የስፖርት ዘገባ | ስፖርት | DW | 19.10.2009
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ስፖርት

የስፖርት ዘገባ

ደቡብ አፍሪቃ ውስጥ ለሚካሄደው የዓለም አግር ኳስ ዋንጫ ፍጻሜ ውድድር ለመድረስ ሲካሄድ የቆየው ማጣሪያ ሊጠናቀቅ እየተቃረበ ነው። በሣምንቱ አጋማሽ በዓለም ዙሪያ ተካሂደው በነበሩት በአብዛኛው ወሣኝ የሆኑ ግጥሚያዎች ተጨማሪ አምሥት አገሮች ማለፋቸውን ሲያረጋግጡ በጠቅላላው ከወዲሁ ለተሳትፎ የበቁት አገሮች ቁጥር ከ 19 ወደ 23 ከፍ ብሏል።

default

ደቡብ አፍሪቃ ውስጥ በሚካሄደው የዓለም እግር ኳስ ዋንጫ ፍጻሜ ውድድር ተሳታፊ ከሚሆኑት 32 አገሮች የ 23ቱ ማንነት፤ የአብዛኞቹ ቀደም ብሎ፤ የተወሰኑትም ባለፈው ሣምንት አጋማሽ ላይ ለይቶለታል። የተቀሩትን ዘጠኝ ቦታዎች የሚይዙት አገሮችም እስከፊታችን ሕዳር ወር ድረስ ይታወቃሉ። ደቡብ አፍሪቃ ውስጥ በስምንት ምድቦች ተከፍሎ በሚጀምረው የፍጻሜ ውድድር ማን ከማን እንደሚገናኝ ዕጣ የሚወጣውም በተከታዩ ታሕሣስ ወር ነው። የዓለም ዋንጫ ፍጻሜ በአፍሪቃ ምድር የሚካሄደው ለመጀመሪያ ጊዜ ሲሆን ታላላቅ ከሚባሉት አገሮች መካከል ለምሳሌ ፈረንሣይን የመሳሰሉት ተከታይ ማጣሪያ ማድረግ ስላለባቸው በዚህ ታሪካዊ ትዕይንት ላይ መሳተፋቸው ገና እርግጠኛ አይደለም። ታላላቅ የሚባሉትን ካነሣን አርጄንቲናም በደቡብ አሜሪካ ምድብ ለጥቂት ነው ከውርደት የተረፈችው።

በአውሮፓ ማጣሪያ ዴንማርክ፣ ጀርመን፣ ስፓኝ፣ እንግሊዝ፣ ሰርቢያና ኢጣሊያ፤ እንዲሁም ኔዘርላንድ፣ ስዊድንና ስሎቫኪያ የየምድባቸው አንደኞች በመሆን በቀጥታ ያለፉት ዘጠኝ አገሮች ናቸው። ውድድሩን በሁለተኝነት ከፈጸሙት ስምንት አገሮች መካከል አራቱ ደግሞ የተቀሩትን የመቀላቀል ዕድል ሲኖራቸው በተጨማሪ ግጥሚያ መለየት ይኖርባቸዋል። በዚሁ የደርሶ መልስ ግጥሚያ በመጪው ወር የመጨረሻ ዕድላቸውን የሚሞክሩት አገሮች ፖርቱጋል፣ ግሪክ፣ ቦስና፣ ኡክራኒያ፣ ፈረንሣይ፣ አየርላንድ፥ ሩሢያና ስሎቬኒያ ናቸው። በደቡብ አፍሪቃው ፍጻሜ ውድድር በጠቅላላው 13 የአውሮፓ አገሮች ተሳታፊ ይሆናሉ ማለት ነው። በነገራችን ላይ በቀድሞይቱ ዩጎዝላቪያ ከሰርቢያ ማለፍ ሌላ የቦስናና የስሎቬኒያም ለፍጻሜ መቃረብ ታላቅ ብሄራዊ ስሜትን መቀስቀሱ አልቀረም። የቦስና ማለፍ የተለያዩ ማሕበረሰቦች በሚኖሩባት ግዛት አንድነትን የሚያጠነክር እንደሚሆን ሲጠበቅ ስሎቬኒያ ውስጥ ደግሞ ጠቅላይ ሚኒስትር ቦሩት ፓሆር ብሄራዊው ቡድን ለፍጻሜው ካለፈ የተጫዋቾቹን ጫማ ለመጥረግ ቃል ገብተዋል። ስፖርት የአገር-ፍቅርና የብሄራዊ ስሜት መንኮራኩር ሲሆን መታየቱ በጣሙን የሚያስደስት ነው።

በደቡብ አሜሪካ ምድብ ብራዚል፣ ፓራጉዋይና ቺሌ ወደ ፍጻሜው ዙር ማለፋቸውን ቀደም ብለው ሲያረጋግጡ አራተኛዋ አርጄንቲና በሣምንቱ አጋማሽ ኡሩጉዋይን በጠባቡ በማሸነፍ ካልተጠበቀ ከስረት ተርፋለች። የደቡብ አሜሪካ ማጣሪያ ከሃያላኑ የእግር ኳስ አገሮች አንዷ ለሆነችው ለአርጄንቲናና ለአሠልጣኙ ለዲየጎ ማራዶናም ከጅምሩ የቀና አልነበረም። የአርጄንቲና ብሄራዊ ቡድን በቦሊቪያ 6-1፤ በብራዚል 3-1፤ ከዚያም በፓራጉዋይ 1-0 ከተሽነፈ በኋላ የመጨረሻው የሞንቴቪዴዎ ድሉ በመርፌ ቀዳዳ የማለፍን ያህል ነው የሆነው። ማሪዮ ቦላቲ በኡሩጉዋይ ላይ በ 84ኛዋ ደቂቃ ላይ ያስቆጠራት ብቸኛና፤ ምናልባትም ታሪካዊ ግብ የጋውቾዎችን ትንሣዔ ስታበስር የአገሪቱን የኳስ አፍቃሪዎች እንደ ሕጻን ልጅ ነው ያስፈነደቀችው። ያለ ብራዚል ወይም አርጄንቲናና መሰል አገሮች ተሳትፎ የዓለም ዋንጫው ፍጻሜ ግርማ ሞገሱን የሚያጣ በሆነ ነበር።
ለአምሥተኛዋ ለኡሩጉዋይ የሚቀረው ማጽናኛ ከሰሜንና ማዕከላዊ አሜሪካ የኮንካካፍ ምድብ አራተኛ ከኮስታ ሪካ ጋር በመጋጠም ለፍጻሜው ልትደርስ የምትችል መሆኗ ነው። በተቀረ በኮንካካፍ ምድብ ዩ.ኤስ.አሜሪካ፣ ሜክሢኮና ሆንዱራስ በቀጥታ አልፈዋል። በተረፈ ከእሢያ ጃፓንና ሁለቱ ኮሪያዎች ለፍጻሜ ሲደርሱ የኦሺኒያ ቀደምት ተጠሪ የምትሆነው ደግሞ አውስትራሊያ ናት። ከዚህ በተጨማሪ ከኒውዚላንድና ከባሕሬይን አንዱም ወደ ደቡብ አፍሪቃ የማምራት ቀሪ ዕድል ይኖረዋል። በአፍሪቃ ክፍለ-ዓለም ማጣሪያ ከአስተናጋጇ ደቡብ አፍሪቃ ሌላ ጋናና አይቮሪ ኮስት የፍጻሜው ተሳታፊዎች ሲሆኑ የተቀሩት ሶሥት አገሮች ማንነት ገና በሚቀጥሉት ግጥሚያዎች የሚለይለት ነው። አልጄሪያ፣ ግብጽ፣ ካሜሩን፣ ናይጄሪያ ወይም ቱኒዚያ ገና ዕድል አላቸው። ሁሉንም የሚወስነው በፊታችን ሕዳር ወር በምድብ አንድ፣ ሁለትና ሶሥት ውስጥ የሚካሄዱት ግጥሚያዎች ውጤት ነው።

አፍሪቃን ካነሣን አይቀር ጋና ግብጽ ውስጥ በተካሄደው ከሃያ ዓመት በታች ወጣቶች የዓለም ዋንጫ ውድድር የድል ባለቤት ለመሆን መብቃቷ ደቡብ አፍሪቃ ውስጥ የክፍለ-ዓለሚቱን ተሳታፊ አገሮች የድል ተሥፋና ወኔ ሊቀሰቅስ የሚችል ነው። አፍሪቃ ለዚህ ታላቅ ክብር መድረሷን የጋና ወጣት ተጫዋቾች ባለፈው አርብ ፍጻሜ
ግጥሚያ ብራዚልን ለ 120 ደቂቃዎች ገትሮ በመያዝ በአስደናቂ ሁኔታ አሳይተዋል። ጋና ዳኒየል አዶ በ 37ኛው ደቂቃ ላይ የብራዚሉን ተጫዋች አሌክስ ቴክሢየራን ጠልፎ ከሜዳ ቢወጣባትም መደበኛና ተጨማሪውን ጊዜ ባዶ-ለባዶ ለመፈጸም በቅታለች። ጨዋታው የለየለት በፍጹም ቅጣት ምቶች 4-3 ነበር። ውጤቱ ለአፍሪቃ የሞራል ማጠናከሪያ ሲሆን ለብራዚል በአንጻሩ የደቡብ አፍሪቃው መጪ ጉዞ ቀላል ሽርሽር እንደማይሆን ከወዲሁ ማስጠንቀቂያ ነው።

ጂምናስቲክ/ፎርሙላ-አንድ

እንግሊዝ ውስጥ ሲካሄድ የሰነበተው የዓለም ጂምናስቲክ ውድድር በቻይና ልዕልና ሲጠናቀቅ ትናንት ብራዚል-ሣኦ-ፓውሎ ላይ በተካሄደው የፍርሙላ-አንድ አውቶሞቢል እሽቅድድምም የብሪታኒያው ዘዋሪ ጄሰን ባተን የዘንድሮው የዓለም ሻምፒዮን ሊሆን በቅቷል። ሃና ደምሴ በነዚህ ሁለት ጉዳዮች ከለንደን ያጠናቀረችው ዘገባ የሚከተለው ነው።

አትሌቲክስ

በትናንትናው ዕለት ዮርዳኖስ ውስጥ የተካሄደው የአማን ዓለምአቀፍ ማራቶን የኬንያና የኢትዮጵያ አትሌቶች ልዕልና የታየበት ሆኖ አልፏል። 71 ሃገራትን የሚወክሉ ከአሥር ሺህ የሚበልጡ ሯጮች በተሳተፉበት ውድድር በወንዶች ኬንያዊው ዴቪድ ኪፕቱም ሲያሸንፍ ገዛኸን በየነ ከኢትዮጵያ ሁለተኛ ወጥቷል። ሩጫውን በሶሥተኝነት የፈጸመው የኢጣሊያው ተወዳዳሪ ሣኢድ ቡዳሊያ ነበር። በሴቶች ታደለች ጠለላና እታፈራሁ ጌታሁን አንደኛና ሁለተኛ ሲወጡ ኬንያዊቱ ሊሊያን ቸሊሞ ደግሞ ሶሥተኛ ሆናለች። በውድድሩ ግዛው በቀለንና ክሪስቶፈር ሮኖን የመሳሰሉ 25 ዓለምአቀፍ ዕውቅና ያላቸው አትሌቶች ተሳትፈዋል።

በቤይጂንግ ዓለምአቀፍ ማራቶንም በወንዶች የኬንያው ሣሙዔል ሙጎ በ 2 ሰዓት ከ 8 ደቂቃ 20 ሤኮንድ ጊዜ አሸናፊ ሆኗል። ሁለተኛና ሶሥተኛ የወጡትምእንዲሁ የኬንያ አትሌቶች ናቸው። በርጋ በቀለ ከኢትዮጵያ አምሥተኛ! በሴቶች በዚህ ዓመት የበርሊን የዓለም ሻምፒዮና አሸናፊ የነበረችው ቻይናዊቱ ባይ ሹዌ ሶሥት የአገሯን ተወዳዳሪዎች በማስከተል ለድል በቅታለች።

MM /SL