የስፖርት ዘገባ | ስፖርት | DW | 29.04.2009
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ስፖርት

የስፖርት ዘገባ

እግር ኳስ፣ አትሌቲክስ፣ ቴኒስ፣ ቡጢ፣ የአውቶሞቢል እሽቅድድም!

የለንደን ማራቶን

የለንደን ማራቶን

አትሌቲክስ

የሣምንቱ ታላቅ የአትሌቲክስ ውድድር ትናንት ለንለን ላይ የተካሄደው የማራቶን ሩጫ ነበር። በዚሁ ውድድር በወንዶች የቤይጂንጉ ኦሎምፒክ ባለድል ኬንያዊው ሣሚይ ዋንጂሩ አሸናፊ ሆኗል። የፈጀበት ጊዜ 2 ሰዓት ከ 5 ደቂቃ ከአሥር ሤኮንድ ሲሆን ይህም ለለንደን ማራቶን አዲስ ክብረ-ወሰን ነው። ላለፈው ዓመት አሸናፊ ለሌላው ኬንያዊ ማርቲን ሌል በአንጻሩ ለአራተኛ ጊዜ የለንደን ማራቶን አሸናፊ ለመሆን የነበረው ሕልም ዕውን አልሆነለትም። በታፋ ሕመም ምክንያት ሳይወዳደር ቀርቷል። ሩጫው ጠንካራ ፉክክር የታየበት ሆኖ ሲያልፍ ጸጋዬ ከበደ ከኢትዮጵያ በአሥር ሤኮንዶች ብቻ በመቀደም ሁለተኛ ወጥቷል። ሶሥተኛ ጃዋድ ጋሪብ ከሞሮኮ! ከኤርትራ ተወዳዳሪዎች መካከል ዮናስ ክፍሌ ሰባተኛ ሲወጣ ይበልጥ የተጠበቀበት ታዋቂው ዘረሰናይ ታደሰ ግን በ 35ኛው ኪሎሜትር ላይ ወጥቶ ቀርቷል።

በሴቶች ጀርመናዊቱ ኢሪና ሚኪቴንኮ ልዕልና በታየበት ሁኔታ ያለፈውን ዓመት ድሏን ደግማዋለች። የካዛክስታን ተወላጅ የሆነችው ሚኪቴንኮ ከ 29ኛው ኪሎሜትር በኋላ ፍጥነት በመጨመር ተፎካካሪዎቿን ጥላ ስትበር ሩጫውን የፈጸመችው ግሩም በሆነ የ 2 ሰዓት ከ 22 ደቂቃ ከ 11 ሤኮንድ ጊዜ ነበር። የብሪታኒያ ተወዳዳሪ ማራ ያማኡቺ ሁለተኛ፤ ሊሊያ ሾቡኮቫ ከሩሢያ ሶሥተኛ! ከኢትዮጵያ አትሌቶች መካከል ደግሞ ብርሃኔ አደሬ አምሥተኛ፤ እንዲሁም ጌጤ ዋሚ ዘጠነኛ በመሆን ሩጫውን ፈጽመዋል። በሌላ በኩል ሩሜኒያዊቱ የኦሎምፒክ ሻምፒዮን ኮንስታንቲና ዲታ በትንፋሽ እጥረት የተነሣ ሩጫውን በግማሹ ጥላ ወጥታለች።

ትናንት በዚህ በጀርመን ተካሂዶ በነበረ 24ኛ የሃምቡርግ ከተማ ማራቶን ደግሞ ኢትዮጵያዊው አትሌት ሰለሞን ጽዴ ኬንያዊ ተፎካካሪውን ቻርልስ እንጎሌፑስን አስከትሎ ከግቡ በመድረስ አሸናፊ ሆኗል። የፈጀበት ጊዜ 2 ሰዓት ከ 11 ደቂቃ ከ 47 ሤኮንድ ሲሆን ያን ያህል ፈጣን የሚባል አልነበረም። የስፓኙ ሁሊዮ ሬይ ከሶሥት ዓመታት በፊት ካስመዘገበው የሃምቡርግ ፈጣን ሰዓት ሲነጻጸር ከአራት ሤኮንዶች በላይ የዘገየ ነው። ለማንኛውም የብራዚሉ አትሌት ሆሴ-ቴሌስ-ዴ-ሱዛ ሶሥተኛ በመሆን ሩጫውን ፈጽሟል። በሴቶች አሸናፊ የሆነችው የስፓኛ አሌሣንድራ አጊላር ነበረች። ኢትዮጵያዊቱ ትዕግሥት ሸኒ ደግሞ ሁለተኛ ሆናለች።

እግር ኳስ

በአውሮፓ ቀደምት ዲቪዚዮኖች ውስጥ የሚካሄደው የዘንድሮው ውድድር ቀስ በቀስ ወደ ፍጻሜው እየተጠጋ ባለበት በአሁኑ ጊዜ የሻምፒዮንነቱ ፉክክርም በአብዛኛው ጠባብ እየሆነ በመሄድ ላይ ነው። በኢጣሊያ ሊጋ ቀደምቱ ኢንተር ሰንበቱን በሽንፈት ሲያሳልፍ በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ ማንቼስተርና ሊቨርፑል የሚለያዩት በጥቂት ነጥቦች ብቻ ነው። በጀርመን ቡንደስሊጋም ሣምንቱ የመሪዎቹ ቡድኖች አልነበረም። በፈረንሣይና በስፓኝም እንዲሁ ሁኔታው ከሞላ-ጎደል ተመሳሳይ ነው።

በኢጣሊያ ሤሪያ-አ ውድድሩ ሊጠናቀቅ አምሥት ግጥሚያዎች ብቻ ቀርተው ሳለ ኢንተር ሚላን በናፖሊ 1-0 በመሸነፉ አመራሩ ወደ ሰባት ነጥብ አቆልቁሏል። የዚህ ውጤት ተጠቃሚ ፓሌርሞን አስተማማኝ በሆነ ሁኔታ 3-0 የረታው የኢንተር የከተማ ተፎካካሪ ኤሢ.ሚላን ነው። ከጥቂት ሣምንታት በፊት አልቆለታል የተባለው ኤ.ሢ.ሚላን አሁን በመጨረሻው ሂደት ኢንተር አንድ ሁለቴ ከተንሸራተተ ሻምፒዮን ሊሆን ይችላል። በሌላ በኩል ባለፈው ሣምንት ወደ ሶሥተኛው ቦታ ዝቅ ያለው ጁቬንቱስ ከሬጂና ሁለት-ለሁለት ብቻ ሲለያይ ከእንግዲህ ቀደምት የመሆን ዕድሉ የመነመነ ነው። በጎል አግቢነት 21 በማስቆጠር የቦሎኛው ማርኮ-ዲ-ቫኢዮ ይመራል።

በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ ማንቼስተር ዩናይትድ ከብዙ ትግል በኋላ ቶተንሃም-ሆትስፐርን 5-2 በመርታት ከሽንፈት ሊያመልጥ በቅቷል። ማንቼስተር በ 22 ደቂቃዎች ውስጥ አምሥቱን ጎሎች አስቆጥሮ ዕፎይ ከማለቱ ከዕረፍት በፊት ሁለት-ለባዶ እየተመራ ነበር። ሰውሮታል። በሁለተኛ ቦታ ላይ የሚገኘው ሊቨርፑልም ሃል-ሢቲይን 3-1 ሲሸኝ ሁለቱ ቀደምት ቡድኖች የሚለያዩት በሶሥት ነጥቦች ብቻ ነው። ሶሥተኛው ቼልሢይ በዌስትሃም-ዩናይትድ 1-0 ሲረታ ከማንቼስተር ያለው ልዩነት ወደ ስድሥት ነጥቦች ከፍ ብሏል። ሌላው የሰንበቱ የእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ ቀደምት ዜና የማንቼስተር ዩናይትድ አንጋፋ ተጫዋች ራያን ጊግስ በፕሮፌሺናል እግር ኳስ ተጫዋቾች ማሕበር ለመጀመሪያ ጊዜ የዓመቱ ተጫዋች ተብሎ መመረጡ ነው። የ 35 ዓመቱ ዌልሽ በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ ውስጥ ሲጫወት 12 ዓመታት አሳልፏል።

በስፓኝ ፕሪሜራ ዲቪዚዮን ሻምፒዮን ለመሆን ዕድል ባላችው ብቸኛ ሁለት ክለቦች መካከል የሚደረገው ፉክክር እንደገና ጠበብ ብሏል። አምሥት ግጥሚያዎች ቀርተው ሳለ አሁን ባርሤሎና የሚመራው በአራት ነጥቦች ልዩነት ብቻ ነው። የባርሣ አመራር የጠበበው ቡድኑ ከቫሌንሢያ ጋር ባደረገው ግጥሚያ እኩል-ለእኩል 2-2 በሆነ ውጤት በመወሰኑ ነው። የቅርብ ተፎካካሪው ሬያል ማድሪድ በአንጻሩ ሤቪያን 4-2 በማሸነፍ ዕድሉን ተጠቅሞበታል። ሶሥተኛ ሤቪያ፣ አራተኛ ቫሌንሢያ፣ እንዲሁም ቪላርሬያል አምሥተኛ በመሆን ለመጪው የአውሮፓ ክለቦች ሻምፒዮና ሊጋ ውድድር ተሳትፎ ለሚያበቃው ሶሥተኛ ቦታ መታገላቸውን ይቀጥላሉ። በጎል አግቢነት 27 በማስቆጠር የሚመራው የባርሣው ሣሙዔል ኤቶ ነው፤ የቫሌንሢያው ኮከብ ዴቪድ ቪያ ደግሞ በ 25 ግቦች በቅርብ ይከተለዋል።

በጀርመን ቡንደስሊጋ ቮልፍስቡርግ ትናንት በኮትቡስ 2-0 በመረታቱ አመራሩን ወደ አምሥት ነጥቦች ለማስፋት የነበረው ዕድል ሲያመልጠው የተቀሩት ቀደምት ቡድኖች ሃምቡርግና ባየርን ሙንሺንም በየፊናቸው በመሽነፍ ከቁንጮው ቡድን ጋር በነጥብ ለመስተካከል የተገኘውን አጋጣሚ ሳይጠቀሙበት ቀርተዋል። ቮልፍስቡርግ ከብዙ ግጥሚያዎች በኋላ ትናንት ለሽንፈት የበቃው አሠልጣኙ ፌሊክስ ማጋት እንዳለው በተለይ ያጋጠመውን ዕድል ሁሉ በሚገባ መጠቀም ባለመቻሉ ነው።
“ዕድላችንን በጣም ፍቱን በሆነ መንግድ ከተጠቀምንባቸው ካለፉት ጊዜያት ሲነጻጸር ዛሬ ግሩም አጋጣሚዎችን ገቢር ማድረጉ አልተሳካልንም። ምክንያቱ ምናልባት በአንድ በኩል የራሳችን ድክመት ሊሆን ይችላል። በሌላ በኩል ግሩም በነበረው የኮትቡስ በረኛ በጌርሃርድ ትሬምል ጥንካሬ ጭምር! እና ማሸነፋቸው የሚገባቸው ነው”

በሌላ በኩል ባለፈው ቅዳሜ በገዛ ሜዳው በሻልከ 1-0 የተሽነፈው የጀርመኑ ቀደምት ክለብና የብዙ ጊዜ ሻምፒዮን ባየርን ሙንሺን በአውሮፓ ሻምፒዮና ሊጋ በቅርቡ በባርሤሎና 4-0 ተቀጥቶ መሰናበቱ፤ በፌደሬሺኑ ዋንጫ ውድድር መሰናከሉና በቡንደስሊጋው ውስጥም የተለመደውን ስኬት ማጣቱ የክለቡ ሃላፊዎች ዕርምጃ መውሰዳቸውን ግድ አድርጎታል። ክለቡ ዛሬ ከቡድኑ አሠልጣኝ ከዩርገን ክሊንስማን መለያየቱን ይፋ አድርጓል። የዘንድሮው ውድድር እስኪያበቃ በጊዜያዊነት ተተኪ ሆኖ የተሰየመው አዲስ አሠልጣኝ ዩፕ ሃይንከው ነው። ዩፕ ሃይንከስ ከዚህ ቀደምም እ.ጎ.አ. ከ 1987 እስከ 1991 ዓ.ም. የባየርን አሠልጣኝ ነበር።

ለማንኛውም የሰንበቱ የቡንደስሊጋ ውጤት በአንጻሩ በርሊንንና ሽቱትጋርትን በጅቷል። ሄርታ-በርሊን ሆፈንሃይምን 1-0 በመርታት ወደ ሁለተኛ ወደ ቦታ ከፍ ሲል ሽ’ቱትጋርትም ፍራንክፉርትን 2-0 በማሸነፍ አሁን አራተኛ ነው። ግን የቡንደሊጋው ውድድር ሊፈጸም አምሥት ግጥሚያዎች ቀርተው ሳለ ከአንድ እስከ አምሥት በተሰየሙት ቡድኖች መካከል ያለው የነጥብ ልዩነት ሶሥት ብቻ በመሆኑ ፉክክሩ የጦፈ እንደሆነ ይቀጥላል። በጎል አግቢነት አመራሩን እንደያዘ ያለው አሁንም በውድድሩ ሂደት እስካሁን 22 ግቦችን ያስቆጠረው የቮልፍስቡርግ ብራዚላዊ አጥቂ ግራፊት ነው።

በፈረንሣይ አንደኛ ዲቪዚዮን ኦላምፒክ ማርሤይ ሊልን 2-1 በመርታት ከ 17 ዓመታት በኋላ መልሶ ሻምፒዮን የመሆን ተሥፋውን ሲያጠናክር አንድ ጨዋታ የሚጎለው ዢሮንዲን-ቦርዶው በፊታችን ረቡዕ ቀሪ ግጥያውን ካሸነፈ በሁለት ነጥቦች ብቻ ዝቅ ብሎ ይከተለዋል። ሶሥተኛውና ሰባት ጊዜ በማከታተል የፈረንሣይ ሻምፒዮን የነበረው ኦላምፒክ ሊዮን በአንጻሩ ማቆልቆሉን እንደቀጠለ ነው። በትናንት ግጥሚያው ከፓሪስ-ሣንት-ዠርማን በገዛ ሜዳው ከባዶ-ለባዶ ውጤት ለማለፍ አልቻለም። በመሆኑም አሁን ከማርሣይ ስድሥት ነጥቦች ይለዩታል። በኔዘርላንድ ሻምፒዮና አልክማር ባለፈው ሣምንት ቀድሞ አንደኝነቱን ማረጋገጡ የሚታወስ ሲሆን በፖርቱጋል ሊጋ ደግሞ ፖርቶ በአራት ነጥብ ልዩነት አመራሩን ይዞ በድል አቅጣጫ መራመዱን እንደቀጠለ ነው።

በተቀረ የአውሮፓ ክለቦች ሻምፒዮና ሊላ ግማሽ ፍጻሜ የመጀመሪያ ዙር ግጥሚያዎች በዚህ ሣምንት ዓበይቱ የዓለም ስፖርት አፍቃሪ ማተኮሪያዎች ናቸው። የነገዎቹ ተጋጣሚዎች ባርሤሎናና ቼልሢይ ሲሆኑ፤ የተቀሩት ሁለት የእንግሊዝ ክለቦች ማንቼስተር ዩናይትድና አርሰናል ደግሞ ረቡዕ ምሽት ይገናኛሉ። በሶሥት ሃያል የእንግሊዝ ክለቦች የተከበበው የስፓኙ ባርሣ ዘንድሮ ቢቀር ለፍጻሜ መድረሱ ይሳካለት ይሆን? ሰሞኑን ብዙ እያነጋገረ ያለ ጉዳይ ነው። እርግጥ ባርሤሎና ቀላል ተጋጣሚ አይደለም። አርጄንቲናዊ አጥቂውን ሊዮኔል ሜሢን እንዴት ማቆም ይቻላል? በወቅቱ የቼልሢይን ተጫዋቾችና አሠልጣኝ ናላ ያዞረ ጉዳይ መሆኑ አልቀረም።

ለማንኛውም በአረብ ሻምፒዮና ሊጋ ደግሞ የቱኒዚያው ኤስፔራንስና የሞሮኮው ዊዳድ-ካዛብላንካ ለፍጻሜ ለመድረስ በቅተዋል። ኤስፔራንስ ትናንት የአልጄሪያውን እንቴንቴ-ሴቲፍን በመልስ ግጥሚያ 2-0 ሲረታ በአጠቃላይ 3-0 በሆነ ውጤት ነው ለፍጻሜ ያለፈው። ዊዳድም እንዲሁ የቱኒዚያ ተጋጣሚውን ስፋክሢየንን በአጠቃላይ 3-1 ውጤት አሰናብቷል። ወደ ማዕከላዊው አሜሪካ ስናተኩር ደግሞ ወረርሺኝ ብዙ ሰዎችን በፈጀባት በሜክሢኮ ትናንት አደባባዮች ብቻ አልነበሩም ባዶ ሆነው የታዩት። በተላላፊው በሽታ የተነሣ የእግር ካስ ግጥሚያዎች የተካሄዱትም ተመልካቾች ባሌሉባቸው ወና ስታዲዮሞች ውስጥ ነበር።

ቡጢ/ቴኒስ/አውቶሞቢል

አሜሪካ-ኮኔክቲከት ውስጥ በተካሄደ የዓለም የመካከለኛ ክብደት ቡጢ የማዕረግ ግጥሚያ ብሪታኒያዊው ካርል ፍሮች የአሜሪካ ተጋጣሚውን ጀርሜይን ቴይየርን በመጨረሻዋ ዙር ላይ ለማሸነፍ በቅቷል። እስካሁን አንዴም ተሸንፎ የማያውቀው ካርል ከተዘረረ በኋላ እንደገና አገግሞ በመመለስ ነው የረታው። ዳኛው 12ኛው ዙር, ሊያበቃ ጥቂት ሲቀረው ግጥሚያውን ባያቆም ኖሮ ድሉ የቴይለር ነበር። ግን ቴይለር 14 ሤኮንዶች ሲቀሩት መዘረሩ ላይ ነው ችግሩ! በዚህ በጀርመን ደግሞ የአገሪቱ የዓለም የቡጢ ማሕበር የመካከለኛ ክብደት ሻምፒዮን ፌሊክስ ሽቱርም ጃፓናዊውን ኮጂ ሣቶን በሰባተኛው ዙር ላይ በቃ በማሰኘት አሸንፏል።

በተረፈ በቴኒስ ፌደሬሺን ዋንጫ ውድድር ኢጣሊያ ያለፈውን ዓመት ሻምፒዮን ሩሢያን በአስደናቂ ውጤት በመርታት ከአሜሪካ ጋር ለፍጻሜ ስትደርስ ትናንት ባሕሬይን ላይ የተካሄደው የፎርሙላ-አንድ አውቶሞቢል እሽቅድድም አሸናፊም የብሪታኒያው ጄንሰን ባተን ሆኗል። በአጠቃላይ ነጥብ ባተን ይመራል፤ ሁለተኛ ሩበንስ ባሪኬሎ ሲሆን ሶሥተኛው ወጣቱ ጀርመናዊ ሴባስቲያን ፌትል ነው።

AFP/RTR
መሥፍን መኮንን፣

ተክሌ የኋላ፣