የስፖርት ዘገባ | ስፖርት | DW | 15.06.2009
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ስፖርት

የስፖርት ዘገባ

ከአንድ ዓመት በኋላ በአፍሪቃ ምድር ለመጀመሪያ ጊዜ የሚካሄደውን የዓለም አግር ኳስ ዋንጫ ፍጻሜ በምታስተናግደው በደቡብ አፍሪቃ የኮንፌደሬሺን ዋንጫ ውድድር ትናንት ተጀምሯል። ሰንበቱ የዘንድሮው የአትሌቲክስ ጎልደን-ሊግ ውድድር በዚህ በበርሊን የተጀመረበትም ነበር።

default

አትሌቲክስ

የዘንድሮው የአትሌቲክስ ጎልደን-ሊግ የመጀመሪያ ውድድር በፊታችን ነሐሴ ወር የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና በሚካሄድባት በበርሊን ትናንት ተካሂዷል። ቀነኒሣ በቀለ በ 5 ሺህ ሜትር ሩጫ የኬንያ ተፎካካሪዎቹን ቀድሞ በመግባት አንድ ሚሊዮን ዶላር ለማግኘት የመጀመሪያውን ጥርጊያ ሲያመቻች የምርኩዝ ዝላይ የዓለም ሻምፒዮን የሆነችው ሩሢያዊት የለና ኢዚምባየቫም እንደተጠበቀው አሸንፋለች። በ 5 ሺህ ሜትሩ ሩጫ ኬንያውያኑ አብራሃም ቼቢና ሚካ ኮጎ ቀነኒሣን ተከትለው ሁለተኛና ሶሥተኛ ሲሆኑ ባካና ዳባ ከኢትዮጵያ አምሥተኛ ሆኗል። የተቀሩትን ግሩም ውጤቶች አሜሪካዊቱ ሣኒያ ሪቻርድስ በ 400 መቶ ሜትር፤ እንዲሁም ኬንያዊው አጉስቲን ቾጌ በ 1,500 ሜትር አስመዝግበዋል።
በተለይ ለጀርመን ታላቁ ደስታ አሪያነ ፍሪድሪሽ በብሄራዊ አዲስ ክብረ-ወሰን ክሮኤሺያዊቱን የዓለም ሻምፒዮን ብላንካ ቭላዚችን ማሸነፏ ነበር። ፍሪድሪሽ ከዚህ ቀደም ቭላዚችን በአዳራሽ ውስጥ ውድድር ስታሽንፍ ባለፈው ዓመትም በጎልደን-ሊጉ የመጨረሻ ውድድር ክሮኤሺያዊቱ ለሚሊዮኑ ሽልማት እንዳትበቃ መሰናክል መሆኗ የሚታወስ ነው። ለማንኛውም አሪያነ ፍሪድሪሽ ትናንት ሁለት ሜትር ከዘጠኝ በመዝለል ስታሸንፍ ቭላዚች በሁለት ሜትር ከሶሥት ሤንቲሜትር በሁለተኝነት ተወስና ቀርታለች። ጀርመናዊቱ አትሌት በራስ መተማመን ቢታይባትም በዚህ መጠን ጠንክራ መታየቷ አሠልጣኟ ጉንተር አይዚንገር እንኳ የጠበቀው አልነበረም።

“ተሥፋ ያደረግኩት በዚህ ዓመት ሁለት ሜትር ከስድሥት ትዘላለች ብዬ ነበር። ተሥፋዬ ይሄ ነበር። ዕውነቱን ለመናገር በርሊን ውስጥ ይሆናል ብዬ አላሰብኩም። እና ዛሬ ሁኔታው የተሟላ ነበር። አየሩ ሞቃት፤ ተመልካቹም ግሩም ነበር። ድጋፉ እጅግ ስሜትን የሚነዝር ነው”

የተቀሩት አምሥት ጎልደን-ሊግ ውድድሮች በፊታችን ሐምሌና ነሐሴ በኦስሎ፣ በሮማ፣ በፓሪስ፣ በዙሪክና በብራስልስ በተከታታይ ይካሄዳሉ። ለውድድሩ የተመደበውን አንድ ሚሊዮን ዶላር ሽልማት መውሰድ የሚችለው ስድስቱንም ውድድሮች ለማሸነፍ የሚበቃ አትሌት ነው። ይህ ካልሆነ አምሥቴ ያሸነፉ አትሌቶች 500 ሺህ ዶላር እንዲያገኙ ወይም እንዲከከፋፈሉ ይደረጋል።

ባለፈው ሣምንት በዚህ በአውሮፓ ሌሎች መለስተኛ የአትሌቲክስ ውድድሮችም ሲካሄዱ የኢትዮጵያ ሯጮችም ጥሩ ውጤት አስመዝግበዋል። ፖላንድ ውስጥ በሣምንቱ አጋማሽ በተካሄደ ዓለምአቀፍ ውድድር ከኢትዮጵያ ሃሊማ ሃሰን በ 3 ሺህ ሜትር መሰናክል ሶሥተኛ ስትወጣ ቀደም ሲል ፕራግ ላይ ደግሞ ዳዊት ወልዴ የ 1,500 ሜትር ሩጫ አሸናፊ ሆኖ ነበር። በተረፈ በአካል ጉዳት ምክንያት ለፊታችን ነሐሴ የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና መዘጋጀቱን በበምረጥ ከጎልደን-ሊጉ ውድድር የተቆጠበው የኦሎምፒክ ባለድልና የዓለም ክብረ-ወሰን ባለቤት ጃማይካዊው ኡሤይን ቦልት ቶሮንቶ ላይ በመቶ ሜትር ሩጫ አሸንፏል። በዝናብ ሮጦ ያስመዘገበው አሥር ሤኮንድ ጊዜ ምንም እንኳ ከ 9,69 ሤኮንድ ክብረ-ወሰኑ የራቀ ቢሆንም የሚደነቅ ነው።

እግር ኳስ

የመጪው 2010 ዓ.ም. የዓለም እግር ኳስ ዋንጫ ፍጻሜ አስተናጋጅ በሆነችው በደቡብ አፍሪቃ ትናንት የኮንፌደሬሺኑ ዋንጫ ውድድር በደመቀ ስነ ስርዓት ተከፍቷል። በጆሃንስበርግ ኤሊስ ስታዲዮም የተካሄደው መክፈቻ ስነ ስርዓት በባሕላዊ ዳንስና በትርዒት ሲደምቅ ፕሬዚደንት ጄኮብ ዙማ ዕለቱን ለአፍሪቃ ታላቅ ቀን ነው ብለውታል።
ውድድሩ የሚካሄደው በሁለት ምድብ ተከፍሎ ሲሆን ተሳታፊዎቹ ከአስተናጋጇ ደቡብ አፍሪቃ ባሻገር የየክፍለ-ዓለማቱ ሻምፒዮን ሃገራትና ያለፈው የዓለም ዋንጫ ባለቤት ኢጣሊያ ናቸው። ውድድሩ ትናንት በምድብ አንድ ግጥሚያዎች ሲጀመር የአውሮፓ ሻምፒዮን ስፓኝ ኒውዚላንድን በፍጹም የበላይነት 5-0 በማሸነፍ ልዕልናዋን እንደገና አስመስክራለች። ደቡብ አፍሪቃ በአንጻሩ ከእሢያ ሻምፒዮን ከኢራቅ ባዶ-ለባዶ ስትለያይ ውጤቱ በውድድሩ ወደፊት መግፋት መቻሏን አጠያያቂ ያደረገ ነበር። ቡድኑ በአብዛኛው ያሳየው አጨዋወት ሃምሣ ሺህ የሚሆኑ ግሩም ተመልካቾቹን ያረካ አልነበረም።

በሌላው ግጥሚያ ኒውዚላንድ ለአውሮፓው ሻምፒዮን የስፓኝ ቡድን ጨርሶ አቻ ተፎካካሪ ለመሆን አልቻለችም። ፈርናንዶ ቶሬስ የኒውዚላንድን የመከላከል ድክመት በመጠቀም በ 17 ደቂቃዎች ውስጥ የመጀመሪያዎቹን ሶሥት ጎሎች ሲያስቆጥር ጨዋታው ያለቀለት ከወዲሁ ነበር ለማለት ይቻላል። ከዚያም ፋብሬጋስ አራተኛዋን ጎል አስቆጥሮ የመጀመሪያው አጋማሽ ሲያበቃ ከዕረፍት በኋላ አምሥተኛና የመጨረሻዋን ጎል ያገባው ደግሞ ዴቪድ ቪያ ነበር። የስፓኝ ብሄራዊ ቡድን እስካሁን 33 ግጥሚያዎችን ሳይሸነፍ ሲያሳልፍ ከብራዚል ክብረ-ወሰን ላይ ለመድረስ የሚቀሩት ሁለት ግጥሚያዎች ብቻ ናቸው።
የምድብ አንድ ተከታይ ግጥሚያዎች ከነገ በስቲያ ረቡዕ ይካሄዳሉ። በብሎምፎንቴን ተጋጣሚዎቹ ስፓኝና ኢራቅ ሲሆኑ ደቡብ አፍሪቃና ኒውዚላንድ ደግሞ ሩስተንቡርግ ውስጥ ይገናኛሉ። የምድቡ ሶሥተኛ ግጥሚያዎች የሚካሄዱት በፊታችን ቅድሜ ነው። ምድብ-ሁለት ብራዚል፣ ግብጽ፣ ኢጣሊያና ዩ.ኤስ.አሜሪካ የሚገኙበት ሲሆን የዚህ ድልድል ግጥሚያዎች የሚጠናቀቁት ዛሬ ማምሻውን ነው። ብራዚል ከግብጽ፤ እንዲሁም አሜሪካ ከኢጣሊያ ይገናኛሉ። ምድቡ ከመጀመሪያው ይልቅ ጠንከር ያለ ይመስላል። ብራዚል ከደቡብ አሜሪካ ሻምፒዮንነቷ ባሻገር ያለፈው ኮንፌደሬሺን ዋንጫ ባለቤትም ናት። ከአራት ዓመታት በፊት በዚህ በጀርመን ተካሂዶ በነበረው የኮንፌደሬሺን ዋንጫ ፍጻሜ ግጥሚያ አርጄንቲናን 4-1 መርታቷ ይታወሣል።

ብራዚል በወቅቱ የላቲን አሜሪካውን የዓለም ዋንጫ ማጣሪያ ምድብም እየመራች ሲሆን ምንም እንኳ የቅርቡ የቡድኑ የመከላከል አጨዋወት ስልት በአገር ውስጥ ትችትን ቢያስከትልም ጠንካራ ሆኖ ወደ ደቡብ አፍሪቃ መጓዙ ነው የሚነገረው። የሆነው ሆኖ ሁሉም ነገር በውድድዱ ሂደት የሚታይ ይሆናል። በተረፈ የፊታችን ረቡዕና ሐሙስ ሣምንት የግማሽ ፍጻሜው ግጥሚያዎች የሚካሄዱ ሲሆን ተጋጣሚዎቹ የምድብ አንድ አሸናፊ ከምድብ ሁለት ሁለተኛ፤ እንዲሁም የምድብ አንድ ሁለተኛ ከምድብ ሁለት አንደኛ ይሆናሉ። የኮንፌደሬሺኑ ዋንጫ ፍጻሜ ግጥሚያ የሚካሄደው ደግሞ ጆሃንስበርግ ላይ የፊታችን ዕሑድ ሣምንት ነው። በውድድሩ ሂደት ደመቅ ያሉ ጨዋታዎች እንደሚታዩ ተሥፋ እናደርጋለን።

በእግር ኳሱ ዓለም ሌላው ሰሞኑን ብዙ ሲያነጋግር፤ አንዱን ሲያስገርም ሌላውንም ሲያስቆጣ የሰነበተው ነገር በተጫዋቾች ግዢው ገበያ ላይ ወሰን እያጣ የሄደው የገንዘብ ፍሰት ነው። እርግጥ የአውሮፓ ቀደምት ክለቦች ድንቅ ተጫዋቾችን በሚሊዮኖች ሲገዙና ሲሸጡ መኖራቸው አዲስ ነገር አይደለም። ጉዳዩን አሁን እስከ ዩኤፋ ባለሥልጣናት ድረስ የትችት መንስዔ ያደረገው የገንዘቡ ጣራ መጠን እያጣ በመሄዱ ነው። የስፓኙ ቀደምት ክለብ ሬያል ማድሪድ ከባርሤሎና ጥላ ለመውጣት ዘንድሮ የፈጀውን ያህል ይፍጅ ቆርጦ በመነሣቱ የፖርቱጋሉን ኮከብ ክሪስቲያኖ ሮናልዶን ከማንቼስተር ዩናይትድ በሬኮርድ 131 ሚሊዮን ዶላር፣ የብራዚሉን ካካ በ 95 ሚሊዮን ገዝቷል። በስፓኙ ብሄራዊ ቡድን ተጫዋች በዴቪድ ቪያም ላይ እንዲሁ ገፍ ገንዘብ ነው የሚፈሰው።

በዚህ ብቻም አልበቃም፤ ክለቡ ለጀርመን ቡንደስሊጋ ክለብ ለባየርን ሙንሺን የሚጫወተውን የፈረንሣይ ብሄራዊ ቡድን ባልደረባ ፍራንክ ሪቤሪን ከ 60 ሚሊዮን ዶላር በሚበልጥ ገንዘብ ለመግዛት፤ ሌሎች አሉ የተባሉ ከዋክብትንም ለማሰባሰብ በመጣሩ እንደቀጠለ ነው። የክለቡ ፕሬዚደንት ፍሎሬንቲኖ ፔሬዝ በዓለምአቀፉ የፊናንስ ቀውስ ሳቢያ በአገራቸው ሥራ አጦች በተበራከቱበት ሰዓት ይህን ያህል ገንዘብ በማፍሰሳቸው በሞራል ዓልባነት በመወቀስ ላይ ናቸው። ከዚሁ ሌላ አንድ ወጣት ተጫዋች ይህን ያህል ገንዘብ ማውጣት አለበት ወይ? የሚለው ጥያቄ ብዙ እያነጋገረ ነው።

የአውሮፓ እግር ኳስ ፌደሬሺኖች ማሕበር የዩኤፋ ፕሬዚደንት ሚሼል ፕላቲኒ ሬያል ማድሪድ ለክሪስቲያኖ ሮናልዶ የሚያፈሰውን ገንዘብ ሲበዛ የተጋነነ ነው ብሎታል። ሌሎች የክለቦች ባለሥልጣናትም ተመሳሳይ ትችት ነው የሚሰነዝሩት። የፌደሬሺኖቹ ጥላ ድርጅት ለተጫዋች ግዢ የሚያወጣው ገንዘብ ገደብ እንዲደረግበት በፍጥነት አንድ ደምብ ማስፈኑ ግድ ነው። አለበለዚያ የክለቦችን ዕድገት የተጣጣመ ማድረጉ ከባድ እየሆነ እንደሚሄድ አንድና ሁለት የለውም።

በተረፈ ስዊድን ውስጥ ከ 21 ዓመት በታች ወጣቶች የዓለም እግር ኳስ ዋንጫ ውድድር ዛሬ ይከፈታል። በሁለት ምድቦች ተከፍሎ በሚካሄደው የመጀመሪያ ዙር ማጣሪያ ማምሿውን ስፓኝ ከጀርመን፤ እንዲሁም እንግሊዝ ከፊንላንድ ይጋጠማሉ። አስተናጋጇ ስዊድን በነገው ዕለት ከቤላሩስ የምትገናኝ ሲሆን ሁለተኛው የምሽቱ ግጥሚያ የሚካሄደው ደግሞ በኢጣሊያና በሰርቢያ መካከል ነው። የፍጻሜው ግጥሚያ ሰኔ 22 ቀን ማልመ ላይ ይካሄዳል።

MM/DW/RTR/AFP/AA