የስፖርት ዘገባ | ስፖርት | DW | 17.08.2009
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ስፖርት

የስፖርት ዘገባ

በርሊን ላይ በሚካሄደው የዓለም አትሌቲክስ ውድድር በተለይ የትናንቱ ምሽት እጅግ አስደናቂ ውጤት የተመዘገበበት ሆኖ አልፏል። ጃማይካዊው ድንቅ አትሌት ኡሴይን ቦልት ከቤይጂንግ ኦሎምፒክ በኋላ የራሱን የአንድ መቶ ሜትር የዓለም ክብረ-ወሰን በ 11 መቶኛ ሤኮንድ ሲያሻሽል ሩጫውን የፈጸመው ተዓምር በሚያሰኝ ፍጥነት ነበር።

ሰብዓዊው መንኮራኩር ቦልት

ሰብዓዊው መንኮራኩር ቦልት

በርሊን ላይ የሚካሄደው የዓለም አትሌቲክስ ውድድር ባለፈው ቅዳሜ ሲጀምር በተለይ ለኢትዮጵያ ሴት አትሌቶች ብዙም የቀና አልነበረም። ቀደም እንዳለው ጊዜ ሁሉ አስተማማኝ ድል የተጠበቀበት የአሥር ሺህ ሜትር ሩጫ እንደታሰበው ሳይሆን ቀርቷል። በተለይም የቀድሞዋ ሻምፒዮን የጥሩነሽ ዲባባ በአካል ጉዳት የተነሣ በውድድሩ አለመሳተፍ እጅግ ብዙ ነው ያጎደለው። ለወትሮው የተለመደው ፍጥነት በጎደለው ሩጫ በመጨረሻ ተጠቃሚ የሆነችው ኬንያዊቱ አትሌት ሊኔት ማሣይ ነበረች።

የ 19 ዓመቷ ወጣት በመጨረሻዎቹ ዕርምጃዎች ቀድማ ስታሸንፍ መሰለች መልካሙ ሁለተኛ፤ እንዲሁም ውዴ አያሌው ሶሥተኛ በመሆን ሩጫውን ፈጽመዋል። ጠንከር ካለ ቡድን ጋር ስትመራ የቆየችው መሠረት ደፋርም በመጨረሻው መቶ ሜትር ላይ በመዳከም ሩጫውን በአምሥተኝነት ፈጽማለች። የኢትዮጵያ አትሌቶች ውጤት እርግጥ የማይናቅ ቢሆንም ድሉ በመነጠቁ ቅሬታ ወይም ቁጭት መፈጠሩ አልቀረም። ለኬንያ በአንጻሩ ድሉ ከ 12 ዓመታት በኋላ የመጀመሪያው በመሆኑ ደስታው ወሰን አላገኘም። በተረፈ መሠረት ደፋር በዕለቱ ሩጫ በደረሰባት ጉዳት የተነሣ ሃያል በሆነችበት በአምሥት ሺህ ሜትር መሳተፏ ለጊዜው አጠያያቂ ሆኗል።
የኢትዮጵያና የኬንያ አትሌቶች ፉክክር ዛሬ ማምሻውንና ሣምንቱንም የሚቀጥል ነው። በመክፈቻው ዕለት በተካሄዱ ሌሎች ውድድሮች ሩሢያዊው የኦሎምፒክ የወርቅ ሜዳይ ተሸላሚ ቫሌሪይ ባርቺን በሃያ ኪሎሜትር የመሄድ ውድድር በማሸነፍ ድሉን በዓለም ሻምፒዮናው ላይ ደግሞታል። አሜሪካዊው ክሪስ ካንትዌል ደግሞ በአሎሎ ውርወራ 22,03 ሜትር በማስመዝገብ በቶማሽ ማዬቭስኪ ደርሶበት የነበረውን የኦሎምፒክ ሽንፈት አካክሷል። የመክፈቻው ዕለት በርካታ የማጣሪያ ውድድሮችም የተካሄዱበት ነበር። ፍጻሜያቸው በታላቅ ጉጉት ይጠበቃል።

በሌላ በኩል የበርሊኑ የዓለም አትሌቲክስ ውድድር ገና እስከፊታችን ዕሑድ የሚዘልቅና ብዙ ድንቅ ውጤቶች የሚታዩበት ቢሆንም በተለይ በትናንቱ ምሽት ልዩ የመቶ ሜትር ክብረ-ወሰን የተነሣ ከወዲሁ የማይረሳ ታሪክ ነው ያስመዘገበው። ጃማይካዊው ኡሤይን ቦልት ከአንድ ዓመት በፊት በቤይጂንግ ኦሎምፒክ ላይ ያስመዘገበውን ፈጣን ጊዜ በመሻር ሊያስቡት በሚያዳግት ፍጥነት የአዲስ የዓለም ክብረ-ወሰን ባለቤት ለመሆን በቅቷል። በሰዓት አርባ ኪሎሜትር ያህል ፍጥነት የሚከንፈው አትሌት በፍጥነቱ የተሽከርካሪን ያህል እየሆነ መሄዱ እንደገና ብዙዎችን ሳያስገርም አልቀረም። የ 22 ዓመቱ ቦልት ለወርቅ ሜዳሊያ ያበቃውን ሩጫ የፈጸመው 9,58 ሤኮንድ በሆነች ጊዜ ነው። አንዳንድ የቀድሞ ሻምፒዮኖች ትናንት አብረውት ቢሮጡ ኖሮ ሁለትና ሶሥት ሜትር ከኋላው በቀሩ ነበር። አሜሪካዊው ታይሰን ጌይ በ 9,71 ሁለተኛ ሲሆን ሌላው ጃማይካዊ አሳፋ ፓውል ደግሞ በ 9,84 ሤኮንድ የናስ ሜዳሊያ ተሸላሚ ሆኗል።

በዕለቱ በተካሄዱት በተቀሩት ውድድሮች በሴቶች የሃያ ኪሎሜትር መሄድ ሩሢያዊቱ ኦልጋ ካኒስኪና ስታሸንፍ ኦሊቭ ላፍኔም ከአየርላንድ ሁለተኛ፤ እንዲሁም ሆንግ ሊዩ ከቻይና ሶስተኛ ሆናለች። ምሽቱን በተጠናቀቀው የሴቶች አሎሎ ውርወራ የወርቅ ሜዳሊያው ድል የኒውዚላንዷ ተወላጅ የቫሌሪይ ቪሊ ነበር። የአስተናጋጇ አገር አትሌት ናዲን ክላይነርትና የቻይናዋ ተወዳዳሪ ጎንግ ሊጂያዎ ደግሞ ሁለተኛና ሶሥተኛ በመሆን የብርና የናስ ሜዳሊያ ተሸላሚ ሆነዋል። በቅይጥ የሰባት ዲሲፕሊኖች ውድድር የብሪታኒያ ጄሲካ ኤኒስ በ 6731 ነጥቦች የወርቅ ሜዳሊያ ባለቤት ስትሆን ጀርመናዊቱ ጄኒፈር ኡዘር ሁለተኛ፤ የፖላንዷ ካሚላ ቹጂክም ሶሥተኛ ወጥታለች።

በዛሬው ምሽትም የተለያዩ የፍጻሜ ውድድሮች የሚካሄዱ ሲሆን በተለይ በኢትዮጵያውያን ዘንድና በመላው ዓለም በከፍተኛ ጉጉት የሚጠበቀው ታላቁ የወንዶች የአሥር ሺህ ሜትር ሩጫ ነው። ቀነኒሣ በቀለ ሴት አትሌቶቻችን ባለፈው ቅዳሜ ያጡትን የወርቅ ድል ዕውን እንደሚያደርግ ብዙም አያጠያይቅም። በምሽቱ ከዚሁ ሌላ የምርኩዝ ዝላይ፣ የ 1,500 ሜትር፣ የ 3000 ሜትር መሰናክልና የመቶ ሜትር ፍጻሜ ሩጫዎችም ይካሄዳሉ። እስካሁን በተካሄዱት ውድድሮች በሜዳሊያ ብዛት ሩሢያ በሁለት ወርቅ የምትመራ ሲሆን አሜሪካ በአንድ ወርቅና በአንድ ብር ሁለተኛ፤ እንዲሁም ጃሜይካ በአንድ ወርቅና በአንድ ናስ ሶሥተኛ ናቸው። ኬንያ በአንድ ወርቅ አምሥተኛ ስትሆን ኢትዮጵያ ደግሞ በአንድ ብርና በአንድ ናስ ዘጠነኛ ናት።

ከበርሊን ሌላ ኒውዮርክ ውስጥ ትናንት በተካሄደ የግማሽ ማራቶን ሩጫ ውድድር የብሪታኒያዋ አትሌት ፓውላ ሬድክሊፍ አንድ ሰዓት ከዘጠኝ ደቂቃ ከ 45 ሤኮንድ በሆነ ጊዜ አሸናፊ ለመሆን በቅታለች። ሬድክሊፍ በትናንቱ ውድድር የተሳተፈችው የዘጠኝ ወራት ቆይታ ካደረገች በኋላ ነው። ማሚቱ ዳስካ ከኢትዮጵያ ሁለተኛ ስትወጣ ኬንያዊቱ ካትሪን እንዴሬባ ደግሞ ሩጫውን በሶሥተኝነት ፈጽማለች። ሬድክሊፍ ወደ በርሊኑ የዓለም ሻምፒዮና የምታመራ ሲሆን በማራቶን ሩጫ መሳተፏን የምትወስነው ሰሞኑን ሁኔታዋን ካጤነች በኋላ ነው። የበርሊኑ የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ሰሞኑን አልፎ አልፎ የምንመለስበት ጉዳይ ይሆናል።

እግር ኳስ

በአውሮፓ ቀደምት ሊጋዎች ውስጥ ሰንበቱን የወቅቱ ውድድር ወቅት ሁለተኛ ግጥሚያዎች ተካሂደዋል። በዚህ በጀርመን ቡንደስሊጋ ያለፈው ሻምፒዮን ቮልፍስቡርግ ሁለተኛ ግጥሚያውንም በማሸነፍ ከሻልከ ጋር አመራሩን ሲይዝ በአንጻሩ ባየርን ሙንሺን እንደገና በእኩል ለእኩል ውጤት በመወሰን ለጊዜው 11ኛ ነው። ቀደምቱ ሻልከ ቦሑምን 3-0 ሲረታ ቮልፍስቡርግ ደግሞ ኮሎኝን 3-1 አሸንፏል። በአንጻሩ ባየርን በገዛ ሜዳው ከብሬመን 1-1 በሆነ ውጤት መወሰኑ ግድ ሆኖበታል። በተቀረ ሌቨርኩዝን ሁፈንሃይምን 1-0፤ ሃምቡርግ ዶርትሙንድን 4-1፤ ሽቱትጋርት ፍራይቡርግን 4-2፤ መንሸን ግላድባህ በርሊንን 2-1 ሲያሸንፉ ፍራንክፉርትና ኑርንበርግ፤ እንዲሁም ሃኖቨርና ማይንስ ደግሞ አቻ ለአቻ ተለያይተዋል።

በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ ሰንበቱ የዘንድሮው ውድድር ሃ-ብሎ የተጀመረበት ነበር። ባለፈው ቅዳሜና ትናንት ዕሑድ በተካሄዱት ግጥሚያዎች ማንቼስተር ዩናይትድ በርሚንግሃም ሢቲይን 1-0 ሲረታ ቼልሢይ ሃል-ሢቲይን 2-1፤ አርሰናል ደግሞ ኤቨርተንን 6-1 ሸኝቷል። በተቀረ ዊጋን አትሌቲክ ኤስተን ቪላ 2-0፤ ሰንደርላንድ ወንደረርስ 1-0፤ ማንቼስተር ሢቲይ ሮቨርስ 2-0፤ ፉልሃም ፖርትማውዝ 1-0!

በፈረንሣይ አንደኛ ዲቪዚዮን ናንሢይና ቦርዶው ሁለተኛ ግጥሚያቸውንም በድል በመወጣት ሊጋውን በስድሥት ነጥብ ይመራሉ። ቀደምቱ ክለቦች ፓሪስ ሣን ጀርማን፣ ኦላምፒክ ሊዮንና ኦላምፒክ ማርሤይ በአንጻሩ በመጀመሪያው ግጥሚያ ማሽነፍ ባለመቻላቸው በወቅቱ አራተኛ፣ ሰባተኛና ስምንተኛ ናቸው። በኔዘርላንድ ሊጋ ውስጥ ሰንበቱን ሶሥተኛ ግጥሚያዎች ሲደረጉ ኤንሼዴ፣ ፋየኖርድ፣ ኡትሬኽትና ብሬዳ በሰባት ነጥቦች በቀደምትነት ይመራሉ። የሰንበቱ ግጥሚያዎች የጎል ፌስታም ያጀባቸው ነበሩ። ያለፈው ውድድር ወቅት ሻምፒዮን አልክማር ቫልቪይክን 6-0 ሲያሰናብት አይንድሆፈን ደግሞ አያክስ አምስተርዳምን 4-3 አሸንፏል። አልክማር፣ አምስተርዳምና አይንድሆፈን ከሰንበቱ ግጥሚያ ወዲህ አምስተኛ፣ ስድሥተኛና ሰባተኛ ናቸው።

በስፓኝ ሱፐር-ካፕ ግጥሚያ የፕሪሜራ ዲቪዚዮኑ ሻምፒዮን ባርሤሎና ትናንት አትሌቲክ ቢልባዎን 2-1 በማሸነፍ ብሄራዊ ልዕልናውን እንደገና አስመስክሯል። ባርሣ ለድል የበቃው አንድ ለባዶ ከተመራ በኋላ በሣቪና በፔድሮ አማካይነት ሁለቱን ጎሎች በማስቆጠር ነው። በኢጣሊያ ሊጋ ደግሞ ሰንበቱ ያለፈው በብሄራዊ ዋንጫ የሶሥተኛ ዙር ማጣሪያ ግጥሚያዎች ነበር። በተቀረ በፖርቱጋል ሊጋ ያለፈው ሻምፒዮን ፖርቶ በዘንድሮው ውድድር መክፈቻ ከፓኮስ-ዴ-ፌሬይራ በአንድ ለአንድ ውጤት በመወሰን ጅማሮው ሳይሰምርለት ቀርቷል።

ከአውሮፓ ውጭ በአፍሪቃ የሻምፒዮና ሊጋ የምድብ ግጥሚያዎች የሱዳኑ አል ማሬይክና የዛምቢያ ዜስኮ ዩናይትድ 2-3 ሲለያዩ፤ የሱዳን አል ሂላል የናይጄሪያን ካኖ ፒላርስ 2-0፤ የሬፑብሊክ ኮንጎ ማዜምቤ የዚምባብዌን ሞኖማታፓ 5-0፤ የናይጄሪያ ኸርትላንድ የቱኒዚያን ኤቶል ሣሄል 3-0 አሸንፈዋል። ከትናንቱ ግጥሚያ ወዲህ አል ሂላል ምድብ አንድን ይመራል፤ በምድብ ሁለት ውስጥ ደግሞ ቀደምቱ ማዜምቤ ነው። በላቲን አሜሪካ በብራዚል አንደኛ ዲቪዚዮን ውስጥ ደግሞ ፓልሜይራስ ከ 19 ግጥሚያዎች በኋላ ቀደምቱን ቦታ ይዞ በሻምፒዮንነት አቅጣጫ ማምራቱን እንደቀጠለ ነው።

ቴኒስ

የብሪታኒያው ኤንዲይ መሪይ ትናንት ሞንትሬያል ላይ በተካሄደ የማስተርስ ፍጻሜ ግጥሚያ የአርጄንቲና ተጋጣሚውን ሁዋን-ማርቲን-ዴል-ፖርቶን ሁለት ለአንድ በሆነ ውጤት አሸንፏል። መሪይ በዚሁ ድል በዓለም የቴኒስ ማዕረግ ተዋረድ ላይ የስፓኙን ኮከብ ራፋኤል ናዳልን በሁለተኛ ቦታ ለመተካት በቅቷል። በሢንሢናቲ ኦፕን ደግሞ የሰርቢያዋ ተወላጅ የለና ያንኮቪች በዓለም ላይ አንደኛ የሆነችውን ሩሢያዊት ዲናራ ሣፊናን በሁለት ምግብ ጨዋታ በማሸነፍ በማዕረጉ ተዋረድ ላይ ወደ አራተኛው ቦታ ከፍ ለማለች በቅታለች።

MM/AA/RTR/AFP