የስፖርት ዘገባ | ስፖርት | DW | 29.06.2009
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ስፖርት

የስፖርት ዘገባ

መጪውን የዓለም እግር ኳስ ዋንጫ ፍጻሜ ውድድር በምታስተናግደው በደቡብ አፍሪቃ የሚካሄደው የኮንፌደሬሺን ዋንጫ ጨዋታ ወደ ግማሽ ፍጻሜው ዙር እየተሸጋገረ ነው። ሰንበቱ የአፍሪቃ የዓለም ዋንጫ ማጣሪያ ግጥሚያዎችና ሌሎች ዓለምአቀፍ ውድድሮችም የተካሄዱበት ነበር።

default

ደቡብ አፍሪቃ ውስጥ የሚካሄደው መጪው የ 2010 የዓለም እግር ኳስ ዋንጫ ፍጻሜ ውድድር ሊከፈት የቀረው አንድ ዓመት ያህል ጊዜ ነው። ታዲያ ሰሞኑን የእግር ኳሱ ዓለም የደቡብ አፍሪቃን የዝግጅት ብቃት መፈተሻ፤ ከዚያም ባሻገር የታላላቆቹ አገሮች ይዞታ መለኪያ ሆኖ በታየው ውድድር ላይ ዓይኑን በሰፊው ማሳረፉ አልቀረም። በሁለት ምድቦች ተከፍሎ ሲካሄድ የሰነበተው ደቡብ አፍሪቃ እንደ አስተናጋጅ አገር፤ ኢጣሊያ እንደ ዓለም ዋንጫ ባለቤትና የየክፍለ-ዓለማቱ ሻምፒዮኖች የተሳተፉበት የመጀመሪያ ዙር ትናንት ተጠናቆ ወደ ግማሽ ፍጻሜው ተሸጋግሯል።

ለአስተናጋጇ ደቡብ አፍሪቃ አስደሳቹ ነገር ምንም እንኳ በምድብ-አንድ የመጨረሻ ግጥሚያዋ በሃያሏ ስፓኝ 2-0 ብትረታም ወደ ግማሽ ፍጻሜው ካለፉት አራት አገሮች መካከል አንዷ ለመሆን መብቃቷ ነው። በአንጻሩ በመክፈቻው ግጥሚያ ከደቡብ አፍሪቃ ባዶ-ለባዶ ወጥታ የነበረችው የእሢያ ሻምፒዮን ኢራቅ ከኒውዚላንድ ጋር በተመሳሳይ ውጤት በመለያየቷ በሶሥተኝነት ተወስኖ መቅረቱ ግድ ሆኖባታል።
የወቅቱ የአውሮፓ ሻምፒዮን ስፓኝ ሶሥቱንም የምድብ ጨዋታዎች በማሽነፍ ስትፈጽም በተከታታይ በዓለምአቀፍ ግጥሚያዎች 15 ጊዜ በማሸነፍም ክብረ-ወሰኑን ከብራዚል ተረክባለች። የወዳጅነት ግጥሚያዎች ከተቆጠሩ እንዲያውም ከየካቲት 2007 ዓ.ም. ወዲህ በ 35 ግጥሚያዎች አንዴም አልተሽነፈችም። ውጤቱ የስፓኝን ጥንካሬ የሚያሳይ ሲሆን ብሄራዊ ቡድኑ በወቅቱ የኮንፌደሬሺንም ሆነ በመጪው የዓለም ዋንጫ ፍጻሜ ውድድር የድል ባለቤት ይሆናሉ ተብለው ከሚጠበቁት አንዱ ነው። በዚሁ ምድብ ግብጽን 3-0 የሸኘችው ዩ.ኤሰ.አሜሪካ የመጀመሪያውን ዙር በሁለተኝነት ፈጽማለች።

በሌላ በኩል በምድብ-ሁለት ያለፈው የዓለም ዋንጫ ባለቤት ኢጣሊያ ትናንት በብራዚል እንዳልነበር ሆና 3-0 በመቀጣት ከኮንፌደሬሺኑ ዋንጫ ውድድር ከወዲሁ ተሰናብታለች። የብራዚል ድል በቀለጠፈ አጨዋወት ገና በመጀመሪያው አጋማሽ ሲረጋገጥ ጨዋታው እንደታለመለት ተመልካቹን እጅግ ያረካ ነበር። ሉዊስ ፋቢያኖ በስድሥት ደቂቃዎች ልዩነት ሁለቱን ጎሎች ሲያስቆጥር ሶሥተኛዋን ወደ ራሱ ግብ የሸኛት አንድሬያ ዶሤና ነበር። ለነገሩ የብራዚል ቡድን 5-0 አሸንፎ ቢሆን ኖርም ብዙ የሚደነቅ ተመልካች ባልኖረ ነበር። የኢጣሊያ ብሄራዊ ቡድን እጅግ ደካማ ሆኖ ነው የታየው።

በነገራችን ላይ የኢጣሊያ ብሄራዊ ቡድን በአንድ በዓለምአቀፍ ግጥሚያ በግማሽ ጊዜ ሶሥት ጎል ሲገባበት ከ 52 ዓመታት ወዲህ ለመጀመሪያ ጊዜ መሆኑ ነው። ያኔ በዩጎዝላቪያ 6-1 ተቀጥቶ ከሜዳ መውጣቱ ይታወሣል። የሆነው ሆኖ አሠልጣኙ ማርቼሎ ሊፒ ለዓለም ዋንጫው ፍጻሜ ያወጡትን ዕቅድ እንደማይለውጡ ነው የተናገሩት። ሆኖም ቡድኑ ያረጀ ነው የሚል ትችት ከአንዳንድ ወገን ተሰንዝሮባቸዋል። ለማንኛውም ኢጣሊያ በዓለም ዋንጫ ፍጻሜ ውድድሮች ላይ እስካሁን ሁልጊዜም ጠንካራ በመታየቷ በጊዜው ከቀደምቱ መካከል አንዷ ልትሆን እንደምትችል የሚጠበቅ ነው።

በደቡብ አፍሪቃው የኮንፌደሬሺን ዋንጫ ውድድር በግማሽ ፍጻሜው ከነገ በስቲያ ረቡዕ ስፓኝ ከዩ.ኤስ.አሜሪካ ትጋጠማለች። በማግሥቱ በሚካሄደው ሁለተኛ ግጥሚያ የሚገናኙት ደግሞ ብራዚልና አስተናጋጇ ደቡብ አፍሪቃ ናቸው። የፍጻሜው ግጥሚያ በፊታችን ዕሑድ ይካሄዳል።

የኮንፌደሬሺኑ ዋንጫ ውድድር በዚህ መልክ እየተራመደ ባለበት ጊዜ ትናንት በዚያው በአፍሪቃ ክፍለ-ዓለም የዓለም ዋንጫ ማጣሪያ ግጥሚያዎች ተካሂደው ነበር። በምድብ-አንድ ሞሮኮ ከቶጎ ባዶ-ለባዶ ስትለያይ በምድብ-ሁለት ቱኒዚያና ናይጄሪያም ግጥሚያቸውን በተመሳሳይ ውጤት ፈጽመዋል። በምድብ-ሶሥት አልጄሪያ ዛምቢያን በውጭ 2-0 ስትረታ በምድብ-አራት ውስጥ ጋናም ዛምቢያን በዚያው ውጤት አሸንፋለች። በምድብ-አምሥት ግጥሚያ ደግሞ አይቮሪ ኮስት ቡርኪና ፋሶን 3-2 ረትታለች። ከዚሁ ሌላ ማሊ ቤኒንን 3-1 ስታሸንፍ ጊኒም ማላዊን 2-1 ሸኝታለች። ከዚሁ ውጤት በኋላ ምድብ-አንድን የምትመራው ጋቦን ስትሆን የሚያስገርም ሆኖ ሞሮኮ ሶሥተኛ ካሜሩን ደግሞ የመጨረሻዋ ናት።
ምድብ-ሁለትን ቱኒዚያና ናይጄሪያ ይመራሉ፤ በምድብ ሶሥት አልጄሪያ አንደኛ ስትሆን፤ እዚህም ጉድ ነው የአፍሪቃ ዋንጫ ባለቤት ግብጽ በመጨረሻነት ከታች ወደላይ ተመልካች እንደሆነች ነው። ሌሎቹ ሃያል ቡድኖች ጋናና አይቮሪ ኮስት የተቀሩትን ምድቦች በአስተማማኝ ሁኔታ ይመራሉ። ግብጽ፣ ካሜሩንና ሞሮኮ እንዲህ ማቆልቆላቸውን በጅምሩ ያሰበው ማንም አልነበረም። ይህ የሚያሰው የተቀሩት በርካታ የአፍሪቃ አገሮች ባለፉት ዓመታት ታላቅ ዕርምጃ እያደረጉ መምጣታቸውንና ፉክክሩ ጠንካራ እየሆነ መሄዱን ነው። በእሢያ ደግሞ ሰሜን ኮሪያ ከ 1966 የእንግሊዝ የዓለም ዋንጫ ውድድር ወዲህ ለመጀመሪያ ጊዜ ለፍጻሜ የደረሰውን ብሄራዊ ቡድኗን ባለፈው ቅዳሜ ከሳውዲት አረቢያ ግጥሚያው ሲመለስ በደመቀ ሁኔታ ተቀብላለች።
ባለሥልጣናት ተጫዋቾቹን አየር ጣቢያ ሄደው ሲቀበሉ የአገሪቱ ዜና አገልግሎት ኮና እንደዘገበው የዋና ከተማይቱ የፕዮንግያንግ አደባባዮች በሕዝብ ደምቀው ነበር። ደቡብ ኮሪያም ቀደም ሲል ለፍጻሜው ስትደርስ በደቡብ አፍሪቃው የዓለም ዋንጫ ፍጻሜ ውድድር ሁለቱ ኮሪያዎች በአንድላይ ሲሳተፉ የመጀመሪያ ጊዜ ይሆናል። ሰሜን ኮሪያ ከአርባ ሶሥት ዓመታት በፊት እንግሊዝ ላይ በተካሄደው የዓለም ዋንጫ ውድድር ኢጣሊያን በአስደናቂ ሁኔታ 1-0 በማሸነፍ ለሩብ ፍጻሜ ዙር መድረሷ ይታወሣል። የኢጣሊያ ባልታሰበ ሁኔታ ቀድሞ መሰናበት በጊዜው ዓለምን ጉድ ያሰኘ ነገር ነበር።

በአትሌቲክስ ባለፈው ሰንበት ፖርቱጋል-ሌይሪያ ላይ በተካሄደ የአውሮፓ የቡድን ሻምፒዮና ጀርመን በጠቅላላው 326,5 ነጥቦችን በማስመዝገብ አንደኛ ሆናለች። የሩሢያ ቡድን በ 320 ነጥቦች ሁለተኛ፤ ብሪታኒያ በ 303 ሶሥተኛ እንዲሁም ፈረንሣይ በ 301 ነጥቦች አራተኛ በመሆን ውድድሩን ፈጽመዋል።

በሣምንቱ አጋማሽ ቼክ ሬፑብሊክ ውስጥ የተካሄደው የኦስትራቫ ግራንድ-ፕሪ ደግሞ የኢትዮጵያ አትሌቶችም ገነው የታዩበት ነበር። በሴቶች 5 ሺህ ሜትር ሩጫ መሰለች መልካሙ ሊኔት ማሣይንና ቪቪያን ቼሩዮትን የመሳሰሉትን ጠንካራ የኬንያ አትሌቶች ቀድማ ስታሸንፍ ድሬ ጡኔም በ 20 ኪሎሜትር ሩጫ በተመሳሳይ ሁኔታ ኬንያውያንን በማስከተል ለድል በቅታለች። የኬንያ ወንድ አትሌቶች በፊናቸው በ 800 ሜትር፣ በማይልና በ 3 ሺህ ሜትር መሰናክል አሸንፈዋል። በአጭር ርቀት ሩጫ ጃማይካዊው የዓለምና የኦሎምፒክ ሻምፒዮን ኡሤይን ቦልት በ 100 ሜትር ግሩም በሆነ 9,77 ሤኮንድ ጊዜ ለድል በቅቷል። የዓለም ክብረ-ወሰኑ 9,69 ሤኮንድ ነው።

ትናንት ብሪታኒያ ውስጥ የተካሄደው የፎርሙላ-አንድ አውቶሞቢል እሽቅድድም አሸናፊ ጀርመናዊው ወጣት ዘዋሪ ዜባስቲያን ፌትል ሆኗል። ፌትል በንድሮው ውድድር ሲያሽንፍ ለሁለተኛ ጊዜ ሲሆን በአንጻሩ ቀደምቱ የብሪታኒያ ዘዋሪ ጄሰን ባተን በገዛ አገሩ አልቀናውም። በስድሥተኝነት ተወስኖ ቀርቷል። ከትናንቱ ውድድር ወዲህ በአጠቃላይ ነጥብ ባተን በ 64 ይመራል፤ ብራዚላዊው ሩበንስ ባሪቼሎ በ 41ነጥብ ሁለተኛ ሲሆን ዜባስቲያን ፌትል በ 39 ሶሥተኛ ነው።

በዚህ በጀርመን ባለፈው ቅዳሜ ምሽት ተካሂዶ በነበረ የቡጡ ግጥሚያ የኡክራኒያው ተወላጅ ቭላዲሚር ክሊችኮ የኡዝቤኪስታን ተጋጣሚውን ሩስላን ቻጋዬቭን በዘጠነኛው ዙር ላይ በበቃኝ በማሸነፍ የዓለም ቡጢ ማሕበር WBA የከባድ ሚዛን ሻምፒዮንነቱን አስመልሷል። ክሊችኮ ከቅዳሜው ድሉ ወዲህ የተለያዩት የቦክስ ማሕበራት የ IBF, IBO, WBO ና WBA ሱፐር-ሻምፒዮን ነው። በሻልከ የእግር ኳስ ስታዲዮም ውስጥ የተካሄደውን ግጥሚያ 61 ሺህ ሰዎች ተመልክተውታል፤ እ’ጅግ የደመቀ ነበር።

የሰባት ጊዜው የቱር-ዴ-ፍራንስ ሻምፒዮን ላንስ አርምስትሮንግ ትናንት በሰሜናዊው ካሊፎርኒያ ኮረብታ በተካሄደው የኔቫዳ ከተማ ክላሢክ የቢስክሌት እሽቅድድም አሸናፊ ሆኗል። ይህም ወደ ዘንድሮው ቱር-ዴ-ፍራንስ ለመመለስ በሚያደርገው ጥረት እንደሚያበረታታው ይታመናል። አርምስትሮንግ የሚያልመው በያዝነው ወር የመጨረሻ ሣምንት ሞናኮ ላይ በሚከፈተው በዚሁ ታላቅ ውድድር ለመሳተፍ ነው። አሜሪካዊው ቢስክሌተኛ ወደ ውድድሩ የተመለሰው ባለፈው ጥር ወር ነበር። በጊዜው አውስትሪያ ውስጥ ተካሂዶ በነበረው እሽቅድድም 29ኛ መውጣቱም ይታወሣል። ስዊትዘርላንድ ውስጥ ትናንት ተካሂዶ በነበረ እሽቅድድም ደግሞ የአገሪቱ ተወላጅ የኦሎምፒኩ ሻምፒዮን ፋቢያን ካንሤላራ አሽናፊ ሆኗል። ጀርመናዊው ቶኒይ ማርቲን ሁለተኛ ሲሆን በጠቅላላ ነጥብ ሶሥተኝነቱን የያዘው የቼኩ ተወዳዳሪ ሮማን ክሮይሢገር ነው።

በዓለም ላይ ታላቁ ክብደት የሚሰጠው የእንግሊዙ የዊምብልደን የቴኒስ ውድድር በዛሬው ዕለት ተጀምሯል። ቀደምቱ የዓለም የቴኒስ ኮከብ የስፓኙ ተወላጅ ራፋኤል ናዳል በአካል ጉዳት የማይሳተፍ ቢሆንም ተከታዩ ሮጀር ፌደረር፣ ኤንዲይ መሪይና መሰሎቻቸው ውድድሩን እንደያደምቁት ተሥፋ ይደረጋል። ኤንዲይ መሪይ ዘንድሮ ከቀናው በዊምብልደን ታሪክ ውስጥ ከ 73 ዓመታት በኋላ የመጀመሪያው የብሪታኒያ ባለድል ይሆናል። በ 1936 ዓ.ም. ብሪታኒያን ለዚህ እስካሁን ብቸኛው ለሆነው ድል ያበቃው ፍሬድ ፔሪይ ነበር።

በተረፈ የዓለም ቴኒስ ማሕበር ዛሬ ባወጣው የማዕረግ ተዋረድ በወንዶች ራፋኤል ናዳል አንደኝነቱን ሲያረጋግጥ ሮጀር ፌደረር ሁለተኝነቱን እንደያዘ ነው፤ ኤንዲይ መሪይ ደግሞ ሶሥተኛ ነው። እርግጥ ናዳል በዊምብልደን የማይሳተፍ በመሆኑ ፌደረር አሸናፊ ከሆነ ማዕረጉን ለስዊሱ ኮከብ ማስረከቡ የሚቀር አይመስልም። በሴቶች ሩሢያዊቱ ዲናራ ሣፊና ቀደምቱን ቦታ ስትይዝ እሕትማማቾቹ የአሜሪካ ከዋክብት ሤሬናና ቬኑስ ዊሊያምስ ሁለተኛና ሶሥተኛ ናቸው።

MM/RTR/AFP

HM