የስፖርት ዘገባ | ስፖርት | DW | 29.06.2009
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ስፖርት

የስፖርት ዘገባ

ደቡብ አፍሪቃ ከአንድ ዓመት ባነሰ ጊዜ ውስጥ ለምታስተናግደው የዓለም እግር ኳስ ዋንጫ በምታደርገው ዝግጅት ትናንት በደመቀ ሁኔታ በተጠናቀቀው የኮንፌደሬሺን ዋንጫ ውድድር ፈተናዋን አልፋለች። ድሉ የብራዚል ሲሆን የተመልካቹ ስሜትና የሕዝቡ እንግዳ ተቀባይነት፤ የዝግጅቱም ሂደት እንዲሁ ብዙዎችን አስደስቷል።

default

“አንተማመንባችኋለን። በናንተ፤ በአፍሪቃ፤ በደቡብ አፍሪቃ ላይ!” የዓለም እግር ኳስ ፌደሬሺኖች ማሕበር የፊፋ ፕሬዚደንት ሤፕ ብላተር ከሁለት ሣምንታት በፊት የኮንፌደሬሺኑ ዋንጫ ውድድር ሲጀመር እንደተናገሩት በአስተናጋጇ አገር ላይ የጣሉት ዕምነት አልተጓደለም። በአገሪቱ በተለመደው ቩቩዜላ፤ ማለት እምቢልታ ስታዲዮሞችን የሚያደምቁት ኳስ አፍቃሪዎች ለዝግጅቱ የተለየ ውበት ነበሩ። እርግጥ በዝግጅቱ ሂደት እስከ ዓለም ዋንጫው ፍጻሜ ድረስ በስታዲዮሞች ግንቢያ፣ በትራንስፒርትና በጸጥታ ጥበቃ ረገድ ገና መሟላት የሚኖርባቸው ነገሮች አይታጡም። ቢሆንም ሰሞኑን የኮንፌደሬሺኑን ዋንጫ ውድድር ሲከታተል የሰነበተው የዶቼ ቬለ የስፖርት ፕሮግራም ክፍል ባልደረባ አርኑልፍ በትቸር እንደሚያምነው ሁሉም ነገር ተሥፋን የሚያጠናክር ነው።

“ዝግጅቱ የተጠናቀቀበት ጥሩ ሁኔታ ዓለምን እንዳስደነቀ አምናለሁ። በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ ለሚካሄደው የዓለም ዋንጫ ውድድር የተሣካ ፍተሻ ነበር። ከሞላ ጎደል ይህ ነው የሚባል ትልቅ ችግር አልደረሰም። እርግጥ ስታዲዮሞች ደቡብ አፍሪቃ ስትጫወት ወይም በኋላ በግማሽ ፍጻሜና ፍጻሜ ግጥሚያዎች ላይ ካልሆነ በስተቀር በተመልካች የተሞሉ አልነበሩም። እዚህ ላይ አዘጋጆቹ አንድ መላ መፈለግ አለባቸው። ግን ይህም ሊሣካ የሚችል ነገር ነው”

የኮንፌደሬሺኑ ዋንጫ ውድድር ሂደት ደቡብ አፍሪቃ በ 2010 ዓለምን በግሩም ፌስታ ለመማረክ ብቁ እንደሆነች ተጠራጣሪዎች ሳይቀር አምነው እንዲቀበሉ ነው ያደረገው። የዩ.ኤስ.አሜሪካ ብሄራዊ ቡድን አሠልጣኝ ቦብ ብራድሊይ እንዳለው ለምሳሌ ሕዝቡ ያሳየውን ወዳጅነት፣ የእግር ኳስ ፍቅሩና የደህንነት አስከባሪዎች የፈገግታ አቀባበል፤ ሁሉም ግሩም ነገር ነበር። የቡድናችን ተጫዋቾች ቶሎ ማጣሪያቸውን አልፈው በሚቀጥለው ዓመት ወደ ደቡብ አፍሪቃ የሚመለሱበትን ጊዜ ነው የሚናፍቁት ሲል ነበር ትናንት አድናቆቱን የገለጸው።

ለሚቀጥለው የዓለም ዋንጫ ውድድር የሚደረገው ዝግጅት በጊዜው ይጠናቀቅ አይጠናቀቅ ቀደም ሲል ይሰማ የነበረው ጥርጣሬም ጨርሶ ተወግዷል እንኳ ባይባል ከሰሞኑ መስተንግዶ ወዲህ ቢቀር እየረገበ በመሄድ ላይ ነው።

“የስታዲዮሞቹ ግንቢያ በተጠናከረ ሁኔታ እየተካሄደ ነው። በጊዜው ይጠናቀቃል ብዬ አምናለሁ። በጊዜው እንደሚጠናቀቅ እርግጠኛም ነኝ። በትራንስፓርት ረገድም ችግሩ የት ላይ እንደሆነ ለማየት ተችሏል። ሊወገድ የሚችል ነው። ከዚህ ሌላ እርግጥ ጸጥታን በተመለከተ ብዙም አልተወራም። በመሆኑም ምን እንደደረሰ በትክክል ለማወቅ አይቻልም። ትልቁ ችግር የሚመጣው በሚቀጥለው ዓመት ነው። ምናልባት አንድ ሚሊዮን ያህል ደጋፊዎች፤ በትክክል ምን ያህል ለጊዜው አይታወቅም ከውጭ ሊሄዱ ይችላሉ። በስታዲዮሞች ዙሪያ እርግጥ ጸጥታው የተረጋገጠ ነው የሚሆነው። በሆቴሎችም እንዲሁ! በተቀረው ቦታ የሚሆነውን ግን አሁን ለመናገር ያዳግታል”

በሌላ በኩል አብዛኛው አገሬው ተመልካች በዓለም ዋንጫው ፍጻሜ ውድድር ወቅት ገንዘብ ከፍሎ ስታዲዮሞች ለመግባት ያለው አቅም የተወሰነ መሆኑ በኮንፌደሬሺኑ ዋንጫ ውድድር ሰሞን አንዱ አነጋጋሪ ጉዳይ ሆኖ ነው የሰነበተው። ስታዲዮሞች በከፊል ባዶ እንዳይሆኑ ስጋታቸውን የሚገልጹ አልጠፉም። ሆኖም ብሄራዊው አዘጋጅ ኮሚቴና ፊፋ በመጨረሻ መፍትሄ እንደማያጡ ባልደረባችን አርኑልፍ በትቸር እርግጠኛ ነው።

“በመጀመሪያ በዓለም አቀፍ ደረጃ የቲኬቶች ሽያጭ በምን መጠን እንደሚራመድ መጠበቁ ግድ ነው። ምን ያህል ደጋፊዎች ከውጭ ሊሄዱ ይችላሉ? ለጊዜው በትክክል አይታወቅም። በመሆኑም ከዚህ ሽያጭ በኋላ ነው ምን ያህል እንደሚተርፍ የሚታየው። ያ ግልጽ ሲሆን ተራው ደቡብ አፍሪቃዊ ስታዲዮሞች መግባት በሚችልበት አቅም መጠን ዋጋውን ዝቅ አድርጎ ለመወሰን ይቻላል። መፍትሄው በዋጋ ቅነሣ ይሁን ወይም ቲኬቶችን በነጻ በማደል መላ የሚታጣ አይመስለኝም። ለነገሩ ነጻ ቲኬት የማደሉ ዘይቤ ከአሁኑ መሥራቱም ታይቷል። እና ስታዲዮሞቹን መሙላቱ ይሳካል ባይ ነኝ”

ወደሰሞኑ የኮንፌደሬሺን ዋንጫ ውድድር ግጥሚያዎች እንሻገርና ብራዚል ባለፈው ምሽት ጆሃንስበርግ ላይ ከዩ.ኤስ.አሜሪካ ጋር ባካሄደችው ፍጻሜ ግጥሚያ ለሶሥተኛ ጊዜ የኮንፌደሬሺኑ ዋንጫ ባለቤት ለመሆን በቅታለች። 52,291 ተመልካቾች በተገኙበት በኤሊስ-ፓርክ ስታዲዮም አሜሪካ በተፋጠነ የማጥቃት አጨዋወት በ 27 ደቂቃዎች ውስጥ 2-0 ስትመራ ዳዊት ጎልያድን ሊያዋርድ ነው ብለው ያሰቡት ተመልካቾች ጥቂቶች አልነበሩም። ሆኖም ከአረፍት በኋላ አንበሶች ሆነው ሜዳ የገቡት የብራዚል ተጫዋቾች የመጀመሪያ ጎላቸውን ለማስቆጠር ከአንዲት ደቂቃ በላይ አልወሰደባቸውም።
ድንቁ አጥቂ ሉዊስ ፋቢያኖ በ 46 ኛና 74ው ደቂቃ ላይ ሁለት ጎሎች በማስቆጠር ውጤቱን እኩል-ለእኩል ሲያደርግ ብራዚል ለድል የበቃችው ሉሢዮ በ 84ኛዋ ደቂቃ ላይ በአናት ባስቆጠራት ግሩም ግብ ነበር። የብራዚል ብሄራዊ ቡድን ከኋላ ተነስቶ በቀለጠፈ የማጥቃት ስልት ሲያሸንፍ ግሩም አጨዋወቱ በዓለም ዙሪያ ተመልካቾችን እንዳረካ አንድና ሁለት የለውም። ብራዚል ለፍጻሜ የደረሰችው በግማሽ ፍጻሜው ደቡብ አፍሪቃን ለጥቂት በመርታት ነበር። የአስተናጋጇ አገር ብሄራዊ ቡድንም ታዲያ በአጠቃላይ ባሣየው አቀራረብ ከያቅጣጫው ሳይወደስ አልቀረም።

“የደቡብ አፍሪቃ ብሄራዊ ቡድን በጣም ነው ያስደነቀኝ። በተለይ በግማሽ ፍጻሜው ከብራዚል ጋር በተካሄደው ግጥሚያ ደቡብ አፍሪቃን እኩል አድርጌ ነው የተመለከትሁት። በተጨማሪ ሰዓት መሽነፏ በጣም ያሳዝናል። ልትረታ በቻለችም ነበር። በአጠቃላይ የደቡብ አፍሪቃ እግር ኳስ በጣም ነው ዕርምጃ ያደረገው። ቡድኑ በታላቅ ዲሲፕሊን ነበር የሚጫወተው። የደቡብ አፍሪቃ ብሄራዊ ቡድን እንደ ጀርመን የ 2002 የዓለም ዋንጫ ፍጻሜ በአገሩ ሕዝብ ፊት ሲጫወት ወደፊት ሊራመድ የሚችል ነው። ጥሩ መጫወት መቻሉን ከአሁኑ አሳይቷል”

እንግሊዝ ዊምብልደን ላይ የሚካሄደው አንጋፋውና በዓለም ላይ ታላላቅ ከሚባሉት አንዱ የሆነው የዘንድሮው የቴኒስ ውድድር ዛሬ ወደ ሁለተኛ ሣምንቱ ተሽጋግሯል። ታዲያ እንደተለመደው በሂደቱ አንዳንድ አስደናቂ ውጤት መታየቱም አልቀረም። ወኪላችን ሃና ደምሴ የውድድሩን ሂደት ከታሪካዊ አመጣጡ ጋር በማጠናቀር ከለንደን የላከችውን ዘገባ አድምጡ።

በእግር ኳስ ለማጠቃለል ስዊድን ውስጥ ሲካሄድ የሰነበተው ከ 21 ዓመት በታች ወጣቶች የዓለም ዋንጫ ውድድር ዛሬ ማምሻውን ይፈጸማል። በፍጻሜው ግጥሚያ የሚገናኙት ጀርመንና እንግሊዝ ናቸው።

መሥፍን መኮንን፣

ተክሌ የኋላ፣