የስፖርት ዘገባ | ስፖርት | DW | 08.06.2009
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ስፖርት

የስፖርት ዘገባ

ደቡብ አፍሪቃ ውስጥ የሚካሄደው መጪው የዓለም እግር ኳስ ዋንጫ ፍጻሜ ውድድር ሊከፈት የቀረው አንድ ዓመት ገደማ ያህል ነው። ዝግጅቱ ተሥፋ ሰጭ ሲሆን ሣምንቱን በዓለም ዙሪያ በርካታ ማጣሪያ ግጥሚያዎች ተካሂደዋል።

የዓለም ዋንጫ ስታዲዮም ግንቢያ

የዓለም ዋንጫ ስታዲዮም ግንቢያ

እግር ኳስ

ደቡብ አፍሪቃ በክፍለ-ዓለሚቱ የመጀመሪያው የሆነውን የዓለም ዋንጫ ፍጻሜ ውድድር በማዘጋጀቱ ረገድ ብቃት ይኑራት-አይኑራት እስከ አንድ ዓመት ገደማ በፊት ድረስ አጠያያቂ ያደረጉት ተጠራጣሪዎች ጥቂቶች አልነበሩም። የወንጀል መስፋፋት፣ የሕዝብ ማመላለሻ ዘዴ እጥረትና ያልተጣጣመ መዋቅራዊ ይዞታ አገሪቱን ይህን መሰል ፌስታ ለማዘጋጀት የሚያበቃት አይደለም ነበር የተባለው። ሆኖም የደቡብ አፍሪቃ አዘጋጆችና የጉዳዩ ባለቤት የዓለም እግር ኳስ ፌደሬሺኖች ማሕበር ፊፋ ግን አገሪቱ የተሳካ መንተንግዶ ለማድረግ እንደምትበቃ በተደጋጋሚ ሲያስረግጡ ነው የቆዩት።

በዕውነትም በተለያዩ ምክንያቶች በጅምሩ አስቸጋሪና የተጎተተ መስሎ የታየው ዝግጅት ዛሬ ከሞላ-ጎደል ጊዜውን ጠብቆ እየተራመደ ነው። በፊታችን ሣምንት የአገሪቱ ብቃት መፈተሻ ሆኖ የሚታየው የኮንፌደሬሺን ዋንጫ ውድድር የሚካሄድባቸው አራት ስታዲዮሞች ታድሰው አብቅተዋል፤ የተቀረው ዝግጅትም በሚያበረታታ ሁኔታ እንደቀጠለ ነው። በነገራችን ላይ በኮንፌደሬሺኑ ዋንጫ ውድድር የሚሳተፉት የዓለም ሻምፒዮኗ ኢጣሊያ፣ የአውሮፓ ሻምፒዮን ስፓኝ፣ ያለፈው ኮንፌደሬሺን ዋንጫ አሸናፊ ብራዚል፣ የአፍሪቃ ዋንጫ ባለቤት ግብጽ፤ እንዲሁም ኢራቅ፣ ኒውዚላንድ፣ አሜሪካና አስተናጋጇ ደቡብ አፍሪቃ ናቸው።
ውድድሩ በሚካሄድባቸው ስታዲዮሞች አኳያ አሥር ሺህ ፖሊሶች ጸጥታን እንዲያስከብሩ ይመደባሉ። ደቡብ አፍሪቃ የዓለም ዋንጫ ስታዲዮሞቿን ግንቢያ ከውድድሩ ግማሽ ዓመት በፊት በፊታችን ታሕሣስ ወር እንደምታጠናቅቅና ዓለም ከዚህ ቀደም ያላየውን ትርዒት ዕውን እንደምታደርግ አገሬው ባለሥልጣናት እርግጠኞች ናቸው። እንግዲህ መላው አፍሪቃ የሚኮራበት ዝግጅት እንደሚሆን ነው የሚጠበቀው። እስካሁን 430 ሺህ ገደማ የሚደርስ ቲኬት መሸጡ ውድድሩ ከወዲሁ ምን ያህል በጉጉት እንደሚጠበቅ የሚያሳይ ነው።
ከዚሁ ሌላ ከዓለም ዙሪያ 450 ሺህ የእግር ኳስ አፍቃሪዎች ወደ አገሪቱ እንደሚጎርፉ የሚጠበቅ ሲሆን የሆቴልና መሰል አገልግሎት አሰጣጡ እርግጥ በዚያው መጠን መዘጋጀት ይኖርበታል። በተረፈ በሕንድና በአትላንቲክ ውቂያኖስ አኳያ በሚገኙት ከተሞች የሚገኙት ስታዲዮሞች አቀማመጥ ራሱ አገር ጎብኚን እጅጉን የሚማርክ ነው። ይህ በዚህ እንዳለ ሰንበቱን ለዚሁ ፍጻሜ ውድድር ለመድረስ በሚደረገው ትግል በዓለም ዙሪያ በርካታ የዓለም ዋንጫ ማጣሪያ ግጥሚያዎች ተካሂደዋል። ሣምንቱ ታዲያ አንዳንድ አገሮች ቀድመው ማለፋቸውን ያረጋገጡበትም ነበር። በአውሮፓ ለፍጻሜው በማለፍ ኔዘርላንድ የመጀመሪያዋ ሆናለች፤ ቀደም ሲል ጃፓን፣ አውስትራሊያና ደቡብ ኮሪያም እንዲሁ ፈተናቸውን ተወጥተዋል።

በላቲን አሜሪካ ምድብ እንጀምርና የአምሥት ጊዜዋ የዓለም ዋንጫ ባለቤት ብራዚል ባለፈው ቅዳሜ ኡሩጉዋይን 4-0 በማሸነፍ አመራሩን ልትይዝ በቅታለች። ብራዚልን ለቁንጮነት ያበቃው እስካሁን ቀደምት ሆና የቆየችው የፓራጉዋይ በቺሌ 2-0 መረታት ነው። ለብራዚል አራቱን ጎሎች ያስቆጠሩት ዳኒየል አልቬስ፣ ሁዋን፣ ሉዊስ ፋቢያኖና ካካ ነበሩ። ለወትሮው በማጥቃት ስልቱ የሚታወቀው የብራዚል ቡድን ድል እርግጥ አስደናቂ ቢሆንም በሌላ በኩል በመከላከል ላይ የተመሠረተ አጨዋወቱ በአሠልጣኙ ታክቲክ ላይ በተለይ በአገር ውስጥ ብዙ ወቀሣን አስነስቷል። ከቀድሞዎቹ የብራዚል ኮከቦች አንዱ ቶስታኦ የዱንጋን ስልት ከኢጣሊያው ካቴናቾ፤ ግጥም አድርጎ ዘግቶ የመጫወት ዘይቤ ነው ያመሳሰለው።

ለማንኛውም ብራዚል በ 24 ነጥቦች የምትመራ ስትሆን ፓራጉዋይም በጎል ልዩነት ብቻ በመበለጥ በተመሳሳይ ነጥብ ሁለተኛ ናት። ሁለቱ ብሄራዊ ቡድኖች ከነገ በስቲያ ረቡዕ እርስበርስ ይገናኛሉ። በተቀረ ቺሌ ሶሥተኛ እንደሆነች ስትቀጥል ከሁለት ወራት በፊት ሳይጥበቅ በቦሊቪያ 6-1 ተቀጥታ የነበረችው አርጄንቲናም ኮሉምቢያን 1-0 አሸንፋ በማገገም አራተኛ እንደሆነች ነው። አምሥተኛ ኡሩጉዋይ! አሥር ሃገራትን ካቀፈው የላቲን ምድብ ለደቡብ አፍሪቃው የዓለም ዋንጫ በቀጥታ የሚያልፉት አራት ቡድኖች ናቸው።

በሰሜንና ማዕከላዊ አሜሪካ በኮንካካፍ ማጣሪያ ምድብ ደግሞ ሜክሲኮ በኤል-ሣልቫዶር 2-1 ስትሸነፍ ወደ አምሥተኛው ቦታ አቆልቁላለች። በአንጻሩ ዩ.ኤስ.አሜሪካ ሆንዱራስን በተመሳሳይ ውጤት ስታሸንፍ በተሻለ ሁኔታ ላይ ነው የምትገኘው። ምድቡን በአንደኝነት የምትመራው ትሪኒዳድና ቶባጎን 3-2 የረታችው ኮስታ-ሪካ ናት። ከሰንበቱ ውጤት በኋላ አዩ.ኤስ.አሜሪካ ከኮስታ-ሪካ ቀጥላ ሁለተኛ ናት፣ ኤል-ሣልቫዶር ደግሞ በሶሥተኝነት ትከተላለች። ከምድቡ ለዓለም ዋንጫ ፍጻሜ የሚያልፉት የመጀመሪያዎቹ ሶሥት አገሮች ሲሆኑ አራተኛው ከላቲን አሜሪካ አምሥተኛ ጋር ተጨማሪ ግጥሚያ ማካሄድ ይኖርበታል።

በአፍሪቃ የዓለም ዋንጫው ማጣሪያ ሃያል ለሚባሉት ግብጽንና ካሜሩንን ለመሳሰሉት አገሮች ይበልጥ የፈተና ጉዞ እየሆነ ነው። በምድብ አንድ ውስጥ ካሜሩን ከሞሮኮ ባዶ-ለባዶ በመለያየት በአራተኛና መጨረሻ ቦታ እንደተወሰነች ቀጥላለች። ምድቡን በስድሥት ነጥቦች የምትመራው ትናንት ቶጎን 3-0 የሽኘችው ጋቦን ናት። ቶጎ በሶሥት ነጥቦች ሁለተኛ ስትሆን እያንዳንዳቸው አንዲት ነጥብ ይዘው ከታች ወደ ላይ ተመልካች የሆኑት ቀደምት ይሆናሉ ተብለው የተጠበቁት ሞሮኮና ካሜሩን ናቸው። በምድብ ሁለት ቱኒዚያ ሞዛምቢክን 2-0 ስትረታ ናይጄሪያ ደግሞ ኬንያን 3-0 አሸንፋለች። ቱኒዚያ በስድሥት ነጥቦች አንደኛ፣ ናይጄሪያ በአራት ሁለተኛ! ኬንያ በባዶ ነጥብ የመጨረሻዋ ናት።
ምድብ ሶሥትን አልጄሪያና ዛምቢያ በእኩል አራት ነጥም የሚመሩ ሲሆን ያስገርማል መጨረሻዋ ሃያሏ የአፍሪቃ ዋንጫ ባለቤት ግብጽ ናት። የግብጽን ብሄራዊ ቡድን ከዚህ ከባድ ፈተና ላይ የጣለው በአልጄሪያ 3-1 መሸነፉ ነው። እንደ ሩዋንዳ ሁሉ አንዲት ነጥብ ብቻ ናት ያለችው። የካሜሩንና የግብጽ የዓለም ዋንጫ ተሳትፎ ዕድል እያለቀለት ይሆን? ሁለቱም ተሥፋውን ሕያው ለማድረግ በመጪዎቹ ግጥሚያዎች ማሸነፋቸው ግድ ነው። በምድብ አራት ጋና ማሊን 2-0 በማሽነፍ አመራሩን ለብቻዋ ስትይዝ ቤኒንም ሱዳንን 1-0 በመሸኘት ሁለተኛ ናት። በምድብ አምሥት አይቮሪ ኮስት ጊኒን 2-1 ፤ እንዲሁም ቡርኪና ፋሶ ማላዊን 1-0 አሸንፋው በእኩል ስድሥት ነጥብ ይመራሉ። ጊኒና ማላዊ አንዳች ነጥብ የላቸውም።

ወደዚህ ወደ አውሮፓው ማጣሪያ እንመለስና ከሰንበቱ ግጥሚያዎች በኋላ ኔዘርላንድ ለፍጻሜ ማለፏን ቀድማ ስታረጋግጥ ሌሎች ታላላቅ ቡድኖችም ግባቸውን መቃረባቸው አልቀረም። በምድብ አንድ ዴንማርክ ስዊድንን 1-0 በመርታት አመራሯን ስታጠናክር የሚያስገርም ሆኖ በሁለተኝነት የምትከተለው ሁንጋሪያ ናት። የስዊድን ብሄራዊ ቡድን በበኩሉ በገዛ አገሩ በደረሰበት ሽንፈት ያለቀለት ነው የሚመስለው። በዚህ ምድብ ውስጥ በተለይ ብዙ የተጠበቀባት ሶሥተኛዋ ፖርቱጋልም አልባኒያን 2-1 ብትረታም ከዓለም ዋንጫው ፍጻሜ ለመድረስ መብቃቷ ያጠያይቃል።
በምድብ ሁለት መሪዋ ግሪክ፣ ስዊትዘርላንድ፣ ሊቱዋኒያና እሥራኤል የሚለያዩት በአራት ነጥቦች ሲሆን ፉክክሩ እንደተጠናከረ ይቀጥላል። ስሎቫኪያና ሰሜን አየርላንድ ደግሞ ሶሥተኛውን ምድብ በቀደምትነት ይመራሉ። ሶሥተኛዋ ፖላንድም ጥቂት ተሥፋ ሲኖራት ቼክ ሬፑብሊክ በአንጻሩ ያከተመላት ነው የሚመስለው። በምድብ አራት ጀርመን አመራሩን እንደያዘች ሲሆን ሩሢያና ፊንላንድም ዕድላቸውን እንደጠበቁ ነው።

በምድብ አምሥት የአውሮፓ ሻምፒዮን ስፓኝ ስድሥት ግጥሚያዎቹን በሙሉ በማሸነፍ በ 18 ነጥቦች የበላይ ነው። ቦስና በ 12 ነጥቦች ሁለተኛ ስትሆን አራት ነጥቦች ወረድ ብላ በሶሥተኝነት የምትከተለው ቱርክ ናት። እንግሊዝም በምድብ ስድሥት እስካሁን መላ ግጥሚያዎቿን ስታሸንፍ ክሮኤሺያና ቤላሩስ ተከታዮቿ ናቸው። እንግሊዝ ከነገ በስቲያ የምትጋጠመው ከአንዶራ ጋር ሲሆን የዓለም ዋንጫ ተሳትፎዋን ቀድማ ለማረጋገጥ ትልቅ ዕድል ነው ያላት። የምድብ ስምንትና ዘጠኝ መሪዎች ደግሞ ኢጣሊያና ፈተናዋን ከወዲሁ የተወጣችው ኔዘርላንድ ናቸው። በነገራችን ላይ ከአውሮፓው ማጣሪያ የየምድቡ አንደኞች ለዓለም ዋንጫው ፍጻሜ በቀጥታ ያልፋሉ። የተቀሩት አራቱ የሚውጣጡት ስምንት የተሻሉ የየምድቡ ሁለተኞች በደርሶ መልስ ግጥሚያ ተወዳድረው ይሆናል።

አትሌቲክስ

በዩ.ኤስ.አሜሪካ-ኦሬገን ትናንት ተካሂዶ በነበረ ዓለምአቀፍ የአትሌቲክስ ውድድር አንዳንድ ግሩም ውጤቶች ተመዝግበዋል። የቤይጂንግ ኦሎምፒክ የአራት መቶ ሜትር የወርቅ ሜዳይ ተሸላሚ አሜሪካዊው ላሽዋን ሜሪት አዘውትሮ ባልተለመደ ሶሥት መቶ ሜትር ሩጫ በተለየ ጥንካሬ ሲያሸንፍ የዚህ ዓመት ዋነኛ ግቡ በጥቂት ሣምንታት ውስጥ በዚህ በበርሊን በሚካሄደው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ላይ ድል መጎናጸፉ ነው። ሌላው አስደናቂ ውጤት አሜሪካዊው ድዋይት ፊሊፕስ በርዝመት ዝላይ ያስመዘገበው ነበር።
የሁለት ጊዜው የዓለም ሻምፒዮንና የአንዴው የኦሎምፒክ ወርቅ ተሸላሚ 8,74 ሲዘል ወደ ቀድሞ ክብሩ ለመመለስ እንደሚፈልግ ግልጽ አድርጓል። ሁለተኛ የሆነው የቤይጂንጉ ኦሎምፒክ አሸናፊ ፓናማዊው ኢርቪንግ ሣላዲኖ ነበር። በተረፈ ከብዙ በጥቂቱ በአንድ ማይል ሩጫ ሁለት የኬንያ አትሌቶች ተከታትሎ በመግባት ሲያሸንፉ በሶሥት ሺህ ሜትር መሰናክልም ድሉ የኬንያ ነበር። ጋሪይ ሮባ ከኢትዮጵያ ሁለተኛ ወጥቷል። ሌላው አስደሳች ዜና በሴቶች 1,500 ሜትር ሩጫ ገለቴ ቡርቃ አሸናፊ መሆኗ ነው።

ቴኒስ

ፓሪስ ላይ ሲካሄድ የሰነበተው የፍሬንች-ኦፕን ታላቅ የቴኒስ ውድድር እሸናፊ የስዊሱ ሮጀር ፌደረር ሆነ። ፌደረር ለዚህ ክብር የበቃው 1 ሰዓት ከ 55 ደቂቃ በፈጀ ጊዜ የስዊድን ተጋጣሚውን ሮቢን ሶደርሊንግን በሶሥት ምድብ ጨዋታ 6-1, 7-6, 6-4 በማሸነፍ ነው። ብዙም ያልታወቀው ስዊድናዊ በውድድሩ አራተኛ ዙር የስፓኙን ኮከብና ያለፉትን ዓመታት ባለድል ራፋኤል ናዳልን አሸንፎ በማስወጣት ዓለምን ማስደነቁ አይዘነጋም።
በናዳል ከዙፋኑ እስከወረደ ድረስ በዓለም የቴኒስ ማዕረግ ተዋረድ ላይ ቀደምቱ የነበረው የስዊሱ ሮጀር ፌደረር እርግጥ በስፖርቱ መድረክ ላይ ብዙ ድሎችን አስመዝግቧል። ግን ፓሪስ ላይ የመጀመሪያው መሆኑ ነው። ስለዚህም እንባ የተዋሃደው ደስታው ወሰን አልነበረውም። በሴቶች ፍጻሜ ደግሞ ሁለቱ የሩሢያ ከዋክብት ስቬትላና ኩዝኔትሶቫና ዲናራ ሳፊና ሲገናኙ ኩዝኔትሶቫ በለየለት 6-4, 6-2 ውጤት በማሸነፍ ለሁለተኛ ታላቅ ድሏ በቅታለች።

ለማጠቃለል ቱርክ-ኢስታምቡል ላይ በዚህ ሰንበት የተካሄደው የፎርሙላ-አንድ አውቶሞቢል እሽቅድድም አሸናፊ እንደገና የብሪታኒያው ጄንሰን ባተን ሆኗል። የአውስትራሊያው ማርክ ዌበር ሁለተኛ ሲወጣ እሽቅድድሙን በሶሥተኝነት የፈጸመው ወጣቱ ጀርመናዊ ዘዋሪ ዜባስቲያን ፌትል ነበር። ባተን ከትናንቱ ውጤት ወዲህ በአጠቃላይ 61 ነጥቦች ይመራል። ብራዚላዊው ሩበን ባሪቼሎ በ 35 ነጥቦች ሁለተኛ ሲሆን ሶሥተኛው ፌትል ነው።

MM/RTR/AFP