የስፖርት ዘገባ | ስፖርት | DW | 20.07.2009
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ስፖርት

የስፖርት ዘገባ

ከቀነኒሳ አንስቶ እስከ ቱር ደ ፍሯንስ፣ ከዴቪድ ቤካም እስከ እንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ፤ በርካታ አሳዛኝ፣ አስገራሚ፣ አጓጊና አዝናኝ ክስተቶችን የሣምንቱ መጨረሻ አስተናግዷል። የስፖርት ዘገባ ዳሰሳ ያደርግበታል።

default

አንድ ሚሊዮን ዶላሩ ይሳካለት ይሆን?

ጤና ይስጥልኝ አድማጮች እንደምን ውላችኋል?

በዛሬው የስፖርት ዘገባችን፤ ብስክሌት፣ አትሌቲክስና እግር ኳስ ነክ ዜናዎችን ይዘናል። ዘንድሮ ቱር ደ ፍሯንስ የብስክሌት ውድድር በርካታ አስገራሚ ነገሮችን አስተናግዷል። አሳዛኝ ሁኔታም ተከስቶበታል። ሁለት ታዳጊ ወጣቶች ከዛፎች ስር ተከልለው በቤት ውስጥ በተሰራ መሳሪያ ተኩሰው ሁለት የብስክሌት ተወዳዳሪዎችን በቀላሉ አቁስለዋል። አንዲት የስድሳ አንድ ዓመት አንጋፋ ውድድሩን ሲከታታሉ በፖሊስ ሞተር ተገጭተው ህይወታቸውን አጥተዋል። የቱር ደ ፍሯንስ ውድድር የምንግዜውም ዝነኛ አርምስትሮንግ ተሸንፏል። ሌሎች ስፖርታዊ ክንውኖችንም አካተናል።

ቀነኒሳ፤ አንድ ሚሊዮን ዶላር...?

በፓሪሱ የጎልደን ሊግ ውድድር የሶስት ሺህ ሜትር ሩጫ ውድድር አሽናፊው ቀነኒሳ በቀለ የአንድ ሚሊዮን ዶላር ሽልማቱን ለማፈስ ከሚገሰግሱት አራት ምርጦች መካከል አንዱ መሆኑ ተገለፀ። በጎልደን ሊግ ውድድር በተደጋጋሚ ድል በማድረግ የአንድ ሚሊዮን ዶላር ሽልማቱን ለመጠቅለል እየተቃረቡ ካሉት ሶስት ሴት አትሌቶች መካከል፤ ቀነኒሳ ብቸኛው ወንድ እንደሆነም ታውቋል። ከተፋላሚዎቹ ብርቅዬ አትሌቶች መካከል፤ በከፍታ ምርኩዝ ዝላይ አቻ የለሽነቷን ያስመሰከረችው ሩሲያዊቷ ዬሌና ኢዚንባዬቫ፣ በአራት መቶ ሜትር የዱላ ቅብብል ታዋቂ አሜሪካዊቷ ሳንያ ሪቻርድስ እና በአንድ መቶ ሜትር ፈጣን የሩጫ እሽቅድምድም እንደቀስት ተስፈንጣሪ ጃማይካዊቷ ኬሮን ስቴዋርት ይገኙበታል። ኢትዮጵያዊው ጀግና አትሌት ቀነኒሳ በቀለ የአንድ ሚሊዮን ዶላር ሽልማቱን የማሸነፍ ከፍተኛ ተስፋ እንዳለውም ከወዲሁ ተገምቷል።


የጎልደን ሊግ ሽልማትን ለማግኘት ተወዳዳሪ አትሌቶች በስድስት የተለያዩ ፉክክሮች ማሸነፍ ይጠበቅባቸዋል። አለበለዚያ ደግሞ የአምስት ጊዜ አሽናፊ አምስት መቶ ሺህ ዶላር ተሸላሚ ይሆናል፤ ወይንም አምስት መቶ ሺህዉን ይካፈላል ማለት ነው። ዘንድሮ በፓሪሱ የጎልደን ሊግ ቀነኒሳ የታወቀበት የአምስት ሺህና አስር ሺህ የሩጫ ውድድር ባይኖርም፤ አርብ ለት ጀግናው ቀነኒሳ በሶስት ሺህ ሜትር የሩጫ ውድድርም አይበገሬ ነኝ ብሏል።

በትንቅንቁ ቀነኒሳ አሜሪካዊው የኬንያ ተወላጅን ነበር የረታው። እስካሁን አራት ውድድሮች በርሊን፣ ኦስሎ፣ ሮምና ፓሪስ ከተሞች ውስጥ መከናወናቸው ይታወቃል። ቀጣይ ውድድሮች የፊታችን ነሐሴ ሃያ ሁለት በስዊዘርላንድ ዙሪክ፣ ነሐሴ ሃያ ዘጠኝ ደግሞ በቤልጂየም ብራስልስ ከተሞች ላይ የሚከናወኑ ይሆናል። ከዚያም መስከረም ሲጠባ ግሪክ ቴሳሎኒኪ ላይ አንድ ሚሊዮን ዶላሩን ማን ጠቅልሎ እንደሚወስደው ይለያል። መስከረም ሁለት እና ሶስት ላይ የአደይ አበባ ፍካት ለጀግናው አትሌት ቀነኒሳ በቀለም ታላቅ ተስፋ እንደሚያጭር እምነታችን ነው።

አጫጭር ስፖርታዊ ዘገባዎች

ማንቸስተር ዩናይትድ ዛሬ በጃካርታ ሊያካሂድ የነበረውን ግጥሚያ ቡድኑ ሊያርፍበት በነበረው ሆቴል በተከሰተ ፍንዳታ ምክንያት መሰረዙ ተገለፀ።

ቶጎዋዊው የአርሰናሉ ኢማኑኤል አደባዮር ለማንቸስተር ሲቲ የአምስት አመት ኮንትራት መፈረሙ ታወቀ።

ብራዚሊያዊው አጥቂ ሪካርዶ ኦሊቬራ ከሪያል ቤቲስ ወደ አልጀዚራ ክለብ በውዝውውር መፈረሙ ተነገረ። የኢሚሬቱ ክለብ ለኦሊቬራ ከደረጃው ዝቅ ያለ ሊሆንበት እንደሚችልም ኦሊቬራ ሳይገልፅ አላለፈም።

ዴቪድ ቤካም ቼልሲ ላይ አይኑን ሳያሳርፍ እንዳልቀረም እየተነገረ ነው።
ቱር ደ ፍሯንስ ላይ የተከሰቱ አስገራሚ ነገሮችም በዝርዝር ይቀርባሉ አሁንም አብራችሁን ቆዩ።

ማንቸስተር ዩናይትድ በእስያ እያካሄደ ያለውን የእግር ኳስ ግጥሚያ ቀጥሎ ትናንት የማሌዢያ ማሌዢያ አስራ አንድን ሶስት ለሁለት መርታቱ ታወቀ። ሆኖም ማንቸስተር ከኢንዶኔዢያው ኦል ስታር አስራ አንድ ጋር ሊያካሂድ የነበረውን የሰኞ ግጥሚያ በአርብ ለቱ የሆቴል ፍንዳታ ምክንያት መሰረዙን አዣንስ ፍራንስ ፕሬስ ዘግቧል። ፍንዳታው የተከናወነው ማንቸስተር ዩናይትድ ሊያርፍበት በነበረው ሆቴል እንደሆነም ታውቋል። በሪትዝ ካርልቶን እና ማሪዮት ሆቴሎች በተከሰቱ የቦንብ ፍንዳታዎች ቢያንስ ዘጠኝ ሰዎች እንደተገደሉ ተዘግቧል። ፍንዳታውን ተከትሎ ማንቸስተር ዩናይትድ በኢንዶኔዢያ ጃካርታ እንደማይጫወት መግለፁን አስመልክቶ የኢንዶኔዢያ መንግስት ቃል አቀባይ ውሳኔው ተገቢ አይደለም ሲሉ ተችተዋል።

የተሳሳተ መልዕክትና ውሳኔ ሊሆን ይችላል። እንደማስበው ይህ የወዳጅነት ጨዋታ ነው። እናም የወዳጅነት ምልከታ ሊሆን የሚችለው ማንቸስተር ዩናይትድ በኢንዶኔዤያ መልካምና መጥፎ አጋጣሚዎች ሁሉ አብሮ ሲሆን ነው። ማንቸስተር ዩናይትድ በርካታ የእግር ኳስ ውድድሮችን አሸንፏል፣ በእግር ኳስ ዓለሙም ተሳክቶለታል። ሆኖም ግን በነዚያ ሁሉ ድሎቻቸው በደህናውም በአስቸጋሪውም ወቅት ወደ ኢንዶኔዢያ መምጣታቸው ለደጋፊዎቻቸው ታላቅ መነቃቃት፤ በታሪክ ደግሞ ለዘመናት ሲታሰብ የሚቆይ ይሆን ነበር።

ቃል አቀባዩ ያን ቢሉም፤ ማንቸስተር የኢንዶኔዢያ የዛሬ ግጥሚያውን ሰርዞ በምትኩ ትናንት ከማሌዢያው ማሌዢያ አስራ አንድ ጋር ተጋጥሟል። ሰማንያ አምስት ሺህ ተመልካች በታደመበት ስታዲየም ማንቸስተር ዩናይትድ ማሌዢያ አስራ አንድን ሶስት ለሁለት አሰንፏል። በዕለቱ ለጃካርታው ጨዋታ የስታዲየም መግቢያ ቲኬት ገዝተው ለነበሩ ሶስት ሺህ ተመልካቾች በማሌዢያ መቀመጫ ተይዞላቸው እንደነበረም ተገልጿል። ማንቸስተር ዩናይትድ በእስያ የማፍታቺያ ግጥሚያው የፊታችን አርብ ወደ ደቡብ ኮሪያ ቅዳሜ ደግሞ ቻይና እንደሚያቀናም ታውቋል።


ቶጎዋዊው የአርሰናሉ አጥቂ ኢማኑኤል አደባዮር ከአርሰናል ወደ ማንቸስተር ሲቲ መዘዋወሩ እርግጥ ሆነ። የቶጎ ብሔራዊ ቡድን ተሰላፊው አደባዮር በሃያ ዘጠኝ ሚሊዮን ዩሮ ለማንቸስተር ሲቲ ለአምስት ዓመት የፈረመው ቅዳሜ ለት መሆኑንም የጀርመን ዜና አገልግሎት ድርጅት ዘግቧል። ለማንቸስተር ሲቲ በደጋፊው ፊት እስክጫወት ድረስ ጨንቆኛል ሲል አደባዮር ለጋዜጠኞች ገልጿል።

በሌላ የሰሞኑ የዝውውር ዜና ደግሞ፤ ብራዚሊያዊው አጥቂ ሪካርዶ ኦሊቬራ ለአቡዳቢው አልጀዚራ ቡድን መፈረሙ ታውቋል። ኦሊቬራ ለአልጀዚራ የፈረመው ከሪያል ቤቲስ በአስራ አራት ሚሊዮን ዩሮ የዝውውር ክፍያ እንደሆነም ተነግሯል። በብራዚል አስራ አንድ ዋንጫዎችን ያገኘው ኦሊቬራ የኢሚሬቱ ሊግ ስፔን ከነበረው የእግር ኳስ ስልት በደረጃው አነስ ሊል እንደሚችል አልሸሸገም። ሆኖም ግን፤ የቀረበለትን ጥቅም እሱም ሆነ ቤተሰቡ በቀላሉ ሊተዉት የማይችሉት እንደሆነ መግለፁን አዣንስ ፍራንፕሬስ ዘግቧል። የአልጀዚራ ቡድን በነዳጅ ሀብት በበለፀገችው አቡዳቢ ባለፀጋ የሆኑት የእንግሊዙ ማንቸስተር ሲቲ ቡድን ባለቤት ሼክ ማንሱር ቤን ዛይድ ንብረት እንደሆነ ይታወቃል።

ዴቪድ ቤካም ወደ ቸልሲ...?!

እንግሊዛዊው ዴቪድ ቤካም ቸልሲን በፕሪዬም ሊጉ ለድል ማን ሊያበቃው እንደሚችል ገለፀ። ያለምንም ጥርጥር የቸልሲው አሰልጣኝ ካርሎ አንቼሎቲ ዋንጫውን ወደ ስታምፎርድ ብሪጅ ያመጡታል ሲልም አስታውቋል። ቸልሲ የፕሪሚየር ሊጉ የቅርብ ጊዜ ድሉ የዛሬ አራትና ሶስት ዓመት በተከታታይ በሞሪንሆ ፊታውራሪነት እንደነበረ ይታወቃል። ሆኖም ቀጥለው በተተኩት አሰልጣኞች፤ ማለትም አቭራም ግራንት፣ ሉዊዝ ፌሊፔ ስኮላሪ እና ጉስ ሒዲክ ቡድኑ ዋንጫ ማንሳት ተስኖት ቆይቷል። እንደ ዴቪድ ቤካም ገለፃ ከሆነ ግን አሁን ባሉት አሰልጣኝ አንቼሎቲ ቸልሲ የፕሪሚየር ሊጉን ዋንጫ ማንሳቱ የማያጠራጥር ነው። «ቸልሲ ሲበዛ እድለኛ ነው። ምክንያቱም ካርሎ ታላቅ ሰው፣ ታላቅ አሰልጣኝ ነውና» ሲል ቤካም ተናግሯል። አክሎም «ካርሎ በስራውና በእግር ኳስ ጥበቡ ቆፍጣና ሲሆን፤ የዚያን ያህል ደግሞ ሲበዛ አዝናኝ ነው። መጨናነቅ አያውቅም። ቀልድ ከማወቁም መሬት ነው» ሲል ካርሎ አንቼሎቲን አወድሷል።

የቀድሞው የማንቸስተር ዩናይትድ ተጫዋች ዴቪድ ቤካም ባለፈው የውድድር ዘመን በሳንሲሮ ቆይታው በአሰልጣኝ ካርሎ አንቼሎቲ ስር መሰልጠኑ ይታወቃል። በተያያዘ ዜና ዴቪድ ቤካም ቸልሲን ለመቀላቀል ጠጋ ጠጋ እያለ እንደሆነም ተገልጿል። በዩናይትድ ስቴትሱ ሎስ አንጀለስ ጋላክሲ ቡድን ውስጥ ያለው የሰላሳ አራት ዓመቱ ቤካም ላይ ቶትናም ሆትስፐርና ቸልሲ አይናቸውን እናዳሳረፉበት እየተነገረ ነው። ዴቪድ ቤካም ለደቡብ አፍሪቃው የዓለም ዋንጫ የእንግሊዝ ብሔራዊ ቡድን ተሰላፊ መሆን እንደሚፈልግ፤ ለዚያ ደግሞ በእንግሊዝ ክለቦች ውስጥ መጫወቱ ወሳኝነት እንዳለው በቅሩ መግለፁ ይታወቃል። ለዚያም ይመስላል ብዙዎች ቤካም የቸልሲውን አሰልጣኝ ማወደሱ ጠጋ ጠጋ የማለት ነው ሲሉ የሚደመጡት። በዚህም አለ በዚያ ቤካም« አንቼሎቲ ቸልሲን ባለድል ለማድረግ ምንም አይሳነውም። ለዚያ ምንም ጥርጥር የለኝም። ይህንንም የምለው ብዙዎች እንደሚያውቁት ማንቸስተር ዩናይትድን ምንግዜም በልቤ ብይዝም ነው» ብሏል።

ቱር ደ ፍሯንስ

በቱር ደ ፍሯንስ የብስኪሌት ውድድር ስፔናዊው አልቤርቶ ኮንታዶር የዓለማችን ምርጥ ብስክሌተኛ መሆኑን ባስመሰከረ ሁናቴ እሁድ ለት አሸናፊ ሆነ። ዋነኛ ተፎካካሪው ላንስ አርምስትሮንግ ለኮንታዶር ብቃት እጅ መስጠቱን አመነ። «አሁን በዓለማችን ብቃት ያለው ብስክሌተኛ ማን እንደሆነ ታውቋል። ባለፉት ጊዜያት ምርጡ እኔ ነበርኩ፤ አሁን ግን ተራው የሱ ሆኗል» ሲል እሁድ አስራ አምስተኛውን የዙር ውድድር ስፔናዊው ማሸነፉን ተከትሎ አርምስትሮንግ ለጋዜጠኞች ገልጿል።

በእሁዱ የብስኪሌት እሽቅድምድም አልቤርቶ ኮንታዶር በአምስት ሰዓት ከዜሮ ሶስት ደቂቃ ከሃምሳ ስምንት ሰኮንድ አንደኛ ሲወጣ፤ አንዲ ሽሌክ ሁለተኛ፣ ቪንቼንዞ ኒባሊ ሶስተኛ ወጥተዋል። በዚህ ውድድር ጀርመናዊው አንድሪያስ ክሎይደን ስምንተኛ መውጣቱም ታውቋል። ታዋቂው ብስኪሌተኛ ላንስ አርምስትሮንግ ጀርመናዊውን ተከትሎ በዘጠነኛነት አጠናቋል።

እስካሁን በተደረጉት አጠቃላይ የዙር ውድድሮች ስፔናዊው አልቤርቶ ኮንታዶር በስልሳ ሶስት ሰዓት ከአስራ ሰባት ደቂቃ ከአምሳ ስድስት ሰከንድ በአንደኛነት ሲመራ፤ አሜሪካዊው ላንስ አርምስትሮንግ በአንድ ደቂቃ ከሰላሳ ሰባት ሰከንድ ልዩነት ይከተላል። እንግሊዛዊው ብራድሌይ ዊጊንስ ደግሞ እንዲሁ በስምንት ሰከንድ ልዩነት አርምስትሮንግ ጫፍ ላይ ደርሶ ያዝኩህ እያለው ነው።


ከዚሁ ከቱር ደ ፍሯንስ የብስኪሌት እሽቅድምድም ሳንወጣ፤ በአስራሶስተኛው ዙር ውድድር ወቅት አርብ ሁለት ታዳጊዎች ከዛፎች ስር ተከልለው ሁለት ተወዳዳሪዎችን ተኩሰው በቀላሉ ማቁሰላቸውም ተዘግቧል። ታዳጊዎቹ ጥቃቱን ፈፀሙ የተባለው ቤት ውስጥ በሚሰራና በእምቅ አየር በሚተኮስ መሳሪያ እንደሆነም ተዘግቧል። ተጠርጣሪ ታዳጊዎቹ በአስራ ስድስትና አስራ ሰባት ዓመት እድሜ ክልል ውስጥ እንደሚገኙ ታውቋል።
በተኩሱ ቀላል ጉዳት የደረሰባቸው ብስኪሌተኞች፤ ስፔናዊው ኦስካር ፍራይረ እና ኒው ዚላንዳዊው ጁሊያን ዲን ሲሆኑ፤ ኦስካር ቀኝ ታፋውን ሲመታ፣ ጁሊያን ደግሞ ተኩሱ አመልካች ጣቱን አግኝቶታል። ኦስካር ለቢቢሲ እንደገለፅው ድርጊቱን የፈጸመበት እብድ መሆን እንዳለበት ተናግሯል።


ይሄ እብድ ሰው መሆን አለበት። ሁል ጊዜ እንደዚህ ይሆናል ብዬ አላስብም። በርግጥ አንዳንድ ጊዜ መንገዱን በሚሻገሩና እየተከተሉን በሚሮጡ ሰዎች የተነሳ ችግር ሊያጋጥመን እንደሚችል ቢሰማንም፤ ይኜኛው ግን የተልየ ነው። ይሄ ያበደ ሰው ይመስለኛል።

ጥቃቱ ቢፈፀምባቸውም ሁለቱም ብስኪሌተኞች ውድድራቸውን ማጠናቀቃቸውን ሮይተር ዘግቧል። ታዳጊዎቹን ለመያዝ የፈረንሳይ ፖሊስ ክትትል እያደረገ መሆኑም ታውቋል። ወጣቶቹ ከተያዙና ጥፋተኛነታቸው ከተረጋገጠ፤ ሆን ብሎ ሰው ላይ መሳሪያ የመተኮስ ጥፋት በመፈፅም በሚል ክስ የሶስት ዓመታት እስራትና የአርባ አምስት ሺህ ዩሮ ቅጣት ይጠብቃቸዋል።

በአስራሶስተኛው ዙር የቱር ደ ፍሯንስ የብስኪሌት ውድድር የታዳጊዎቹ ጥቃት እንደተሰማ፤ በበነጋታው ቅዳሜ ለት በተከናወነው አስራ አራተኛው ዙር ውድድር አንዲት የስልሳ አንድ ዓመት አንጋፋ ውድድሩን ሲከታተሉ መገደላቸው ደግሞ የጀርመን ዜና አገልግሎት ዘግቧል። እንደ አይን ምስክሮች ከሆነ ሴትዮዋ ለህልፈት የተዳረጉት ዊቴልሻይም በተባለ ከተማ ውስጥ መንገድ ሲሻገሩ ነው። እንደ ፍራንስ ኢንፎ ራዲዮ ደግሞ የስልሳ አንድ ዓመቷ መንገደኛን የገጨው የፖሊስ ሞተር ብስኪሌት ተንሸራቶ አንድ በእድሜ ጠና ያሉ ሰውና የሰላሳ ሰባት ዓመት ሴትን አቁስሏል። ቆየት ብሎ በወጡ ዘገባዎች ሞተር ብስኪሌቱ ሌሎች ሶስት ሴቶችንም መግጨቱ ታውቋል። ቱር ደ ፍሯንስ የብስኪሌት እሽቅድምድም የፊታችን የቱር ደ ፍሯንስ አጠቃላይ የዙር ውድድር የፊታችን ሐምሌ አስራ ዘጠኝ ፓሪስ ከተማ ውስጥ ይጠናቀቃል።

ማንተጋፍቶት ስለሺ