የስፖርት ዘገባ | ስፖርት | DW | 15.12.2014
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ስፖርት

የስፖርት ዘገባ

ቸልሲ መሪነቱን እንዳስጠበቀ ነው። መከረኛው ሊቨርፑል ወደ አስረኛ ደረጃ ሲያሽቆለቁል፤ ባላንጣው ማንቸስተር ዩናይትድ ደረጃውን በሚገርም ሁናቴ አሻሽሏል። በጀርመን ቡንደስ ሊጋ ኃያሉ ባየር ሙይንሽንን ከግስጋሴው የሚገታው አልተገኘም። ከኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን እና ከአንድ የስፖርት ጋዜጠኛ ተንታኝ ጋር የተደረጉ ቃለ መጠይቆችን አካተናል።

በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ የእግር ኳስ ፍልሚያ ሊቨርፑል ትናንት በማንቸስተር ዩናይትድ ጉድ ተሰርቷል። ዋይኔ ሩኒ፣ ጁዋን ማታ እና ሮበን ቫን ፔርሲ ባስቆጠሯቸው ግቦች ማንቸስተር ዩናይትድ ሊቨርፑልን 3 ለ ዜሮ ሸኝቷል።

የማንቸስተር ዩናይትዱ አማካኝ ሚካኤል ካሪክ ዛሬ በቡድኑ የቴሌቪዥን ጣቢያ ቀርቦ ለቸልሲም አንተኛም ብሏል። ቀደም ሲል ማንቸስተር ዩናይትድ ከዘንድሮ ውድድር መክፈቻ ጀምሮ ባደረጋቸው 10 ተከታታይ ጨዋታዎች ሦስቱን ብቻ በማሸነፍ 10ኛ ደረጃ ላይ ለመንገታገት ተገዶ ነበር። ሆኖም ማንቸሰተር ዩናይትዶች ከዚያ በኋላ ጥርሳቸውን ነክሰው 6 ተከታታይ ጨዋታዎችን በማሸነፋቸው በደረጃ ሠንጠረዡ ሦስተኛ ለመሆን በቅተዋል። በምትኩ ለተደጋጋሚ ሽንፈት የተዳረገው ሊቨርፑል ቁልቁል 10ኛ ደረጃ ላይ እየዳከረ ይገኛል። የማንቸስተር ዩናይትዱ አሠልጣኝ ዴቪድ ሞየስ የተደጋጋሚ ድል ሚሥጥራቸው ምን እንደሆነ ተጠይቀው መልስ ሰጥተዋል። «ሚሥጥሩ የተጋጣሚያችን ብቃት ላይ ትኩረት የሚያደርግ የአጨዋወት ስልት መከተላችን ነው» ሲሉ አሠልጣኙ ለጋዜጠኞች ተናግረዋል።

ትናንት ቶትንሐም ሆትስፐር ስዋንሲን 2 ለ1 አሸንፏል። ቅዳሜ አርሰናል ኒውካስል ዩናይትድን በሰፊ ልዩነት 4 ለ1 መቅጣት ብቻ አይደለም ለመሪው ቸልሲም ተበቅሎለታል። ቸልሲ በፕሬሚየር ሊጉ የ2 ለ1 የመጀመሪያ ሽንፈቱን በኒውካስል ዩናይትድ የቀመሰው ከሣምንት በፊት ነበር። አርሰናል ለእራሱ ግን እንደ ማንቸስተር ዩናይትድ በጊዜ ያወቀበት አይመስልም። 26 ነጥብ ይዞ ስድተኛ ደረጃ ላይ ነው የሚገኘው።

የማንቸስተር ዩናይትዱ ዋይኔ ሩኒ

የማንቸስተር ዩናይትዱ ዋይኔ ሩኒ

በ39 ነጥብ የደረጃ ሠንጠረዡ አናት ላይ የሚገኘው ቸልሲ ሁል ሲቲን 2 ለባዶ አሰናብቷል። ከቸልሲ 3 ነጥብ ዝቅ ብሎ በ36 ነጥብ የሚከተለው ማንቸስተር ሲቲ በሠንጠረዡ ግርጌ 20ኛ ደረጃ ላይ የተጋደመው ሌስተር ሲቲን በጠባብ ልዩነት 1 ለዜሮ አሸንፏል። ዌስት ብሮሚች አስቶን ቪላን፣ በርንሌይ ሳውዝሀምተንን ከትናንት በስትያ 1 ለባዶ ረትተዋል። ሰንደርላንድ ከዌስት ሐም ዩናይትድ እንዲሁም ክሪስታል ፓላስ ከስቶክ ሲቲን ጋር ቅዳሜ ዕለት አንድ እኩል ተለያይተዋል።

ማንቸስተር ሲቲው ሠርጂዮ አጉዌሮ በ14 ግቦች የፕሬሚየር ሊጉ ኮከብ ግብ አግቢነቱን እየመራ ነው። የቸልሲው ዲዬጎ ኮስታ በ12 ግቦች ይከተለዋል። የአርሰናሉ አሌክሲስ ሳንቼዝ በ9 ከመረብ ያረፉ ኳሶች ይሰልሳል።

«እጅግ በጣም ኮርቻለሁ፤ ምክንያቱም እዚህ ማሸነፍ ምን ያህል ከባድ እንደሆነ አስቀድሜም አውቀው ነበር» የባየር ሙይንሽኑ አሠልጣኝ ፔፕ ጉዋርዲዮላ ነበሩ ይኽን የተናገሩት። በጀርመን ቡንደስ ሊጋ ከትናንት በስትያ ኃያሉ ባየር ሙይንሽን እንደተለመደው በሰፊ ልዩነት አውስቡርግን 4 ለዜሮ አንኮታኩቶዋል። ቦሩስያ ዶርትሙንድ በሔርታ ቤርሊን 1 ለዜሮ ተሸንፏል። ዳግም በወራጅ ቃጣናው ውስጥ በስጋት ተውጧል። ኮሎኝ ሻልካን 2 ለ1 ሲረታ፤ ቬርደር ብሬመንከሐኖቨር 3 እኩል እንዲሁምፍራይቡርግ ከሐምቡርግ ያለምንም ግብ አቻ ተለያይተዋል።ማይንትስ እና ሽቱትጋርት አንድ እኩል በመለያየት ነጥብ ተጋርተዋል። ትናት ፓዴርቦርን ከዎልፍስቡርግ እንዲሁም ባየር ሌቨርኩሰን ከቦሩሲያ ሞይንሽንግላድባኅ አንድ እኩል አቻ ወጥተዋል።

የደረጃ ሠንጠረጁን ባየር ሙይንሽን በ39 ነጥብ ይመራል። ዎልፍስቡርግ በ30 ነጥብ ይከተላል። ባየር ሌቨርኩሰን 24 ነጥብ ይዞ ሦስተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል። የአይንትራኅት ፍራንክፉርቱ አሌክሳንደር ማየር በቡንደስ ሊጋው 10 ግቦችን በማስቆጠር ቀዳሚ ሆኗል። የባየር ሙይንሽኑ አርየን ሮበን በ8 ከመረብ ያረፉ ኳሶች ኹለተኛ ኮከብ ግብ አግቢነቱን አስጠብቋል። የማይንትሱ ሺንጂ ኦካዛኪ እና የሻልካው ኤሪክ ማክሲም ቾፖ ሞቲግም እንደ ሮበን 8 ግቦች አስቆጥረዋል።

የባየር ሙይንሽኑ አሠልጣኝ ፔፕ ጓርዲዮላ

የባየር ሙይንሽኑ አሠልጣኝ ፔፕ ጓርዲዮላ

የስፔን ላሊጋ እና የጣሊያን ሴሪኣ ውጤቶች እንዲሁም ኮከብ ግብ አግቢዎችን በተመለከተ ወደ በኃላ እንመለስበታለን። አሁን ባለፈው ሣምንት ቃል በገባነው መሠረት አሠልጣኝ ማሪዮ ባሬቶን በተመለከተ ከኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን እና ከአንድ የስፖርት ጋዜጠኛ ጋር ያደረግነውን ቃለመጠይቅ እናስከትላለን። በመጀመሪያ ያነጋገርነው በኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የሕዝብ ግንኙነት ክፍል ኃላፊ የሆኑት አቶ ወንድምኩን አላየውን ነው። ቅዳሜ ዕለት በነበረው የፌዴሬሽኑ ጠቅላላ ጉባኤ አሠልጣኝ ማሪዮ ባሬቶን በተመለከተ ምን ተነጋግራችኋል በሚል ነበር ጥያቄዬን ያስቀደምኩት።

በመቀጠል ስፖርት 365 በሚባለው የሬዲዮ ዝግጅት ላይ ከሚሠራው የስፖርት ጋዜጠኛ አዩ ወልደሚካኤል ጋር ወዳደረግነው ቃለምልልስ እናምራ።

በስፔን ላሊጋ ትናንት ኤስፓኞላ ግራናዳን 2 ለ1፣ ቪላሪያል አትሌቲኮ ማድሪድን 1 ለባዶ አሸንፈዋል። ሪያል ሶሴዳድ ከአትሌቲክ ክለብ ጋር አንድ እኩል ሲወጣ፤ ሴቪላ ከአይበር ያለምንም ግብ ተለያይተዋል። የደረጃ ሠንጠረዡን ሪያል ማድሪድ በ39 ነጥብ ይመራል። ባርሴሎና 35 ነጥብ፣ አትሌቲኮ ማድሪድ 32 ነጥብ ይዘው ኹለተኛ እና ሦስተኛ ደረጃ ላይ ይገኛሉ። የሪያል ማድሪዱ ክሪስቲያኖ ሮናልዶ 25 ግቦችን ከመረብ በማሳረፍ በብቸንነት የኮከብ ግብ አግቢነት ግስጋሴውን ተያይዞታል። የባርሴሎናው ሊዮኔል ሜሲ 13 ግቦች አሉት። ሌላኛው የባርሴሎና ግብ አዳኝ ኔይማር 11 ግቦችን በማስቆጠር በሦስተኛነት ይከተላል።

በጣሊያን ሴሪ ኣ መሪው ጁቬንቱስ ትናንት ከሳምፕዶሪያ ጋር አንድ እኩል በመውጣት ነጥብ ተጋርቷል። ፊዮሬንቲና ኤሲ ሴሴናን 4 ለ1፣ ኤሲ ሚላን ናፖሊን 2 ለባዶ፣ ሮማ ጄኖዋን 1 ለምንም እንዲሁም ሔላስ ቬሮና ኡዲኒዜን 2 ለ1 ረትተዋል። ፓርማ እና ካጊሊያሪ ያለምንም ግብ ነጥብ ተጋርተዋል። በደረጃ ሠንጠረዡ ጁቬንቱስ 36 ነጥብ ይዞ አንደኛነቱን አስጠብቋል። ሮማ በ35 ነጥብ ይከተላል። ላትሲዮ በ26 ነጥብ ሦስተኛ ነው።

የጁቬንቱስ ተጨዋች ኳስ ለመቀማት ሲታገል

የጁቬንቱስ ተጨዋች ኳስ ለመቀማት ሲታገል

በሴሪ ኣው ውድድር የጁቬንቱሱ ታቬዝ እስካሁን 9 ግቦች አሉት። የናፖሊው ካሌጆን፣ የኡዲኔዜው ዲ ናታላ፣ የኢንተር ሚላኑ ኢካርዲ እና የኤሲ ሚላኑ ሜኔትስ እያንዳንዳቸው 8 ግቦችን አስቆጥረው በኹለተኛ ደረጃ ኮከብ ግብ አግቢነት ይከተላሉ። የፓሌርሞው ዲባላ እና የናፕሌሱ ሒጉያን 7 ግቦችን ይዘው ሦስተኛነት ናቸው።

አጫጭር የስፖርት ዘገባዎች

የፎርሙላ አንድ የመኪና ሽቅድምድም የዘንድሮው አሸናፊ እንግሊዛዊው ሌዊስ ሐሚልተን በBBC ስፖርት የዓመቱ ምርጥ ሰው ተብሎ ተመረጠ የ29 ዓመቱ የመርሴዲስ አሽከርካሪ «በእውነቱ እኔ ይኽን አልጠበቅኩም ነበር» ሲል መደነቁን ገልጧል።

ጃፓናውያኑ የ14 ዓመት ታዳጊዎች ሚማ ኢቶ እና ሚዩ ሒራኖ በሜዳ ቴኔስ የሴቶች ውድድር ታሪክ የ1 ሚሊዮን ዩሮ ሽልማት አሸናፊ በመሆን የመጀመሪያዎቹ ታዳጊ ወጣቶች ሆኑ። ወጣቶቹ ናታልያ ፓቲካ እና ካታርዚና ግሪዚቦውስኪን በማሸነፍ እያንዳንዳቸው 400 000 ዩሮ ተሸላሚ ለመሆን ችለዋል።

በሻምፒዮንስ ሊግ የሩብ ፍፃሜ አራት የጀርመን ቡድኖች አላፊ ሆኑ። አራቱ የጀርመን ቡድኖች ባየር ሙይንሽን፣ ቦሩስያ ዶርትሙንድ፣ ባየር ሌቨርኩሰን እና ሻልካ ናቸው። ቦሩስያ ሞይንሽንግላድባኅ እና ዎልፍስቡርግ ደግሞ ለአውሮጳ ሊግ አልፈዋል።

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ነጋሽ መሐመድ

Audios and videos on the topic