የስፖርት ዘገባ | ስፖርት | DW | 14.10.2009
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ስፖርት

የስፖርት ዘገባ

ደቡብ አፍሪቃ ውስጥ የሚካሄደው የዓለም እግር ኳስ ዋንጫ ፍጻሜ ውድድር ሊከፈት የቀረው ስምንት ወራት ገደማ ነው። ታዲያ በዓለም ዙሪያ እስካሁን ሲደረግ በቆየው ማጣሪያ ውድድር ሰንበቱን በርካታ ወሣኝ ግጥሚያዎች ተካሂደው ነበር።

አንድሬይ አርሻዊንና ሚሻኤል ባላክ

አንድሬይ አርሻዊንና ሚሻኤል ባላክ

እግር ኳስ

ለደቡብ አፍሪቃው የዓለም ዋንጫ ፍጻሜ ውድድር በሚካሄደው ማጣሪያ ማለፋቸውን ያረጋገጡት አገሮች ቁጥር ካለፈው ቅዳሜ ግጥሚያዎች ወዲህ ከ 15 ወደ 19 ከፍ ብሏል። ደቡብ አፍሪቃ እንደ አስተናጋጅ አገር በቀጥታ የተመደበች ሲሆን ኔዘርላንድ፣ እንግሊዝ፣ ስፓኝ፣ ጀርመን፣ ሰርቢያ ዴንማርክና ኢጣሊያ ከአውሮፓ፤ ጋናና አይቮሪ ኮስት ከአፍሪቃ፤ ብራዚል፣ ፓራጉዋይና ቺሌ ከደቡብ አሜሪካ፤ ከሰሜንና ማዕከላዊ አሜሪካ ዩ.ኤስ.አሜሪካና ሜክሢኮ፤ ከእሢያ ጃፓን፣ ሰሜንና ደቡብ ኮሪያ፤ እንዲሁም አውስትራሊያ እስካሁን ለፍጻሜው ያለፉት አገሮች ናቸው።

በደቡብ አሜሪካ ማጣሪያ ምድብ ውስጥ ምንም እንኳ ብራዚል ለፍጻሜ ማለፏን ቀደም ብላ ብታረጋግጥም ትናንት በላፓዝ የ 3,600 ሜትር ከፍታ እስትንፋስ የሚያሳጣ ከባድ የአየር ሁኔታ በቦሊቪያ 2-1 መረታቱ ግድ ሆኖባታል። ለብራዚል ብሄራዊ ቡድን ይሄው ከተከታታይ 19 ድሎች በኋላ የመጀመሪያው ሽንፈት መሆኑ ነበር። ብራዚል ከትናንቱ ግጥሚያ በኋላ ከፓራጉዋይ ጋር እኩል 33 ነጦቦች ቢኖሯትም በጎል ብልጫ በአንደኝነት መምራቷን ቀጥላለች። በተቀሩት የምድቡ ግጥሚያዎች አርጄንቲና ፔሩን 2-1 ስታሸንፍ፤ ኮሎምቢያ ከቺሌ 2-4፤ ኤኩዋዶር ከኡሩጉዋይ 1-2፤ ቬኔዙዌላም እንዲሁ ከፓራጉዋይ በተመሳሳይ 1-2 ውጤት ተለያይተዋል።

በደቡብ አሜሪካው ምድብ የሰንበቱ ዋነኛ አሸናፊ በሶሥተኝነት ለፍጻሜ ማለፏን ያረጋገጠችው ቺሌ ነበረች። ቺሌ በአርጄንቲናዊው ግሩም አሠልጣኟ በማርሤሎ ቢየልሣ አቀናባሪነት በዚህ የዓለም ዋንጫ ማጣሪያ ታላቅ ተሃድሶ ነው ያደረገችው። ሁለት ዓመት በሆነው በቢየልሣ የአሠልጣኝነት ዘመን አርጄንቲናን ለመጀመሪያ ጊዜ ለመርታት በቅታለች። ቺሌ ፐሩ-ሊማ ላይ ከ 24 ዓመታት በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ለድል ስትበቃ ፓራጉዋይ ውስጥም ከ 28 ዓመታት በኋላ እንደገና መርታቷ ታሪክ ነው የሆነው።

የቺሌ የኳስ አፍቃሪዎች በፊታችን ረቡዕ በብሄራዊው ስታዲዮም በሚካሄደው የመጨረሻ ግጥሚያ በተለይም ለድንቅ አሠልጣኛቸው ያላችውን አክብሮትና ምሥጋና በፌስታ ይገልጻሉ። የአገሪቱ ሕዝብ ከደስታው የተነሣ ማርሤሎ ቢየልሣ ምንም እንኳ የአገሪቱ ዜጋ ባይሆኑም ለፕሬዚደንተት ይወዳደራሩ እስከማለትም ደርሷል። የአርጄንቲናው አሠልጣኝ እንዲህ እስከመመለክ ሲደርሱ በዲየጎ ማራዶና የሚመራው የአገራቸው ብሄራዊ ቡድን ግን ገና ከጭንቁ አልተላቀቀም። ለአርጄንቲና ብሄራዊ ቡድን ከነገ በስቲያ ሞንቴቪዴዎ ላይ ከፓራጉዋይ የሚያካሂደው ግጥሚያ በጣሙን ወሣኝ ነው። ለደቡብ አፍሪቃው ፍጻሜ ውድድር በቀጥታ ለማለፍ ቢቀር እኩል ለእኩል መውጣት ይኖርበታል።

በዚህ በአውሮፓ ባለፈው ቅዳሜ በተካሄዱት ማጣሪያ ግጥሚያዎች ደግሞ ጀርመን፣ ዴንማርክ፣ ሰርቢያና ኢጣሊያ በተጨማሪ ለፍጻሜ መድረሳቸውን ሲያረጋግጡ ጠንከር ብለው ከታዩት ግጥሚያዎች አንዱ ሞስኮ ላይ በጀርመንና በሩሢያ መካከል የተካሄደው ነበር። የሩሢያ ብሄራዊ ቡድን በግሩም ጨዋታ ብዙ የጎል ዕድል ቢያገኝም ሳይጠቀምበት ቀርቷል። ለጀርመን በአንጻሩ አጥቂዋ ሚሮስላቭ ክሎዘ በ 35ኛዋ ደቂቃ ላይ ያስቆጠራት ግብ ፈውስ ነው የሆነችው። ቡድኑ ጠንካራ ተጋጣሚውን አሸንፎ የደቡብ አፍሪቃ ቲኬቱን እንዲቆርጥ አምበሉ ሚሻኤል ባላክ እንዳለው በተለይ ዲሲፕሊንና የነርቭ ጥንካሬ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ነበረው።

“ዛሬ በነርቭ ጠንካሮች ነበርን። በራስ መተማመን መንፈስ ከመጀመሪያ አንስቶ በዲሲፕሊን ወደፊት ነው የተጫወትነው። ኋላ በመደርደር አልተወሰንንም። ስለዚህም የፈለግነውን ውጤት ማግኘታችን ተገቢ ነው ብዬ አስባለሁ”

ቡድኑ እርግጥ በተለይ ሁለት ሶሥት ያለቀላቸው የሩሢያ ጎሎችን ያጨናገፈውን በረኛውን ሬኔ አድለርን በጣሙን ሊያመስግን ይገባዋል። ለማንኛውም ጀርመን በምድብ-አራት የዓለም ዋንጫ ፍጻሜ ተሳትፎዋን ስታረጋግጥ ሁለተኛ የሆነችው ሩሢያ በየምድቡ ጠንካራ ሁለተኞች መካከል በሚካሄደው ተከታይ ማጣሪያ ገና የማለፍ ዕድል ይኖራታል።

በተቀሩት ግጥሚያዎች በምድብ-አንድ ውስጥ የማጣሪያው ሂደት ያልቀናት ፖርቱጋል ሁንጋሪያን 3-0 በመርታት ወደ ሁለተኛ ቦታ ከፍ ስትል ቢቀር የተከታይ ማጣሪያ ዕድሏን ለመጠበቅ በቅታለች። በፊታችን ረቡዕ ተጋጣሚዋ ማልታ ስትሆን ከባድ ትግል የሚጠብቃት አይመስልም። ምድብ ሁለት ውስጥ ስዊስ ሉክሰምቡርግን 3-0 በመርታት በ 20 ነጥቦች መምራቷን ስትቀጥል ግሪክም ሊቱዋኒያን 5-2 በማሽነፍ በሁለተኝነት ትከተላለች። በሁለቱ መካከል ያለው ልዩነት የሶሥት ነጥብ ብቻ ሲሆን ማን በአንደኝነት እንደሚያልፍ ገና አልለየለትም።
ከነገ በስቲያ ግሪክ ከሉክሰምቡርግ፤ ስዊስ ከእሥራኤል ይጋጠማሉ። በምድብ-ሶሥት ውስጥ ከተጠበቀው በታች ሆነው የተገኙት ቼክ ሬፑብሊክና ፖላንድ 2-0 ሲለያዩ ለአንደኝነቱ መታገል የያዙት ስሎቫኪያና ስሎቬኒያ ናቸው። በፊታችን ረቡዕ ስሎቫኪያ ፖላንድ ውስጥ የምትጫወት ሲሆን ሣን-ማሪኖን የመሰለ ቀለል ያለ ተጋጣሚ የሚጠብቃት ስሎቬኒያ ናት። እነዚህ አገሮች ለዓለም ዋንጫ ፍጻሜ ካለፉ በታሪካቸው ለመጀመሪያ ጊዜ ነው የሚሆነው።

በምድብ አምሥት ማለፉን ቀደም ብሎ ያረጋገጠው የስፓኝ ብሄራዊ ቡድን አርሜኒያን 2-1 በማሸነፍ እስካሁን ያካሄዳቸውን ግጥሚያዎች በሙሉ በድል ሲፈጽም ስምንት ነጥቦች ወረድ ብላ የምትከተለው ቦስና በሁለተኞች መካከል በሚካሄደው ማጣሪያ አማካይነት ወደ ደቡብ አፍሪቃ ለማምራት ማለሟ እንደቀጠለ ነው። ቦስና ኤስቶኒያን 2-0 ስትረታ የፊታችን ረቡዕ ተጋጣሚዋ ስፓኝ ናት። በምድብ ስድሥት ውስጥ እንግሊዝ በማጣሪያው ሂደት በዘጠኝ ግጥሚያዎች ለመጀመሪያ ጊዜ ልትሽነፍ በቅታለች። ቢሆንም ቀደም ብለው ለፍጻሜ ካለፉት አገሮች አንዷ ናት።
እንግሊዝ ኡክራኒያ ውስጥ 1-0 ስትረታ ውጤቱ እርግጥ አሸናፊውን ቡድን ለሁለተኝነት አብቅቷል። በምድብ-ሰባት ሰርቢያ ከፈረንሣይ ቀድማ ለፍጻሜ አልፋለች። በዚሁ ቀደምት ከሚባሉት አገሮች አንዷ ለሆነችው ፈረንሣይ የሚቀረው በሁለተኛው መንገድ ለማለፍ መታገል ነው። በተቀረ የምድብ-ስምንት ማጣሪያ በኢጣሊያ አንደኝነት፤ የምድብ-ዘጠኝም እንዲሁ በኔዘርላንድ ግንባር ቀደምነት ቀደም ብሎ ተጠናቋል።

በአፍሪቃ የዓለም ዋንጫ ማጣሪያ አይቮሪ ኮስት ከአስተናጋጇ ደቡብ አፍሪቃና ከጋና ቀጥላ ሶሥተኛዋ የፍጻሜ ተሳታፊ ለመሆን በቅታለች። አይቮሪ ኮስት ከማላዊ 1-1 ስትለያይ ቡድኑን የአቻነቷን ጎል በማስቆጠር ለዚህ ያበቃው የቼልሢው ኮከብ ዲዲየር ድሮግባ ነው። የተቀሩት ሶሥት የፍጻሜ ተሳታፊዎች ማንነት ገና አልለየለትም። አልጄሪያ፣ ካሜሩንና ቱኒዚያ በወቅቱ ለፍጻሜ የተቃረቡ የሚመስሉት የየምድባቸው መሪዎች ናቸው።

በሰሜንና ማዕከላዊ አሜሪካ የኮንካካፍ ምድብ ዩ.ኤስ.አሜሪካ ሆንዱራስን 3-2፤ ሜክሢኮም ኤል-ሣልቫዶርን 4-1 በማሽነፍ ለፍጻሜ ደርሰዋል። ኮስታ ሪካ ደግሞ በቀጥታ ለማለፍ የሚያበቃውን ሶሥተኛ ቦታ ስትይዝ ሆንዱራስ ሁለት ነጥቦች ወረድ ብላ አራተኛ ናት። የዚህ ምድብ አራተኛ ለዓለም ዋንጫ ለማለፍ ከደቡብ አሜሪካ አምሥተኛ ጋር መጋጠም ይኖርበታል። ከዚሁ ሌላ የኒውዚላንድና የባሕሬይን አሸናፊም አንዱ የዓለም ዋንጫ ተሳታፊ ነው። ሁለቱ አገሮች በመጀመሪያ ግጥሚያቸው አቻ-ላቻ ሲለያዩ ፉክክሩ በሚቀጥለው ወር ዌሊንግተን ላይ በሚካሄደው የመልስ ግጥሚያ ይለይለታል።

አትሌቲክስ

በትናንትናው ዕለት አሜሪካ ውስጥ በተካሄደው የቺካጎ ማራቶን ውድድር በወንዶች ኬንያዊው የኦሎምፒክ ሻምፒዮን ሣሙዔል ዋንጂሩ ግሩም በሆነ 2 ሰዓት ከ 5 ደቂቃ ከ 41 ሤኮንድ ጊዜ ሲያሸንፍ የሞሮኮው አብደርራሂም ጉምሪ በሁለተኝነት ጣልቃ ከመግባቱ በስተቀር ኬንያውያን አትሌቶች እስከ ሰባተኛው ቦታ ተከታትለው ገብተዋል። ከኢትዮጵያ ታደሰ ቶላ ዘጠነኛ! ዋንጂሩ ምንም እንኳ በአሜሪካ ምድር እስካሁን ፈጣኑን ጊዜ ቢያስመዘግብም የሃይሌ ገ/ሥላሴን የዓለም ክብረ-ወሰን ለመስበር ካለው ሕልም ግን ሊቃረብ አልቻለም። በሴቶች ደግሞ ሩሢያዊቱ ሊሊያ ሾቡኮቫ አሸንፋለች። ሩሢያዊቱ ያሸነፈችው የዚህን ዓመት የለንደን ማራቶን ባለድል ጀርመናዊቱን ኢሪና ሚኪቴንኮን በ 36 ሤኮንዶች በመቅደም ነው። ሌላዋ ሩሢያዊት ሊዲያ ግሪጎሪየቫ ሩጫውን በሶሥተኝነት ስትፈጽም የኢትዮጵያ ተወዳዳሪዎች ጠይባ ኤርኬሶና ብርሃኔ አደሬ ደግሞ አራተኛና አምሥተኛ ሆነዋል።

እንግሊዝ-በርሚንግሃም ላይ ትናንት በተካሄደ የዓለም ግማሽ ማራቶን ሩጫ ውድድር ኤርትራዊው ዘረሰናይ ታደሰ በተከታታይ ለአራተኛ ዓመት አሸናፊ ሆኗል። ኬንያዊው በርናርድ ኪፕየጎ ሁለተኛ ሲወጣ አሜሪካዊው ዳታን ሪዘንሃይም ደግሞ ሶሥተኛ ሆኗል። በቡድን ኬንያ አንደኛ፣ ኤርትራ ሁለተኛ፣ ኢትዮጵያ ሶሥተኛ! በሴቶች ግማሽ ማራቶን ኬንያዊቱ ሜሪይ ካይታኒ የአገሯን ልጅ ፊልስ ኦንጎሪን አስከትላ ስታሸንፍ የኢትዮጵያ ተወዳዳሪዎች አበሩ ከበደ ሶሥተኛ፤ መስታወት ቱፋ አምሥተኛ፤ እንዲሁም ቲርፊ ጸጋዬ ስድሥተኛ ወጥታለች። በቡድን ኬንያ ኢትዮጵያንና ሩሢያን አስከትላ የወርቅ ባለቤት ሆናለች።

ለማጠቃለል ዓለምአቀፉ የኦሎምፒክ ኮሚቴ በሣምንቱ ማብቂያ ላይ ዴንማርክ ውስጥ ባካሄደው 121ኛ ጠቅላይ ጉባዔ ፕሬዚደንቱ ዣክ ሮግን ለተጨማሪ አራት ዓመታት በሥልጣን እንዲቆዩ መልሶ መርጧል። የቤልጂጉ ተወላጅ ከ 93 ድምጽ 88ቱን አግኝተው ሲመረጡ ተፎካካሪ ዕጩ አልነበራቸውም።

MM/DW/AFP/RTR

ነጋሽ መሐመድ