የስፖርት ዘገባ | ስፖርት | DW | 13.07.2009
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ስፖርት

የስፖርት ዘገባ

ባለፈው ሣምንት ማብቂያ ላይ የዘንድሮው የአትሌቲክስ ጎልደን-ሊግ ሶሥተኛ ዙር ውድድር ሮማ ላይ ተካሂዷል። በዚሁ በስድሥት ደረጃ በሚካሄደው ውድድር ቀነኒሣ በቀለ የአንድ ሚሊዮን ዶላር ሽልማት ለማግኘት ዕድላቸውን እንደጠበቁ ካሉት አራት አትሌቶች አንዱ ሆኖ እንደቀጠለ ነው።

ክሪስቲያኖ ሮናልዶ በቤራቤው ስታዲዮም

ክሪስቲያኖ ሮናልዶ በቤራቤው ስታዲዮም

ለጥቅል አሸናፊው አንድ ሚሊዮን ዶላር ሽልማት በተመደበለት በዘንድሮው ጎልደን-ሊግ ውድድር ሶሥተኛው ባለፈው አርብ ምሽት ሮማ ላይ ተካሂዶ ነበር። በዚሁ ውድድር ከተገኙት ግሩም ውጤቶች አንዱና ምናልባትም ዋነኛው አሜሪካዊው ታይሰን ጌይ በአንድ መቶ ሜትር ያስመዘገበው ነው። ከሁለት ዓመታት በፊት የዓለም ሻምፒዮን የነበረው ጌይ መቶ ሜትሩን በ 9,77 ሤኮንድ ሲፈጽም የዓመቱን ፈጣን ጊዜ በመሮጥ ነው ያሸነፈው።
ድሉ በፊታችን ነሐሴ ወር በርሊን ላይ በሚካሄደው የዓለም አትሌቲክስ ውድድር የዓለምና የኦሎምፒክ ሻምፒዮኑ ጃማይካዊ ኡሤይን ቦልት ቀላል ፉክክር እንደማይጠብቀው ማስጠንቀቂያ ሣይሆን አልቀረም። ቦልት ቀደም ሲል ደርሶበት ከነበረ የአካል ጉዳት ለማገገም ሲል በጎልደን-ሊጉ ውድድር እንደማይሳተፍ የሚታወቅ ነው። ይሄው ውድድር ሊጠናቀቅ ገና ሶሥት ዙር የሚቀረው ሲሆን ዘንድሮ ስድሥቱንም ውድድሮች በማሸነፍ ማነው ለአንድ ሚሊዮን ዶላሩ ሽልማት የሚበቃው? ይህ ጥያቄ በአትሌቲክሱ መድረክ ላይ በወቅቱ ብዙ እያነጋገረ ያለ ጉዳይ ነው።

እስካሁን በበርሊን፣ በኦስሎና በሮማ በተካሄዱት ሶሥት ውድድሮች አራት አትሌቶች በሁሉም አሸናፊ በመሆን የመሸለም ዕድላቸውን እንደጠበቁ ቀጥለዋል። እነዚሁም በአምሥት ሺህ ሜትር ቀነኒሣ በቀለ፣ ጃማይካዊቱ የመቶ ሜትር ሯጭ ኬረን ስቱዋርት፣ በአራት መቶ ሜትር አሜሪካዊቱ ሣኒያ ሪቻርድስና የምርኩዝ ዝላይ ኮከቧ ሩሢያዊት የለና ኢዚምባየቫ ናቸው። በሮማው ውድድር እርግጥ ሌሎቸ በርከት ያሉ ድንቅ ውጤቶችም ተመዝግበዋል።

በወንዶች አራት መቶ ሜትር የባሃማስ ተወላጅ ክሪስቶፈር ብራውን ሲያሸንፍ በስምንት መቶ ሜትር ኬንያዊው አልፍሬድ የጎ ፈጣኑ ነበር። በ 1,500 ሜትር ሩጫም እንዲሁ ድሉ የኬንያ ነበር። አስቤል ኪፕሮፕ አሸንፏል። በአምሥት ሺህ ሜትር ቀነኒሣ በቀለ ሶሥት ኬንያውንን ከኋላው አስቀርቶ ሲያሽንፍ የተቀሩት የኢትዮጵያ ተወዳዳሪዎች በካና ዳባ አምሥተኛ፣ ኢማን መርጋ ስድሥተኛ፤ እንዲሁም ዲኖ ሰፈር 12ኛና አሊ አብዶሽ 14ኛ ሆነዋል። በሴቶች ስምንት መቶ ሜትር አሜሪካዊቱ ሜጊ ቬሤይ አንደኛ ስትወጣ በ 1,500 ሜትር ያሸነፈችው ደግሞ የባሕሬይኗ ማሪያም-ዩሱፍ-ጀማል ነበረች።
ከኢትዮጵያ ተወዳዳሪዎች መካከል ቃል ኪዳን ገዛኸኝ ሰባተኛ፤ መስከረም ለገሰ 12ኛ! በሶሥት ሺህ ሜትር መሰናክል ሩሢያዊቱ ጉልናራ ሣሚቶቫ ስታሸንፍ ሶፊያ አሰፋ ሶሥተኛ፣ መቅደስ በቀለ አሥረኛና ዘርዘም አሕመድ ደግሞ 17ኛ በመሆን ሩጫውን ፈጽመዋል። የሮማው የጎልደን-ሊግ ውድድር ውጤት ከሞላ-ጎደል ይህን የመሰለ ነበር። የተቀሩት የየመቱ ጎልደን-ሊግ ውድድሮች በሚቀጥሉት ሣምንታት ውስጥ በፓሪስ፤ በዙሪክና በብራስልስ ይካሄዳሉ።

ባለፈው ሣምንት ስዊትዘርላንድ ውስጥም የሉዛን ግራንድ-ፕሪ ውድድር ተካሂዶ ነበር። በዚሁ ውድድር የኢትዮጵያ አትሌቶች ጥሩ ውጤት ለማስመዝገብ በቅተዋል። በሶሥት ሺህ ሜትር ሩጫ ደረሰ መኮንን አራት ኬንያውንን ቀድሞ ሲያሸንፍ ስምኦን ተሥፋዬ 13ኛ ወጥቷል። በሴቶች 1,500 ሜትር ደግሞ ገለቴ ቡርቃ ግሩም በሆነ ጊዜ ለድል በቅታለች።

የፖርቱጋሉ ብሄራዊ ቡድን ተጫዋች ክሪስቲያኖ ሮናልዶ በቅርቡ ከመቶ ሚሊዮን ዶላር በሚበልጥ ገንዘብ በመሸጥ ወይም በመገዛት በዓለም ላይ ውዱ የእግር ኳስ ተጫዋች ለመሆን መብቃቱ ይታወሣል። ታዲያ አንድ ተጫዋች ይህን ያህል ገንዘብ ማውጣቱ ተገቢ ይሆን? ጉዳዩ ብዙዎችን የማስደነቁን ያህል ማከራከሩም አልቀረም። ለመሆኑ ሮናልዶ ማነው? ከየት ተነስቶ ነው ለዚህ ለዛሬው ክብር የበቃው? የዕድገት ታሪኩን በአጭሩ ለመዳሰስ ያህል ክሪስቲያኖ-ሮናልዶ-ዶሽ-ሣንቶሽ-አቬይሮ እ,ጎ.አ. የካቲት 5 ቀን. 1985 ዓ.ም. ተወለደ። ወላጆቹ ከአንድ ፖርቱጋላዊ በማይጠበቅ ሁኔታ ከአራት አንዱ የሆነውን ልጃቸውን በአርባኛው የአሜሪካ ፕሬዚደንት በሮናልድ ሬገን ስም ሊሰይሙት ይወስናሉ። ምናልባት የወደፊት ታላቅነቱ ታይቷቸው ይሆን?

ለማንኛውም የክሪስቲያኖ ሮናልዶ የኳስ ፍቅር ገና በሶሥት ዓመት ጨቅላ ዕድሜው ይጀምራል። ከሚወዳት ኳስ ጋር የመጀመሪያ ንኪኪ ያደረገውም በዚያን ጊዜ ነበር። በስድሥት ዓመቱ አንደኛ ደረጃ ትምሕርቤት ሲገባ የኳስ ፍቅሩና ተሰጥኦውም እየጎላ መሄድ ይጀምራል። ከዚያም አሥር ዓመት ሲሞላው ችሎታው በትውልድ ስፍራው በማዴይራ ብቻ ሣይሆን በመላው ፖርቱጋል መነጋገሪያ እየሆነ ይሄዳል። የመጀመሪያ ክለቡ አባቱ ግምጃቤት የነበረበት አማተር ክለብ ሢ.ኤፍ አንዶሪኛ ነበር። ከዚያም በተለያዩ ክለቦች ውስጥ ሲጫወት ከቆየ በኋላ በ 1997 ዓ.ም. ወደ ቀደምቱ የዋና ከተማይቱ ክለብ ወደ ስፖርቲንግ ሊዝበን ይሸጋገራል።

ክሪስቲያኖ ሮናልዶ በክለቡ ወጣት ቡድን ውስጥ ከቆየ በኋላ በ 2002 ለአንደኛው ዲቪዚዮን በመሰለፍ ከስፖርቲንግ ብራጋ ሲጫወት በሁለተኛ ግጥሚያውም ከሶሥት ሁለቱን የድል ጎሎች በማስቀጠር አድናቆትን ያተርፋል። ዴንማርክ ውስጥ በዚያው ዓመት ለተካሄደው ከ 17 ዓመት በታች ወጣቶች የአውሮፓ ዋንጫ ውድድር ለብሄራዊው ቡድን የተመረጠውም ያኔ ነበር። በዚሁ ውድድር ላይ ባሳየው ድንቅ አጨዋወትም ዓለምአቀፍ ትኩረትን ይስባል። ወዲያውም የእንግሊዙ ቀደምት ክለብ የኤፍ.ሢ.ሊቨርፑል አሠልጣኝ ወጣቱን ኮከብ ለመግዛት ፍላጎት ማሣየቱ አልቀረም። ግን የክለቡ ባለሥልጣናት ገና ልጅ ነው፤ ለዕድገቱ ጊዜ ያስፈልገዋል በማለታቸው የአሠልጣኙ ፍላጎት አይሳካም።

ይሁንና ሮናልዶ ከአንዲት ዓመት ቆይታ በኋላ የሌላው የእንግሊዝ ቀደምት ክለብ የማንቼስተር ዩናይትድ አሠልጣኝ የሰር አሌክስ ፈርጊሰንና የተጫዋቾቹ ዓይን ማረፊያ ይሆናል። ለዚሁ ምክንያት የሆነውም ለሊዝበን ሆሴ-አልቫላዴ ስታዲዮም ምረቃ በዩናይትድና በስፖርቲንግ መካከል በተካሄደ ግጥሚያ ላይ ሮናልዶ በክንፍ አጨዋወትም ሆነ በታክቲክ ያሳየው የረቀቀ ብቃት ነበር። ብዙም አልቆየ በነሐሴ ወር 2003 በ 17 ሚሊዮን ዶላር ገደማ ወደ ማንቼስተር ዩናይትድ ይሻገራል።

ከዚህ ወዲህ ያለው የቅርብ ታሪክ ነው። ክሪስቲያኖ ሮናልዶ ከክለቡ ጋር በእግሊዝና ከእንግሊዝ ባሻገር በአውሮፓ ሻምፒዮና ሊጋም የዋንጫዎች ባለቤት ሲሆን በአጨዋወቱ ይበልጥ እየሰከነ የመጣውም በዚያው ነው። በተለይ ከ 2006 ዓ.ም. ወዲህ የአንግሊዝ፤ የአውሮፓና የዓለም ድንቅ ተጫዋች በመባል ለመሸለም በቅቷል። የ 24 ዓመቱ ወጣት ኮከብ በአጨዋወቱ በወቅቱ በዓለም ላይ የተሟላውና ጠንካራው ነው ቢባል ብዙም ማጋነን አይሆንም። ሮናልዶ በአንዲት ቅጽበት የጨዋታን ውጤት ለመቀየር ብቃት እንዳለው ባለፉት ዓመታት በተደጋጋሚ አሳይቷል።

ክስቲያኖ ሮናልዶ አሁን ከመቶ ሚሊዮን ዶላር በሚበልጥ ገንዘብ ወደ ስፓኙ ቀደምት ክለብ ወደ ሬያል ማድሪድ ተሸጋግሯል። በቅርቡ በዝነኛው በርናቤዉ ስታዲዮም ሲተዋወቅ አርባ ሺህ ያህል ተመልካች ነበር የወደፊት ኮከቡን ለማየት የተሰበሰበው። ከአዲሱ ክለቡና ደጋፊዎቹ የሚጠበቅበት ብዙ፤ ምናልባትም ተዓመር ነው ሊባል ይችላል። ታዲያ ግፊቱን ይወጣው ይሆን? ሻምፒዮናው ከጥቂት ሣምንታት በኋላ ሲከፈት በጅምሩ ከቀናው መልካም፤ አለበለዚያ ግን ከባድ ጊዜ ነው የሚጠብቀው። አንድ ተጫዋች ይህን ያህል መዓት ገንዘብ ማውጣት ይገባዋል ወይ የሚለው ጥያቄም መልሶ መነጋገሪያ ሊሆን ይችላል።

በጀርመን ኑርቡርግሪንግ ትናንት ተካሂዶ የነበረው የፎርሙላ-አንድ አውቶሞቢል እሽቅድድም አሸናፊ አውስትራሊያዊው ማርክ ዌበር ሆኗል። ዌበር በ 130 ውድድሮች ሲያሸንፍ ለመጀመሪያ ጊዜ ሲሆን ባለፈው ሕዳር ወር ደርሶበት ከነበረው ከባድ አደጋ አንጻር ለዚህ መብቃቱ እጅግ የሚደነቅ ነው። ዌበር ባለፈው ሕዳር ወር በቢስክሌት ላይ እንዳለ ከአንድ ተሽከርካሪ ጋር በመጋጨቱ በቀኝ እግሩ ላይ ከባድ ስብራት ደርሶበት ነበር። ስኬቱ ለአውስትራሊያም ታላቅ ኩራት ነው። አገሪቱ ከአላን ጆንስ በኋላ ይህን ድል ስትጠብቅ 28 ዓመታት ነበር ያሳለፈችው።

በአንጻሩ በአገሩ ብዙ የተጠበቀበት ጀርመናዊው ሤባስቲያን ፌትል ሁለተኛ ሲወጣ የብራዚሉ ፌሊፔ ማሣ ሶሥተኛ ሆኗል። የብሪታኒያው ጄሰን ባተን ደግሞ ከአምሥተኝነት አላለፈም። ባተን ይሁንና በአጠቃላይ ነጥብ አሁንም ቀደምቱ ነው። በ 68 ነጥቦች ይመራል። ሤባስቲያን ፌትል በ 47 ነጥቦች ሁለተኛ ሲሆን ዌበርና ብራዚላዊው ሩበንስ ባሪቼሎ ደግሞ ጥቂት ወረድ ብለው ይከተላሉ።

በቡጢ ስፖርት ጋናዊው ጆዜፍ አግቤኮ ባለፈው ቅዳሜ አርመናዊ ተጋጣሚውን ቪክ ዳርቺኒያንን በአንድ-ወጥ የዳኞች ውሣኔ በማሸነፍ የዓለም ቡጡ ፌደሬሺን የቀላል ክብደት ሻምፒዮንነቱን ሊያረጋግጥ በቅቷል። አግቤኮ በሰባተኛው ዙር ላይ በደረሰበት መዘረር የግጥሚያውን ውጤት ጥቂትም ቢሆን አከራካሪ አድርጎት ነበር። ሆኖም ድሉን አላሳጣውም። በዚህ በጀርመን የአገሪቱ ተወላጅ ፌሊክስ ሽቱርምም እንዲሁ በአንድ-ወጥ የዳኞች ውሣኔ አርሜኒያዊውን ኮረም ጌቮርን በማሸነፍ የዓለም ቡጢ ማሕበር የመካከለኛ ክብደት ማዕረጉን አስከብቷል።

በዚህ የስፖርት መድረክ ላይ አሳዛኙ ዜና የቀድሞው ካናዳዊ የዓለም ሻምፒዮን አርቱሮ ጋቲ ትናንት ብራዚል ውስጥ ሞቶ መገኘቱ ነው። በአጨዋወቱ “መብረቅ” የሚል ቅጽል ስያሜ ተሰጥቶት የነበረው ስፖርተኛ አሟሟት ሁኔታ ጥርጣሬን በማስከተሉ የብራዚል ፖሊስ ጉዳዩን በመመርመር ላይ ይገኛል። ከኢጣሊያ የመነጨው ጋቲ ያደገው በሞንትሬያል ሲሆን ያለፉትን ዓመታት ያሳለፈውም በዚያው ነበር።

MM/RTR/AFP