የስፖርት ዘገባ | ስፖርት | DW | 29.10.2012
 1. Inhalt
 2. Navigation
 3. Weitere Inhalte
 4. Metanavigation
 5. Suche
 6. Choose from 30 Languages

ስፖርት

የስፖርት ዘገባ

በትናንቱ ሰንበት በዚህ በጀርመን ተካሂዶ የነበረው የፍራንክፉርት ማራቶን ሩጫ በኬንያና በኢትዮጵያ አትሌቶች ልዕልና ተፈጽሟል።

default

በትናንቱ ሰንበት በዚህ በጀርመን ተካሂዶ የነበረው የፍራንክፉርት ማራቶን ሩጫ በኬንያና በኢትዮጵያ አትሌቶች  ልዕልና ተፈጽሟል። በወንዶች ኬንያዊው የዓለም ክብረ-ወሰን ባለቤት ፓትሪክ ማካው ሲያሸንፍ ደሬሣ ጪምሣ ከኢትዮጵያ ሁለተኛ ወጥቷል። ጂልበርት ኪሩዋ ከኬንያ ሶሥተኛ! የፍራንክፉርት አየር መቀዝቀዝ በዕለቱ ለአዲስ ክብረ-ወሰን ሙከራ አመቺ አልነበረም። ማካው እንዲያውም ሩጫውን የፈጸመው የጡንቻ መታመም ችግር በታየበት ሁኔታ ነበር።                                                                                 

ፓትሪክ ማካው ሩጫውን በሁለት ሰዓት ከስድሥት ደቂቃ ከስምንት ሤኮንድ ጊዜ ሲፈጽም ይህም ከዓለም ክብረ-ወሰኑ በሁለት ደቂቃ ተኩል የዘገየ መሆኑ ነው። በሴቶች መሰለች መልካሙ ለዚያውም በመጀመሪያ የማራቶን ሩጫዋ አሸናፊ ስትሆን ለስፍራው አዲስ ክብረ-ወስን የሆነው የሁለት ሰዓት ከ 21 ደቂቃ ከአንድ ሤኮንድ ጊዜዋም እጅግ የሚያኮራ ነው። ማሚቱ ዳስቃም ሶሥተኛ በመሆን ሩጫውን መፈጸሟ የወቅቱን የኢትዮጵያን ሴት አትሌቶች ዓለምአቀፍ ጥንካሬ እንደ,ገና አረጋግጧል።                           

ወደ ብሪታኒያ ሻገር እንበልና የብሪታኒያ አትሌቲክስ ፌደሬሺን ሁለት የለንደን ኦሎምፒክ ሻምፒዮኖቹን ሞ ፋራህንና ጄሲካ ኤኒስን ባለፈው አርብ የዓመቱ አትሌቶች ብሎ ሰይሟል። ፋራህ በአሥርና አምስት ሺህ ሜትር የወርቅ ሜዳሊያዎችን ሲያሸንፍ ኤኒስ ደግሞ የሄፕታትሎን የቅይጥ ውድድሮች ባለወርቅ መሆኗ አይዘነጋም።       

በአውሮፓ ቀደምት የእግር ኳስ ሊጋዎች ሻምፒዮና በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ ማንቼስተር ዩናይትድ የቼልሢን አመራር ገደብ ሲያደርግ በጀርመን ቡንደስሊጋ ደግሞ ባየርን ሙንሺን ትናንት ከብቻ ጉዞው ተገትቷል።

በስፓኝ ፕሪሜራ ዲቮዚዮን እንጀምርና ቀደምቱ ባርሤሎናና ሬያል ማድሪድ የተመካከሩ ይመስል የየበኩላቸውን የውጭ ግጥሚያዎች በየፊናቸው 5-0 በሆነ ውጤት በማጠቃለል በጎል ፌስታ የደመቀ ሰንበት አሳልፈዋል።  ባርሣ ራዮ ቫሌካኖን ሲረታ ሬያል ደግሞ ያሸነፈው ማዮርካን ነበር። ባርሤሎና ከሰንበቱ ዘጠነኛ ግጥሚያ በኋላ በ 25 ነጥቦች ሊጋውን በአምሥት ጎሎች ብልጫ በአንደኝነት የሚመራ ሲሆን ኦሣሱናን 3-1 የረታው አትሌቲኮ ማድሪድም በእኩል ነጥብ ሁለተኛ ነው።                                                                                       

ከኤስፓኞል 0-0 የተለያየው ማላጋ በ 18 ነጥቦች ሶሥተኛ ሲሆን ዘንድሮ ጅማሮው ያልሰመረለት ያለፈው ውድድር ወቅት ሻምፒዮን ሬያል ማድሪድ ከአመራሩ ቁንጮ በስምንት ነጥቦች ዝቅ ብሎ አራተኛ ነው። ድንቁ የባርሤሎና ኮከብ ሊዮኔል ሜሢ ባለፈው ሰንበትም ሁለት ጎሎችን ሲያስቆጥር ለክለቡና ለአገሩ ለአርጄንቲና ያስገባቸውን ጎሎች ወደ 301 ከፍ ሊያደርግ በቅቷል። በነገራችን ላይ ሜሢ በፕሪሜራ ዲቪዚዮኑ ጎል አግቢነትም ከወዲሁ 11 አስቆጥሮ እየመራ ነው።

በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ ብዙ ውዥምብር በታየበት በሰንበቱ ዓቢይ ግጥሚያ ማንቼስተር ዩናይትድ ቼልሢይን 3-2 በማሸነፍ የለንደኑን ክለብ አመራር ወደ አንዲት ነጥብ ሊያጠብ በቅቷል። ኤፍ ሲ ቼልሢይ በ 22 ነጥቦች ይመራል፤ ማኒዩ በ 21 ሁለተኛ ነው። ጨዋታው ለአንድ አፍታም እፎይ የሚያሰኝ አልነበረም። የሜክሢኮው ተወላጅ ሃቪየር  ሄርናንዴስ ለማኒዩ በ75ኛው ደቂቃ ላይ ያስቆጠራት የድል ግብ በኦፍሣይድነት ስታከራክር የቼልሢይ ሁለት ተጫዋቾች ብሮኒስላቭ ኢቫኖቪችና ፌርናንዶ ቶሬስ ከሜዳ እንዲወጡ መደረጋቸውም ማወዛገቡ አልቀረም።                                                                                                   

ቼልሢይ በዚሁ የተነሣ በዳኛው ላይ ለፌደሬሺኑ አቤቱታ አሰምቷል። ያለፈው ሻምፒዮን ማንቼስተር ሢቲይም በበኩሉ ግጥሚያ ስዋንሢይ ሢቲይን 1-0 ሲረታ በማኒዩ በጎል ልዩነት ብቻ በመበለጥ ሶሥተኛ ነው። በተቀረ ቶተንሃም ሆትስፐር፣ ኤቨርተን፣ አርሰናልና ፉልሃም በቅርብ ይከተላሉ።

 

በጀርመን ቡንደስሊጋ የባየርን ሙንሺን ያልተቋረጠ የድል ጉዞ ከስምንት ስኬታማ ግጥሚያዎች በኋላ ትናንት ለዚያውም በገዛ ሜዳው በሌቨርኩዝን በደረሰበት 2-1 ሽንፈት አክትሟል። ለሌቨርኩዝን በ87ኛው ደቂቃ ላይ ሁለተኛዋን ወሣኝ ግብ ሢድኒይ ሣም በአናቱ የመታትን ኳስ ገጭቶ ወደ ራሱ ጎል የላካት የባየርን ተከላካይ ዤሮም ቦዋቴንግ ነበር። በነገራችን ላይ ባየርን ሙንሺን በሌቨርኩዝን ሲሸነፍ ከ 23 ዓመታት ወዲህ ለመጀመሪያ ጊዜ መሆኑ ነው። የዶቼ ቬለ የስፖርት ፕሮግራም ክፍል ባልደረባ አርኑልፍ በትቸር እንደታዘበው የባየርን ሙንሺን ሽንፈት ምክንያት በአመዛኙ በጎል ማግባት ረገድ አንደወትሮው ፍቱን ሆኖ አለመገኘት ነበር።     

«ለቡንደስሊጋ ይሄ በጣም ጥሩ ነገር ነው። ምክንያቱም ባየርኖች አሁን በቅርብ ከሚከተላቸው ከሻልከ በአራት ነጥቦች ብቻ ነው የሚለዩት። ለባየርን ሽንፈት ዋናው ምክንያት ዕድልን ለመጠቀም አለመቻል ነበር። ብዙ ዕድል ቢያገኙም ኳሷ ግን ጎል ውስጥ ለመግባት አልፈቀደችም። ከዚህም በላይ በዕለቱ ገደ ቢሶች ነበሩ። ሁለት የዕድል ጎሎች ናቸው የተቆጠሩባቸው። የመጨረሻዋን እንዲያውም ራሳቸው ናቸው ያገቧት። ባየርኖች እንግዲህ በሚወዱት ተጋጣሚያቸው በሌቨርኩዝን ፊት ትናንት ገዳም አልነበሩም። የሆነው ሆኖ መልሰው እንደሚጠናከሩና በመጪው ሰንበት በሃምቡርግ ላይ ድል እንደሚቀዳጁ ዕምነቴ ነው»  

የባየርን ሙንሺን የትናንት ሽንፈት የመዳከም አዝማሚያ ከሆነ የቡንደስሊጋው ውድድር መልሶ ፉክክር የሰፈነበት መሆኑ የሚያደስታቸው ብዙዎች ናቸው። ግን ጥያቄው ባየርን በቀላሉ ይንገዳገዳል ወይ ነው። በአርኑልፍ በትቸር ዕምነት በመሠረቱ የባየርን ሻምፒዮን መሆን ዘንድሮ ብዙም አያጠያይቅም።

«አዎን፤ አሁን የቡንደስሊጋው ፉክክር መልሶ የተቀራረበና ማራኪ እየሆነ ነው። ሁሉም ባየርንን የሚከተሉ ክለቦች አመራሩን ቀስ በቀስ የመቃረብ ዕድል አላቸው። ባየርን ሙንሺን እንዴት ሊሸነፍ እንደሚችልም ሌቨርኩዝን ትናንት በመከላከል አጨዋወቱ ጥሩ አድርጎ አሳይቷል። እና ሌሎችም ባየርንን በዚህ መንገድ ሊያሸንፉ ይችላሉ። ይህ ምናልባት ከሣምንት በኋላ ለሃምቡርግም ይሳካለት ይሆናል። ግን ሃቁን ለመናገር ባየርን በዘንድሮው ውድድር በማያሻማ ሁኔታ ሻምፒዮን እንደሚሆን እርግጠኛ ነኝ»  

በሌላ በኩል ባየርን ሙንሺን በወቅቱ ብዙ ተጫዋቾች የቆሰሉበት ሲሆን ሂደቱ ካልተገታ በቡንደስሊጋውና በአውሮፓ ሻምፒዮና ሊጋ ውድድር ጭምር አደገኛ ሊሆንበት ይችላል። ይህን አጋጣሚ ሁለተኛው ሻልከና አሁን መልሶ በመጠናከር ወደ አራተኛው ቦታ ከፍ ያለው ያለፉት ዓመታት ሻምፒዮን ዶርትሙንድም ሊጠቀሙበት እንደሚጥሩ ግልጽ ነው። መጨረሻው ምን እንደሚሆን ግን ጠብቆ ከመታዘብ በስተቀር በወቅቱ ሌላ ምርጫ የለም።

በተረፈ በኢጣሊያ ሤሪያ-አ ጁቬንቱስ ካታኛን 1-0 በማሸነፍ በአመራሩ ሲቀጥል በፈረንሣይ ሻምፒዮናም ፓሪስ-ሣንት-ዠርማን ናንሢይን በተመሳሳይ ውጤት በመርታት የበላይ እንደሆነ ነው። በኔዘርላንድ የክብር ዲቪዚዮን ትዌንቴ ኤንሼዴ ቀደምቱ ሲሆን በፖርቱጋል ሻምፒዮና ደግሞ ቤንፊካና ፖርቶ በእኩል ነጥብ ይመራሉ።

አድማጮች፤ የሚቀጥለው ዓመት 2013 የአፍሪቃ  ዋንጫ ውድድር የምድብ ዕጣ ደቡብ አፍሪቃ ወደብ ከተማ ደርባን ላይ ባለፈው ሣምንት አጋማሽ መውጣቱ አይዘነጋም። 16ቱ ሃገራት በፊታችን ጥርና የካቲት ደቡብ አፍሪቃ ውስጥ በአራት ምድቦች ተከፍለው የሚወዳደሩ ሲሆን ኢትዮጵያም ከረጅም ጊዜ ወዲህ እንደገና ተሳታፊ ናት። የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን በምድብ-ሶሥት ውስጥ ካለፈው ዋንጫ አሸናፊ ከዛምቢያ፣ ከናይጄሪያና ከቡርኪና ፋሶ ጋር በአንድ የተደለደለ ሲሆን በዚህ ካባድ ምድብ ውስጥ ብርቱ ፈተና ነው የሚጠብቀው።                                                                                                   

መለስ ብሎ ለማስታወስ ያህል ኢትዮጵያ በአፍሪቃ ዋንጫ ፍጻሜ ውድድር ከተሳተፈች ከሶሥት አሠርተ-ዓመታት በላይ ሆኗታል። ስለዚህም አሁን ይህ ዕድል መገኘቱ እጅግ የሚያስደስት ነው። እኛም እስከዚያው የሚደረገውን ዝግጅትና ውድድሩን በቅርብ እንደምንከታተል ከወዲሁ ልንገልጽ እንወዳለን።

በትናንትናው ዕለት ሕንድ ውስጥ በተካሄደው የፎርሙላ-አንድ አውቶሞቢል እሽቅድድም ጀርመናዊው ዜባስቲያን ፌትል አሸናፊ በመሆን በተከታታይ ለአራተኛ ድሉ በቅቷል። ያለፉት ሁለት ዓመታት ሻምፒዮን እሽቅድድሙን ከጅምሩ እንደመራ በፍጹም ልዕልና ሲፈጽም በማከታተል ለሶሥተኛ ጊዜ የዓለም ሻምፒዮን ለመሆን ጥሩ ዕርምጃ ነው ያደረገው። በአጠቃላይ ነጥብ ፌትልን በ 39 ነጥቦች ይበልጥ የነበረው የስፓኙ ተወላጅ ፌርናንዶ አሎንሶ በእሽቅድድሙ ሁለተኛ ሲወጣ አመራሩን ለፌትል ማስረከቡ ግድ ነው የሆነበት። 

ፌትል አሁን 240 ነጥቦች ሲኖሩት አሎንሶን በ 13 ነጥቦች ልዩነት በማስከተል ይመራል። የፎርሙላው-አንድ የውድድር ወቅት የሚያበቃው ከአንድ ወር ገደማ በኋላ በራዚል ውስጥ በሚደረግ እሽቅድድም ነው።

በቴኒስ ሤሬና ዊሊያምስ ትናንት ኢስታምቡል ላይ ተካሂዶ በነበረ የዓለም ቴኒስ ማሕበር ሻምፒዮና ፍጻሜ ግጥሚያ ሩሢያዊት ተጋጣሚዋን ማሪያ ሻራፖቫን በለየለት ውጤት 6-4,6-3 አሸንፋለች ። የ 31 ዓመቷ አሜሪካዊት በዚህ ድል ዓመቱን በስኬት ለመፈጸም ስትቃረብ ቀደም ሲል የዊምብልደንና የለንደን ኦሎምፒክ አሸናፊ እንደነበረች ይታወሳል። ሻራፖቫ ከውድድሩ የተሰናበተችው ለሤሬና ወሰን የሌለው አድናቆቷን በመግለጽ ነው። በዕውነትም በቴኒሱ የስፖርት መድረክ ዓመቱ ከሁሉም በላይ የሤሬና ዊሊያምስ ነበር ቢባል ማጋነን አይሆንም።

በዓለም የቴኒስ ማዕረግ ተዋረድ ላይ አንደኛ የሆነው የስዊሱ ሮጀር ፌደረር በአንጻሩ በአገሩ ለስድሥተኛ ጊዜ የባዝል ሻምፒዮን ለመሆን የነበረው ሕልም ትናንት በአርጄንቲናዊ ተጋጣሚው ሁዋን-ማርቲን-ዴል ፖትሮ ተገቷል። ዴል-ፖትሮ በትናንቱ ፍጻሜ ግጥሚያ 2-1 በሆነ ውጤት ሲያሸንፍ ይህም ፌደረርን በመጪው ሣምንት በፓሪስ ማስተርስ ለመሳተፍ የነበረውን ዕቅድ እስከመሰረዝ ነው ያደረሰው። ከዚሁ ሌላ በስፓኝ የቫሌንሢያ-ኦፕን ፍጻሜ ደግሞ የአገሩ ተወላጅ ዴቪድ ፌሬር የኡክራኒያ ተጋጣሚውን አሌክሳንድር ዶልጎፖሎቭን 2-1 አሸንፏል።

መሥፍን መኮንን

Audios and videos on the topic

 • ቀን 29.10.2012
 • አዘጋጅ
 • ያትሙ ገፁን ያትሙ
 • Permalink https://p.dw.com/p/16Yzd
 • ቀን 29.10.2012
 • አዘጋጅ
 • ያትሙ ገፁን ያትሙ
 • Permalink https://p.dw.com/p/16Yzd