የስፖርት ዘገባ | ስፖርት | DW | 09.11.2009
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ስፖርት

የስፖርት ዘገባ

ናይጄሪያ ውስጥ የሚካሄደው ከ 17 ዓመት በታች ወጣቶች የዓለም እግር ኳስ ዋንጫ ውድድር ወደ ግማሽ ፍጻሜው እየተቃረበ ነው። ማዜምቤ የዘንድሮው የአፍሪቃ ክለቦች ሻምፒዮና ሊጋ አሸናፊ ሆኗል፤ የአውሮፓ ሊጋዎች ፉክክርም ቀጥሏል።

ቡንደስሊጋ፤ የሌቨርኩዝን ጎል አግቢ ኪስሊንግ

ቡንደስሊጋ፤ የሌቨርኩዝን ጎል አግቢ ኪስሊንግ

ማዜምቤ የአፍሪቃ ሊጋ ሻምፒዮን

የዘንድሮው የአፍሪቃ ሻምፒዮና ሊጋ ውድድር አሸናፊ የኮንጎ ዴሞክራቲክ ሬፑብሊኩ ክለብ ቲ.ፒ.ማዜምቤ ሆኗል። ማዜምቤ ለዚህ ታላቅ ድል የበቃው ባለፈው ቅዳሜ 35 ሺህ ተመልካቾቹ በተገኙበት በሉቡምባሺ ስታዲዮም የናይጄሪያ ተጋጣሚውን Heartland FC-ን በፍጻሜው መልስ ግጥሚያ 1-0 ከረታ በኋላ ነው። ብቸኛዋን የድል ጎል በ 74ው ደቂቃ ላይ ያስቆጠረው ቪክቶር ኤዙሪኬ ነበር። የናይጄሪያው ክለብ Heartland ምንም እንኳ የመጀመሪያውን ግጥሚያ 2-1 በሆነ ውጤት ቢያሸንፍም አጠቃላዩ ውጤት ይሁንና በመጨረሻ 2-2 መሆኑ አልጠቀመውም። ማዜምቤ በውጭ ባስቆጠራት ጎል ድሉን ሊያረጋግጥ በቅቷል። በነገራችን ላይ ይህ በውጭ የተቆጠረ ጎል ወሣኝነት ደምብ በአፍሪቃ እግር ኳስ ኮን-ፌደሬሺን የቀደምት ሊጋ ሻምፒዮና የ 44 ዓመታት ታሪክ ውስጥ በሥራ ላይ ሲውል ለመጀመሪያ ጊዜ መሆኑ ነው። ማዜምቤ የአፍሪቃ ክለቦች ሻምፒዮንነት ሲበቃ ለሶሥተኛ ጊዜ ሲሆን ያለፈው ቅዳሜ ድሉ የ 1,5 ሚሊዮን ዶላር ተሸላሚ አድርጎታል።

የኮንጎው ክለብ በውድድሩ ስኬት ማግኘቱ ያለ ምክንያት አልነበረም። ክለቡ በአፍሪቃ ታላቁ የሆነውን ክብር ለማግኘት በዚህ ዓመት አምሥት ሚሊዮን ዶላር በጀት ሲመድብ ከዚሁ ግማሹን ገንዘብ አፍሶ የፈረንሣዩን አሠልጣኝ ዲየጎ ጋርዚቶን መቅጠሩም አሁን በመጨረሻ እንደሚታየው በጅቶታል። የሻምፒዮናው ሊጋ ድል ለማዜምቤ ገንዘብና ክብር ከማስገኘቱ ባሻገር ክለቡን በቅርቡ በተባበሩት ኤሚሮች ግዛት በሚካሄደው የዓለም አግር ካስ ፌደሬሺኖች ማሕበር የፊፋ የክለቦች ዓለም ዋንጫ ውድድር እንዲሳተፍም የሚያበቃው ነው። በውድድሩ የስፓኙን ሻምፒዮን ባርሤሎናን የመሳሰሉት ታላላቅ ክለቦች ይጠብቁታል። ማዜምቤ ደቡብ አፍሪቃ ውስጥ በሚካሄደው የዓለም አግር ኳስ ዋንጫ ፍጻሜ ውድድር ዋዜማ በዓለምአቀፉ መድረክ ላይ የአፍሪቃን ክብር እንደሚያስጠብቅ ተሥፋችን ነው። የፊፋን የክለቦች የዓለም ዋንጫ ካነሣን ዘንድሮ እሢያን ወክሎ የሚሳተፈው ደግሞ የደቡብ ኮሪያው ፖሃንግ-ስቲለርስ ነው። ክለቡ ባለፈው ቅዳሜ ተካሂዶ በነበረው የእሢያ ሻምፒዮና ሊጋ ፍጻሜ ግጥሚያ የሳውዲት አረቢያን ተጠሪ አል-ልቲሃድን 2-1 አሸንፏል።

ወደ አፍሪቃ መለስ እንበልና ናይጄሪያ ውስጥ በሚካሄደው ከ 17 ዓመት በታች ወጣቶች የዓለም እግር ኳስ ዋንጫ ውድድር ሩብ ፍጻሜ ዛሬ ስፓኝ ከኡሩጉዋይ፤ እንዲሁም ደቡብ ኮሪያ ከናይጄሪያ ይጋጠማሉ። ትናንት በተካሄዱት በተቀሩት ግጥሚያዎች ኮሎምቢያ ቱርክን በፍጹም ቅጣት ምት (በፔናልቲ) 5-3 ስትረታ፤ ስዊትዘርላንድ ደግሞ ኢጣሊያን 2-1 አሸንፋለች። ኮሎምቢያና ቱርክ በመደበኛና በተጨማሪ ሰዓት 1-1 ነበር የተለያዩት። ብቸኛዋ የአፍሪቃ ክፍለ-ዓለም ተወካይ አስተናጋጇ ናይጄሪያ በቅርቡ ጋና ከሃያ ዓመት በታች ወጣቶች የዓለም ሻምፒዮን እንደሆነችው ሁሉ ምናልባት ዋንጫውን ታስቀር ይሆን? ከሆነ በደቡብ አፍሪቃው የዓለም ዋንጫ ፍጻሜ ለሚወዳደሩት የአፍሪቃ ቡድኖች በራስ የመተማመን ስሜትን ይበልጥ የሚያጠናክር እንደሚሆን አንድና ሁለት የለውም። የዓለም ዋንጫን ከጠቀስን ከአፍሪቃ እስከ አውሮፓ ወሣኝና የመጨረሻ ማጣሪያ የሆኑት ግጥሚያዎች ከፊታችን ቅዳሜ ጀምሮ ይካሄዳሉ። የተቀሩት ተሳታፊዎች ማንነት ሊለይለት ተቃርቧል ማለት ነው።

የአውሮፓ ሊጋዎች ውድድር

በሣምንቱ የአውሮፓ ቀደምት ሊጋዎች ውድድር በታላቅ ጉጉት የተጠበቀው በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ ውስጥ በቼልሢይና በማንቼስተር ዩናይትድ መካከል የተካሄደው ነበር። ጨዋታው ምንም እንኳ የተጠበቀውን ያህል ባይሆንም ቼልሢይ ጆን ቴሪይ በ 74ው ደቂቃ ላይ በአናት ባስቆጠራት ግብ 1-0 በማሸነፍ አመራሩን በአምሥት ነጥቦች ሊያሰፋ በቅቷል። ቼልሢይ ከትናንቱ ግጥሚያ በኋላ ሰላሣ ነጥቦች ሲኖሩት አምሥት ነጥቦች ወረድ ብሎ በሁለተኝነት የሚከተለው ዎንደረርስን 4-1 የሸኘው የለንደን ተፎካካሪው አርሰናል ነው። እርግጥ አርሰናል ገና አንድ ጨዋታ ይጎለዋል። በሌላ በኩል ማንቼስተር ዩናይትድ በተመሳሳይ ነጥብ ወደ ሶሥተኛው ቦታ ሲያቆለቁል ቶተንሃም-ሆትስፐር ደግሞ ሰንደርላንድን ሁለት-ለባዶ በመርታት በአራተኛ ቦታው እንደጸና ነው። ኤስተን-ቪላ አምሥተኛ፤ ማንቼስተር-ሲቲይ ስድሥተኛ፤ ሊቨርፑል ሰባተኛ በመሆን ይከተላሉ።

በስፓኝ ፕሪሜራ ዲቪዚዮን ላ-ሊጋ ቀደምቱ ክለቦች በሙሉ በማሸነፋቸው ባለፈው ሰንበት በአመራሩ ላይ የተደረገ ለውጥ የለም። ባርሤሎና-ሬያል-ማዮርካ 4-2፤ ሬያል ማድሪድ-አትሌቲኮ 3-2፤ ሤቪያ-ቪላርሬያል 3-1፤ ቫሌንሢያና ሣራጎሣም እንዲሁ 3-1 በሆነ ውጤት ተለያይተዋል። በአጠቃላይ ባርሤሎና በአንዲት ነጥብ ብልጫ መምራቱን ሲቀጥል ሬያል ሁለተኛ ነው፤ ሤቪያ በሶሥተኝነት ይከተላል። ሬያልን ካነሣን አይቀር ኮከብ ተጫዋቹ ክሪስቲያኖ ሮናልዶ ሰሞኑን ከማድሪድ እስከ ሊዝበን መከራከሪያ ጉዳይ ሆኖ ነው የሰነበተው። ለክርክሩ መንስዔ የሆነው ሬያል የፖርቱጋል እግር ኳስ ፌደሬሺን አገሪቱ ከቦስና ጋር ለምታካሂዳቸው ሁለት የዓለም ዋንጫ ማጣሪያ ግጥሚያዎች ሮናልዶን ለማሰለፍ ያለውን ፍላጎት መቃወሙ ነው። ለፖርቱጋል ወሣኝ የሆኑት ግጥሚያዎች የሚካሄዱት በፊታችን ቅዳሜና በተከታዩ ረቡዕ ሲሆን ክለቡ የውድድሩን ክብደት አጢኖ ውሣኔውን ቢያለዝብ ይመረጣል።

ወደ ኢጣሊያ ሤሪያ-አ ሻገር ስንል ደግሞ ኢንተር በገዛ ሜዳው ከሮማ 1-1 ቢለያይም አመራሩን እንደያዘ ቀጥሏል። የሣምንቱ ተጠቃሚ በተለይ የጎል ፌስታ በታየበት ግጥሚያ አታላንታ በርጋሞን 5-2 በማሽነፍ ኢንተርን በአምሥት ነጥቦች የተቃረበው ጁቬንቱስ ነው። ኤ.ሢ.ሚላንም ላሢዮን 2-1 በመርታት ወደ ሶሥተኛው ቦታ ከፍ ብሏል። በውድድሩ ጅማሮ አልበገር ብሎ የነበረው ሣምፕዶሪያ በአንጻሩ ከሣምንት ሣምንት ማቆልቆሉን ቀጥሏል። ቡድኑ ትናንት በካልጋሪ ሁለት-ለባዶ ሲረታ አሁን አምሥተኛ ነው።

በሌላ በኩል የጀርመን ቡንደስሊጋ ውድድር የጠበበ ፉክክር የሰፈነበት እንደሆነ ቀጥሏል። ቀደምቱ ክለቦች በአብዛኛው ግጥሚያቸውን በእኩል-ለእኩል ውጤት ሲፈጽሙ የሁኔታው ተጠቃሚ ሊጋውን የሚመራው ሌቨርኩዝን ብቻ ነበር። ቡድኑ ፍራንክፈርትን 4-0 ሲረታ አመራሩን ከአንድ ወደ ሶሥት ነጥቦች ከፍ ሊያደርግ በቅቷል። ሁለተኛው ከዶርትሙንድ 1-1 የተለያየው ቬርደር-ብሬመን ሲሆን ልዩነቱን ለማጥበብ የነበረውን ዕድል በገዛ ሜዳው ሳይጠቀምበት ቀርቷል። ከሁለተኛው እስከ ስምንተኛው ቦታ ድረስ ያለው የነጥብ ልዩነት ሶሥት ብቻ ሲሆን የዘንድሮው የቡንደስሊጋ ፉክክር እንደጦፈ ይቀጥላል። ለቀደምቱ ሌቭርኩዝን እርግጥ በፊታችን ቅዳሜ ከባየርን ሙንሺን ጋር የሚያካሂደው ግጥሚያ ውጤት አቅጣጫ ጠቋሚ ሊሆን የሚችል ነው። ሌቨርኩዝን እጅግ የሚፈራውን ክለብ በማሸነፍ የአመራር ስክነቱን ማስመስከር ይኖርበታል ወይም በወቅቱ ከሻልከ እኩል-ለእኩል ከተለያየ በኋላ ወደ ስምንተኛ ቦታ ያቆለቆለው ባየርን ግጥሚያውን ከገባበት ቀውስ መላቀቂያ ሊያደርገው ይችላል። ለማንኛውም የሁለቱ ክለቦች ግጥሚያ በመጪው ሣምንት ዋነኛው የቡንደስሊጋ ማተኮሪያ መሆኑ ከወዲሁ የሚታይ ነው። በተረፈ ከብዙ በጥቂቱ ዢሮንዲን-ቦርዶ በፈረንሣይ፤ አይንድሆፈን በኔዘርላንድ፤ ብራጋ በፖርቱጋል፤ እንዲሁም ፓናቴናኢኮስ-አቴን በግሪክና ሩቢን-ካዛን በሩሢያ ከሰንበቱ ግጥሚያዎች በኋላ የየሊጋቸው ቁንጮዎች ናቸው።

አፍሪቃና የኦሎምፒክ መስተንግዶ ተሥፋ

“እ.ጎ.አ. በ 2020 ዓ.ም. የኦሎምፒኩ ተራ የአፍሪቃ ክፍለ-ዓለም ነው” ይህን የሚሉት የደቡብ አፍሪቃ የዓለም አግር ኳስ ዋንጫ ፍጻሜ ውድድር አዘጋጅ ኮሚቴ ዋና ሥራ አስኪያጅ ዳኒይ ጆርዳን ናቸው። የደቡብ አፍሪቃ የዓለም ዋንጫ መስተንግዶ ስኬት ዓለምአቀፉ የኦሎምፒክ ኮሚቴ ጨዋታውን ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ አፍሪቃ እንዲያሻግር ታላቅ ግፊት እንደሚሆን የባለሥልጣኑ ዕምነት ነው። ጆርዳን የብራዚል ከተማ ሪዮ-ዴ-ጃኔይሮ የ 2016-ን ኦሎምፒክ እንድታዘጋጅ መመረጧም ለአፍሪካ በር ከፋች መሆኑ አይቀርም ባይ ናቸው። ሪዮ የኦሎምፒክ ጨዋታ ለማዘጋጀት የተመረጠችው የመጀመሪያዋ የደቡብ አሜሪካ ከተማ ስትሆን በዕውነትም ሁኔታው አፍሪቃ ተረኛዋ ልትሆን ይገባታል የሚያሰኝ ነው። እርግጥ የደቡብ አፍሪቃ የዓለም ዋንጫ መስተንግዶ ስኬት የአፍሪቃን ብቃት ለመመዘን ወሣኝነት ይኖረዋል። ምናልባት ሁለት ወይም ሶሥት ተጎራባች አገሮች ጨዋታውን በጋራ ማዘጋጀታቸው አንዱ አማራጭ ሊሆንም ይችላል። ለጊዜው ግን ሁሉንም ጠብቆ መታዘቡ ግድ ነው።

የጃማይካ ብሄራዊ አትሌቲክስ አሠልጣኝ ግሌን ሚልስ ከ 22 ዓመታት የስኬት ዘመን በኋላ ስንብት ማድረጋቸው በዓለምአቀፍ ደረጃ ትኩረትን ስቧል። ሚልስ ብሄራዊ ቡድኑን የተዉት ዝነኛውን አትሌት ዩሤይን ቦልትንና ክለቡን ለማሰልጠን ተጨማሪ ጊዜ ማግኘት ፈልገው መሆኑን ተናግረዋል። ግን ምክንያታቸው ይህ ብቻ አይደለም። የጃማይካን አትሌቲክ ታላቅ ያደረጉት አሰልጣኝ “እንዳማረብኝ ላብቃ” ማለታቸውም አልቀረም። በሚልስ የአሰልጣኝነት ዘመን ከ 1987 ዓ.ም. ወዲህ የጃማይካ ብሄራዊ ቡድን 71 የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮናና 33 የኦሎምፒክ ሜዳሊያዎችን ለማግኘት በቅቷል። ይህ ደግሞ ጃማይካን ለመሰለች ትንሽ አገር ታላቅ ነገር ነው። ግሌን ሚልስን እርግጥ የሚያሰለጥኑት ዩሤይን ቦልት በመቶና ሁለት መቶ ሜትር ያስመዘገባቸው ግሩም ክብረ-ወሰኖችም ይበልጥ ታዋቂ አድርገዋቸዋል። በቀላሉ የሚተኩ አይሆኑም። የጃማይካ አትሌቲክስ ፌደሬሺንም በ 2011 ደቡብ ኮሪያ ውስጥ የሚካሄደው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና እስከሚቃረብ ድረስ አዲስ አሰልጣኝ መሰየሙን ይሳካል ብሎ አይጠብቅም።

በቴኒስ ለማጠቃለል ሰንበቱን ስፓኝ ውስጥ በተካሄደ የቫሌንሢያ-ኤቲፒ የቴኒስ ፍጻሜ ግጥሚያ የብሪታኒያው ኤንዲይ መሪይ የሩሢያውን ሚካሊ ዩዥኒን በለየለት 6-3, 6-2 ውጤት ለማሽነፍ በቅቷል። በዓለም የቴኒስ ማዕረግ ተዋረድ ላይ አራተኛው ለሆነው የብሪታኒያ ኮከብ ይህ በጠቅላላው 14ኛው የፍጻሜ ድል መሆኑ ነው። ስዊትዘርላንድ-ባዝል ላይ ደግሞ ኖቫክ ጆኮቪች የዓለም አንደኛውን ሮጀር ፌደረርን በአዳራሽ ውስጥ ግጥሚያ 2-1 በሆነ ውጤት በማሸነፍ ብዙዎችን አስደንቋል። ፌደረር ባዝል ውስጥ ያለፉት ሶሥት ዓመታት አሸናፊ ነበር። ስለዚህም በተለይ በአገሩ መሽነፉ እጅግ ሳይቆጨው አይቀርም። ሆኖም ግን የኖቫክ አጨዋወት እጅግ ጠንካራ እንደነበር መስክሮለታል። ድክመትን አምኖ መቀበል የጥሩ ስፖርተኛ ባህርይ ነው፤ ሊወደስ ይገባዋል።

MM/RTR/AA