የስፖርት ዘገባ | ስፖርት | DW | 02.04.2012
 1. Inhalt
 2. Navigation
 3. Weitere Inhalte
 4. Metanavigation
 5. Suche
 6. Choose from 30 Languages

ስፖርት

የስፖርት ዘገባ

በአውሮፓ እግር ኳስ ሊጋዎች ውድድር ቀደምቱ ክለቦች ለሻምፒዮንነት የሚያደርጉት ትግል ተጠናክሮ ቀጥሏል።

በአውሮፓ እግር ኳስ ሊጋዎች ውድድር ቀደምቱ ክለቦች ለሻምፒዮንነት የሚያደርጉት ትግል ተጠናክሮ ቀጥሏል። በጀርመን ቡንደስሊጋ አንዴ አስክ ስምንት ነጥቦች ሰፍቶ የነበረው የዶርትሙንድ አመራር ወደ ሶሥት ሲጠብ በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ ደግሞ የማንቼስተር ሢቲያ መዳከም ለቅርብ ተፎካካሪው ለማኒዩ እየበጀ ነው።

በስፓኝ ፕሪሜራ ዲቪዚዮን ላ-ሊጋ ቀደምቱ ሬያል ማድሪድ ኦሳሱናን 5-1 ሲቀጣ ከአራት ዓመታት በኋላ መልሶ ሻምፒዮን ለመሆን መቃረቡን ቀጥሏል። ጎሎቹን ያስቆጠሩት ክሪስቲያኖ ሮናልዶ፣ ካሪም ቤንዜማና ጎንዛሉ ሂጉዌይን ነበሩ። ባርሤሎናም በበኩሉ ግጥሚያ አትሌቲኮ ቢልባዎን 2-0 ሲረታ በስድሥት ነጥቦች ዝቅ ብሎ በሁለተኝነቱ ቀጥሏል። በጎል አግቢነት ሮናልዶ በ 37 የሚመራ ሲሆን የባርሣው ሊዮኔል ሜሢም በ 36 ሁለተኛ ነው። በአጠቃላይ ሬያል ሰባት ግጥሚያዎች ቀርተው ሳል በ 78 ነጥቦች የሚመራ ሲሆን  ባርሣ 72 ነጥቦች አሉት፤ ሶሥተኛው ቫሌንሢያ ነው።

በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ ውድድር ማንቼስተር ሢቲይ ከሰንደርላንድ ለዚያውም ዘግይቶ ባስቆጠራቸው ጎሎች 3-3 ሲለያይ ሁለት ጠቃሚ ነጥቦችን ማጣቱ ገና ዛሬ ማምሻውን ከብላክበርን ሮቨርስ የሚጋጠመው ማንቼስተር ዩናይትድ አመራሩን እንዲያሰፋ መልካም ሁኔታን ፈጥሯል። ማንቼስተር ዩናይትድ አሁን አንድ ጨዋታ ጎሎት እንኳ  በሁለት ነጥቦች ብልጫ በ 73 የሚመራ ሲሆን በዛሬው ምሽት ከቀናው ሢቲይን የሚያስከትለው በአምሥት ነጥቦች ልዩነት ነው። አርሰናል በኩዊንስ ፓርክ ሬንጀርስ 2-1 ተረትቶ በ 58 ነጥቦች  ሶሥተኛ ሲሆን ቶተንሃም ሆትስፐርም በተመሳሳይ ነጥብ አራተኛ ነው።

ቡንደስሊጋ

በጀርመን ቡንደስሊጋ ውድድር በጥቂቱም ቢሆን ያለቀለት መስሎ የነበረው የሻምፒንነት ፉክክር እንደገና ታድሷል። ቀደምቱ ዶርትሙንድ ከሽቱትጋርት ባደረገው ግጥሚያ  4-4 ሲለያይ እስከ ስምንት ዘልቆ የነበረው የነጥብ ብልጫው አሁን ወደ ሶሥት ዝቅ ብሏል። የዶርትሙንድ በእኩል ለእኩል ውጤት መወሰን በተለይም የጠቀመው በሁለተኛነት ለሚከተለው ለባየርን ሙንሺን ነው። ባየርን በበኩሉ ግጥሚያ ኑርንበርግን 1-0 ማሸነፉ ተሳክቶለታል። ውጤቱ እርግጥ ጠባብ ቢሆንም ለቡድኑ የመሃል ሜዳ ተጫዋች ለባስቲያን ሽቫይንሽታይገር ግን ወሣኙ ነገር ከኑርንበርግ ሶሥት ነጥቦችን ይዞ መመለሱ ነበር።

«ዛሬ አስፈላጊው ነገር ድል ብቻ ነበር። እና ይህም ተሳክቶልናል። እርግጥ በጨዋታው አንዳንድ ዕድሎች አምልጠውናል። እንዲያ ባይሆን ኖሮ ጨዋታው ቀድሞ በለየለት ነበር። ስለዚህም በሶሥቱ ነጥቦች በጣሙን ደስተኞች ነን»                                                                       

ባየርን በዚህ ጠቃሚ ድሉ በሶሥት ሻምፒዮናዎች፤ ማለትም በአውሮፓ ሻምፒዮና ሊጋ ፣ በጀርመን ፌደሬሽን ዋንጫና በቡንደስሊጋው ውድድር ሶሥትዮሽ ድል ለመጎነጸፍ ያለውን ዕድል ጠብቋል። በሌላ በኩል ለመጪው የአውሮፓ ሻምፒዮና ሊጋ ውድድር በቀጥታ ለማለፍ የሚያስችለውን ሶሥተኛ ቦታ ለማረጋገጥ ሻልከና ግላድባህ ሲፎካከሩ የኋለኛው በሃኖቨር መሸነፍ ለሻልከ በጅቶታል። ሻልከ በበኩሉ ግጥሚያ ምንም እንኳ ከሆፈንሃይም 1-1 ቢለያይም ሶሥተኛነቱን ከማረጋገጥ ባሻገር ከግላድባህ ጋር ያለውን የነጥብ ልዩነት ወደ ሶሥት ማስፋቱም ሆኖለታል።

በተቀረ በዚህ ሰንበት ይበልጡን በአቆልቋይ ሂደታቸው ቀጥለው የታዩት በተለይም ሌቨርኩዝን፣ ብሬመንና ኮሎኝ ነበሩ። ብሬመንና ሌቨርኩዝን በየበኩላቸው ገጥሚያዎች በመሸነፍ ለአውሮፓ ሊጋ ተሳትፎ የሚያበቃውን አምሥተኛና ስድሥተኛ ቦታ ለመጀመሪያ ጊዜ ለቀዋል። ሁኔታውን በመጠቀም በቦታቸው የተተኩት ደግሞ ቀደምቱን ክለቦች ዶርትሙንድንና ግላድባህን ያንገዳገዱት ሃኖቨርና ሽቱትጋርት ናቸው። ሌቨርኩዝን ሰባተኛ፤ ብሬመን ስምንተኛ!                                                                                        

በነገራችን ላይ ሌቨርኩዝን ትናንት ለክስረቱ ተጠያቂ ያደረገውን አሠልጣኙን ሮቢን ዱትን ከስራ አሰናብቷል። ሌቨርኩዝን በአዲስ የፊንላንድ አሠልጣኝ ከወደቀበት አዘቅት ለመውጣት ዕርምጃ ሲወስድ በሌላ በኩል ሌላው የራይን ወንዝ አካካቢ ክለብ ኮሎኝ ወደ 16 ኛ ቦታ ማቆልቆሉ በወቅቱ የከተማው ዓቢይ መነጋገሪያ ርዕስ ነው።                                                    

በዝቅተኛው ክለብ በአውግስቡርግ 2-1 የተረታው ኮሎኝ ባለፉት ሣምንታት ድክመቱ ከቀጠለ ወደ ሁለተኛው ዲቪዚዮን መከለሱ የማይቀርለት ነገር ነው የሚሆነው። በሌላ በኩል ሃምቡርግ የመጨረሻውን ካይዘርስላውተርንን 1-0 ረትቶ ራሱን ወደ 15ኛው ቦታ ከፍ በማድረግ በሣምንቱ ጥቂትም ቢሆን ዕፎይ ሊል በቅቷል።  በርሊን በአንጻሩ በቮልፍስቡርግ 4-1 ሲሸነፍ 17ኛ ነው።

በኢጣሊያ ሤሪያ-አ ቀደምቱ ኤሲ ሚላን ከካታኛ 1-1 ብቻ በመለያየቱ ከቅርብ ተፎካካሪው ከጁቬንቱስ ጋር ያለው የነጥብ ልዩነት ወደ ሁለት ጠበብ ብሏል። ይህም ውድድሩ ሊፈጸም ስምንት ግጥሚያዎች ቀርተው ሳለ የሁለቱን ክለቦች ፉክክር ይበልጥ የሚያጠናክር ነው። ጁቬንቱስ በበኩሉ ግጥሚያ ናፖሊን 3-0 በመርታት ሰንበቱን በስኬት አሳልፏል። ሶሥተኛው በፓርማ 3-1 የተሸነፈው ላሢዮ ነው። ውድድሩ ሊፈጸም  ስምንት ግጥሚያዎች ቀርተው ሳለ የቀደምቱ ክለቦች ልዩነት መጥበብ ለሻምፒዮንነት የሚደረገውን ትግል ይበልጥ የሚያጠናክር እንደሚሆን አንድና ሁለት የለውም።                               

በሌላ በኩል በኢጣሊያ ሊጋ ሰንበቱ ሃዘን የጋረደውም ነበር። የ 14 ጊዜው የኢጣሊያ ብሄራዊ ቡድን ተጫዋች የጆርጆ ቺናግሊያ መሞት የስፖርቱን አፍቃሪዎች በጣሙን አሳዝኗል። የአንዴው የሮማ አጥቂ ቺናግሊያ እጎአ በ 1983 ኢጣሊያን ትቶ ወደ ሰሜን አሜሪካ በመሻገር ፔሌን ከመሳሰሉት ከዋክብት ጋር ለኮዝሞስ ኒውዮርክ ሲጫወት አራት ጊዜ በሊጋው ጎል አግቢነት መሸለሙ ይታወሳል። ቺናግሊያ በልብ ሕመም ሳቢያ ትናንት በ 65 ዓመት ዕድሜ ያረፈው ፍሎሪዳ ውስጥ ነበር። በተቀረ በፈረንሣይ ሊጋ ሞንትፔሊዬር፣ በፖርቱጋል ሻምፒዮና ፖርቶና በኔዘርላንድ ደግሞ አያክስ አምስተርዳም መሪዎቹ ናቸው።

Flash-Galerie Leichtathletik Weltmeisterschaften Daegu Südkorea 2011

አትሌቲክስ

በትናንትናው ዕለት በዚህ በጀርመን ተካሂዶ የነበረው የዘንድሮው የበርሊን ግማሽ ማራቶን ውድድር በወንዶችና በሴቶችም የኬንያውያን ልዕልና የታየበት ሆኖ አልፏል። በወንዶች ዴኒስ ኮች የዓለም ሻምፒዮኑን ዊልሰን ኪፕሮፕን በቀለጠፈ አፈጻጸም ቀድሞ ሲያሸንፍ በ 59,14 ደቂቃ የግል ሬኮርዱንም አሻሽሏል። ሩጫውን በሶሥተኝነት የፈጸመው ደግሞ ኤዜኪየል ቼቢ ነበር። ኬናያውያኑ በወንዶች ከአንድ እስከ ሶሥት ተከታትለው ሲያሸንፉ በሴቶችም ይህንኑ ድል ደግመውታል። ፊልስ ኦንጎሪ  ሄላህ ኪፕሮፕን አስከትላ ስታሸንፍ ካሮሊን ቼፕኮኒይ ደግሞ ሶሥተኛ ወጥታለች።

በካሊፎርኒያ-ካርልስባድ ዓመታዊ የመንግድ የ 5 ሺህ ሜትር ሩጫ ደግሞ ድሉ የኢትዮጵያውያን ነበር። ደጀን ገብረመስቀል ሩጫውን በ 13 ደቂቃ ከ 11 ሤኮንድ ጊዜ በመፈጸም ሲያሸንፍ ወጣቱ ሃጎስ ገ/ሕይወት ሁለተኛ፤ እንዲሁም የኬንያው ኤሊዩድ ኪፕቾጌ ሶሥተኛ ሆኗል። በሴቶች የኦሎምፒኳ የአምሥትና አሥር ሺህ ሜትር ሻምፒዮን ጥሩነሽ ዲባባ ተፎካካሪዎቿን ወደመጨረሻው ላይ ጥላ በመሄድ ስታሸንፍ ወርቅነሽ ኪዳኔ ሁለተኛ ወጥታለች።

Novak Djokovic

ቴኒስ

በትናንትናው ዕለት አሜሪካ ውስጥ በተጠቃለለው የማያሚ ማስተርስ የወንዶች ፍጻሜ ግጥሚያ የሰርቢያው የዓለም አንደኛ ኖቫክ ጆኮቪች የብሪታኒያ ተጋጣሚውን ኤንዲይ መሪያን 6-1,7-6 በመርታት የውድድሩ አሸናፊ ሆኗል። ጆኮቪች ማያሚ ላይ ሲያሸንፍ ለሶሥተኛ ጊዜ መሆኑ ነው። በሴቶች ደግሞ በዓለም የማዕረግ ተዋረድ ላይ አምሥተኛ የሆነችው የፖላንዷ አግኒየሽካ ራድቫንስካ አንድ ቀን ቀደም ሲል ባልተጠበቀ ሁኔታ ሩሢያዊቱን ማሪያ ሻራፖቫን በሁለት ምድብ ጨዋታ በማሸነፍ ታዛቢዎችን አስደንቃለች። በተረፈ ዛሬ የወጣ ወቅታዊ የማዕረግ ተዋረድ በወንዶች ኖቫክ ጆኮቪችና በሴቶች ደግሞ የቤላሩሷ ቪክቶሪያ አዛሬንካ ግንባር ቀደም ሆነው መቀጠላቸውን አመልክቷል።     

የጠረጴዛ ቴኒስ

ጀርመን ከተማ ዶርትሙንድ ውስጥ የተካሄደው የዓለም የጠረጴዛ ቴኒስ የቡድን ሻምፒዮና በቻይና ወንዶችና ሴቶች አጠቃላይ ድል ትናንት ተፈጽሟል። ቻይና በወንዶች የአስተናጋጇን አገር የጀርመንን ቡድን ሰትረታ ሴቶቹ ያሸነፉት ደግሞ ያለፈውን ውድድር ሻምፒዮን ሲንጋፑርን ነበር። ቻይና በውድድሩ በመላው 24 ተናጠል ጨዋታዎች ስታሸንፍ የትናንቱ የዓለም ሻምፒዮና ድል በተከታታይ ስድሥተኛ መሆኑ ነው። ጀርመን በአውሮፓ ጠንካራው ቡድን ሲኖራት ታዋቂ ተጫዋቿ ቲሞ ቦል ቻይና ላይ ለመድረስ መጣሩ እንደሚቀጥል ነው የተናገረው።

«ጥቂትም ቢሆን በራሳችን ልንኮራ ይገባናል ብዬ ነው የማስበው። ምክንያቱም ከቻይና ቀጥሎ ሁለተኛ ጠንካራ አገር እንደሆንን አስመስክረናል። ሁልጊዜም ጠንካሮቹን በመፎካከሩ ላይ ነው ያተኮርነው። እና ይህም ነው መለያችን። ጃፓንንና ኮሪያን ለማለፍ በመፈለግ ብቻ አንወሰንም። ከቻይና ላይ ለመድረስም ነው የምንፈልገው። በቀላሉ ገባችን አሁንም ወደፊትም ይህ ነው» 

ለማንኛውም የቻይና ስኬት እጅግ ከፍተኛ ነው። አገሪቱ ውድድሩ ከተጀመረ ከ 1926 ወዲህ በሴቶችና በውንዶች በአጠቃላይ 36 ወርቅ ሜዳሊያዎችን አሸንፋለች። ሁለቱም ቡድኖች፤ ማለት ወንዶቹም ሆኑ ሴቶቹ ዘንድሮ ወደ ለንደን ኦሎምፒክ የሚጓዙት ድላቸውን ለመድገም ነው። ከአራት ዓመት በፊት በቤይጂንግ ኦሎምፒክ የወርቅ ሜዳሊያ አሸናፊዎች እንደነበሩ ያታወሳል።

በእግር ኳስ ለማጠቃለል ነገና ከነገ በስቲያ በዚህ በአውሮፓ የሻምፒዮና ሊጋው ሩብ ፍጻሜ የመልስ ግጥሚያዎች ይካሄዳሉ። በነገው ምሽት የጀርመኑ ባየርን ሙንሺን የኦሎምፒክ ማርሤይ አስተናጋጅ ነው። ባየርን በመጀመሪያው ጨዋታ 2-0 ማሸነፉ ሲታወስ በገዛ ሜዳው በሚያካሂደው ግጥሚያ ወደፊት መራመዱ የሚገደው አይመስልም። የፈረንሣዩ ክለብ ማርሤይ በአንጻሩ ውጤቱን ለመገልበጥ በጣም መታገል ይኖርበታል።

የምሽቱ ሁለተኛ ግጥሚያ የባርሤሎናና የአሲ ሚላን  ከሁሉም በላይ በታላቅ ጉጉት የሚጠበቀው ሲሆን የመጀመሪያው ግጥሚያ 0-0 ነበር ያበቃው። በመሆኑም በመሠረቱ ሁለቱም ክለቦች እኩል ዕድል ሲኖራቸው ምናልባት ባርሣ በሜዳው የሚጫወት በመሆኑ  በተሻለ ሁኔታ ላይ ነው ሊባል ይችላል። ግን በዚህ የተነሣ ዕድሉ ወደ ባርሣ ማዘንበሉ የግድ እርግጠኛ አይደለም።

በማግሥቱ ረቡዕ ምሽት ተራው የሬያል ማድሪድ ከኒኮዚያና የቼልሢይ ከቤንፊካ ነው። ሬያል ማድሪድ አፓል ኒኮዚያን በመጀመሪያው ጨዋታ 3-0 ማሸነፉ ሲታወስ በሜዳው በቤርናቤው ስታዲዮም በሚያካሂደው የመልስ ግጥሚያ ችግር የሚገጥመው አይሆንም። ቼልሢይም ቢሆን ሊዝበን ላይ 1-0 አሸንፎ በመመለሱ ከቤንፊካ ጋር የተሻለው ዕድል ነው ያለው። የሆነው ሆኖ ግን ሁሉንም ጠብቆ መታዘቡ ግድ ነው።

መሥፍን መኮንን

Audios and videos on the topic

 • ቀን 02.04.2012
 • አዘጋጅ
 • ያትሙ ገፁን ያትሙ
 • Permalink https://p.dw.com/p/14WeV
 • ቀን 02.04.2012
 • አዘጋጅ
 • ያትሙ ገፁን ያትሙ
 • Permalink https://p.dw.com/p/14WeV