የስፖርት ዘገባ | ስፖርት | DW | 11.05.2009
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ስፖርት

የስፖርት ዘገባ

እግር ኳሰ፣ አትሌቲክስ፣ ሆኬይ፣ የአውቶሞቢል እሽቅድድም

የሣምንቱ የቡንደስሊጋ ኮከብ ማሪዮ ጎሜስ

የሣምንቱ የቡንደስሊጋ ኮከብ ማሪዮ ጎሜስ

በስፓኝ ፕሪሜራ ዲቪዚዮን የባርሤሎና ሻምፒዮንነት የቅርብ ተፎካካሪው ሬያል ማድሪድ ሰንበቱን በቫሌንሢያ 3-0 ከተሸነፈ በኋላ ከሞላ ጎደል ያለቀለት ጉዳይ ሆኗል። ባርሣ ምንም እንኳ ከቪላርሬያል እኩል ለእኩል 3-3 በሆነ ውጤት ቢወሰንም አመራሩን ወደ ስምንት ነጥቦች ከፍ አድርጓል። ውድድሩ ሊጠናቀቅ ሶሥት ግጥሚያዎች ቀርተው ሳለ ሻምፒዮንነቱን ለማረጋገጥ የምታስፈልገው አንዲት ነጥብ ብቻ ናት። ባርሣ በትናንቱ ግጥሚያው ተከላካዩ ኤሪክ አቢዳል ቀይ ካርድ ተሰጥቶት ከሜዳ በመሰናበቱ ባይዳከም ኖሮ ቪላርሬያልን በመርታት ከወዲሁ ሻምፒዮን ሊሆን በበቃም ነበር። ጨዋታው ሊያበቃ አሥር ደቂቃ ያህል እስከቀረው ድረስ 3-1 በሆነ ውጤት ይመራ ነበር። የቡድኑ ኮከብና ፕሪሜራ ዲቪዚዮኑን 28 ግቦችን በማስቆጠር በጎል አግቢነት የሚመራው ሣሙዔል ኤቶ እንዳለው ከእንግዲህ ዋንጫዋ ከባርሣ ዕጅ ከወጣች ተዓምር ነው የሚሆነው።

በኢጣሊያ ሤሪያ-አም ሁኔታው በጣሙን ተመሳሳይ ነው። ኢንተር ሚላን ምንም እንኳ ከቬሮና ጋር 2-2 ብቻ ቢለያይም የሰባት ነጥብ አመራሩን እንደጠበቀ ሊቀጥል ችሏል። ለዚህም ምክንያቱ በሁለተኝነት የሚከተለው ኤ.ሢ.ሚላንም ከጁቭቱስ 1-1 መለያየቱ ነው። ኢንተር ሚላን በፊታችን ሰንበት በሜዳው ሢየናን ማሸናፉ ከተሳካለት በተከታታይ ለአራተኛ ጊዜ ሻምፒዮንነቱን ያረጋግጣል። በጎል አግቢነት የሚመራው 22 ያስቆጠረው የቦሎኛ አጥቂ ማርኮ-ዲ-ቫኢዮ ነው፤ የኢንተር ስዊድናዊ ኮከብ ዝላታን ኢብራሂሞቪች ደግሞ በ 21 ይከተለዋል።

በጀርመን ቡንደስሊጋ በአንጻሩ በሶሥት ነጥቦች ልዩነት ይመራ የነበረው ቮልፍስቡርግ በሽቱትጋርት 4-1 በመሽነፉ ሻምፒዮናው ይበልጥ እየጠበበ ሄዷል። የመጀመሪያዎቹ አራት ቡድኖች በሁለት ነጥቦች ብቻ ነው የሚለያዩት። ውድድሩ ሊጠናቀቅ ሶሥት ጨዋታዎች ሲቀሩት በመሠረቱ ከአንድ እስከ ስድሥት በአምሥት ነጥቦች ልዩነት የተሰለፉት ቡድኖች በሙሉ ሻምፒዮን የመሆን ዕድል አላቸው። ወደ መጨረሻው ብርክ የያዘው ቀደምቱ ቮልስቡርግና ባየርን ሙንሺን እኩል 60 ነጥብ ሲኖራቸው ባየርን ሻምፒዮንነቱን እንደሚያረጋግጥ የሚተነብዩት ታዛቢዎች ብዙዎች ናቸው። በአንዳንድ ነጥብ ወረድ ብለው በሶሥተኝነትና በአራተኝነት የሚከተሉት ሄርታ-በርሊንና ሽቱትጋርትም ተሥፋ መጣላቸው አልቀረም።

በአንጻሩ ትናንት በብሬመን 2-0 ተሸንፎ ወደታች የተንሸራተተው ሃምቡርግ መልሶ መንሰራራት መቻሉ ያጠራጥራል። ቡድኑ በሁለት ሣምንት ተኩል ጊዜ ውስጥ በቬርደር ብሬመን በተከታታይ ተሸንፎ ከጀርመን ፌደሬሺን ዋንጫና ከዩኤፋ ፍጻሜ ሕልሙ ሲሰናበት የትናንቱም የቡንደስሊጋው ሻምፒዮንነት ተሥፋው ማክተሚያ ሣይሆን አልቀረም። በሊጋው ውድድር ዘንድሮ አቆልቁሎ በአሥረኛ ቦታ ላይ ለሚገኘው ለብሬመን በአንጻሩ ለሁለት ዋንጫዎች ፍጻሜ መድረሱ የጎደለውን ማካካሻ የሚሆነው ነው። ለማንኛውም የዘንድሮው የጀርመን ቡንደስሊጋ ውድድር ፉክክሩ እንደጦፈ ቆይቶ ምናልባት በመጨረሻው ዕለት የሚለይለት ነው የሚመስለው። በጎል አግቢነት በቮልፍስቡርግ ላይ አራቱንም የሽቱትጋርት ግቦች ያስመዘገበው ማሪዮ ጎሜስ በጠቅላላው 23 በማስቆጠር ከቮልፍስቡርጉ ብራዚላዊ አጥቂ ከግራፊት ሊስተካከል በቅቷል።

በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግም ገና አራት ግጥሚያዎች ቀርተው ሳለ የሻምፒዮናው አዝማሚያ በግልጽ ሳይለይለት እንደቀጠለ ነው። ቀደምቱ ማንቼስተር ዩናይትድ ማንቼስተር ሢቲይን 2-0 በመሸኘት የሶሥት ነጥብ ልዩነትን ሳያስነካ ቀጥሏል። እርግጥ ገና አንድ የጎደለ ጨዋታም አለው። ሁለተኛው ሊቨርፑል ዌስት-ሃም-ዩናይትድን 3-0 ሲያሸንፍ ሶሥተኛው ቼልሢይም በአራተኝነት የሚከተለውን አርሰናልን 4-1 ረትቷል። ለቼልሢይ ድሉ በሣምንቱ አጋማሽ ከአውሮፓ ሻምፒዮና ሊጋ ውድድር ላደረገው ስንብት ምናልባት መጽናኛ ሳይሆን አልቀረም። በአጠቃላይ የፕሬሚየር ሊጉ ድል በተለይ የማንቼስተር ዩናይትድና የሊቨርፑል ፉክክር የሰመረበት ሆኖ የሚከርም ነው የሚመስለው። በጎል አግቢነት የቀደምቱ ክለብ ኮከብ ክሪስቲያኖ ሮናልዶ 18 በማስቆጠር አመራሩን ይዟል።

በተቀረ ከኔዘርላንዱ አልክማር ቀጥሎ የኡክራኒያው ክለብ ዲናሞ ኪየቭ ትናንት ታቪያ-ሢምፈሮፖልን 3-2 በመርታት ለ 13ኛ ጊዜ ብሄራዊ ሻምፒዮን ሆኗል። ዲናሞ ገና ሶሥት ጨዋታዎች ቀርተው ሳለ ቀድሞ ሻምፒዮንነቱን ያረጋገጠው ባለፈው ሐሙስ ከዩኤፋ ዋንጫ ፍጻሜ ያገደውን ሻክታር ዶኔትስክን በ 12 ነጥቦች ልዩነት በማስከተል ነው። ዲናሞ ኪየቭ ገና በሶቪየቱ ዘመን በአውሮፓ ሃያል ከሚባሉት ክለቦች አንዱ እንደነበር ይታወቃል። ይህን ለትውስት ያህል፤ የአውሮፓን ሻምፒዮና ካነሣን አይቀር የዘንድሮው የሻምፒዮና ሊጋ ውድድር ፍጻሜ እንዳለፈው ዓመት የእንግሊዝ ክለቦች ማንቼስተር ዩናይትድና ቼልሢይ መልሰው የሚገናኙበት ሣይሆን ቀርቷል። ያለፈው ዓመት ሻምፒዮን ማቼስተር ዩናይትድ የግማሽ ፍጻሜ ተጋጣሚውን አርሰናልን በመጀመሪያው ግጥሚያ 1-0 ከረታ በኋላ በመልሱም 3-1በማሸነፍ በለየለት ሁኔታ ነው ለፍጻሜ የደረሰው።

በአንጻሩ በቼልሢይና በባርሤሎና መካከል የተካሄዱት ግጥሚያዎች ትዕግሥት የሚያስጨርሱ ነበሩ። ሁለቱ ክለቦች ስፓኝ ውስጥ በተካሄደው የመጀመሪያ ግጥሚያ ባዶ ለባዶ ሲለያዩ በሁለተኛው ግጥሚያም ቼልሢይ በኤሢየን ግሩም ጎል አማካይነት ለረጅም ጊዜ መምራቱ ባርሤሎናን አልቆለታል አሰኝቶ ነበር። ይሁንና በወቅቱ በዓለም ላይ ጠንካራው እንደሆነ የሚነገርለት ቡድን መደበኛው ጊዜ ካበቃ በኋላ በ 93ኛዋ ደቂቃ ላይ በኢኒየስታ አማካይነት ባስቆጠራት ግብ ለፍጻሜ በቅቷል። ቼልሢይ በሁለቱም ግጥሚያዎች ግጥም አድርጎ ዘግቶ በመጫወት ለስኬት ለመብቃት ያደረገው ሙከራ ለራሱ መሰናክል ነው የሆነበት። የዋንጫው ጨዋታ የሚካሄደው ሮማ ላይ ነው። በዩኤፋ ዋንጫ ፍጻሜ ደግሞ የጀርመኑ ቬርደር ብሬመንና የኡክራኒያው ሻክታር ዶኔትስክ ቱርክ-ኢስታምቡል ላይ ይገናኛሉ።

አትሌቲክስ

የኬንያ አትሌቶች ባለፈው ሣምንትም በየቦታው በተካሄዱ ዓለምአቀፍ ውድድሮች እንደገና ልዕልና አሳይተዋል። በዚህ በጀርመን ትናንት በርሊን ላይ በተካሄደ የ 25 ኪሎሜትር ሩጫ ከአንድ እስከ ሶሥት ተከታትለው የገቡት ኬንያውያን ነበሩ። ማቲው ኮች በዚህ ርቀት የዓመቱን ፈጣን ጊዜ በማስመዝገብ ሲያሸንፍ ፍሬድ ኮስጋይ ሁለተኛ፤ እንዲሁም ሉክ ኪቤት ሶሥተኛ በመሆን ሩጫውን ፈጽመዋል። በሴቶችም ያሸነፈችው ኬንያዊቱ አትሌት ፔኒና አሩሣይ ነበረች።

ባለፈው አርብ ካታር ላይ በተካሄደ የአትሌቲክስ ግራን-ፕሪ ውድድርም ኬንያውያን በወንዶች ሶሥት ሺህ ሜትር መደበኛና መሰናክል ሩጫዎች ከአንድ እስከ ሶሥት በመከታተል ሲያሸንፉ በ 800 ሜትር አስቤል ኪፕሮፕ ቅድሚያውን ለሱዳኑ አቡባከር ካኪ መስጠቱ ግድ ሆኖበታል። በ 1,500 ሜትር ኬንያዊው አውጉስቲን ቾጌ ሲያሸንፍ ሃሮን ካይታኒ ሁለተኛ ሆኗል፤ በሶሥተኝነት ሩጫውን የፈጸመው ደግሞ ኢትዮጵያዊው ደረሰ መኮንን ነው። በሴቶች 1,500 ሜትር ገለቴ ቡርካ ኬንያዊቱን ቪቪያን ቼሩዮትን አስከትላ ስታሽንፍ መስከረም አሰፋ አሥረኛ ወጥታለች። በሶሥት ሺህ ሜትር መሰናክል ደግሞ ኬንያዊቱ ሩት ኒያንጋው አንደኛ ስትሆን ከኢትዮጵያ ዘምዘም አሕመድ ሁለተኛ፤ ሶፊያ አሰፋ ሶሥተኛ፤ እንዲሁም መቅደስ በቀለ አምሥተኛ በመሆን ውድድሩን ፈጽመዋል።

ወደ እግር ኳሱ ዓለም መለስ እንበልና ደቡብ አፍሪቃ ውስጥ በ 2010 ዓ.ም. የሚካሄደው የዓለም ዋንጫ ፍጻሜ ውድድር ቀስ በቀስ መቃረብ እየያዘ ነው። በዝግጅቱ ሂደት በተለይ የስታዲዮም ግንቢያው ጉዳይ በሥራ ማቆም ዓድማና ሌሎች ምክንያቶች ለአዘጋጆቹ የራስ ምታት የሆነበት ጊዜ ጥቂት አልነበረም። ዝግጅቱ በተመደበለት ጊዜ መጠናቀቁም ብዙ አከራክሯል። ይሁንና አሁን እንደሚነገረው የዓለም ዋንጫው ውድድር መክፈቻና ፍጻሜ ግጥሚያዎች የሚካሄዱበት የጆሃንስበርግ ስታዲዮም የሶከር-ሢቲይ ግንቢያ ጊዜውን ተከትሎ በመጠናቀቅ ላይ ነው። በሌሎች ከተሞችም ዝግጅቱ ተጠናክሮ ቀጥሏል።
94 ሺህ ተመልካቾችን የሚይዘው ታላቁ የጆሃንስበርግ ስታዲዮም በመጪው በልግ፤ በጥቂት ወራት ውስጥ ለዓለም አግር ኳስ ፌደሪሺኖች ማሕበር ለፊፋ በይፋ ይረከባል። የስታዲዮሙን ዘመናዊ ጣራ የሚሰራው የጀርመን ኩባንያ ሃይቴክስ ሲሆን 75 የደቡብ አፍሪቃ ሙያተኞችም በዚሁ ተግባር ተሰማርተው ይገኛሉ። ኩባንያው ከብዙ በጥቂቱ በደቡብ አፍሪቃ የፑዛን የዓለም ዋንጫ ስታዲዮምና የበርሊን ኦሎምፒክ ስታዲዮም ግንቢያዎች የተሳተፈ ታዋቂ ኩባንያ ሲሆን ሶከር-ሢቲይ በአስተማማኝ ሁኔታ ለመጠናቀቁ ከእንግዲህ ብዙም ጥርጣሬ አይኖርም። እንግዲህ በአፍሪቃ ምድር ለመጀመሪያ ጊዜ የሚካሄደው የዓለም ዋንጫ ፍጻሜ ውድድር ግሩም ፌስታ ሊሆን እየተቃረበ ነው።

ለማጠቃለል፤ የብሪታኒያው ፎርሙላ-አንድ አውቶሞቢል ዘዋሪ ጄንሰን ባተን ትናንት የስፓኝ ግራን-ፕሪ እሽቅድድም አሸናፊ ሆኗል። ለባተን የትናንቱ ድል የዘንድሮው የፎርሙላ-አንድ ውድድር ከተጀመረ ወዲህ ከአምሥት አራተኛው መሆኑ ነው። ብራዚላዊው ሩበን ባሪኬሎ ሁለተኛ ሲሆን የአውስትራሊያው ማርክ ዌበር ሶሥተኛ ወጥቷል። ስዊትዘርላንድ ውስጥ በተካሄደው የዓለም የበረዶ ሆኬይ ሻምፒዮና ደግሞ ሩሢያ ትናንት ካናዳን በፍጻሚው ግጥሚያ 2-1 በማሸነፍ በተከታታይ ለሁለተኛ ጊዜ ለድል በቅታለች። ሩሢያ ባለፈው ዓመት በካናዳ ምድር በተጨማሪ ጊዜ 5-4 በማሸነፍ ሻምፒዮን መሆኗ ይታወሣል። የካናዳ ቡድን ትናንት የተሸነፈው አንድ-ለባዶ ከመራ በኋላ ነው። በተረፈ ለሶሥተኝነት በተካሄደ ግጥሚያ ስዊድን አሜሪካን 4-2 በመርታት የናስ ሜዳሊያ ተሸላሚ ሆናለች።

MM/AA/DW/RTR/AFP