የስፖርት ዘገባ | ስፖርት | DW | 07.05.2012
 1. Inhalt
 2. Navigation
 3. Weitere Inhalte
 4. Metanavigation
 5. Suche
 6. Choose from 30 Languages

ስፖርት

የስፖርት ዘገባ

በአውሮፓ የእግር ኳስ ሊጋዎች ውድድር ጁቬንቱስ ቱሪን በዚህ ሣምንት የኢጣሊያ ሤሪያ-አ ሻምፒዮንነቱን ሲረጋግጥ ማንቼስተር ሢቲይም ከ አርባ ዓመታት ከበለጠ ቆይታ በኋላ መልሶ የእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ ቁንጮ ለመሆን እየተቃረበ ነው።

በአውሮፓ የእግር ኳስ ሊጋዎች ውድድር ጁቬንቱስ ቱሪን በዚህ ሣምንት የኢጣሊያ ሤሪያ-አ ሻምፒዮንነቱን ሲረጋግጥ ማንቼስተር ሢቲይም ከ አርባ ዓመታት ከበለጠ ቆይታ በኋላ መልሶ የእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ ቁንጮ ለመሆን እየተቃረበ ነው። በስፓኝ ሬያል ማድሪድ ቀደም ብሎ ሻምፒዮን ሲሆን የሁለተኛው ክለብ የባርሤሎና ኮከብ ሊዮኔል ሜሢ ደግሞ ኤስፓኞል ላይ አራት ግቦችን በማስቆጠር ቢቀር በጎል አግቢነት ቀደምትነቱን ያዟል። የጀርመን ቡንደስሊጋ ውድድርም እንዲሁ ሁለት ሣምንት ቀደም ብሎ ሲለይለት ለተከታታይ ሁለተኛ ጊዜ ሻምፒዮን የሆነው ቦሩሢያ ዶርትሙንድ በ 81 ነጥቦች የሊጋ ክብረ-ወሰን አስመዝግቧል። 

በኢጣሊያ ሊጋ ጁቬንቱስ ቱሪን ትናንት ካልጋሪን 2-0 በመርታት ለ 28ኛ የሤሪያ-አ ድሉ በቅቷል። ጨዋታው እንዳበቃ በርካታ የጁቬንቱስ ደጋፊዎች የካልጋሪይን ሜዳ ሲወሩ ቀውስ እንዳይፈጠር ጥቂትም ቢሆን አስግቶ ነበር። ይሁንና አንዳች መጥፎ ነገረ አልተከተለም። ለጁቬንቱስ የመጀመሪያውን ጎል ሚርኮ ቩቺኒች ገና በአምሥተኛዋ ደቂቃ ላይ ሲያስቆጥር ሁለተኛዋን ደግሞ በራሱ ጎል ላይ ያስገባው ሚኬሌ ካኒኒ ነበር።                              

የቶሪኖው ክለብ ውድድሩ ከመጠቃለሉ በፊት አንድ ጨዋታ ቀድሞ ሻምፒዮን ሊሆን የበቃው የቅርብ ተፎካካሪው ኤሲ ሚላን በበኩሉ ግጥሚያ በመሸነፉ ነው። ኤሲ ሚላን በከተማ ተፎካካሪው በኢንተር 4-2 ሲረታ እስክ ሁለተኛው አጋማሽ የመጀመሪያ ደቂቃዎች ድረስ 2-1 ይመራ ነበር። ሆኖም ዲየጎ ሚሊቶ ሁለት መደበኛ ጎሎችንና ሁለት ፍጹም ቅጣቶችን በማግባት የኢንተርን ድል ያረጋግጣል።                                                                   

በ 37 ግጥሚያዎቹ በሙሉ ሳይሸነፍ የዘለቀው ጁቬንቱስ ከ 2003፤ ማለት ከዘጠን ዓመታት ወዲህ ለመጀመሪያ ጊዜ የዋንጫ ባለቤት ለመሆን መብቃቱ ነው። በመሃሉ በ 2005 እና በ 2006 የጨዋታዎችን ውጤት በሕገ ወጥ መንገድ በመቆጣጠር ክስ የተነሣ ማዕረጉን መነጠቁ የሚዘነጋ አይደለም። የመጨረሻዎቹ ሁለት ክለቦች ኖቫራና ቼሤና ደግሞ ወደ ሁለተኛው ዲቪዚዮን መከለሳቸው ከወዲሁ ተረጋግጧል። በጎል አግቢነት 28 ያስቆጠረው የኤሲ ሚላን አጥቂ ዝላታን ኢብራሂሞቪች የሚመራ ሲሆን በ 23 ሁለተኛው የኢንተሩ ዲየጎ ሚሊቶ ነው። 

UEFA Champions League 2011 2012 Bayern München gegen Manchester City

በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ ውድድሩ ሊጠቃለል አንዲት ግጥሚያ ብቻ ቀርታ ሳለ  ማንቼስተር ሢቲይ ኒውካስል ዩናይትድን 2-0 በማሸነፍ በጎል ብልጫም ቢሆን አንደኝነቱን ከማንቼስተር ዩናይትድ ሊነጥቅ በቅቷል። ማንቼስተር ዩናይትድ ምንም እንኳ ስዋንሢ ሢቲይን በተመሳሳይ ውጤት ቢረታም በስምንት ጎሎች በመበለጡ ሁለተኛ ነው። ባለፈው ሰኞ በሁለቱ ክለቦች ቀጥተኛ ግጥሚያ በማሸነፍ ሻምፒዮናውን መልሶ ላደመቀው ለማንቼስተር ሢቲይ ሁለቱን የዘገዩ ጎሎች ያስቆጠረው ያያ ቱሬ ነበር።                                       

በፊታችን ሰንበት ማኒዩ በዘጠን ጎሎች ልዩነት ካላሸነፈና ማንቼስተር ሢቲይ በፊናው ካልተሸነፈ ሻምፒዮንነቱ ያለቀለት ነገር ነው። ደጋፊዎቹን ከ 44 ዓመታት በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ታሪካዊ ፌስታ ይጠብቃቸዋል። ከዚህ ሌላ አርሰናል በሶሥተንነቱ ሲቀጥል ቶተንሃም ሆትስፐር ደግሞ አራተኛ ነው።                                                             

የዘንድሮው የአውሮፓ ሻምፒዮና ሊጋ የፍጻሜ ግጥሚያ ተሳታፊ ቼልሢይ በበኩሉ በለንደኑ ዌምብሌይ ስታዲዮም በተካሄደ የእንግሊዝ እግር ኳስ ማሕበር የ FA ፍጻሜ ግጥሚያ ሊቨርፑልን 2-1 በመርታት የዋንጫ ባለቤት ሆኗል። ዎልበርሃምፕተን ከወዲሁ ወደ ሁለተኛው ዲቪዚዮን ሲከለስ ብላክበርን ሮቨርስና ቦልተን ወንደረርስም ተመሳሳይ ዕጣ ነው የሚጠብቃቸው። በጎል አግቢነት የአርሰናሉ ሮቢን-ፋን-ፐርሲ 30 አስቆጥሮ ቀደምቱ  ሲሆን የማንቼስተሩ ዌይን ሩኒይ በ 26 ሁለተኛ ነው።

በስፓኝ ላ-ሊጋ የሬያል ማድሪድ ሻምፒዮንነት ከአራት ዓመታት የባርሣ ልዕልና በኋላ ባለፈው ሣምንት አጋማሽ ላይ  ሲለይለት ባርሤሎናም ጎረቤቱን ኤስፓኞልን በኑው-ካምፕ ስታዲዮም 4-0 በማሸነፍ የአሰልጣኙን የፔፕ ጉዋርዲዮላን ስንብት አኩሪ አድርጎታል። የጨዋታውን አራት ጎሎች በሙሉ አርጄንቲናዊው ሊዮኔል ሜሢ ሲያስቆጥር በ 50 ጎሎች የፕሪሜራ ዲቪዚዮኑ ቁንጮ ነው። ባለፉት ዓመታት በተከታታይ የዓለም ድንቅ ተጫዋች በመባል የተመረጠው ሜሢ በዘንድሮው የውድድር ወቅት የተለያዩ ውድድሮች በሙሉ 72 ጎሎችን በማስቆጠር በአውሮፓ አዲስ ክብረ-ወሰን አስመዝግቧል።

በጀርመን ቡንደስሊጋ ሻምፒዮናው ቀድሞ ሲለይለት ሰንበቱን ይበልጥ ትኩረትን የሳቡት ወደታች ላለመከለስ የሚደረጉት ግጥሚያዎች ነበሩ። በዚሁ ትግልም ቀድሞ ገናና ከነበሩት የቡንደስሊጋ ክለቦች አንዱ ኤፍሲ ኮሎኝ እንደ ካይዘርስላውተርን ሁሉ ወደ ሁለተኛው ዲቪዚዮን መውረዱ ግድ ሆኖበታል። ኮሎኝ በመጨረሻ ግጥሚያው ስንብት ያደረገው በሜዳው በባየርን ሙንሺን 4-1 ከተሸነፈ በኋላ ነው። በመጨው የውድድር ወቅት ለአርሰናል የሚጫወተው የቡድኑ መንኮራኩር ሉካስ ፖዶልስኪ ክለቡን በሃዘን ሲሰናበት ውድቀቱ እርግጥ የቆየ መንስዔ እንዳለው ሳይጠቅስም አላለፈም።

«ዛሬና አሁን አይደለም ወደታች የወረድነው። በኔ አስተሳሰብ ይሄ ሁሉ ያለፉት ሣምንታትና ወራት ድክመት አጠቃላይ ውጤት ነው። ብዙ ሽንፍቶች የደረሰበትና መዓት ጎሎች የተቆጠሩበት ቡድን በመሠረቱ በመጨረሻ ላይ እንዳለ ለመቆየት ማሰብ የለበትም፤ የሚገባውም አይደለም። ይህ በቀላሉ መባል ያለበት ነገር ነው»

ሄርታ በርሊን በአንጻሩ ሆፈንሃይምን 3-1 በማሸነፍ ከፍተኛው ሊጋ ውስጥ ለመቆየት ያለውን ዕድል ለመጠበቅ ችሏል። ክለቡ ባለበት እንዲቀጥል እርግጥ የሁለተኛውን ዲቪዚዮን ሶሥተኛ ዱስልዶርፍን ማሸነፉ ግድ ነው። የሆነው ሆኖ የጀርመን ቡንደስሊጋ በመጪው የውድድር ወቅት ከሁለተኛው ዲቪዚዮን ከፍ በሚሉት በፍራንክፉርትና በፉርት የሚደምቅ ይሆናል። በተቀረ የሚቀጥለው ሣምንት ደግሞ የጀርመን ፌደሬሺን ዋንጫ ፍጻሜ ግጥሚያ የሚካሄድበት ሲሆን ዶርትሙንድ ከባየርን ጋር በሚያደርገው ግጥሚያ የሁለተኛ ድል ዕድል ይጠብቀዋል።

ፍጻሜ ግጥሚያን ካነሣን ከነገ በስቲያ ረቡዕ የዘንድሮው የአውሮፓ ሊግ ዋንጫ የመጨረሻ ግጥሚያ ሩሜኒያ፤ ቡካሬስት ላይ ይካሄዳል። ግጥሚያው በሁለቱ የስፓን ክለቦች በአትሌቲኮ ማድሪድና በአትሌቲክ ቢልባዎ መካከል የሚካሄድ ሲሆን የስፓኝ እግር ኳስ መለያዎች ባርሣና ሬያል ብቻ እንዳልሆኑ የሚታይበትም ነው። የአውሮፓ ሻምፒዮና ሊጋ ፍጻሜ ተጋጣሚዎች ደግሞ ባየርን ሙንሺንና ቼልሢይ መሆናቸው ይታወቃል።   

አትሌቲክስ

በትናንትናው ዕለት በርሊን ላይ በተካሄደው የ 25 ኪሎሜትር ሩጫ ኬንያዊው ዴኒስ ኪሜቶ በአዲስ የዓለም ክብረ-ወሰን አሸናፊ ሆኗል። ክብረ-ወሰኑ በጥንታዊው የጀርመን የመንገድ ሩጫ ውድድር ሂደት እስካሁን ሰባተኛው መሆኑ ነው። ኪሜቶ የአገሩ ልጅ ከሁለት ዓመት በፊት አስመዝግቦት የነበረውን ክብረ-ወሰን በ 32 ሤኮንዶች ሲያሻሽል በሴቶችም ቀዳሚ ሆና ከበርሊኑ ኦሊምፒያ ስታዲዮም የገባቸው ኬንያዊቱ አትሌት ካሮሊን ቼፕኮኒይ ነበረች።

በዚሁ በጀርመን ሰንበቱን በሃኖቨርና በማይንስ ከተሞች የተካሄዱት የማራቶር ሩጫ ውድድሮችም የኬንያና የኢትዮጵያ አትሌቶች ልዕልና ያመዘነባቸው ነበሩ። በሃኖቨር በወንዶች ኬንያዊው ጆዜፍ ኪፕቱም ሲያሸንፍ መገርሣ ባቻ ከኢትዮጵያም አብሮ ከግቡ በመድረስ ለጥቂት ሁለተኛ ሆኗል። ኬንያዊው ፒተር ኪሩዊ ሶሥተኛ ሲወጣ ከአራት እስከ ስድሥት ተከታትለው የገቡት ኢትዮጵያውያን ነበሩ። በሴቶች ሩሢያዊቱ ናታሊያ ፑችኮቫ ስታሸንፍ ከሁለት እስክ ስድሥት የተከታተሉትም የኢትዮጵያ አትሌቶች ናቸው።

በማይንስ ማራቶን ደግሞ የኬንያው ሢካስ ቶክ ሲያሸንፍ የታንዛኒያው ሞሐመድ ምዜንዱኪ ሁለተኛ ወጥቷል፤ ሶሥተኛ ካሣ ብርሃኑ ከኢትዮጵያ! በሴቶች ድሉ የሩሢያና የኡክራኒያ ሲሆን ኬንያዊቱ ኤስተር ማሃሪያ ሶሥተኛ ወጥታለች። ድርቤ ኩምሣና ቢሰጠኝ ተቋም ደግሞ አራተኛና አምሥተኛ ሆነዋል።

በጃፓን፤ ካዋዛኪ ግራንድ-ፕሪ የአትሌቲክስ ውድድር በአጭር ሩጫና ዝላይ ቻይናና አውስትራሊያ አየል ብለው ሲታዩ በ 3 ሺህ ሜትር መሰናክል የኢትዮጵያው አትሌት  ጋሪ ሮባ ሁለት ኬንያውያንን ተከትሉ በሶሥተኝነት ሩጫውን በመፈጸም ግሩም ውጤት አስመዝግቧል። በሴቶች 800 ሜትር እንዲያውም ዓለም ገ/እግዚአብሄር የአውስትራሊያና የአሜሪካ ተፎካካሪዎቿን ከኋላዋ በማስቀረት አሸናፊ ሆናለች።

በጃሜይካ  ዓለምአቀፍ ውድድር ደግሞ የድርብ ክብረ-ወሰን ባለቤት የሆነው ድንቅ አትሌት ዩሤይን ቦልት በመቶ ሜትር ሩጫ በ 9,82 ሤኮንድ በማሸነፍ የዓመቱን ቀደምት ጊዜ አስመዝግቧል። ቦልት በዚህ ዓመት በመቶ ሜትር ሲወዳደር ለመጀመሪያ ጊዜ መሆኑ ነው። ሌላው ጃማይካዊ ዮሃን ብሌክም 200 ሜትር ሩጫውን በዓለም ላይ ፈጣን በሆነ 19,91 ሤኮንድ ጊዜ ፈጽሟል። በሴቶች 400 ሜትርም ኖቭሊን ዊሊያምስ ግሩም ወጤት አስመዝግባለች።                                                                                             

በ 1500 ሜትር ሩጫ የኢትዮጵያው አማን ወቴ አንደኛ ሲሆን በ 3 ሺህ ሜትር መሰናክል ያሸነፈው ደግሞ የአሜሪካው አትሌት ቤን ብሩስ ነው። የአትሌቲክስ ውድድርን ካነሣን የ 2015 የአውሮፓ የአዳራሽ ውስጥ አትሌቲክስ ሻምፒዮና በፕራግ እንዲስተናገድ ተወስኗል። 33ኛው የአውሮፓ ሻምፒዮና ለቼክ ሬፑብሊክ መሰጠቱን ያፋ ያደረጉት የአውሮፓ አትሌቲክስ ፕሬዚደንት ሃንስ ዮርግ ቪርትስ ናቸው። ቀደም የሚለው መጨው የአውሮፓ የአዳራሽ ውስጥ ሻምፒዮና ስዊድን ከተማ ጎተቦርግ ላይ ይካሄዳል።

በተረፈ በፊታችን ሐምሌ ወር የኦሎምፒክ ጨዋታ የሚካሄድበት የለንደን ኦሎምፒክ ስታዲዮም ባለፈው አርብ በብሪታኒያ ተማሪዎች ውድድር ለመጀመሪያ ጊዜ ተፈትሿል። 1500 ገደማ የሚጠጉ ተመልካቾች በስታዲዮሙ ተገኝተው የታሪክ ምስክር ለመሆን ሲበቁ ለይፋው መክፈቻ ስነ ስርዓት ሃያ ደቂቃ በሚሆን ጊዜ ውስጥ 40 ሺህ ቲኬቶች ሊሸጡ በቅተዋል። ስታዲዮሙ በጠቅላላው 80 ሺህ ተመልካችን መያዝ የሚችል ነው።

Philipp Kohlschreiber

ቴኒስ

ትናንት ፖርቱጋል ውስጥ ተካሂዶ በነበረ የኤስቶሪል ፍጻሜ ግጥሚያ አርጄኒቲናዊው ሁዋን-ማኑዌል-ዴል-ፖትሮ ሪቻርድ ጋስኬትን 6-4,6-2 በማሸነፍ ዘንድሮ ሁለተኛ ለሆነው ድሉ በቅቷል። ጋስኬት በአንጻሩ በኤስቶሪል ፍጻሜ ሲሸነፍ ለሁለተኛ ጊዜ መሆኑ ነው። በሚዩኒክ-ኦፕን ፍጻሜ ግጥሚያ ደግሞ ጀርመናዊው ፊሊፕ ኮልሽራይበር ክሮአቱን ማሪን ቺሊችን በማሸነፍ ለሁለተኛ ድሉ በቅቷል። በሰርቢያ የቴኒስ ፍጻሚ ግጥሚያም እንዲሁ የኢጣሊያው አንድሬያስ ሤፒ የፈረንሣይ ተጋጣሚውን ቤኑዋ ፔይርን በቀላሉ 6-3, 6-2 ለማሸነፍ በቅቷል። በተቀረ የዓለም ቴኒስ የማዕረግ ተዋረዱን አሁንም በወንዶች የሰርቢያው ኖባክ ጆኮቪችና በሴቶችም የቤላሩሷ ቪክቶሪያ አዛሬንካ ይመራሉ።

መሥፍን መኮንን

Audios and videos on the topic

 • ቀን 07.05.2012
 • አዘጋጅ
 • ያትሙ ገፁን ያትሙ
 • Permalink https://p.dw.com/p/14rNy
 • ቀን 07.05.2012
 • አዘጋጅ
 • ያትሙ ገፁን ያትሙ
 • Permalink https://p.dw.com/p/14rNy