የስፖርት ዘገባ | ስፖርት | DW | 07.09.2009
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ስፖርት

የስፖርት ዘገባ

በዓለምአቀፉ የአትሌቲክስ መድረክ ላይ ከታላላቆቹ አንዱ የሆነው የዘንድሮው ጎልደን ሊግ ውድድር ባለፈው አርብ ምሽት ብራስልስ ላይ ተከናውኗል። የውድድሩን አንድ ሚሊዮን ዶላር ሽልማት ሶሥት አትሌቶች ሲጋሩ ከነዚሁም አንዱ ድንቁ ቀነኒሣ በቀለ ነበር።

default

በእግር ኳስ ደግሞ ደቡብ አፍሪቃ በመጪው 2010 ዓ.ም, የምታስተናግደው የዓለም ዋንጫ ፍጻሜ ውድድር ሊከፈት 270 ቀናት ገደማ ሲቀሩት ማጣሪያውም ወደ ፍጻሜው በመቃረብ ላይ ነው። ሰንበቱን በዓለም ዙሪያ በርካታ በከፊልም ወሣኝ የሆኑ ግጥሚያዎች ተካሂደዋል፤ የያዝነው ሣምንት አጋማሽም ለብዙዎች የሞት-የሽረት መሆኑ አልቀረም።

አስደናቂ ታሪክ ደግሞ ደጋግሞ ማስመዝገብ የታላላቅ አትሌቶችም መለያ ልዩ ባህርይ ነው። ታዲያ ባለፈው ነሐሴ የበርሊን የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮናና ከሁለት ሣምንታት በኋላ ባለፈው አርብ ምሽት ብራስልስ ላይ በተጠቃለለው ጎልደን-ሊግ ውድድር የጃማይካውን የአጭር ርቀት ሩጫ መንኮራኩር የዩሤይን ቦልትንና የቀነኒሣ በቀለን ያህል ይህን ባህርይ በሚገባ ያንጸባረቀ ማንም አልነበረም። ቀነኒሣ በቀለ ከአንድ ዓመት በፊት በቤይጂንግ ኦሎምፒክ የተቀዳጀውን የአምሥትና አሥር ሺህ ሜትር ድርብ ድል በርሊን ላይ ሲደግመው የጎልደን-ሊጉን ስድሥት ውድድሮች ደግሞ በተከታታይ በማሽነፍ አልደፈር እንዳለ ቀጥሏል። በነገራችን ላይ በዓለም አትሌቲክስ ውድድር በሁለቱ ርቀቶች ድርብ ድል በማግኘት ቀነኒሣ የመጀመሪያው ሲሆን ይህም ራሱን የቻለ ታሪክ ነው።

ዘንድሮ የጎልደን-ሊጉን ውድድሮች የአንድ ሚሊዮን ዶላር ሽልማት ከበርሊን እስከ ብራስልስ አከታትሎ ስድሥት ጊዜ በማሸነፍ የተጋሩት አትሌቶች ከቀነኒሣ ሌላ አሜሪካይቱ የ 400 ሜትር የዓለም ሻምፒዮን ሣኒያ ሪቻርድስና ሩሢያዊቱ የምርኩዝ ዝላይ ንግሥት የለና ኢዚምባየቫ ናቸው። የጎልደን ሊጉ ውድድር በስኬት መጠናቀቅ በተለይ ለሩሢያዊቱ አትሌት ታላቅ ትርጉም አለው። ኢዚምባየቫ ከድል ወደ ድል ስትሻገር ከቆየች በኋላ በበርሊኑ የዓለም አትሌቲክስ ውድድር ላይ ከጅምሩ ተሰናክላ በመቅረቷ ካደረባት ሃዘን በጣሙን እንድትጽናና የሚያደርግ ነው። የለና ኢዚምባየቫ በበርሊን ሣምንት ዙሪክ ላይ የራሷን የዓለም ክብረ-ወሰን እንደገና ስታሻሽል ልዕልናዋ በመጪዎቹም ጥቂት ዓመታት ባለበት የሚቀጥል ነው የሚመስለው።

በብራስልሱ ምሽት አጠቃላይ ውጤቶች ላይ በጥቂቱ እናተኩርና በመቶ ሜትር የዓለም ሻምፒዮኑ ጃማይካዊ ዩሤይን ቦልት ባይሳተፍም የአገሩ ልጅ አሣፋ ፓውል ሶሥት አሜሪካውያንን ከኋላው በማስቀረት ግሩም በሆነ 9,90 ሤኮንድ ጊዜ ለማሸነፍ በቅቷል። በሁለት መቶ ሜትር እርግጥ ምሽቱ እንደገና የዩሤይን ቦልት ነበር። ድካም ተሰምቶኛል የሚለው ቦልት ምንም እንኳ የዓለም ክብረ-ወሰኑን ሊደግመውም ሆነ ሊያሻሽለው ባይ’ችልም ሩጫውን የፈጸመው ግሩም በሆነ ጊዜ ነበር። ይህም እስካሁን በዓለም ላይ አራተኛው ፈጣን ጊዜ መሆኑ ነው። አሜሪካዊው ዋላስ ስፒርመን ሁለተኛ ሲወጣ አዜሪው ራሚል ጉሊየቭ ሶሥተኛ ሆኗል። ጨርሶ ያልታወቀው የአዘርባይጃን አትሌት ለዚህ ክብር መብቃቱ ብዙዎችን ሳያስገርም አልቀረም።

በ 400 መቶ ሜትር ሩጫ አሜሪካዊው ጀረሚይ ዋሪነር በተለመደ ጥንካሬው ለድል ሲበቃ በ 800 መቶ ሜትር ደግሞ ኬንያዊው ዴቪድ ሩዲሻ የአገሩን ልጅ አልፍሬድ የጎን በማስከተል አሸናፊ ሆኗል። ቀነኒሣ በቀለ የጎልደን ሊግ ድሉን ባበሰረበት በ 5000 ሜትር ሩጫ የኢትዮጵያ አትሌቶች ድል እጥፍ ድርብ ነበር። ኢማነ መርጋ ሁለተኛ ሲወጣ አሊ አብዶሽም አራተኛ ሆኗል። ጠንካሮቹ የኬንያ አትሌቶች ከሶሥተኝነት የማለፍ ዕድል አልነበራቸውም። በሌላ በኩል ኬንያውያኑ በወንዶች 1,500 እና ሶሥት ሺህ ሜትር ሩጫ የተለመደ ልዕልናቸውን ሲያሳዩ በሴቶች ሁለት ሺህ ሜትር ግን ድሉ የገለቴ ቡርቃ ነበር። ኢትዮጵያዊቱ አትሌት ያሸነፈችው ቪቪያን ቼሩዮትንና ሜርሢይ ቼሮኖን የመሳሰሉትን ጠንካራ የኬንያ አትሌቶች በመቅደም ነው። አዳጊዋ ኮከብ ለመሆኗ አንድና ሁለት የለውም።

በተረፈ ብራስልስ ላይ የተካሄደው ጎልደን ሊግ የአትሌቲክስ ውድድር በ 12 ዓመት ታሪኩ የመጨረሻው መሆኑ ነበር። በዓለምአቀፉ የአትሌቲክስ ፌደሬሺኖች ማሕበር ውሣኔ መሠረት ውድድሩ ከፊታችን 2010 ዓ.ም. አንስቶ 14 ተከታታይ ዝግጅቶች በሚካሄዱበት ዲያመንድ ሊግ ይተካል። አከታትሎ ለሚያሸንፈው አትሌት የሚሰጠው ሽልማትም 80 ሺህ ዶላር የሚያወጣ አልማዝ ነው የሚሆነው። ከሃይሌ ገብረ ሥላሴ እስከ ቀነኒሣ በቀለ ለኢትዮጵያ አትሌቶችም ስኬታማ ከነበረው የጎልደን ሊግ ዘመን በዚሁ ስንሰናበት ትናንት በኢጣሊያ-ሪየቲም ዓለምአቀፍ የአትሌቲክስ ውድድር ተካሂዶ ነበር።

በውድድሩ ከሁሉም በላይ ትኩረትን የሳበው በ 800 ሜትር ሩጫ የዓመቱን የዓለም ፈጣን ጊዜ በማስመዝገብ ያሸነፈው የሃያ ዓመቱ ወጣት ኬንያዊ ዴቪድ-ሌኩታ-ሩዲሻ ነው። ሩዲሻ ሁለት ቀናት ቀደም ሲል ብራስልስ ላይም ለተመሳሳይ ድል ሲበቃ መጪው ጠንካራ አትሌት መሆኑን አስመስክሯል። በተቀረ በ 1,500 እና በሶሥት ሺህ ሜትርም ኬንያውያን ሲያሸንፉ በኋለኛው ሩጫ አብርሃም ጨርቆስ አራተኛ ሆኗል።

እግር ኳስ

ደቡብ አፍሪቃ ውስጥ በፊታችን 2010 ዓ.ም. ለሚደረገው የዓለም እግር ኳስ ዋንጫ ፍጻሜ ውድድር በዓለም ዙሪያ የሚካሄደው ማጣሪያ ሊለይለት እየተቃረበ ነው። ሰንበቱን በዓለም ዙሪያ በርከት ያሉ ጨዋታዎች ሲካሄዱ በዚህ ሣምንት አጋማሽ ላይም የሚቀጥሉት የየምድቡ ግጥሚያዎችም በአብዛኛው ወሣኝነት አላቸው። ዝርዝር ውስጥ ከመግባታችን በፊት ያለፈውና የመጪው የዓለም ዋንጫ ፍጻሜ ውድድር አዘጋጆች ጀርመንና ደቡብ አፍሪቃ ባለፈው ቅዳሜ በዚህ በሌቨርኩዝን ባካሄዱት የወዳጅነት ግጥሚያ እንጀምርና ጨዋታው በአስተናጋጇ አገር አሸናፊነት 2-0 ነበር የተፈጸመው።

ግጥሚያው የወዳጅነት ይሁን እንጂ በሁለቱም ቡድኖች ዘንድ የብቃት መፈተሻና የክብር ጉዳይ ሆኖ በመታየቱ ጨዋታው ቸልተኝነት የታየበት አልነበረም። ሆኖም ባለፈው ኮንፌደሬሺን ዋንጫ ውድድር ጆሃንስበርግ ላይ ብራዚልን ያህል ሃያል ተጋጣሚ አንገዳግዶ የነበረው የደቡብ አፍሪቃ ብሄራዊ ቡድን የተጠበቀው ጥንካሬ አልታየበትም። በአንጻሩ የጀርመን ተጫዋቾች በፊታችን ረቡዕ ከአዘርባይጃን፤ ቆየት ብሎም ከሩሢያ ጋር ለሚጠብቃቸው የዓለም ዋንጫ ማጣሪያ ከባድ ግጥሚያ የመንፈስ ጥንካሬ ለማዳበር ችለዋል።

ምሽቱ ከሁሉም በላይ ደግሞ የሃያ ዓመቱ ወጣት አከፋፋይ ቱርካዊ-ጀርመን የሜሱት ኡዚል የኮከብነት ትንሣዔ የተከሰተበት ነበር። በፈጠራ ችሎታ የተካነው ወጣት የቡድኑ መንኮራኩር በመሆን የመጀመሪያውን ግብ ሲያዘጋጅ ሁለተኛውንም ራሱ በማስቆጠር የድል ዋስትና ሆኗል። ለማንኛውም የደቡብ አፍሪቃ ብሄራዊ ቡድን ነገ ዳብሊን ውስጥ ከአየርላንድ ጋር ተከታይ የወዳጅነት ግጥሚያ በማድረግ ጠቃሚ ሊሆን የሚችል ልምድ መቅሰሙን ይቀጥላል።

በዚሁ ወደ ዓለም ዋንጫ ማጣሪያው እንሻገርና በአውሮፓ በዘጠኝ ምድቦች ተከፍሎ በሚካሄደው ውድድር እስካሁን አንዴም ሳትሽነፍ ማለፏን ያረጋገጠችው የመጨረሻውን ምድብ በልዕልና የምትመራው ኔዘርላንድ ብቻ ናት። ቀደምት ከሚባሉት ከተቀሩት አገሮች መካከል ምናልባት ፈረንሣይና በተለይም ፖርቱጋል ተሰናክለው እንዳይቀሩ የሚያሰጋ ነው። ፖርቱጋል ዴንማርክ አመራሩን በያዘችበት ምድብ-አንድ ውስጥ በወቅቱ አራተኛ ናት። ሮናልዶን በመሰለው የዓለም ኮከብ የሚመራው የፖርቱጋል ቡድን ሰንበቱን ኮፐንሃገን ላይ ከዴንማርክ ጋር ባካሄደው ግጥሚያ ከ 1-1 ውጤት ሊያልፍ አልቻለም። በፊታችን ረቡዕ ከሁንጋሪያ የሚገናኝ ሲሆን ሣምንቱ መሰናበቻው እንዳይሆን በጣሙን ነው የሚያሰጋው።

የአውሮፓው ሻምፒዮን ስፓኝ ቤልጂግን 5-0 ሲቀጣ ሰባት ግጥሚያዎቹን በሙሉ በማሸነፍ ምድብ-አምሥትን በልዕልና መምራቱን ቀጥሏል። ስፓኝ በዚሁ ሣምንት ኤስቶኒያን ከረታች ለፍጻሜ ማለፏን ከወዲሁ ማረጋገጥ ትችላለች። ቦስና አርሜኒያን በመርታት የምድቡ ሁለተኛ ናት። በምድብ-ስድሥት እንግሊዝ በሙሉ ነጥብ በአንደኝነት ትመራለች። ክሮኤሺያ እንደ ቦስና ሁሉ የምትታገለው ለሁለተኛው ስፍራ ነው። በፊታችን ሩቡዕ ሁለቱም ቡድኖች ከባድ ትግል ይጠብቃቸዋል። ቦስና ከቱርክ፤ ክሮኤሺያ ደግሞ ከእንግሊዝ ነው የሚጋጠሙት።
ሰርቢያና ኢጣሊያ ደግሞ ምድብ ሰባትና ስምንትን በመምራት በስኬት አቅጣጫ እንደቀጠሉ ናቸው። ኢጣሊያ ጆርጂያን 2-0 ስትረታ የሚያስገርም ሆኖ ሁለቱን ግቦች በራሱ ቡድን ላይ ያስቆጠረው የኤ.ሢ.ሚላን ኮከብ ካላድሤ ነበር። ለመሆኑ ምን ተሰምቶት ይሆን? ሁኔታው በቅርቡ ከህሊናው መሰወሩ ያጠራጥራል። የሆነው ሆነ ከነገ በስቲያ ሰርቢያ ከፈረንሣይ፤ ኢጣሊያም ከቡልጋሪያ በየምድባቸው ብርቱ ግጥሚያዎች ነው የሚጠብቋቸው።

በደቡብ አሜሪካ ማጣሪያ ምድብ የአምሥት ጊዜዋ የዓለም ዋንጫ ባለበት ብራዚል አርጄንቲናን 3-1 በማሸነፍ ለፍጻሜ ማለፏን ከወዲሁ አረጋግጣለች። ካካ በግሩም ጨዋታ ከሊዮኔል ሜሢ ልቆ ሲታይ ጎሎቹን ያስቆጠሩት ሉዊሳዎና ፋቢያኖ ነበሩ። በተቀሩት የምድቡ ግጥሚያዎች ኮሉምቢያ ኤኮዋዶርን 2-0፤ ፔሩ ኡሩጉዋይን 1-0፤ ፓራጉዋይ ቦሊቪያንም እንዲሁ 1-0 ሲያሸንፉ ቺሌና ቬኔዙዌላ ደግሞ አቻ-ለአቻ 2-2 ተለያተዋል። የአርጄንቲና ቡድን በአገር ውስጥ በዚህ መጠን መሸነፍ አሠልጣኙ ማራዶና ይባረር የሚል የብዙ ተመልካቾችን ጥሪ ነው ያስነሣው።
ለማንኛውም ከሰንበቱ ግጥሚያዎች በኋላ ብራዚል ምድቡን በ 30 ነጥቦች ትመራለች። ቺሌና ፓራጉዋይ ሶሥት ነጥቦች ወረድ ብለው ሁለተኛና ሶሥተኛ ሲሆኑ አርጄንቲና አምሥት ነጥቦች ዝቅ ብላ አራተኛ ናት። ሆኖም ኮሉምቢያና ኤኩዋዶር በቅርብ ይከተሏታል። ከደቡብ አሜሪካ ምድብ ለፍጻሜ በቅጥታ የሚያልፉት አራት አገሮች ሲሆኑ አምሥተኛው ከሰሜንና ማዕከላዊ አሜሪካ የኮንካካፍ ምድብ አራተኛ ጋር መጋጠም ይኖርበታል። በነገራችን ላይ የኮሉምቢያን ብሄራዊ ቡድን ድል ለማክበር አገሪቱ ሁለተኛ ከተማ ሜዴይን ውስጥ በአደባባይ በተሰበሰቡ የኳስ አፍቃሪዎች መሃል በጋየ ፈንጂ አንድ ሰው ሲሞት ቢያንስ ሰላሣ ቆስለዋል። ምክንያቱ ምን እንደሆነ ለጊዜው አልታወቀም።

ወደ አፍሪቃ አለፍ እንበልና በአፍሪቃ ማጣሪያ ምድብ አራት ውስጥ ጋና ሱዳንን 2-0 በመርታት የማይደረስባት ሆና ከወዲሁ ለዓለም ዋንጫው ፍጻሜ አልፋለች። በተቀሩት የሰንበቱ ግጥሚያዎች ቶጎ-ሞሮኮ 1-1፤ ናይጄሪያ-ቱኒዚያ 2-2፤ ሞዛምቢክ-ኬንያ 1-0፤ አልጄሪያ-ዛምቢያ 1-0፤ ቤኒን-ማሊ 1-1፤ ጋቡን-ካሜሩን 0-2፤ ሩዋንዳ-ግብጽ 0-1 ተለያይተዋል። በምድብ-አንድ ጋቡን አንደኛ ስትሆን ካሜሩንና ሞሮኮ ሶሥተኛና አራተኛ ናቸው። ምድብ-ሁለት ውስጥ አንደኛ ቱኒዚያ፤ ሁለተኛ ናይጄሪያ! ምድብ-ሶሥትን አልጄሪያና ግብጽ ይመራሉ። የምድብ ስድሥት ቁንጮ ደግሞ አይቮሪ ኮስት ናት። ለዓለም ዋንጫው ፍጻሜ የሚያልፉት ስድሥቱ የምድብ አሸናፊዎች ብቻ ናቸው።

በኮንካካፍ፤ የሰሜንና ማዕከላዊ አሜሪካ ምድብ ሜክሢኮ ኮስታሪካን 3-0፤ ሆንዱራስ ትሪኒዳድና ቶባጎን 4-1፤ ዩናይትድ ስቴትስ ደግሞ ኤል-ሣልቫዶርን 2-1 አሸንፈዋል። ምድቡን ሆንዱራስና ዩናይትድ ስቴትስ ይመራሉ፤ ሜክሢኮ በአንዲት ነጥብ ልዩነት ሶሥተኛ ናት።

/AFP/RTR/dpa

መስፍን መኮንን ፣ሂሩት መለሰ