የስፖርት ዘገባ | ስፖርት | DW | 09.02.2009
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ስፖርት

የስፖርት ዘገባ

ባለፈው ሰንበት በቦስተንና በዚህ በጀርመን በሽቱትጋርት ከተማ ሁለት ዓለምአቀፍ የአዳራሽ ውስጥ የአትሌቲክስ ውድድሮች ሲካሄዱ ሣምንቱ የኢትዮጵያ አትሌቶችም ጎልተው የታዩበት ነበር።

የባየርን የጎል ዋስትና፤ ሚሮስላቭ ክሎዘ

የባየርን የጎል ዋስትና፤ ሚሮስላቭ ክሎዘ

ሰንበቱን በዚህ በጀርመን ሽቱትጋርት ከተማ ውስጥ በተካሄደው የዓለም አትሌቲክስ ፌደሬሺኖች ማሕበር የአዳራሽ ውስጥ ውድድር የኢትዮጵያ አትሌቶችም ግሩም ውጤት አስመዝግበዋል። በተለይ የ 5 ሺህ ሜትር የዓለም ሻምፒዮኗ መሠረት ደፋር በ 7,500 ተመልካች ፊት ያሳየችው የ 3 ሺህ ሜትር ሩጫ የሚደነቅ ነበር። መሠረት በዚሁ ስፋራ ባለፈው ዓመት ያስመዘገበችን የራሷን የአዳራሽ ውስጥ ክብረ-ወሰን ለማሻሻል ባትበቃም ሩጫውን የጨረሰችው በዚህ የውድድር ውቅት አቻ ባልታየለት ፈጣን ጊዜ ነው።

በቤይጂንግ ኦሎምፒክ ግንባር ቀደም ቦታዋን ተነጥቃ የነበረችው ድንቅ አትሌት በአሁን አዝማሚያዋ በፊታችን ነሐሴ ወር በርሊን ላይ በሚካሄደው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ወደተለመደ ጥንካሬዋ የምትመለስ ነው የሚመስለው። በዚሁ ውድድር ሩሢያዊቱ አና አሊሞቫ ሁለተኛ ስትሆን የፖላንዷ ሢልቪያ ኤይዲስ ደግሞ ሶሥተኛ ወጥታለች። በሽቱትጋርቱ ውድድር የኢትዮጵያ ድል በዚህ ብቻ የተወሰነ አልነበረም። በ 1,500 ሜትር ሩጫም ደረሰ መኮንን አዲስ ክብረ-ወሰን በማስመዝብ አሸንፏል።
በወንዶች 3 ሺህ ሜትር ደግሞ አብርሃም ጨርቆስ በሁለተኝነት ውድድሩን መፈጸሙ ሌላው የሚደነቅ ውጤት ነበር። በዚህ ርቀት አሸናፊ የሆነው ኬንያዊው-አሜሪካዊ በርናርድ ላጋት ነበር። ላጋትም ያሽነፈው እንዲሁ አዲስ የዓለም ክብረ-ወሰን በማስመዝገብ ነው። በተረፈ አሜሪካዊቱ ሎሎ ጆንስ በ 60 ሜትር ሩጫ አዲስ የዓለም ክብረ-ወሰን ስታስመዘግብ በከፍታ ዝላይ በቤይጂንግ ኦሎምፒክ ዓለም የጠበቀው ድሏ አምልጧት የነበረችው የክሮኤሺያ ኮከብ ብላንካ ቭላዚች 2 ሜትር ከ 4 ሤንቲሜትር ከፍታን በመሻገር በዚህ የውድድር ወቅት አቻ ላልታየለት ውጤት በቅታለች።
ቭላዚች ይሁንና ለ 32 ዓመታት ጸንቶ የቆየውን የስዊድኗን ተወላጅ የካይሣ በርግኩዊስትን 2,08 ሜትር የአዳራሽ ውስጥ የዓለም ክብረ-ወሰን ለማሻሻል ሶሥት ጊዜ ያደረገችው ሙከራ ሳይሳካላት ቀርቷል። በወንዶች 800 ሜትር ሩጫም የሱዳኑ ተወዳዳሪ ኢስማኢል-አሕመድ-ኢስማኢል በአዲስ ክብረ-ወሰን ሲያሸንፍ የአገሩ ልጅ አቡባከር ካኪ ደግሞ በሺህ ሜትር ርቀት ባለድል ሆኗል። ኢስማኢል በቤይጂንጉ ኦሎምፒክ በዚሁ ርቀት ለብር ሜዳሊያ ሽልማት የበቃ ጠንካራ አትሌት እንደነበር የሚታወስ ነው። በአጠቃላይ የሽቱትጋርት ዓለምአቀፍ የአዳራሽ ውስጥ ውድድር በዚህ ዓመትም ግሩም ጥንካሬ የታየበት ሆኖ ነው ያለፈው።

ከሽቱትጋርት ሌላ በዚህ ሰንበት በዩ.ኤስ.አሜሪካ በቦስተንም ዓለምአቀፍ የአዳራሽ ውስጥ ውድድር ሲካሄድ ወኪላችን አበበ ፈለቀ እንደዘገበው እዚያም የኢትዮጵያ አትሌቶች ያደረጉት ተሳትፎ ስኬት የተመላበት ነበር። ከዚሁ ሌላ ሆንግ ኮንግ ላይ በተካሄደ የማራቶን ሩጫ የኬንያ አትሌቶች ልዩ ጥንካሬ በማሣየት በወንዶችና በሴቶችም አሽናፊ ሆነዋል። በወንዶች ኪፕሪያን ምዎቢ ሲያሸንፍ ሁለተኛና ሶሥተኛ የወጡትም የአገሩ ልጆች ናቸው። በሴቶች ደግሞ ዊኒ ንያንሲኬራ አሸናፊ ሆናለች።

እግር ኳስ

በአውሮፓ ቀደምት ሊጋዎች ውስጥ የዘንድሮው ሻምፒዮና ቀስ በቀስ ወደ ግቡ መቃረብ እየያዘ ሲሆን በተለይ ባርሤሎናና ኢንተር ሚላን አመራራቸውን እያሰፉ መሄዳቸውን ቀጥለዋል። በስፓኝ ፕሪሜራ ዲቪዚዮን ምንም እንኳ ያለፈው ሻምፒዮን ሬያል ማድሪድ በዚህ ሣምንትም ለሰባተኛ ተከታታይ ድሉ ቢበቃም መሪው ባርሤሎና አልበገርም በማለቱ 12 ነጥቦች ዝቅ ብሎ መከተል እንደተገደደ ነው። ሬያል ሣንታንዴርን 1-0 ሲረታ ባርሤሎናም ጊዮንን 3-1 አሸንፏል። ሶሥተኛው ሤቪያ በቤቲስ ተሸንፎ ሲያቆለቁል ዘንድሮ ሻምፒዮናው ሲሆን ከባርሤሎና አለበለዚያም ከሬያል ዕጅ የሚወጣ አይመስልም።

በኢጣሊያ ሊጋ ሤሪያ-አም. ኢንተር ሚላን ሌቼን 3-0 በማሸነፍ በወደፊት ዕርምጃው ቀጥሏል። ጁቬንቱስ ካታኛን 2-1 በመርታት ወደ ሁለተኛው ቦታ ከፍ ሲል ኢንተር አመራሩን በሰባት ነጥቦች እንዲያሰፋ የጠቀመው የኤ.ሢ.ሚላን ከሬጂና ጋር በእኩል ለእኩል ውጤት መወሰን ነው። እርግጥ ለኢንተር አመቺ ሁኔታ ቢፈጠርም ገና ሁሉም ነገር ለይቶለታል ማለት አይደለም። ሶሥቱም ክለቦች ሻምፒዮን የመሆን ዕድላቸውን እንደያዙ ቀጥለዋል።

በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ በአንጻሩ ፉክክሩ ጠበብ እንዳለ ነው። ማንቼስተር ዩናይትድ አንድ ጨዋታ ጎሎትም በሁለት ነጥብ ልዩነት የሚመራ ሲሆን ሊቨርፑል በሁለተኝነት ይከተለዋል። እንደ ማንቼስተርና እንደ ሊቨርፑል ሁሉ የሰንበት ግጥሚያውን በድል የተወጣው ኤስተን ቪላ ወደ ሶሥተኛው ቦታ ከፍ ሲል ከቀደምቱ ቡድኖች የሣምንቱ ተንሸራታች ቼልሢይ ብቻ ነው። ቼልሢይ ከሃል-ሢቲይ ባዶ ለባዶ በመለያየቱ ከአንደኛው ከማንቼስተር ዩናይትድ ጋር ያለው የነጥብ ልዩነት ወደ ሰባት ሊሰፋ በቅቷል።

በዚህ በጀርመን ቡንደስሊጋ የብዙ ጊዜው ሻምፒዮን ባየርን ሙንሺን ትናንት ዶርትሙንድን በግሩም ጨዋታ 3-1 በማሽነፍ የሊጋውን አመራር በአንዲት ነጥብ ልዩነት ለመቃረብ ችሏል። አመራሩን እንደያዘ የቀጠለው ሆፈንሃይም በመጨረሻዋ ደቂቃ ላይ ባስቆጠራት ጎል ከግላድባህ ጋር በመከራ እኩል ለእኩል ሲለያይ ሰንበቱ ለተቀሩት ተከታይ ቡድኖችም የቀና አልነበረም። ለባየርን የሁለተኝነቱን ቦታ የለቀቀው በርሊን በአኩል ለእኩል ውጤት ሲወሰን ሃምቡርግና ሌቨርኩዝን ደግሞ የሰንበቱ ተሽናፊዎች ናቸው።

ከሁሉም በላይ የሣምንቱ ዋነኛ ተሽናፊ ከክረምቱ ዕረፍት በኋላ በተጀመረው ሁለተኛ ዙር ውድድር ሁለቱንም ግጥሚያዎች በመሽነፍ ማቆልቆል የያዘው ቬርደር ብሬመን ነበር። ቬርደር ከሻልከ ጋር ባካሄደው ግጥሚያ ብዙ የጎል ዕድል ባያጣም እንዳለፈው ጊዜ ሁሉ ሳይጠቀምበት ቀርቷል። ዕድል የከዳው ነው የሚመስለው። ሻልከ ብሬመንን ያሽነፈው ይበልጡን በዕድል መሆኑን አሠልጣኙ ፍሬድ ሩተንም አላጡትም።

“ቡድኔ እንዳለፉት ግጥሚዮች ሣይሆን በሚገባ ታግሏል ለማለት እችላለሁ። ግን ዛሬ ምናልባትም ዕድለኞች ነበርን። ለማንኛውም ድሉ ለኛ እጅግ ጠቃሚ ነው። ያሸነፍነው ደግሞ ጥሩ መጫወት የሚችል ቡድንን ነው”

በተቀረ በፈረንሣይ ኦላምፒል ሊዮን፣ በኔዘርላንድ አልክማር፣ በፖርቱጋል ሻምፒዮናም እንዲሁ ፖርቶ አመራራቸውን ይዘው እንደቀጠሉ ነው። ለማጠቃለል ያህል ነገና ከነገ በስቲያ በዓለም ዙሪያ በርክት ያሉ የእግር ኳስ የወዳጅነት ግጥሚያዎች ይካሄዳሉ። ከነዚሁ መካከል በዋነኝነት ኢጣሊያ-ብራዚል፤ ፈረንሣይ-አርጄንቲና፣ ስፓኝ-እንግሊዝ፣ ፖርቱጋል-ፊንላንድና ጀርመን-ኖርዌይ ይገኙበታል። በነገራችን ላይ በዚህ በጀርመን ሰሞኑን ከኖርዌይ ግጥሚያ ይልቅ ዓቢይ መነጋገሪያ ሆኖ የሰነበተው ከቱርክ የመነጨውና እዚሁ ያደገው ወጣት ተጫዋች የሜሱት ኡዚል ለብሄራዊው ቡድን መመረጥ ነው።

የብሬመኑ ወጣት ኮከብ የቱርክና የጀርመን ጥንድ ዜግነት ያለው ሲሆን ቱርክም እንዲሰለፍላት ስትገፋፋ ቆይታለች። በወቅቱ ይህን መሰሉ ሁኔታ በብዙ የአውሮፓ አገሮች እያጋጠመ መሄድ የያዘ ነገር ነው። ለተወለዱበት ወይስ ላደጉበት አገር፤ ምርጫው ለተጫዋቹ ቀላል አይሆንም። ለማንኛውም ውሣኔው የኡዚል የራሱ ሲሆን እርግጥ ወጣቱ በፊታችን ረቡዕ ለጀርመን አንዴ ከተሰለፈ ወደፊት ሃሣቡን ለውጦ ለቱርክ መጫወት አይችልም።

MM