የስፖርት ዘገባ | ስፖርት | DW | 04.01.2010
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ስፖርት

የስፖርት ዘገባ

አንጎላ ውስጥ የሚካሄደው 27ኛው የአፍሪቃ የእግር ኳስ ዋንጫ ውድድር በፊታችን ዕሑድ ይጀምራል። የዘንድሮው ውድድር ከመንፈቅ በኋላ በክፍለ-ዓለሚቱ ለመጀመሪያ ጊዜ በሚካሄደው የዓለም ዋንጫ ፍጻሜ ውድድር ዋዜማ የሚደረግ በመሆኑ ከቀድሞው ይልቅ ለየት ያለ ዓለምአቀፍ ትክረት ማግኘቱ የማይቀር ወይም የሚጠበቅ ነው።

default

አንጎላ ውስጥ የሚካሄደው የአፍሪቃ እግር ኳስ ዋንጫ ውድድር በፊታችን ዕሑድ ይጀመራል። 21 ቀናት የሚፈጀው ውድድር የሚከፈተው አስተናጋጇ አገር አንጎላና ማሊ ሉዋንዳ ላይ በሚያካሂዱት ግጥሚያ ነው። የውድድሩ የመጀመሪያ ዙር በአራት ምድቦች ተከፍሎ የሚካሄድ ሲሆን ብርቱ ፉክክር የሰመረበት እንደሚሆን ከወዲሁ መገመቱ አያዳግትም። አስተናጋጇ አንጎላ በምድብ-አንድ ውስጥ ከማሊ፣ ከማላዊና ከአልጄሪያ ጋር የተደለደለች ሲሆን ቀላል ተፎካካሪ አለ ቢባል ምናልባት ማላዊ ብቻ ናት። ምድብ-ሁለት ውስጥ ለዓለም ዋንጫ ፍጻሜ ያለፉት አይቮሪ ኮስትና ጋና ከቶጎና ከቡርኪና ፋሶ ጋር ተደልድለዋል። ይህ ቢቀር በወረቀት ከሁሉም ምድቦች ጠንከር ያለው ነው። ምድብ-ሶሥት ውስጥም ግብጽና ናይጄሪያ ሞዛምቢክንና ቤኒንን ጠቅለው በአንድ ተሰልፈዋል። ይህም እንዲሁ ቀላል የሚባል ምድብ አይደለም። ምድብ-አራት ካሜሩንን፣ ጋቦንን፣ ዛምቢያንና ቱኒዚያን ሲጠቀልል ማንልባት ካሜሩንን ቀለል ያለው ዕጣ የገጠማት ነው የሚመስለው።

በውድድሩ ሂደት የየምድቡ አንደኛና ሁለተኛ ወደ ተከታዩ የጥሎ ማለፍ ዙር የሚሻገር ሲሆን አራቱ የሩብ ፍጻሜ ግጥሚያዎች ከሁለት ሣምንት ጊዜ በኋላ ይካሄዳሉ። ከዚያም ሁለቱ የግማሽ ፍጻሜ ግጥሚያዎች ጥር ሃያ ቀን ሉዋንዳና ቤንጉዌላ ላይ ከተካሄዱ በኋላ ጥር 23 ቀን የዋንጫው ባለቤት ማንነት ይለይለታል። አንጎላ እንደ አስተናጋጅ አገር የዋንጫ ባለቤት የመሆን ትልቅ ዕድል ያላት ሲሆን ብሄራዊው ቡድን ትናንት ፖርቱጋል ውስጥ ከጋምቢያ ጋር ባደረገው ግጥሚያ 1-1 በመለያየት የመጨረሻ ዝግጅቱን አከናውኗል። እርግጥ የመጪው የዓለም ዋንጫ ተሳታፊዎች ካሜሩን፣ አይቮሪ ኮስት፣ ጋናና አልጄሪያ፤ እንዲሁም ያለፈው ውድድር አሸናፊ ግብጽ ወደ አንጎላ የሚያመሩት የዋንጫ ባለቤት ለመሆን ነው። የነዚህ ሁሉ ጥንካሬ ሲታይ ታዲያ የመጪዎቹ ሣምንታት ፉክክር ቀላል የሚሆን አይመስልም። የአፍሪቃ እግር ኳስ ዕርምጃና የደቡብ አፍሪቃው የዓለም ወንጫ ፍጻሜ መቃረብም ለአንጎላው ውድድር በተለይ በዚህ በአውሮፓ ሰፊ ትኩረትን እየሳበ ነው።

ታሪኩን መለስ ብሎ ለመዳሰስ ያህል የአፍሪቃ እግር ኳስ ዋንጫ ውድድር የተጀመረው እ.ጎ.አ. በ 1957 ከ 52 ዓመታት በፊት ነበር። የመጀመሪያው ውድድር በሶሥት አገሮች፤ በሱዳን፣ በኢትዮጵያና በግብጽ ተሳትፎ ሲካሄድ ግብጽ የመጀመሪያዋ የዋንጫ ባለቤት ትሆናለች። በነገራችን ላይ ደቡብ አፍሪቃም በጊዜው የአፓርታይድ አገዛዝ ፖሊሲዋ ባትወገድ ኖሮ አራተኛዋ ተሳታፊ ልትሆን በቻለች ነበር። ግብጽ ሁለተኛውንም የአፍሪቃ ዋንጫ አስከትላ ስትወስድ ውድድሩ በተጀመረ በአምሥተኛ ዓመቱ የዛሬውን አያድርገውና የሶሥተኛው የአፍሪቃ ዋንጫ ድል እስካሁን ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ የኢትዮጵያ ነበር። ኢትዮጵያ እስከዛሬ የሚናፍቃት በመንግሥቱ ወርቁ፥ ሉቺያኖ፣ ኢታሎና መሰል ተጫዋቾች ያሽበረቀ ብሄራዊ ቡድን ግብጽን ያህል ሃያል ተጋጣሚ አዲስ አበባ ላይ ልብ በሚሰውር ጨዋታ 4-2 በማሸነፍ ዋንጫዋን ነጥቆ ያስቀራል። ወቅቱ በኢትዮጵያ የእግር ኳስ ታሪክ ውስጥ አዲስ ምዕራፍ የተከፈተበት ነበር። ለዚህ ስኬት እርግጥ አሠልጣኙ አቶ ይድነቃቸው ተሰማም ታላቅ አስተዋጽኦ አድርገዋል። ከግብጹ አጥቂ ከአብደል ፋታህ ባዳዊ ጋር ሶሥት ግቦችን በማስቆጠር የውድድሩ ጎል አግቢ ሆኖ ታሪክ ያስመዘገበው መንግሥቱ ወርቁ በአፍሪቃ እግር ኳስ ኮንፌደሬሺን ምሥረታ 50ኛ ዓመት ማግሥት፤ ከሁለት ዓመታት ገደማ በፊት ጊዜውን መለስ ብሎ ሲያስታውስ እንዲህ ነበር ያለን።
ሆኖም ኢትዮጵያ ከዚያን ወዲህ ሁለት የአፍሪቃ ዋንጫ ውድድሮችን ብታዘጋጅም ስድሥተኛው የአፍሪቃ ዋንጫ የጥንካሬ ዘመኗ ማክተሚያ ነበር። የአፍሪቃ እግር ኳስ ግን ዕርምጃ እያሳየ ሲቀጥል ውድድሩ ደግሞ ከ 1968 ዓ.ም. ወዲህ ከማጣሪያ ጋር በ 16 አገሮች ተሳታፊነት በየሁለት ዓመቱ ሲካሄድ ቆይቷል። ከአራተኛው የአፍሪቃ ዋንጫ ውድድር ወዲህ ያለው ዘመን አልፎ አልፎ አንዳንድ አገሮች ጣልቃ ቢገቡበትም በተለይ የጋና፣ የናይጄሪያና የካሜሩን የልዕልና ዘመን ነበር። ግብጽ በጠቅላላው ስድሥት ጊዜ የዋንጫ ባለቤት በመሆን ቀደምቷ ስትሆን ጋናና ካሜሪን እያንዳንዳቸው አራት ጊዜ የዋንጫ ባለቤት ለመሆን በቅተዋል። ኮንጎ ዴሞክራቲክ ሬፑብሊክ የቀድሞይቱ ዛኢርና ናይጄሪያ ሁለቴ ለድል ሲበቁ እንደ ኢትዮጵያ ሁሉ አልጄሪያ፣ ኮንጎ ብራዛቪል፣ ሞሮኮ፣ ደቡብ አፍሪቃ፣ ሱዳን፣ ቱኒዚያና አይቮሪ ኮስትም አንድ አንድ ጊዜ ለሻምፒዮንነቱ ክብር የበቁ ነበሩ።

የአፍሪቃ እግር ኳስ ዛሬ በኮንፌደሬሺኑ የግማሽ ምዕተ-ዓመት ዕድሜ ከፍተኛ ዕርምጃ በማድረግ በዓለምአቀፍ ደረጃ ለተፎካካሪነት የበቃ ነው። ተጫዋቾቹ የአውሮፓ ቀደምት ክለቦች የዓይን ማረፊያ ከሆኑም ውለው አድረዋል። ዲዲየር ድሮግባ፤ ሣሙዔል ኤቶ፣ ማይክል ኤሢየንና በርካታ መሰሎቻቸው ዛሬ በዓለምአቀፉ የእግር ኳስ መድረክ ላይ አኩሪ የአፍሪቃ አምባሣደሮች ናቸው። እንግዲህ አንጎላ ላይ የሚካሄደው የዘንድሮው የአፍሪቃ ዋንጫ ውድድር እነዚህን በመሳሰሉ ከዋክብት የደመቀ ነው የሚሆነው። በአፍሪቃም ለብዙዎቹ ኳስ አፍቃሪዎች እስከ ደቡብ አፍሪቃ የዓለም ዋንጫ የሚዘልቀው ፌስታ ከአሁኑ ይጀምራል። ውድድሩ በሚቀጥሉት ሣምንታት በሰፊው የምናተኩርበት ነው።

Chelsea - Barcelona 1:0 Michael Essien

የቼልሢው ማይክል ኤሢየን

ወደ አውሮፓ መለስ እንበልና ብዙዎች ክለቦች በክረምት ዕረፍት ላይ በሚገኙበት በዚህ ወቅት ቢቀር በጥቂት ቀደምት ሊጋዎች ውስጥ ግጥሚያዎች መካሄዳቸው አልቀረም። በእንግሊዝ ሰንበቱ የፌደሬሺኑ ዋንጫ ስሥተኛ ዙር ግጥሚያዎች የተካሄዱበት ነበር። ከሁሉም በላይ አስደናቂው ውጤት ማንቼስተር ዩናይትድ በገዛ ሜዳው በሊድስ 1-0 ተረትቶ ከውድድሩ መሰናበቱ ነው። በአንጻሩ ዋነኛው ተፎካካሪው ቼልሢይ የሁለተኛ ዲቪዚዮኑን ክለብ ዋትፎርድን በአስተማማኝ ሁኔታ 5-0 አሸንፏል። በተቀሩት ግጥሚያዎች ከብዙ በጥቂቱ ለመጥቀስ አርሰናል ዌስት-ሃም-ዩናይትድ 2-1፤ ኤስተን-ቪላ ብላክበርን-ሮቨርስ 3-1፤ ማንቼስተር-ሢቲይ ሚድልስቦሮህ 1-0፤ ሊቨርፑል ሪዲንግ 1-1 ተለያይተዋል። ትናንት በዌምብሌይ ስታዲዮም በወጣው ዕጣ መሠረት በተከታዩ አራተኛ ዙር በጥቂቱ ቼልሢይ ከሁለተኛ ዲቪዚዮኑ ክለብ ከፕሬስተን-ኖርዝ-ኤንድ፤ ኤቨርተን ከኖቲንግሃም-ፎሬስት፤ አርሰናል ከስቶክ-ሢቲይ፤ እንዲሁም የሊቨርፑልና የሪዲንግ አሸናፊ ከበርንሌይ ይጋጠማሉ።

በዚያው በብሪታኒያ፤ በስኮትላንድ ፕሬሚየር ሊግ ሁለቱ ቀደምት ክለቦች ግላስጎው ሬንጀርስና ሤልቲክ ግላስጎው 1-1 ሲለያዩ ሬንጀርስ በሰባት ነጥቦች ልዩነት ሊጋውን መምራቱን ቀጥሏል። እርግጥ ሤልቲክ አንድ ጨዋታ ስለሚጎለው ልዩነቱን የማጥበብ ዕድል አለው። በተቀረ በስፓኝ ፕሪሜራ ዲቪዚዮን ቀደምቱ ክለቦች ሬያል ማድሪድና ባርሤሎና በየፊናቸው ባደረጉት ግጥሚያ ከእኩል ለእኩል ውጤት ሊያልፉ ባለመቻላቸው የተለወጠ ነገር የለም። ሬያል ከኦሣሱና ባዶ-ለባዶ ሲለያይ ባርሣ ደግሞ ከቪላሬያል 1-1 በሆነ ውጤት ተወስኗል። ሤቪያ በአትሌቲኮ ማድሪድ 2-1 ተሸንፎ ወደ አምሥተኛው ቦታ ሲያቆለቁል ቫሌንሢያ በአንጻሩ ኤስፓኞልን 1-0በመርታት ወደ ሶሥተኛው ቦታ ከፍ ሊል በቅቷል። በጎል አግቢነት 12 አስቆጥሮ የሚመራው የቫሌንሢያው ዴቪድ ቪያ ነው።

ለማጠቃለል የስፓኙ የቴኒስ ኮከብ ራፋኤል ናዳል አቡ ዳቢ ላይ በተካሄደ የቴኒስ የዓለም ሻምፒዮና ውድድር በፍጻሜው የስዊድን ተጋጣሚውን ሮቢን ሶደርሊንግን በሶሥት ምድብ ጨዋታ በማሸነፍ በአዲሱ ዓመት የተሣካ ጅማሮ ለማድረግ በቅቷል። ናዳል ባለፈው ዓመት የባሕረ-ሰላጤው ውድድር በብሪታኒያው ኤንዲይ መሪይ መሸነፉ የሚታወስ ነው። ሶደርሊንግ ለፍጻሜ የደረሰው የስዊሱን ሮጀር ፌደረርን በግማሽ ፍጻሜው ግጥሚያ በመርታት ነበር።

MM/RTR/AFP

SL