የስፖርት ዘገባ | ስፖርት | DW | 14.12.2009
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ስፖርት

የስፖርት ዘገባ

በአውሮፓ ቀደምት ሊጋዎች የሰንበት ግጥሚያዎች በአንግሊዝ ችልሢይና ማንቼስተር ዩናይትድ ጥቂት እንደ ማንቀላፋት ሲሉ ባርሤሎናና ኢንተር በአንጻሩ እንዳየሉ ቀጥለዋል። በጀርመን ቡንደስሊጋም የብዙ ጊዜው ሻምፒዮን ባየርን ሙንሺን ከብዙ ሣምንታት ድክመት በኋላ የአመራሩ ተሻሚ እየሆነ ነው።

ቡንደስሊጋ፤ የባየርን አጥቂ ኢቪትሣ ኦሊች

ቡንደስሊጋ፤ የባየርን አጥቂ ኢቪትሣ ኦሊች

የአውሮፓ ቀደምት ሊጋዎች በሣምንቱ

በኢጣሊያው ሤሪያ-አ እንጀምርና ቀደምቱ ኢንተር ሚላን ምንም እንኳ ከአታላንታ ጋር አቻ-ላቻ 1-1 ቢለያይም አመራሩን ወደ አምሥት ነጥብ ከፍ ሊያደርግ በቅቷል። ለኢንተር ብችኛዋን ጎል ያስቆጠረው አርጄንቲናዊው አጥቂ ዲየጎ ሚሊቶ ነበር። የኢጣሊያው ሻምፒዮን ሆላንዳዊ ተጫዋቹ ዌስሊይ ስናይደር በሁለተኛው አጋማሽ ከሜዳ ባይወጣበት ምናልባት ለድል በበቃም ነበር። ይሁንና በሁለተኝነት የሚከተለው የከተማ ተፎካካሪው ኤ.ሢ.ሚላን በፓሌርሞ 2-0 መሽነፉ በተዘዋዋሪ በጅቶታል። በአንጻሩ ከክስረት መላቀቅ እንዳቃተው የቀጠለው ጁቬንቱስ ቱሪን ነው። ጁቬንቱስ በሣምንቱ አጋማሽ በገዛ ሜዳው በባየርን ሙንሺን 4-1 ተቀጥቶ ከአውሮፓ ሻምፒዮና ሊጋ ውድድር ከተሰናበተ በኋላ ሰንበቱም አልቀናውም። እንደገና ለዚያውም በዝቅተኛው ክለብ በባሪ 3-1 በመሸነፍ ሁለተኛውን ቦታ ከኤ.ሢ.ሚላን ለመንጠቅ የነበረውን ዕድል ሳይጠቀምበት ቀርቷል።

በስፓኝ ላ-ሊጋ ያለፈው ውድድር ወቅት ብሄራዊና የአውሮፓ ሻምፒዮና ሊጋ ባለድል ቀደምቱ ባርሤሎና የማይበገር ሆኖ እንደቀጠለ ነው። ባርሣ በስዊድናዊ አጥቂው በዝላታን ኢብራሂሞቪች አካማይነት ባስቆጠራት ግብ የከተማ ተፎካካሪውን ኤስፓኞልን 1-0 ሲረታ በ 15 ግጥሚያዎች 39 ነጥቦችን በማሰባሰብ ዘንድሮም ልዕልናውን እንዳስከበረ ነው። ሁለተኛው ሬያል ማድሪድም ቫሌንሢያን 3-2 ሲያሽንፍ በወቅቱ ከባርሤሎና የሚለዩት አምሥት ነጥቦች ናቸው። ሤቪያም እንዲሁ ስፖርቲንግ ጊዮንን 1-0 በመርታት በሶሥተኝነቱ ቀጥሏል። እርግጥ ሬያልና ሤቪያ ከባርሣ አንጻር ገና አንድ ጨዋታ ይጎላቸዋል። ለማንኛውም በጎል አግቢነት 12 በማስቆጠር ሊጋውን የሚመራው የቫሌንሢያው ዴቪድ ቪያ ሲሆን የባርሣ ከዋክብት ኢብራሂሞቪች በ 11 እንዲሁም ሊዮኔል ሜሢ በዘጠኝ ቀረብ ብለው ይከተሉታል።

በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ ሰንበቱ ለቀደምቱ ክለቦች ብዙም የቀና አልነበረም። ቼልሢይ ከኤቨርተን 3-3 ብቻ ሲለያይ ማንቼስተር ዩናይትድ ደግሞ በኤስተን ቪላ 1-0 ተሸንፏል። ሁለቱ ክለቦች ይሁንና ግንባር ቀደም ሆነው እንደቀጠሉ ነው። አርሰናልም ሊቨርፑልን በውጭ 2-1 ሲያሸንፍ ሶሥተኝነቱ አላስነካም። በዚህ በሰንበቱ ዓቢይ ግጥሚያ አርሰናል በሊቨርፑል የአንፊልድ ስታዲዮም ለድል ሲበቃ ከስድሥት ዓመታት ወዲህ ለመጀመሪያ ጊዜ መሆኑ ነበር። ከአውሮፓ ሻምፒዮና ሊጋ ውድድር የወጣውና ዘንድሮ ክፉኛ መንገዳገድ የያዘው ሊቨርፑል ከሰንበቱ ሽንፈት ወዲህ ሰባተኛ ሲሆን የሊጋውን አመራር ከያዘው ከቼልሢይ 13 ነጥቦች ይለዩታል። ስለዚህም በውድድሩ መጨረሻ ሻምፒዮን መሆኑ ቀርቶ ለአውሮፓ ሊጋ ተሳትፎ የሚያበቃ ቦታ ከያዘ እንኳ ትልቅ ነገር ነው የሚሆነው።
በተረፈ ኤስተን ቪላ ቼልሢይን፣ ማንቼስተር ዩናይትድንና አርሰናልን ተከትሎ አራተኛ ነው፤ ቶተንሃም ሆትስፐር ደግሞ ሁለት ነጥቦች ዝቅ ብሎ ይከተለዋል። በጎል አግቢነት በ 13 ሊጋውን የሚመራው ሰንበቱን ከቼልሢይ ሶሥት ጎሎች ሁለቱን ያስቆጠረው የአይቮሪ ኮስቱ ኮከብ ዲዲየር ድሮግባ ነው። በሌላ በኩል የማንቼስተር ዩናይትድ የክንፍ መንኮራኩር ራያን ጊግስ ትናንት በሕዝብ ድምጽ የዓመቱ የቢቢሲ የስፖርት ሰው ተብሎ ተሰይሟል። የ 36 ዓመቱ የዌልስ ተወላጅ ክለቡን በተከታታይ ለፕሬሚየር ሊጉ ሻምፒዮንነት በመምራት ባለፈው ሚያዚያ ወር በፕሮፌሺናል የእግር ኳስ ተጫዋቾች ማሕበር ቀደምት ተጫዋች ሆኖ መመረጡም አይዘነጋም። ጊግስ ዩናይትድን ከተቀላቀለ ከዘጠኝ ዓመታት ወዲህ በ 800 ግጥሚያዎች ሲሰለፍ ይህም በክለቡ ታሪክ ውስጥ ልዩ ክብረ-ወሰን ነው።

በጀርመን ቡንደሲጋ ለክረምቱ እረፍት ቦታውን የሚለቀው የመጀመሪያው ዙር ውድድር ሊጠናቀቅ አንድ ግጥሚያ ብቻ ቢቀርም የበልጉ የግማሽ ጊዜ ሻምፒዮን ማንነት ገና አልለየለትም። ማሸነፍን የረሣ የሚመስለው ባየር ሌቨርኩዝን በዚህ ሣምንትም በእኩል ለእኩል ውጤት ሲወሰን አመራሩን መነጠቁ የጊዜ ጉዳይ እየሆነ ነው። የሁለተኛው የብሬመን የድል ማራቶንም ከ 23 ግጥሚያዎች በኋላ በሻልከ ሲሰናከል የሰሜን ጀርመኑ ክለብ ከሁለት ወደ አራተኛው ቦታ መውረዱ ግድ ሆኖበታል። ሻልከ በአንጻሩ ሌቨርኩዝንን በአንዲት ነጥብ ልዩነት ሲቃረብ ቦሁምን 5-1 የቀጣው ባየርን ሙንሺንም ሶሥተኛ ነው። ባየርን በሣምንቱ አጋማሽ ጁቬንቱስን 4-1 በማሸነፍ ከአውሮፓ ሻምፒዮና ሊጋ ውድድር ካስወጣ ወዲህ ሰንበቱን ደግሞ ያሳየው ጨዋታ መልሶ መጠናከሩን ያረጋገጠ ነበር። በዚህ ከቀጠለ በቀላሉ የሚገታ አይሆንም። ስለጨዋታው ከጎል አግቢዎቹ አንዱ ኢቪትሣ ኦሊች!

“ከሶሥት ቀናት በፊት ቱሪን ላይ በጀመርነው ነበር የቀጠልነው። እንደገና ጥሩ ጨዋታ ነበር። ቡድኑ በጠቅላላው ትልቅ ጨዋታ ነው ያሳየው። የተሻልነው እኛ ስንሆን ጥያቄው ምን ያህል ጎል እናስገባለን ብቻ ነበር”

በሌላ በኩል በጀርመን ቡንደስሊጋ ከአንደኛው እስከ አምሥተኛው ቦታ ያለው ልዩነት የአራት ነጥቦች ብቻ ሲሆን ከክረምቱ እረፍት በኋላ የሚቀጥለው የመልስ ውድድርም ብርቱ ፉክክር የሰመረበት ሆኖ እንደሚቀጥል አንድና ሁለት የለውም። በጎል አግቢነት የሌቨርኩዝን አጥቂ ሽቴፋን ኪስሊንግ 12 አስቆጥር ይመራል። በተቀረ በፈረንሣይ አንደኛ ዲቪዚዮን ቦርዶው ኦላምፒክ ሊዮንን 1-0 በመርታት በአራት ነጥቦች ልዩነት መምራቱን ሲቀጥል በኔዘርላንድ ሻምፒዮና ትቬንቴ ኤንሼዴ ብሬዳን 3-1 በማሸነፍ ቀደምቱ እንደሆነ ነው። አይንድሆፈን ሁለተኛ! በፖርቱጋል ሻምፒዮና ደግሞ ፖርቶ አመራሩን የያዙትን ብራጋንና ቤንፊካን በአንዲት ነጥብ ሊቃረብ በቅቷል።

አገር አቋረጭ ሩጫ፣ /የጠረጴዛ ቴኒስ፣ ቡጢ

አየርላንድ-ዳብሊን ላይ ትናንት ተካሂዶ በነበረ የአውሮፓ አገር-አቋራጭ ሩጫ ሻምፒዮና በወንዶች ከኢትዮጵያ የመነጨው ወጣት የስፓኝ ተወዳዳሪ አለማየሁ በዛብህ አሸናፊ ሆኗል። የብሪታኒያው ሞ ፋራህ ሁለተኛ ሲወጣ 9997 ሜትር ርዝመት ያለውን ሩጫ በሶሥተኝነት የፈጸመው ያለፈው ዓመት አሸናፊ የኡክራኒያው ሤርጌይ ሌቢድ ነበር። በሴቶች ደግሞ የብሪታኒያ አትሌት ሄይሊይ ዬሊንግ ባለድል ሆናለች። የ 35 ዓመቷ ታጋይ አትሌት ለአንድ ዓመት ያህል ወዳቋረጠችው ውድድር ተመልሳ ማሽነፏ ብዙዎችን ማስደነቁ አልቀረም። በተቀረ የስፓኝ ተወዳዳሪ ሮዛ ሞራቶ ሁለተኛ ስትሆን አድሪየነ ሄርሶግ ከኔዘርላንድ ደግሞ ሶሥተኛ ወጥታለች።
ላኦስ ውስጥ በመካሄድ ላይ ባለው የደቡብ ምሥራቅ እሢያ ጨዋታ ታይላንድ እስከ ትናንት ድረስ 23 የወርቅ ሜዳሊያዎችን በማግኘት በቀደምትነት እንደቀጠለች ነው። ቪየትናም ሁለተኛ፣ እንዲሁም ሢንጋፑር ሶሥተኛ ሆነው ይከተላሉ። የታይላንድ ስኬት ይበልጡን በአትሌቲክስ ሲሆን ሢንጋፑር ደግሞ በዋና ጥንካሬዋን አሳይታለች። በሌላ ኮሎምቢያ ውስጥ በተካሄደ የዓለም የወጣቶች የጠረጴዛ ቴኒስ ውድድር ቻይና ታላቅ የቡድን ድል ተጎናጸፈች። የቻይና ወጣቶች ቅልጥፍና በዚህ ስፖርት የአገራቸው ልዕልና በቅርቡ ሊደፈር እንደማይችል የሚያሳይ ነበር። የቻይና ወጣቶች አንዴ በጃፓን ከመበለጣቸው በስተቀር ከ 2003 ዓ.ም. ወዲህ መላውን ውድድር ያሸነፉ ናቸው። ድሉ በወንዶችና በሴቶችም የተገኘ ነበር።

ቪታሊ ክሊችኮ

ቪታሊ ክሊችኮ

የካሊፎርኒያው ቲሞቲይ ብራድሊይ ባለፈው ቅዳሜ በተካሄደ ግጥሚያ ላሞንት ፔተርሰንን በአንድ-ወጥ የዳኞች ውሣኔ በማሽነፍ የዓለም ቡጢ ድርጅት የቀላል ሚዛን ማዕረጉን ለማስከበር በቅቷል። ብራድሊይ በደጋፊዎቹ ፊት ባደረገው ግጥሚያ በተለይም በፍጥነቱና የአጨዋወት ጥበቡ ተመልካቹን ሲያስደስት ፔተርሰን በአንጻሩ ጨዋታውን የፈጸመው በ 11ኛው ዙር ላይ ተዘርሮ ከተነሣ በኋላ ነበር። የአውስትራሊያው ቪክ ዳርቺኒያን ደግሞ በሱፐር-ፍላይ ክብደት የሜክሢኮ ተጋጣሚውን ቶማስ ሮያስን በሁለተኛው ዙር በመዘረር የዓለም ቡጢ ካውንስልና የዓለም ቡጡ ማሕበር ማዕርጉን አስመልሷል። ሮያስ ሲሸነፍ በሁለት ዓመት ጊዜ ውስጥ ለመጀመሪያ ጊዜ መሆኑ ነው። ስዊትዘርላንድ-በርን ላይ ደግሞ ኡክራኒያዊው ቪታሊ ክሊችኮ የአሜሪካ ተጋጣሚውን ኬቪን ጆንስንን በቀላሉ በማሸነፍ የ WBC የዓለም ከባድ ሚዛን ማዕረጉን ለማስከበር ችሏል።

ዘገባችንን በአፍሪቃ የእግር ኳስ ዜና ለማጠቃለል ካይሮ ላይ ተቀማጭ የሆነው የአፍሪቃ እግር ኳስ ኮንፌደሬሺን በዓመቱ ድንቅ ተጫዋችነት ለመመረጥ የታጩትን አምሥት ኮከቦች ዝርዝር በሣምንቱ አጋማሽ አውጥቶ ነበር። ከነዚሁ መካከል አንዱ እስካሁን ሶሥት ጊዜ የዓመቱ የአፍሪቃ ድንቅ ተጫዋች በመባል የተሰየመው የካሜሩኑ ሣሙዔል ኤቶ ነው። ኤቶ ከባርሤሎና ወደ የኢንተር ሚላን መሻገሩ ይታወቃል። የተቀሩት ዕጩዎች የቼልሢይ ከዋክብት የአይቮሪ ኮስቱ ዲዲደር ድሮግባና የጋናው ማይክል ኤሢየን፤ እንዲሁም የባርሤሎና የመሃል ሜዳ ተጫዋቾች የማሊው ሰይዱ ኬይታና የአይቮሪ ኮስቱ ያያ ቱሬ ናቸው። አሸናፊው የሚታወቀው የአፍሪቃ እግር ኳስ ኮንፌደሬሺን 53 ዓባል ሃገራት መላ አሠልጣኞች በፊታችን የካቲት አጋማሽ ድምጽ በሚሰጡበት ጊዜ ነው። ዕጩዎቹ በሙሉ ግሩም በመሆናቸው ምርጫው ቀላል የሚሆን አይመስልም።

MM/HM

DW/RTR/AFP