የስፖርት ዘገባ | ስፖርት | DW | 13.04.2009
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ስፖርት

የስፖርት ዘገባ

በአውሮፓ ቀደምት ሊጋዎች እንጀምርና ከእንግሊዝ እስከ ስፓኝ ታላላቆቹ ክለቦች ከሞላ-ጎደል ሁሉም የሰንበት ግጥሚያዎቻቸውን ሲያሸንፉ ከረጅም ጊዜ በኋላ አመራሩን የተነጠቀው የፈረንሣዩ ሻምፒዮን ኦላምፒክ ሊዮን ብቻ ነበር።

ሉሲዮ ባየርን ሙንሺን

ሉሲዮ ባየርን ሙንሺን

እግር ኳስ

በስፓኝ ፕሪሜራ ዲቪዚዮን በሣምንቱ አጋማሽ በአውሮፓ ክለቦች ሻምፒዮና ሊጋ ውድድር አይሎ የታየው ባርሤሎና ሁዌልቫን 2-0 በማሸነፍ የስድሥት ነጥብ አመራሩን አረጋግጦ ቀጥሏል። ሁለተኛው ሬያል ማድሪድም ትናንት ሬያል ቫላዶሊድን በተመሳሳይ ውጤት ሲረታ ቡድኑ ባለፈው ታሕሣስ ወር በባርሤሎና አንዴ ከመሸነፉ በስተቀር እስካሁን አልተደፈረም። የትናንቱ ድሉ ከ 14 ግጥሚያዎች 13ኛው መሆኑ ነበር። ለሬያል ሁለቱን ጎሎች ያስቆጠሩት የቡድኑ አምበል ራውልና የኔዘርላንዱ የክንፍ አጥቂ አርየን ሩበን ናቸው።
ሤቪያ ሶሥተኛ ሲሆን ቫሌንሢያ ደግሞ የአውሮፓው የክለቦች ሻምፒዮና ሊጋ የሩብ ፍጻሜ ተሳታፊ ቪላርሬያል በማላጋ 2-0 በመሸነፉ ወደ አራተኛው ቦታ ከፍ ማለቱ ተሳክቶለታል። ቫሌንሢያ ለዚህ የበቃው ስፖርቲንግ ጊዮንን 3-2 በመርታት ነው። በሌላ በኩል የስፓኝ ፕሪሜራ ዲቪዚዮን ውድድር ሊጠናቀቅ የቀሩት ስምንት ግጥሚያዎች ብቻ ሲሆኑ ከሬያል በ 18 ነጥቦች ዝቅ ብሎ በሶሥተኝነት የሚገኘው ሤቪያ በተለይም ከትናንት ሽንፈቱ ወዲህ የሻምፒዮንነት ሕልም ሊያልም አይችልም። ሁሉም ነገር በባርሣና በሬያል ማድሪድ መካከል የሚለይለት መሆኑ ግልጽ እየሆነ ሄዷል።

በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ አራቱም የአውሮፓ ሻምፒዮና ሊጋ የሩብ ፍጻሜ ዙር ተሳታፊ ክለቦች ማንቼስተር ዩናይትድ፣ ሊቨርፑል፣ ቼልሢይና አርሰናል የሰንበት ግጥሚያቸውን በማሸነፍ በቀደምት ቦታቸው እንዳሉ ናቸው። ማንቼስተር ዩናይትድ ሰንደርላንድን 2-1 ሲረታ እንዳለፈው ሣምንት ሁሉ አሁንም የድሉ ዋስትና የ 17ዓመቱ ኢጣሊያዊ ወጣት ተጠባባቂ ተጫዋች ፌደሪኮ ማቼዳ ነው። ማቼዳ ጎሉን ያስቆጠረው ተቀይሮ ሜዳ ከገባ በኋላ ነበር። ሊቨርፑል ደግሞ ብላክበርን ሮቨርስን በፍጹም ልዕልና 4-0 በማሸነፍ ሁለተኛ ቦታውን አስከብሯል። ሶሥተኛው ቼልሢይ በአንጻሩ ከቦልተን ወንደረርስ ባካሄደው ግጥሚያ ከጅምሩ ያለቀለት መስሎ የታየ ድሉን ከማጣት ለጥቂት ነው ያመለጠው።
ቼልሢይ 4-0 ከመራ በኋላ ሶሥት ጎሎች ተቆጥረውበት በመጨረሻ 4-3 በሆነ ውጤት ነው ግጥሚያውን የፈጸመው። ጨዋታው በዚሁ በማብቃቱ ዕፎይ ሊል ይገባዋል። አርሰናል በአንጻሩ በዊጋን አትሌቲክ ከተመራ በኋላ ተመልሶ 4-1 በማሸነፍ ጥንካሬውን አስመስክሯል። ማንቼስተር ዩናይትድ ከ 31 ግጥሚያዎች በኋላ በ 71 ነጥቦች ይመራል፤ ሊቨርፑል የሚከተለው አንዲት ነጥብ ብቻ ወረድ ብሎ ነው። ቼልሢይም በ 67 ነጥቦች ሶሥተኛ ሲሆን በሻምፒዮናው ውድድር የቅርብ ተፎካካሪ ነው። አርሰናል በ 61 ነጥቦች አራተኛ፤ ኤስተን ቪላና ኤቨርተን ደግሞ ራቅ ብለው ይከተላሉ።

በኢጣሊያ ሊጋ ሤሪያ-አ ቀደምቱ ኢንተር ሚላን ከፓሌርሞ 2-2 ብቻ ቢለያይም ሁለተኛው ጁቬንቱስ በጌኖዋ 3-2 በመሸነፉ አመራሩን ቀረብ ለማለት የነበረውን ዕድል ሳይጠቀምበት ቀርቷል። በመሆኑም ኢንተር ሊጋውን በአሥር ነጥቦች ልዩነት ይመራል። በተቀረ ኤ.ሢ.ሚላን ከቬሮና 1-0፤ ፊዮሬንቲና ከካግሊያሪ 2-1፤ ላሢዮ ከሮማ 4-2፤ ቶሪኖ ከካታኛ 2-1፤ ሣምፕዶሪያ ከሌቼ 3-1፤ እንዲሁም ሢየና ከቦሎኛ 4-1 ተለያይተዋል። በአጠቃላይ ውጤት ኤ.ሢ.ሚላን ከኢንተርና ከጁቬንቱስ ቀጥሎ ሶሥተኛ ነው፤ ጌኖዋ አራተኛ፣ ፊዮሬንቲና አምሥተኛ፣ ሮማ ስድሥተኛ!

በጀርመን ቡንደስሊጋ በአንጻሩ የዘንድሮው ሻምፒዮና ፉክክር ጠባብ ሆኖ እንደቀጠለ ሲሆን የሣምንቱ ተጠቃሚዎች ዎልፍስቡርግና ባየርን ሙንሺን ናቸው። ቮልፍስቡርግ ሙንሸን ግላድባህን 2-1 ሲረታ አመራሩን ለብቻው በመያዝ ወደ ሶሥት ነጥቦች ሊያሰፋ በቅቷል። ሃምቡርግ በሽቱትጋርት 1-0 በመሽነፉ ወደ ሶሥተኛው ቦታ ሲንሸራተት ይሄው ውጤት በተለይ የበጀው ለባየርን ሙንሺን ነው። ባየርን ፍራንክፉርትን 4-0 በመቅጣት ወደ ሁለተኛው ቦታ አሻቅቧል። ይህም ምናልባት ሻምፒዮንነቱን መልሶ እንዲያስከብር አመቺ ጥርጊያ የሚከፍትለት ነው። እርግጥ ጉዞው የሽርሽር የሚሆንለት አይመስልም።

በሌላ በኩል ከጥቂት ሣምንታት በፊት የቡንደስሊጋ ቁንጮ ሊሆን በቅቶ የነበረው ሄርታ በርሊን በዚህም ሰንበት በተከታታይ ለሶሥተኛ ጊዜ በመሽነፉ ወደ አምሥተኛው ቦታ ማቆልቆሉ ግድ ሆኖበታል። በተረፈ ሻልከ ካርልስሩኸን 2-0፤ ኮትቡስ ቢለፌልድን 2-1፤ ዶርትሙንድ ኮሎኝን 3-1 ሲረቱ ሌቨርኩዝንንና ብሬመን ደግሞ 1-1 ተለያይተዋል። ከ 27 ግጥሚያዎች በኋላ ቮልፍስቡርግ በ 54 ነጥቦች አንደኛ ነው፤ ባየርን ሙንሺንና ሃምቡርግ እኩል 51 ነጥብ ይዘው ይከተላሉ። አራተኛ በርሊን፤ አምሥተኛ ሽቱትጋርት! አምሥቱን ክለቦች የሚለዩዋቸው ስድሥት ነጥቦች ብቻ ሲሆኑ ሁሉም ለሻምፒዮንነት እንዳለሙ ይቀጥላሉ።

በፈረንሣይ አንደኛ ዲቪዚዮን ኦላምፒክ ማርሤይ ትናንት ግሬኖብልን በማሸነፍ ኦላምፒክ ሊዮንን በአንዲት ነጥብ ልዩነትም ቢሆን ከአመራሩ ፈንቅሏል። በተከታታይ የሰባት ጊዜው ሻምፒዮን ኦላምፒክ ሊዮን በገዛ ሜዳውም ሞናኮን መሸነፉ አልሆነለትም። 2-2 በሆነ ውጤት ብቻ ተለያይቷል። ሊዮን አመራሩን ሲለቅ ካለፈው መስከረም ወዲህ ለመጀመሪያ ጊዜ መሆኑ ነው። ሂደቱ ማቆልቆያው ይሆን? ኦግዜርን የረታው ሶሥተኛው ዢሮንዲን ቦርዶም አንዲት ነጥብ ብቻ ወረድ ብሎ በቅርብ እየገፋው ነው የሚገኘው። ዘንድሮ የፈረንሣይ ሻምፒዮናም እንደ ጀርመኑ ሁሉ ብርቱ ፉክክር ሰፍኖበት እስከ መጨረሻው እንደሚቀጥል አንድና ሁለት የለውም። ማርሤይ 61፤ ሊዮን 60፤ ቦርዶ 59 ነጥብ! ሰባት ግጥሚያዎች ቀርተው ሳለ በአንዳንድ ነጥብ ብቻ ነው የሚለያዩት።

በኔዘርላንድ ሻምፒዮና አልክማር ከ 28 ዓመታት ቆይታ በኋላ ለመጀመሪያ ድሉ ይበልጥ እየተቃረበ ነው። አልክማር የቤልጂጉ ተጫዋች ሙሣ ዴምቤሌ በአስደናቂ ሁኔታ ባስቆጠራት ግብ ብሬዳን 1-0 ሲያሸንፍ በ 11 ነጥቦች ልዩነት ይመራል። ኤንሼዴ ሁለተኛ፤ እንዲሁም አያክስ አምስተርዳም ሶሥተኛ ሲሆን ቀደምቱ ክለብ አይንድሆፈን በአምሥተኛ ቦታ እንደተወሰነ ነው። በፖርቱጋል ሊጋ ፖርቶ ኤስትሬላ አማዶራን 3-0 በመርታት ለአራተኛ ተከታታይ ሻምፒዮንነት ጥርጊያውን እያመቸቸ ሲሆን አራት ነጥቦች ወረድ ብሎ የሚገኘው ስፖርቲንግ ሊዝበንም ናቫልን 3-1 በማሸነፍ ግፊቱን አጠናክሯል።

የቀደምቱ የአውሮፓ አንደኛ ዲቪዚዮኖች ይዞታ ከሞላ-ጎደል ይህን የመሰለ ሲሆን ነገና ከነገ በስቲያ ደግሞ የአውሮፓ ክለቦች ሻምፒዮና ሊጋ ውድድር ሩብ ፍጻሜ ዙር የመልስ ግጥሚያዎች ይካሄዳሉ። በነገው ምሽት የሚካሄዱት ሁለት ግጥሚያዎች ቼልሢይ ከሊቨርፑልና ባየርን ሙንሺን ከባርሤሎና ሲሆኑ ሁለቱም ጨዋታዎች ከመጀመሪያው ግጥሚያ ተሸናፊዎች ከባድ ትግልን፤ ምናልባት ተዓምርም ሊጠይቁ የሚችሉ ናቸው። ሊቨርፑል ባለፈው ሣምንት የመጀመሪያ ግጥሚያ በሜዳው 3-1 መሸነፉ ሲታሰብ ውጤቱን ለመቀየር መቻሉ ብዙ ያጠራጥራል።
ግን ኳስ ድቦቡልቡል ናት፤ ማን ያውቃል? ምሽቱ ይበልጡን የሚከብደው በኑ ካምፕ ስታዲዮም በባርሣ 4-0 ተቀጥቶ በውርደት ለተመለሰው ለባየርን ሙንሺን ነው። እርግጥ የክብር ጉዳይ በመሆኑ የጀርመኑ ቀደምት ክለብ ብርቱ ትግል የሚያደርግ መሆኑ አያጠያይቅም። ይሁንና አራት ለባዶውን ውጤት ለመቀልበስ መቻሉ ሊያምኑት ያዳግታል። የባርሣ ኮከብ አጥቂዎች ቀድመው አንዲት ጎል ካስቆጠሩ ባየርን እንዲያውም ስድሥት ማስገባት ሊኖርበት ነው። የሚሳካለት አይመስልም።

ለማንኛውም ከአራቱ የእንግሊዝ ክለቦች አንዱ በነገው ምሽት መሰናበቱ ግድ ሲሆን የተቀሩት ሁለቱ በማግሥቱ ረቡዕ ወደፊት ሊዘልቁ ይችላሉ። እርግጥ ማንቼስተር ዩናይትድን ከፖርቶ ጋር በሜዳው እኩል ለእኩል፤ 2-2 ከተለያየ በኋላ በመልሱ ጨዋታ ቀላል ሁኔታ አይጠብቀውም። በሌላ በኩል ከቪላርሬያል 1-1 ወጥቶ ከስፓኝ የተመለሰው አርሰናል በሜዳው መልካም ዕድል አለው። በአጠቃላይ ሶሥት የእንግሊዝ ክለቦች ወደ ግማሽ ፍጻሜው ማለፋቸው ከአሁኑ ያለቀለት ነገር ሲሆን ፍጻሜውም እንደገና በነርሱው መካክል ሊወሰንም ይችላል።

ቴኒስ

በዓለም የቴኒስ ማዕረግ ተዋረድ ላይ ቀድሞ አንደኛ የነበረው አውስትራሊያዊው ሌይተን ሄዊት በሂዩስተን ሻምፒዮና የአሜሪካ ተጋጣሚውን ዌይን ኦዴስኒክን 6-2, 7-5 በሆነ ውጤት በማሸነፍ ትናንት ሁለት ዓመታት ከፈጀ የድርቅ ዘመኑ ተሰናብቷል። ሄዊት ለአሥር ዓመታት ያህል ቢያንስ በአንድ ውድድር ሲያሸንፍ ከኖረ በኋላ ከመጋቢት ወር 2007 ወዲህ ድል ከድቶት ነበር የቆየው። በፍሎሪዳ የዓለም ቴኒስ ማሕበር ውድድር ፍጻሜ ደግሞ የዴንማርኳ ካሮሊን ቮዚኒያችኪ ካናዳዊቱን አሌክሣንድራ ቮዝኒያክን በለየለት 6-1, 6-2 ውጤት አሸንፋለች።
በስፓኝ ማርቤላ የአንዳሉዚያ የሴቶች ፍጻሜ ደግሞ የሰርቢያዋ የለና ያንኮቪች የአገሪቱን ተወላጅ ካርላ ሱዋሬስን በሶሥት ምድብ ጨዋታ ረትታለች። በተረፈ ዛሬ በወጣ አዲስ የቴኒስ ማዕረግ ተዋረድ ዝርዝር በወንዶች ራፋኤል ናዳል መምራቱን እንደቀጠለ ነው፤ ሮጀር ፌደረር በሁለተኝነት ይከተላል፤ ሶሥተኛ ኖቫክ ጆኮቪች ከሰርቢያ፤ እንዲሁም ኤንዲይ መሪይ ከብሪታኒያ አራተኛ ነው። በሴቶች ደግሞ ሤሬና ዊሊያምስ ሩሢያውያኑን ዲናራ ሣፊናንና ኤሌና ዴሜንትየቫን አስከትላ ትመራለች፤ አራተኛ የሰርቢያዋ ኮከብ የለና ያንኮቪች ናት።

የሣምንቱ ቴኒስ-ነክ አስደናቂ ዜና ለወትሮው የጸረ-አፓርታይድ ትግል መለያ የሆነችው የደቡብ አፍሪቃ መንደር ሶዌቶ ይህን ውድድር ልታስተናግድ መነሳቷ ነው። አንድ መቶ ሺህ ዶላር ሽልማት የተመደበለት ውድድር ዛሬ የሚከፈት ሲሆን በዊንብለደን ውድድር ራፋኤል ናዳልን የመሰለ ኮከብ አሸንፎ ያስወጣው የሉክሰምቡርግ ተጫዋች ዢል ሙለርና ሌሎች ታዋቂ ተዋዳዳሪዎችም ይሳተፋሉ። ሶዌቶ-ኦፕን፤ ምናልባት ለሶዌቶ ተሃድሶ ጠቃሚ ድርሻ ሊኖረው ይችል ይ’ሆናል።
ቢስክሌት

ትናንት ፈረንሣይ ውስጥ የተካሄደው ከፓሪስ-ሩቤይ የአንድ ቀን የቢስኬት እሽቅድድም አሸናፊ የቤልጂጉ ተወዳዳሪ ቶም ቡነን ሆኗል። ቡነን ከግቡ ለመድረስ 16 ኪሎሜትር ገደማ ሲቀረው ተፎካካሪዎቹን ጥሎ ሲያመልጥ በታዋቂው ውድድር ለሶሥተኛ ጊዜ አሸናፊ መሆኑ ነው። 259 ኪሎሜትር ርዝመት ባለው እሽቅድድም ኢጣሊያዊው ፊሊፖ ፓዛቶ ሁለተኛ ሲወጣ የኖርዌዩ ተወላጅ ቶር ሁስሆድ ደግሞ ሶሥተኛ ሆኗል። በውድድሩ አኳያ አንድ ሞተር ቢስክሌት ባደረሰው ጉዳት ከአሥር የሚበልጡ ተመልካቾች መቁሰላቸው ዝግጅቱን የጋረደው አሳዛኝ ገጽታው ነበር።

በሌላ ስፓኝ ውስጥ በስድሥት ደረጃ ተከፍሎ በተካሄደ የባስክ የቢስክሌት እሽቅድድም ደግሞ የአገሪቱ ተወላጅ አልቤርቶ ኮንታዶር አሸናፊ ሆኗል። ለዢሮ-ዴ-ኢታሊያና ለስፓኙ የቩዌልታ ሻምፒዮን የባስኩ ድል በተከታታይ ሁለተኛው መሆኑ ነው። ኮንታዶር በ 2007 ዓ.ም. የታላቁ ቱር-ዴ-ፍራንስ አሸናፊም ነበር። በባስኩ እሽቅድድም አጠቃላይ ውጤት ሁለተኛና ሶሥተኛ የሆኑትም የስፓኝ ተወዳዳሪዎች አንቶኒዮ ኮሎምና ሣሙዔል ሣንቼዝ ናቸው።

ደቡብ አፍሪቃ ውስጥ በዚህ ሣምንት በተካሄደ የማውንቴይን-ባይክ አገር አዳራሽ እሽቅድድምም እንዲሁ ድሉ የስፓኝ ነበር። ሁሤ ኤርሚዳ አሸናፊ ሲሆን ፈረንሣዊው የኦሎምፒክ ሻምፒዮን ዡሊየን አብሣሎን በሁለተኝነት መወሰኑ ግድ ነው የሆነበት። በሴቶች የአውስትሪያ ተወዳዳሪ ኤሊዛቤት ኦስል ስታሸንፍ ሩሢያዊቱ ኢሪና ካሌንቲየቫ ሁለተኛ፤ እንዲሁም ሌና ባይበርግ ከኖርዌይ ሶሥተኛ በመሆን እሽቅድድሙን ፈጽመዋል። በቁልቁለት እሽቅድድም ደግሞ በወንዶች ደቡበ አፍሪቃዊው ግሬግ ሚናር ሲያሸንፍ እንግሊዛዊቱ ትሬሢይ ሞስሊይ ለድል በቅታለች።

መሥፍን መኮንን, AFP, dpa