-አ እንጀምርና ኢንተር ሚላን በዚህ ሰንበት በካታኛ 3-1 በመሸነፉ አመራሩ ከአራት ወደ አንዲት ነጥብ ዝቅ ሊል በቅቷል። ሁለተኛው ኤ.ሢ.ሚላን በአንጻሩ ቺየቮን 1-0 ሲረታና ኢንተርን ይበልጥ ሲቃረብ ከሣምንቱ የአውሮፓ ሻምፒዮና ሊጋ ሽንፈት ያጽናናችውን ብቸኛ ጎል በመጨረሻይቱ ደቂቃ ላይ ያስቆጠረው ሆላንዳዊው ክላረንስ ዜዶርፍ ነበር። በሌላ በኩል የቡድኑ ተጫዋች ዴቪድ ቤክሃም በደረሰበት የአካል ጉዳት በፊታችን ሰኔ ደቡብ አፍሪቃ ውስጥ በሚከፈተው የዓለም ዋንጫ ውድድር ለእንግሊዝ መሰለፍ መቻሉ አጠያያቂ ሆኗል። ለማንኛውም ኢንተር 59፣ ኤ.ሢሚላን 58 ነጥቦች ሲኖሩት ሮማ በ 53 ሶሥተኛ ነው።

በስፓኝ ላ-ሊጋ ለሻምፒዮንነቱ የብቻ ፉክክር የያዙት ሁለቱም ቀደምት ክለቦች ባርሤሎናና ሬያል ማድሪድ የሣምንቱን ግጥሚያቸውን በድል ሲወጡ ሁለቱም እኩል ነጥቦች አሏቸው፤ ሬያል የሚመራው በጎል ብልጫ ብቻ ነው። ባርሣ አርጄንቲናዊው ኮከብ ሊዮኔል ሜሢ ባስቆጠራቸው ሶሥት ጎሎች ቫሌንሢያን 3-0 ሲያሸንፍ ሬያልም ቫላዶሊድን 4-1 ረትቷል። በነገራችን ላይ ለሬያል ማድሪድም ሶሥቱን ጎሎች ያስቆጠረው እንዳጋጣሚ ሆኖ አርጄንቲናዊ አጥቂው ጎንዛሉ ሂጉዌይን ነበር። የፕሪሜራ ዲቪዚዮኑ ሣምንት የአርጄንቲናውያን ሣምንት ነበር ለማለት ይቻላል። በጥቅሉ ቫሌንሢያ ከሁለቱ ቀደምት ክለቦች 18 ነጥቦች ዝቅ ብሎ ሶሥተኛ ነው፤ ከአእንግዲህ ሻምፒዮንነቱን ማሰብ ቀርቶ ሊያልም እንኳ አይችልም።

በዚህ በጀርመን ቡንደስሊጋ ሻምፒዮናው የሶሥት ክለቦች ጥብቅ ፉክክር የሚደረግበት እየሆነ ሄዷል። ባየርን ሙንሺን በሜዳው በፍራይቡርግ 1-0 ከተመራ በኋላ 2-1 ሲያሸንፍ አመራሩን በ 56 ነጥብ አጠናክሮ ሊቀጥል ችሏል። ባየርን በሳባት ደቂቃዎች ውስጥ ሁለቱን ጎሎች ያስቆጠረውን የሆላንድ ብሄራዊ ቡድን ድንቅ ተጫዋች አርየን ሮበንን ለድሉ በጣሙን ሊያመሰግን ይገባዋል። እንደ አሠልጣኙ እንደ ሉዊስ-ፋን-ሃል ከሆነ ጨዋታው በሌላ ውጤት ሊያበቃ በቻለም ነበር።

“በሁለተኛው አጋማሽ ከመጀመሪያዋ ደቂቃ አንስተን ጨዋታውን ለመቆጣጠር ችለናል። እናም ለማሸነፍ መብቃታችን በጣም ግሩም ነገር ነው። ግን ጨዋታው 1-1 ወይም በሽንፈት 0-1 ሊያበቃ በቻለም ነበር”
ሻልከም ሽቱትጋርትን በግሩም ጨዋታ በተመሳሳይ ውጤት 2-1 ሲያሸንፍ ከባየርን ሁለት ነጥቦች ወረድ ብሎ ሁለተኛ ነው። የዘንድሮው ድንቅ ክለብ ሌቨርኩዝን ደግሞ ካለፈው ሣምንት ሽንፈቱ በማገገም ሃምቡርግን 4-2 ሲሸኝ በ 53 ነጥቦች የሻምፒዮና ዕድሉን ለመጠበቅ ችሏል።

በተቀረ ሃምቡርግ፣ ዶርትሚንድና ብሬመን ለመጪው የአውሮፓ ሊጋ ውድድር ተሳትፎ ለሚያበቁት ሁለት ቦታዎች የሚፎካከሩ ሲሆን ዘንድሮ ከመጨረሻው ቦታ መላቀቅ ያቃተው የአንዴ ጠንካራ ቡድን የሄርታ በርሊን ዕጣ እየከፋ መሄዱን ቀጥሏል። ቡድኑ በሰንበት ግጥሚያውም በገዛ ሜዳው በኑርንበርግ 2-1 ሲረታ በአንደኛው ቡንደስሊጋ ውስጥ መቆየቱ ገና ከወዲሁ ሲበዛ የሚያጠያይቅ ነው። የሚያሳዝነው አሠልጣኙ ፍሪድሄልም ፉንክል እንዳለው ለነገሩ የቡድኑ አጨዋወት የከፋ አልነበረም።

“ቡድኑ በመጀመሪያዎቹ 45 ደቂቃዎች ያሳየው ጨዋታ በጣም ግሩም ነበር። ግን ታዲያ የተገኙትን ያለቀላቸው ዕድሎች መጠቀም አለመቻሉ ያሳዝናል። እናም ሽንፈቱ ለኛ በተለይም ይህን በመሰለ ስታዲዮም በጣሙን መሪር ነው። አሁን በመጀመሪያ ከዚህ ተጽዕኖ መላቀቅ ይኖርብናል”

ከዚህ የከፋው ደግሞ ባለፈው ቅዳሜ የቡድኑ ግጥሚያ እንዳበቃ በበርሊኑ ስታዲዮም የታየው የዓመጽ ሁኔታ ነበር። ከሄርታ ደጋፊዎች መካከል ከመቶ እስከ መቶ ሃምሣ የሚጠጉ ቁጡ ተመልካቾች ዘለው ሜዳ በመግባት ያሳዩት የዓመጽ ባህርይ ለአጭር ጊዜም ቢሆን አስፈሪ መሆኑ አልቀረም። ግን ተጫዋችም ሆነ ተመልካች አንድም ሰው ሳይጎዳ ሁኔታው በቁጥጥር ውስጥ ሊውል በቅቷል።

ካናዳ-ቫንኩቨር ላይ በሚካሄደው በአሥረኛው የአካል ጉዳተኞች የክረምት ኦሎምፒክ ጨዋታ በፓራሊምፒክስ ለማጠቃለል እስከ ትናንት በተካሄዱት የሁለት ቀናት ውድድሮች የ 14 ሃገራት አትሌቶች ለሚዳሊያ በቅተዋል። በአጠቃላይ ውጤት ሩሢያ በአራት ወርቅ በአራት ብርና በሁለት ነሃስ ሜዳሊያዎች የምትመራ ሲሆን ኡክራኒያ በሁለት ወርቅ አንድ ብርና ሶሥት ነሃስ፤ አውስትሪያ በሁለት ወርቅና በአንድ ነሃስ፤ እንዲሁም ጀርመን በሁለት ወርቅ ለጊዜው ቀደምቶቹ ናቸው።

መስፍን መኮንን

ሸዋዬ ለገሠ