የስፖርት ዘገባ | ስፖርት | DW | 18.01.2010
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ስፖርት

የስፖርት ዘገባ

አንጎላ ውስጥ የሚካሄደው የአፍሪቃ እግር ኳስ ዋንጫ ውድድር የምድብ ማጣሪያ የመጀመሪያ ዙር ለአንዳንድ ሃያል ለሚባሉ አገሮች ከወዲሁ ስንብት እንዳያደርጉ የሚያሰጋ ሆኖ እንደቀጠለ ነው። ሣምንቱ በተጨማሪም በዓለምአቀፍ ደረጃ የኢትዮጵያ አትሌቶች ድል የታየበትም ነበር።

አንጎላና ማላዊ

አንጎላና ማላዊ

የአፍሪቃ እግር ኳስ ዋንጫ ውድድር

27ኛው የአፍሪቃ እግር ኳስ ዋንጫ ውድድር ገና በመጀመሪያ የምድብ ዙሩ ለአንዳንዶቹ ቀደምት የሚባሉ ተሳታፊ አገሮች ፈታኝ እየሆነ ሄዷል። ምድብ-አንድ ውስጥ አስተናጋጇ አንጎላም ሆነች የተቀሩት ለምሳሌ አልጄሪያን የመሰለችው ዋነኛዋ ተፎካካሪ ወደ ቀጣዩ የጥሎ ማለፍ ዙር ለማለፍ ጠንካራ ትግል ነው የሚጠብቃቸው። አንጎላ-ማላዊን 2-0፤ አልጄሪያም ማሊን 1-0 ቢያሸንፉም በሌላ በኩል አልጄሪያ በመጀመሪያው ግጥሚያ በማላዊ 3-0 መረታቷ፤ አንጎላም እንዲሁ ከማሊ ጋር ባካሄደችው የመክፈቻ ግጥሚያ ያለቀለት ድሏን ማስነካቷ ቀደም ሲል ማንም ያሰበው አልነበረም።

አንጎላ ከሣምንት በፊት በተካሄደው የመክፈቻ ግጥሚያ እስከ 79ኛው ደቂቃ ድረስ 4-0 ስትመራ ጨዋታው ቀድሞ የለየለት ነበር የመሰለው። ይሁንና የማሊ ተጫዋቾች ትግላቸውን በማጠናከር በ 14 ደቂቃዎች ውስጥ አራት ጎሎችን አስቆጥረው ውጤቱን እኩል-ለእኩል ሊያደርጉት በቅተዋል። ወኔና ቁርጠኝነታቸው እጅግ የሚደነቅ ነው። በውቅቱ ከሁለት ግጥሚያዎች በኋላ አንጎላ ምድቡን በአራት ነጥብ የምትመራ ሲሆን ማላዊና አልጄሪያ አንዲት ነጥብ ወረድ ብለው በቅርብ ይከተሏታል። አንጎላን ክፉኛ የፈተነችው ማሊ በአንዲት ነጥብ አራተኛ ናት። በዛሬው ዕለት አንጎላ-ከአልጄሪያ፤ እንዲሁም ማሊ-ከማላዊ የሚጋጠሙ ሲሆን በተለይም የመጀመሪያው ጨዋታ ውጤት ምናልባት ወሣኝነት ሊኖረው የሚችል ነው። በተለይ አንጎላ እንደ አስተናጋጅ አገር ከባድ ግፊት አለባት። በውድድሩ ወደፊት መዝለቅ ይጠበቅባታል።

በምድብ-ሁለት አይቮሪ ኮስት ጋናን ያህል ጠንካራ ተጋጣሚ 3-1 ስታሸንፍ ከቡርኪና ፋሶም ባዶ-ለባዶ በመለያየት አራት ነጥቦችን ይዛ ትመራለች። ይህ ምድብ በውድድሩ ዋዜማ በካቢንዳ የዓማጺያን ጥቃት የደረሰበት የቶጎ ብሄራዊ ቡድን ወደ አገሩ በመመለሱ ሶሥት አገሮችን ብቻ የጠቀለለ ሲሆን በተለይ የዋንጫ ባለቤት የመሆን ታላቅ ዕድል አላቸው ይባሉ ከነበሩት አንዷ ጋና ነገ ቡርኪና ፋሶን ካላሽነፈች በአጭሩ እንዳትቀጭ በጣሙን የሚያሰጋት ነው። ምድብ-ሶሥት ውስጥ ያለፉት ዓመታት ሻምፒዮን ግብጽ እንደተጠበቀው እስካሁን በስኬት አቅጣጫ በማምራት ላይ ናት። ናይጄሪያን 3-1 እና ሞዛምቢክን ደግሞ 2-0 በማሸነፍ በስድሥት ነጥቦች ምድቡን ትመራለች። ናይጄሪያ ቤኒንን 1-0 አሸንፋ በሶሥት ነጥቦች ሁለተኛ ስትሆን ቤኒንና ሞዛምቢክ በአንዲት ነጥብ ከወዲሁ ሳያልቅላቸው አልቀረም።

እንደ ናይጄሪያ፣ አልጄሪያ ወይም ጋና ሌላው በጅምሩ ብርቱ ፈተና ገጥሞት የሰነበተው ጠንካራ ቡድን የካሜሩን ነው። ካሜሩን በምድብ-አራት የመጀመሪያ ግጥሚያ ባልተጠበቀ ሁኔታ በጋቦን 1-0 ከተረታች በኋላ ትናንት ዛምቢያን በመጨረሻዋ ደቂቃ 3-2 ባታሸንፍ ኖሮ ባዶ ዕጇን በቀረች ነበር። ሞሐማዱ ኢድሪሶ በ 86ኛዋ ደቂቃ ላይ ባስቆጠራት ወሣኝ ጎል ካሜሪን ሕያው ሆና እንድትቀጥል አብቅቷል። ምድቡን ጋቦን በአራት ነጥቦች የምትመራ ሲሆን ካሜሩን በሶሥት ትከተላለች፤ ሁለት ግጥሚያዎቿን እኩል-ለአኩል የፈጸመችው ቱኒዚያ ደግሞ ስሥተኛ ናት። የቱኒዚያም ድክመት የተጠበቀ አልነበረም። ለማንኛውም በፊታችን ሐሙስ ጋቦን ከዛምቢያ፤ እንዲሁም ካሜሩን ከቱኒዚያ ይጋጠማሉ።

የእስካሁኑ ውድድር ሂደት በጥቅሉ የሚያሳየው የአፍሪቃ እግር ኳስ ባለፉት ዓመታት ብርቱ ዕርምጃ እያደረገ ከመጣ ወዲህ ፉክክሩም በዚያው መጠን መጠናከሩን ነው። እንደቀድሞው ጥቂት አገሮች ሃያል ሆነው ይታዩበት የነበረው ጊዜ ማለፉን እንደገና ለመታዘብ ተችሏል። ምናልባት በጅማሮው የተንገዳገዱት ጋናንና ካሜሩንን የመሳሰሉት አገሮች እንደምንም ወደ ተከታዩ ዙር ያልፉ ይሆናል። ግን ጉዞው የሽርሽርን ያህል የሚሆንላቸው አይመስልም።

አትሌቲክስ

በትናንትናው ዕለት አሜሪካ ውስጥ በተካሄደው የሂዩስተን ማራቶን የኢትዮጵያ አትሌቦች በወንዶችና በሴቶችም በማሸነፍ በተፎካካሪዎቻቸው ላይ ፍጹም ልዕልና ለማሳየት በቅተዋል። ተሾመ ገለና በውድድሩ ፈጣን ጊዜ 2 ሰዓት ከ 7 ደቂቃ 37 ሤኮንድ ሩጫውን ቀደምት ሆኖ በመፈጸም ሲያሸንፍ በሴቶችም ጠይቤ ኤርኬሶ በዚያው አስመዝግባ የነበረውን የራሷን ክብረ-ወሰን በሰላሣ ሤኮንዶች በማሻሻል ቀደም ያለ ድሏን ደግማዋለች። በግማሽ ማራቶን ሩጫ ደግሞ አሜሪካዊቱ የቤይጂንግ ኦሎምፒክ የአሥር ሺህ ሜትር የናስ ሜዳሊያ ተሸላሚ ሻሌን ፍላናጋን አሸናፊ ሆናለች።

የኢትዮጵያ አትሌቶች በሕንድ የሙምባይ ማራቶንም አስደናቂ ውጤት አስመዝግበዋል። በወንዶች ምንም እንኳ ኬንያዊው ዴኒስ እንዲሶ አሸናፊ ቢሆንም ሲራጅ ገና ሩጫውን በሁለተኝነት ለመፈጸም በቅቷል። በሴቶች እንዲያውም ድርብ ድል ነው የተገኘው። ብዙነሽ መሐመድ ሩጫውን በአንደኝነት ስትፈጽም ያለፈው ዓመት አሸናፊ ከበቡሽ ሃይሌ ደግሞ ሁለተኛ ሆናለች። የኢትዮጵያ አትሌቶች በየቦታው የሚያስመዘግቡት ግሩም ውጤት ለመጪው የውድድር ወቅት ተሥፋን የሚያጠናክር ነው።

እግር ኳስ፤ የአውሮፓ ሊጋዎች

Fußball Bundesliga Leverkusen Mainz Flash-Galerie

የጀርመን ቡንደስሊጋ ከአንድ ወር የክረምት አረፍት በኋላ በዚህ ሰንበት ወደ ውድድሩ ሁለተኛ ዙር ተመልሷል። ሶሥቱም ቀደምት ክለቦች የየበኩላቸውን ግጥሚያ በማሽነፍ ሲወጡ በሰልፉ ላይ የተደረገ ለውጥ የለም። ሌቨርኩዝን ማይንስን በግሩም ጨዋታ 4-2 በማሸነፍ አመራሩን ሲያስከብር ሻልከ ኑርንበርግን 1-0፤ እንዲሁም ባየንን ሙንሺን ሆፈንሃይምን 2-0 በመርታት የቅርብ ተከታዮቹ እንደሆኑ ነው። ሌቨርኩዝን ለድል የበቃው በኑርንበርግ ቀድሞ ከተመራ በኋላ ነበር። ግን የቡድኑ አሠልጣኝ ዩፕ ሃይንከስ እንዳለው ተንገዳግዶ አልቀረም።
“እየተወላከፍን ነበር ጨዋታውን የተያያዝነው። ቡድኑ 1-0 ከተመራ በኋላ በትልቅ ስሜትና ትጋት ግሩም ምላሽ ለመስጠት ችሏል። ከሁሉም በላይ ኳስን በሰፊው መቆጣጠርና ወደፊት በማጥቃት መጫወት መቻላችን ወሣኝ ነበር። ከዚያ በኋላ ነው ጎሎቹን ያስቆጠርነው”

በየር ሌቨርኩዝን በመጀመሪያው ዙር ካቆመበት ሲቀጥል እስካሁን ከታዩት ጨዋታዎች አንጻር ከቅርብ ተፎካካሪዎቹ ሁሉ ለሻምፒዮንነቱ የሰከነው ነው የሚመስለው። ይሁንና እስከዚያው ገና 16 ግጥሚያዎች የሚቀሩ ሲሆን ጉዞው ረጅም ነው። ሶሥቱ ክለቦች የሚለያዩት በአንዳንድ ነጥብ ብቻ ሲሆን ዘርድሮ የቡንደስሊጋው ፉክክር የጦፈ የሚሆንም ነው የሚመስለው። በተቀረ ሃምቡርግ አራተኛ፤ እንዲሁም ዶርትሙንድ አምሥተኛ ሲሆኑ በፍራንክፈርት 1-0 የተሽነፈው ብሬመን በአንጻሩ ማቆልቆሉን እንደቀጠለ ነው። ከአሁኑ ከቀደምቱ ከሌቨርኩዝን ጋር ያለው ልዩነት አሥር ነጥብ ደርሷል።

በአጣሊያ ሤሪያ-አ ኢንተር ሚላን ከባሪ ጋር 2-2 በሆነ ውጤት በመወሰኑ ከሁለተኛው ከኤ.ሢ.ሚላን ጋር የነበረው የነጥብ ልዩነት ወደ ስድሥት ዝቅ ብሏል። ኤ.ሢ.ሚላን በፊናው ሢየናን 4-0 ሲያሸንፍ ሶሥቱን ጎሎች ያስቆጠረው ደግሞ ብራዚላዊው ሮናልዲኞ ነበር። የአንዴው ኮከብ ሮናልዲኞ ወደ ቀድሞ ጥንካሬው መመለስ የያዘ መስሎ ታይቷል። በሌላ በኩል ከጥሩ ጅማሮ በኋላ ማቆልቆል የያዘው የጁቬንቱስ ክስረት ባለበት እንደቀጠለ ነው። በቺየቮ 1-0 ተረትቶ ወደ አምሥተኛው ቦታ ተንሸራቷል። በኢጣሊያው ሊጋ ውስጥ በተለይ መጪው ዕሑድ በታላቅ ጉጉት ነው የሚጠበቀው። ምክንያቱም ሰንበቱ አንደኛና ሁለተኛው የሚላን ተፎካካሪ ክለቦች እርስበርስ የሚገናኙበት ነው። ጨዋታው በኢጣሊያው ሻምፒዮና ላይ ጥቂትም ቢሆን ከወዲሁ ወሣኝነት ሊኖረው ይችላል።

በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ ቼልሢይ ሰንደርላንድን 7-2 አከናንቦ በመሸኘት በአመራሩ እንደጸና ቀጥሏል። ማንቼስተር ዩናይትድም በርንሊይን 3-0 ሲያሸንፍ አንዲት ነጥብ ዝቅ ብሎ ሁለተኛ ነው። እርግጥ ማንቼስተር ዩናይትድ የአንድ ጨዋታ ብልጫ አለው። ዘንድሮም እንዳለፉት ዓመታት ሁሉ ሻምፒዮናው በሁለቱ መካከል የሚለይለት ነው የሚመስለው። ሊቨርፑል በአንጻሩ ከስቶክ ሢቲይ 1-1 ሲለያይ ገጽታው ከሻምፒዮናው ከራዳር እየተሰወረ መሄዱን ቀጥሏል፤ ሰባተኛ ነው።

በስፓኝ ላ-ሊጋ በምቹ የአምሥት ነጥቦች ልዩነት እንደገና አመራሩን የያዘው ባርሤሎና ሤቪያን 4-0 በመርታት አርኪ ሰንበት ነው ያሳለፈው። ሬያል ማድሪድ በአንጻሩ በቢልባዎ 1-0 በመሽነፉ አመራሩን ማስረከቡ ግድ ሆኖበታል። ሶሥተኛው ቪላርሬያልን 4-1 ያሽነፈው ቫሌንሢያ ሲሆን ሤቪያ ስድሥተኛ ነው። በፈረንሣይ አንደኛ ዲቪዚዮን ቦርዶው ምንም እንኳ ከማርሤይ እኩል-ለእኩል ቢለያይም በሰባት ነጥቦች ልዩነት ተዝናንቶ መምራቱን ቀጥሏል። ሁለተኛው ያለፉትን ሰባት ግጥሚያዎች በእያንዳንዱ ቢያንስ ሶሥት ጎሎችን አስቆጥሮ በማሸነፍ ታላቅ ትንሣዔ ያደረገው ሊል ነው። በኔዘርላንድ ከክረምት እረፍት መልስ በተጀመረው ውድድር ደግሞ የሊጋው መሪ ኤንሼዴ ለአሸናፊነት ባይበቃም አይንድሆፈንን በሶሥት ነጥቦች እንዳስከተለ ቀጥሏል።

ቴኒስ፤ የሜልበርን ውድድር

ሜልበርን ላይ በተከፈተው የዘንድሮ አውስትሬሊያን-ኦፕን የቴኒስ ውድድር ብዙዎች ዓለምአቀፍ ከዋክብት እንደተጠበቀው የመጀመሪያ ግጥሚያቸውን በማሸነፍ ወደሚቀጥለው ዙር ሲያልፉ የሩሢያዊቱ የቀድሞ ሻምፒዮን የማሪያ ሻራፖቫ ጉዞ ብቻ አሐዱ ሲል አክትሟል። ራፋኤል ናዳል፣ ዲናራ ሳፊና፣ ኤንዲይ መሪይና ኤንዲይ ሮዲክ ጅማሮው ከቀናቸው መካከል ቀደምቱ ናቸው። ሻራፖቫ በአገሯ ልጅ በማሪያ ኪሪሌንኮ ስትረታ በአጨዋወቷ ጨርሶ የቀድሞዋ አልነበረችም። ውድድሩ ነገ ይቀጥላል።

DW/AFP
MM/HM