የስፖርት ዘገባ | ስፖርት | DW | 25.01.2010
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ስፖርት

የስፖርት ዘገባ

የአፍሪቃ እግር ኳስ ዋንጫ ውድድር አስተናጋጇ አገር አንጎላ ከወዲሁ ስንብት ባደረገችበት ሁኔታ ወደ ግማሽ ፍጻሜው በመሸጋገር ላይ ነው። በአትሌቲክሱ መድረክ ላይ ደግሞ ሃይሌ ገ/ስላሤ ምንም እንኳ ክብረ-ወሰኑን ለማሻሻል ባይችልም የዱባይን ማራቶን ለሶሥተኛ ጊዜ ማሸነፉ በሣምንቱ ዓለምአቀፍ ትኩረት ተሰጥቶት ነው የሰነበተው።

ጋናና አንጎላ በሩብ ፍጻሜው ግጥሚያ

ጋናና አንጎላ በሩብ ፍጻሜው ግጥሚያ

የአፍሪቃ እግር ኳስ ዋንጫ ውድድር

27ኛው የአፍሪቃ እግር ኳስ ዋንጫ ውድድር ወደ ግማሽ ፍጻሜው በመሸጋገር ላይ ሲሆን ሂደቱ የዋንጫ ባለቤት የመሆን ከፍተኛ ዕድል ለተሰጣቸው ለአስተናጋጇ ለአንጎላና ለአይቮሪ ኮስት የሃዘንና የስንብት ሆኗል። አንጎላ ዋና ከተማይቱ ሉዋንዳ ውስጥ በ 50 ሺህ ተመልካቾቿ ፊት ትናንት በተካሄደው የሩብ ፍጻሜ ግጥሚያ በጋና 1-0 ስትሽነፍ በ 16ኛዋ ደቂቃ ላይ ብቸኛዋን ጎል ለጋና ያስቆጠረው አሣሞአህ ጊያን ነበር። ጋና ጨዋታውን በሰፊው በመቆጣጠር ልዕልናዋን በሚገባ አሳይታለች። እና ድሏም ተገቢ ነበር ለማለት ይቻላል። በሌላ በኩል ካቢንዳ ውስጥ አልጄሪያ ደግሞ ትንፋሽ በሚቆርጥ ጨዋታ ለዚያውም ሁለቴ ከተመራች በኋላ በመመለስ አይቮሪ ኮስትን በተጨማሪ ሰዓት 3-2 በመርታት የዲዲየር ድሮግባና የመሰሎቹ የድል ተሥፋ ከወዲሁ ከንቱ እንዲሆን አድርጋለች።
አንጎላ በጋና ተረትታ ከውድድሩ ማሰናበቷ ብዙም ባያስደንቅም የአይቮሪ ኮስት ሽንፈት ግን ጨርሶ የተጠበቀ አልነበረም። አልጄሪያ በዓለም ዋንጫ ማጣሪያ ግብጽን አሰናብታ የደቡብ አፍሪቃ ቲኬቷን ከቆረጠች ወዲህ ትናንት ደግሞ በዓለምአቀፍ ከዋክብት የተመላውን የአይቮሪ ኮስትን ብሄራዊ ቡድን አሸንፋ ማለፏ ታላቅ የሚያሰኛት ነው። ቡድኑ በመክፈቻው የምድብ ግጥሚያ በማላዊ 3-0 ተሸንፎ ከሜዳ ሲወጣ ከወዲሁ አልቆለታል ያሉት ጥቂቶች አልነበሩም። ትናንትም በካቢንዳው ቺያዚ ስታዲዮም ሩብ ፍጻሜ ግጥሚያ ሳሎሞን ካሉ ገና በአራተኛዋ ደቂቃ ላይ ለአይቮሪ ኮስት የመጀመሪያዋን ጎል ሲያስቆጥር ቀኑ ለአልጄሪያ የስንብት ነበር የመሰለው። ግን አልሆነም!

የተቀሩት ሩብ ፍጻሜ ጨዋታዎች በዛሬው ዕለት የሚካሄዱ ሲሆን ተጋጣሚዎቹም ናይጄሪያ ከዛምቢያና ካሜሩን ከግብጽ ናቸው። በግማሽ ፍጻሜው ጋና ከናይጄሪያና ከዛምቢያ አሸናፊ ጋር ትገናኛለች፤ አልጄሪያን የሚጠብቃት ደግሞ ከካሜሩንና ከግብጽ አንዱ ነው። አራቱም ቡድኖች እጅግ ጠንካሮች ስለሚሆኑ ለፍጻሜ ማን ይበቃል፤ መተንበዩ በጣሙን ያዳግታል። ግማሽ ፍጻሜው ራሱ የፍጻሜን ያህል ነው የሚሆነው። በእስካሁኑ ውድድር በጎል አግቢነት የአንጎላው ፍላቪዮና የማሊው ሰይዱ ኬይታ እያንዳንዳቸው ሶሥት አስቆጥረው ይመራሉ።

የአውሮፓ ቀደምት ሊጋዎች

በአውሮፓ ሰንበቱ የቀደምቱ እግር ኳስ ሊጋዎች መደበኛ ሻምፒዮናና በከፊልም የፌደሬሺን ዋንጫ ጥሎ-ማለፍ ግጥሚያዎች የተካሄዱበት ነበር። በስፓኝ ፕሪሜራ ዲቪዚዮን ላ-ሊጋ ቀደምቱ ቡድኖች የየበኩላቸውን ግጥሚያ በማሸነፋቸው ባርሤሎና ሬያል ማድሪድን በአምሥት ነጥቦች ልዩነት በማስከተል መምራቱን እንደቀጠለ ነው። ባርሣ ሬያል-ቫላዶሊድን 3-0 ሲያሸንፍ ሬያል ማድሪድም ማላጋን 2-0 በሆነ ውጤት ሸኝቷል። ለሬያል ሁለቱንም ጎሎች ያስቆጠረው ክሪስቲያኖ ሮናልዶ ነበር። ሶሥተኛው ቫሌንሢያ ከቴነሪፋ ባደ-ባዶ ብቻ በመለያየቱ ከአመራሩ ጋር የነበረውን ቅርበት ማጣቱ ግድ ነው የሆነበት። በኢጣሊያ ሤሪያ-አ ሰንበቱ የሻምፒዮኑ የኢንተርና የኤ.ሢ.ሚላን ፉክክር የተለየ ትኩረት ያገኘበት ነበር። በዚሁ ግጥሚያ ኢንተር ሚላን 2-0 ሲያሸንፍ ምንም እንኳ ለጊዜው የአንድ ጨዋታ ብልጫ ቢኖረውም አመራሩን በዘጠን ነጥብ ልዩነት ሊያሰፋ በቅቷል። ኤ-ሢ.ሚላን በሁለተኝነቱ ቢቀጥልም ሶሥተኛው ሮማ በሁለት ነጥቦች ልዩነት ብቻ እየተቃረበው ነው። በሮማ ለዚያውም በገዛ ሜዳው 2-1 የተረታው ጁቬንቱስ በአንጻሩ በአቆልቋይ ሂደቱ ቀጥሏል። በውድድሩ መጀመሪያ ሃያል የነበረው የቱሪን ክለብ አሁን ስድሥተኛ ነው።

በጀርመን ቡንደስሊጋ ዘንድሮ በድንቅ አጨዋወቱ ተወዳጅነትን ያተረፈው ባየር-ሌቨርኩዝን በዚህ ሰንበትም የሚገታ አልነበረም። ቡድኑ በሰከነ አጨዋወት ሆፈንሃይምን 3-0 በማሽነፍ አመራሩን ወደ ሶሥት ነጥቦች ከፍ ሊያደርግ በቅቷል። ሆኖም አሠልጣኙ ዩፕ ሃይንከስ እንዳለው ቡድኑ የተለመደ ጥንካሬውን ያሳየውና ጨዋታውን የተቆጣጠረው ከዕረፍት በኋላ ነበር።
“በመጀመሪያው አጋማሽ ጨዋታውን አልተቆጣጠርንም። የበላይነትም አልነበረንም። ጠንክረን የተጫወትነው ከዕረፍት በኋላ ነው። በተለይ ሁለት ጎሎች ካስቆጠርን በኋላ ፍጹም የበላይነት ስናሣይ በሁለተኛው ግማሽ የተሻልነው እንደነበርን እርግጠኛ ነኝ”

በአንጻሩ ከሌቨርኩዝን የቅርብ ተፎካካሪዎች አንዱ ሻልከ ቦሁምን 2-1 እየመራ ቆይቶ በመጨረሻይቱ ደቂቃ እኩል-ለእኩል 2-2 በመለያየቱ ወደ ሶሥተኛው ቦታ ማቆልቆሉ ግድ ሆኖበታል። ሰንበቱ ይበልጡን የበጀው ብሬመንን በድንቅ ጨዋታ 3-2 ለረታው ለባየርን ሙንሺን ነበር። ሁለተኛ ሊሆን በቅቷል። ብሬመን በአንጻሩ ከተከታታይ አራት ሽንፈቶች በኋላ ከሻምፒዮንነት ሕልሙ ስንብት ነው ያደረገው።

በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ ማንቼስተር ዩናይትድ የቼልሢይንና የአርሰናልን በፌደሬሺን ዋንጫ ግጥሚዮች መተጓጎል በመጠቀም በ 50 ነጥቦች አመራሩን ለመጨበጥ ችሏል። ማኒዩ ሃል-ሢቲይን 4-0 ሲረታ እርግጥ ከአርሰናል የአንድ፤ ከቼልሢይም የሁለት ጨዋታዎች ብልጫ አለው። በመሆኑም ቢቀር የቼልሢይ ወደ አመራሩ መመለስ የሣምንት ጉዳይ ነው። የእንግሊዝን ፌደሬሺን ዋንጫ ጥሎ-ማለፍ አራተኛ ዙር ውድድር ካነሣን አይቀር ቼልሢይ የሁለተኛ ዲቪዚዮን ተጋጣሚውን ፕሬስተን ኖርዝ ኤንድን 2-0 ሲረታ አርሰናል በአንጻሩ በስቶክ ሢቲይ 3-1 ተሸንፎ ወጥቷል። ከአርሰናል በፊት ቀደምቱ የፕሬሚየር ሊግ ክለቦች ማንቼስተር ዩናይትድና ሊቩርፑል ከውድድሩ መሰናበታቸው ይታወሣል። ትናንት በወጣው ዕጣ መሠረት በተከታዩ አምሥተኛ ዙር ከሚጋጠሙት መካከል ማንቼስተር ሢቲይ ከስቶክ ሢቲይ፤ ደርቢይ ካውንቲይ ከበርሚንግሃም ሢቲይ፤ ቦልተን ወንደረርስ ከቶተንሃምና ከሊድስ አሸናፊ፤ ቼልሢይ ከካርዲፍ ሢቲይ ይገኙበታል።

በተረፈ የዓለም እግር ኳስ ፌደሬሺኖች ማሕበር ፊፋ አሻሚ የዳኝነት ሁኔታዎችን ለማጣራት እንዲቀል በጎል መስመሮች አኳያ የቪዲዮ ካሜራዎችን አጠቃቀም ሊያስተዋውቅ እንደሚችል ትናንት ከድርጅቱ መቀመጫ ከዙሪክ ተገልጿል። የፊፋ ፕሬዚደንት ሤፕ ብላተር እንዳሉት እርግጥ ይህ የሚሆነው የአሠራሩ ቴክኒክ ፍቱንና አስተማማኝ ሆኖ ከተገኘ ብቻ ነው። ይሁንና ውሣኔው ለደቡብ አፍሪቃ የዓለም ዋንጫ ውድድር ይደርሳል ተብሎ አይጠበቅም። ብላተር ዳኞችን ለማገዝ የቪዲዮ ካሜራ ሥራ ላይ መዋሉን እስካሁን አጥብቀው ሲቃወሙ መቆየታቸው ይታወቃል። ለማንኛውም የዓለምአቀፉ የእግር ኳስ ማሕበር ቦርድ በፊታችን መጋቢት ወር በጉዳዩ ይመክርበታል። የዚህ ቴክኒክ አስፈላጊነት በተለይ በአውሮፓ የዓለም ዋንጫ ማጣሪያ ፈረንሣይ ቲየሪ ኦንሪ በዕጅ ባስቆጠራት ጎል አየርላንድን ያላግባብ አልፋ ለፍጻሜ ከደረሰች በኋላ እንደገና በሰፊው ማነጋገሩ የሚታወስ ነው።

ሃይሌ ገብረሥላሴ በዱባይ ማራቶን

BdT Berlin Marathon

ሃይሌ ገ/ሥላሴ በሣምንቱ ማብቂያ ላይ በዱባይ ማራቶን ለተከታታይ ሶሥተኛ ጊዜ ለድል ሲበቃ የራሱን የዓለም ክብረ-ወሰን ለማሻሻል ያደረገው ጥረት ግን እንደገና ሳይሳካላት ቀርቷል። ሃይሌ የኬንያና የኢትዮጵያ አትሌቶች ቀደምት ሆነው የታዩበትን ሩጫ የፈጸመው በሁለት ሰዓት ከስድሥት ደቂቃ ከ 33 ሤኮንድ ጊዜ ነበር። ይህም ከዓለም ክብረ-ወሰኑ ከሁለት ደቂቃዎች በላይ የዘገየ መሆኑ ነው። አትሌቱ የወገብ ችግር ገጥሞት እንደነበርም ተጠቅሷል። ለነገሩ ሃይሌ በሩጫው ዋዜማ ለዶቼ ቬለ የገለጸው ክብረ-ወሰኑን ማሻሻሉ ቀላል ነገር እንዳልሆነ ነበር። በዚህ ዓመትም የተለየ ውጥን የለውም።

“ብዙም የተለየ ዕቅድ የለኝም። በዓመቱ የማደርገውን ሩጫ ለመቀነስ ነው የማስበው። እና እዚህም ሆነ በሌላ ቦታ ክብረ-ወሰን ከሰበርኩ የሚያስደንቀኝ ነው የሚሆነው። ለማንኛውም እናያለን። ክብረ-ወሰንን መስበር ቀላል ነገር አይደለም። እንዲሳካ ሁሉም ነገር የተሟላ መሆን ይኖርበታል”

በዱባዩ ማራቶን ኬንያዊው ቻላ ሁለተኛ ሲሆን እሸቱ ወንድሙ ሶሥተኛ፤ አብዮቴ ጉታ አራተኛ፤ እንዲሁም ደጀኔ ይርዳው ሰባተኛ ወጥተዋል። በሴቶች የኢትዮጵያ ድል ድርብ ነበር። ማሜቱ ዳስቃና አበሩ ሸዋዬ ርቀቱን በቀደምትነት ሲያቋርጡ ኬንያዊቱ ሄለን ኪሮፕ ሶሥተኛ፤ እንዲሁም ብዙነሽ በቀለ አራተኛ ወጥታለች።

ከዚሁ ሌላ ኬንያ ውስጥ ባለፈው ቅዳሜ በተካሄደ የጦር ሃይሎች አገር አቋራጭ ሩጫ ውድድር በወንዶች ማርክ ኪፕቶ፤ በሴቶች ደግሞ ኢነስ ቼኖንጌስ አሸናፊ ሆነዋል።

ዘገባችንን በቴኒስ ለማጠቃለል ሜልበርን ላይ በመካሄድ ላይ ባለው አውስትሬሊያን-ኦፕን ዛሬ የስዊሱ ሮጀር ፌደረር ወደ ሩብ ፍጻሜ ዙር በማለፍ ከሤሬናና ቬኑስ ዊሊያምስ፤ እንዲሁም ለመጀመሪያ ጊዜ ከመጨረሻዎቹ ስምንት መካከል ለመሆን ከበቁት ሁለት የቻይና ተወዳዳሪዎች ጋር ተቀላቅሏል። በዓለም የማዕረግ ተዋረድ ላይ ቀደምቱ የሆነው ፌደረር ወደ ተከታዩ ዙር ያለፈው ለዚያውም የአውስትራሊያውን ሌይተን ሄዊትን በለየለት ሁኔታ 6-2, 6-3, 6-4 በማሸነፍ ነው። ቀደም ሲል በውድድሩ ወደፊት ከተራመዱት ጠንካራ ተጫዋቾች መካከል ኒኮላይ ዳቪዴንኮ፣ ኖቫክ ጆኮቪች፣ ራፋኤል ናዳል፣ ኤንዲይ መሪይና ኤንዲይ ሮዲክም ይገኙበታል።

መሥፍን መኮንን

ተክሌ የኋላ