የስፖርት ዘገባ | ስፖርት | DW | 01.02.2012
 1. Inhalt
 2. Navigation
 3. Weitere Inhalte
 4. Metanavigation
 5. Suche
 6. Choose from 30 Languages

ስፖርት

የስፖርት ዘገባ

በአውሮፓ ቀደምት የእግር ኳስ ሊጋዎች ውስጥ የክረምቱ ዕረፍት ተጠናቆ ሁለተኛው ዙር ውድድር የሚከፈትበት ጊዜ እየተቃረበ ሲሆን የተለያዩት ክለቦች ሞቃት በሆኑት የደቡብ አውሮፓ አካባቢዎች ዝግጅታቸውን ጀምረዋል።

በአውሮፓ ቀደምት የእግር ኳስ ሊጋዎች ውስጥ የክረምቱ ዕረፍት ተጠናቆ ሁለተኛው ዙር ውድድር የሚከፈትበት ጊዜ እየተቃረበ ሲሆን የተለያዩት ክለቦች ሞቃት በሆኑት የደቡብ አውሮፓ አካባቢዎች ዝግጅታቸውን ጀምረዋል።

ለምሳሌ ያህል የጀርመን ቡንደስሊጋ ቀደምት ክለቦች ባየርን ሙንሺንና ሻልከ ከአገራቸው ቅዝቃዜ በመሸሽ በካታር ሲከትሙ ቮልፍስቡርግም እዚያው ፈንጠር ብሎ በዱባይ እየተለማመደ ነው። ከሁለት ክለቦች በስተቀር ሌሎቹም በቱርክና በስፓኝ ለመልሱ ዙር ራሳቸውን ማማሟቅ ይዘዋል።

በአጠቃላይ በስፓኝ፣ በኢጣሊያ፤ በፈረንሣይ፣ በኔዘርላንድ፣ በፖርቱጋል ወዘተ... በአዲስ ተጫዋቾች ጭምር ተጠናክሮ ለመመለስ የተለመደው ዝግጅት እየተካሄደ ሲሆን በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ በአንጻሩ ውድድሩ ቀጥሏል። ሊጋውን በአንደኝነት የሚመራው ማንቼስተር ሢቲይ ትናንት በሰንደርላንድ 1-0 ሲረታ የተቀሩት ቀደምት ክለቦች ማንቼስተር ዩናይትድና ቼልሢይም ሰንበቱን ያሳለፉት በሽንፈት ነበር። በተለይም የማንቼስተር ዩናይትድ በሊጋው መጨረሻ በብላክበርን ሮቨርስ ለዚያውም በገዛ ሜዳው በኦልድ-ትፔፎርድ መሸነፍ ለዝናኛ አሠልጣኙ ለሰር/አሌክስ ፈርጊሰን ሰባኛ ዓመት የልደት በዓል የተጠበቀው ስጦታ አልነበረም። ማኒዩ በዚሁ ግጥሚያ 3-2 ሲረታ ሰር/ፈርጊሰንም በደስታ የጀመሩትን ቀን ያጠዋለሉት በብሽቀት ነው። ቼልሢይም በሜዳው በኤስተን ቪላ 3-1 ተሸንፏል።  

በነገራችን ላይ የማኒዩ መሸነፍ በአጥቂው በዌይን ሩኒይ ስነ-ምግባር ጉድለት ላይ የሚደረገው ክርክር እንደገና እንዲጠነክር ነው ያደረገው። እርግጥ ሩኒይ በዕለቱ ለቡድኑ አልተሰለፈም። ለዚህም ምክንያት የሆነው በተለይ በገናው በዓል ወቅት የሌት የመጠጥ ቤት ዙረቱ መጋለጥ ነበር። የብሪታኒያ የዜና ምንጮች እንደሚሉት ፈርጊሰን የ 300 ሺህ ኤውሮ መቀጮ ሳይጥሉበት አልቀረም። መቀጮው ለሩኒይ የአንድ ሣምንት ገቢውን ያህል መሆኑ ሲነገር ታዲያ በዚህ ዕርምጃ ጸባዩን እንዲያሳምር መገፋት መቻሉ እያደር የሚታይ ነው የሚሆነው።                                                                                         
ያም ሆነ ይህ ከሰንበቱ 19ኛ ግጥሚያዎች በኋላ ማንቼስተር ሢቲይ ፕሬሚየር ሊጉን በ 45 ነጥቦች የሚመራ ሲሆን ማንቼስተር ዩናይትድ በተመሳሳይ ነጥብ ሆኖም በጎል ልዩነት በመበለጥ ሁለተኛ ነው። ቶተንሃም ሆትስፐር አንድ ጨዋታ ጎሎት በ 39 ነጥቦች ሶሥተኛ ሲሆን አርሰናል ኩዊንስ-ፓርክ-ሬንጀርስን 1-0 በመርታት ቼልሢይን ተሻግሮ አራተኛ ሊሆን በቅቷል። ሊቨርፑል ስድሥተኛ ነው። የፕሬሚየር ሊጉ ውድድር በአዲሱ ዓመትም ማራኪ ሆኖ የሚቀጥል ሲሆን 17 በማስቆጠር ሊጋውን በጎል አግቢነት የሚመራው ሆላንዳዊው የአርሰናል ተጫዋች ሮቢን-ፋን-ፐርዚ ነው።                                                            
የኒውካስል ዩናይትዱ ዴምባ-ባ በ 14 ሁለተኛ ሲሆን የማንቼስተር ሢቲይና የማንቼስተር ዩናይትድ አጥቂዎች ሤርጆ አጉዌሮና ዌይን ሩኒይ ደግሞ እያንዳንዳቸው 13 ጎሎችን አስቆጥረዋል። የእንግሊዝን ፕሬሚየር ሊግ ካነሣን የወቅቱ የስፓኙ ቀደምት ክለብ የሬያል ማድሪድ አሠልጣኝ ሆሴ ሞሪኞ በሁለት ዓመት ጊዜ ውስጥ ወደ ብሪታኒያ ለመመለስ ያስባል ሲል የተሰራጨውን ዜና የትርጉም ስህተት ነው በማለት አስተባብሏል። የፖርቱጋሉ ተወላጅ የአንዴ የቼልሢይ አሠልጣኝ ሞሪኞ ሬያል ካላባረረኝ በስተቀር ከዚያ ንቅንቅ እልልም ሲል ክለቡን ለማረጋጋት ሞክሯል። ዕውነት ወሬው ሙሉ በሙሉ የፈጥራ ነበር? በተጨባጭ ምን እንደሚከሰት እያደር የሚታይ ነገር ይሆናል።  

Fussball Jungstar Neymar Brasilien

ኔይማር የዓመቱ ተጫዋች

ከአውሮፓ ወደ ላቲን አሜሪካ ሻገር እንበልና የብራዚሉ ወጣት ኮከብ ኔይማር የደቡብ አሜሪካ የ 2011 ዓ.ም. የእግር ኳስ ኮከብ በመባል ተሰይሟል። ለሣንቶስ የሚጫወተው ኔይማር ባለፈው ሰኔ ወር በክፍለ-ዓለሚቱ የኮፓ-ሊበርታዶሬስ ዋንጫ ውድድር የኡሩጉዋዩን ክለብ ፔናሮልን በማሸነፉ ረገድ ግሩም አስተዋጽኦ ሲያደርግ በዚህ ማዕረግ የሚተካው የአርጄንቲናውን አንድሬስ-ዴ-አሌሣንድሮን ነው። ምርጫውን የሚያካሂደው የኡሩጉዋዩ ዕለታዊ ጋዜጣ ኤል-ፓይስ እንዳስታወቀው ኔይማር በአንደኝነት የተመረጠው 130 ድምጽ በማግኘት ነው።                                                                                  
ለኢጣሊያው ክለብ ለናፖሊ የሚጫወተው የቺሌው አጥቂ ኤዱዋርዶ ቫርጋስ በሰባ ድምጽ በሁለተኝነት ተመርጧል። በዓመቱ ግሩም አሠልጣኝነት ደግሞ የኡሩጉዋዩ ኦስካር-ዋሺንግተን-ታባሬስ በተከታታይ ለሁለተኛ ጊዜ ተመርጠዋል። ታባሬስ በደቡብ አፍሪቃ የዓለም ዋንጫ ውድድር ለግማሽ ፍጻሜ ያደረሱትን የኡሩጉዋይን ብሄራዊ ቡድን ባለፈው ሐምሌ ወር ደግሞ ለ 15ኛ የኮፓ-አሜሪካ ድል ማብቃታቸው የሚታወስ ነው። ታባሬስ የኡሩዎችን እግር ኳስ ለከበሬታ አብቅተዋል ቢባል ማጋነን አይሆንም። ኡሩጉዋይ ከሰላሣኛዎቹ ዓመታት ሁለት የዓለም ዋንጫ ድሎች በኋላ ለአያሌ ዓመታት ደካማ ሆና ነበር የኖረችው። ዛሬ ግን ብራዚልንና አርጄንቲናን ከምታስንቅበት ወቅት ላይ ናት።    

በጋቡንና በኤኩዋቶሪያል ጊኒ የጋራ አስተናጋጅነት የሚካሄደው የ 2012 የአፍሪቃ እግር ኳስ ዋንጫ ፍጻሜ ውድድር ሊከፈት የቀረው ከሶሥት ሣምንታት ያነሰ ጊዜ ነው። በውድድሩ መቃረብ የተነሣም ተሳታፊዎቹ አገሮች የሚያደርጉት መሰናዶ መጠናከር ይዟል። ለምሳሌ ያህል በቤልጂጉ ተወላጅ በኤሪክ ጌሬትስ የሚሰለጥነው የሞሮኮ ብሄራዊ ቡድን ዓለምአቀፍ ልምድ ያፈሩ ተጫዋቾቹን ሲያሰባስብ ጊኒም ተመሳሳይ ዕርምጃ ወስዳለች። የሞሮኮ የምድብ ተጋጣሚዎች ጋቡን፣ ኒጀርና ቱኒዚያ ናቸው። በነገራችን ላይ የቱኒዚያ ብሄራዊ ቡድን ባለፈው አርብ ስፓኝ ውስጥ ከካታሎኒያ ምርጥ ጋር ማማሟቂያ ግጥሚያ በማካሄድ ባዶ-ለባዶ ተለያይቶ ነበር።                               
ጊኒ በምድብ-አራት ውስጥ የቦትሱዋና፣ የጋናና የማሊ ተጋጣሚ ናት። ጋናን ካነሣን የቼልሢው ኮከብ ማይክል ኤሢየን ከረጅም ጊዜ የጉልበት ጉዳቱ አገግሞ ለቡድኑ እንደሚሰለፍ ተሥፋ ይደረጋል። ከዚህ ሌላ ስዋዚላንድ ደግሞ ለቀጣዩ 2013 ዓ.ም. የአፍሪቃ ዋንጫ የሚካሄደው ማጣሪያ ከመጀመሩ ከሣምንት በፊት ከውድድሩ መውጣቷን አስታውቃለች። ስዋዚላንድ በፊታችን ሰንበትና ከዚያም በሁለት ሣምንቱ ከሤይሼልስ እንድትጋጠም ተመድባ ነበር። የአገሪቱ ፌደሬሺን ባለሥልጣናት ለአወጣጡ የሰጡት ምክንያት የገንዘብ እጥረት የሚል ነው።                                                                            
የስዋዚላንድ ዘግይቶ መውጣት ከአፍሪቃ እግር ኳስ ኮንፌደሬሺን በኩል የገንዘብ መቀጮን ሊያስከትልና አገሪቱ ከ 2015 የአፍሪቃ ዋንጫ ውድድር እንድትታገድ ሊያደርግም የሚችል ነው። የአፍሪቃ ዋንጫ ውድድር ከዓለም ዋንጫ ፍጻሜ እንዳይጋጭ በማሰብ ከሚቀጥለው ዓመት አንስቶ በጎዶሎ ዓመት እንዲካሄድ መወሰኑ ይታወቃል። ለዚህም ነው በየሁለት ዓመቱ የሚካሄደው ውድድር ዘንድሮና በመጪው ዓመት መከታተሉ።

Olympia 2008 Äthiopien Gold für Tirunesh Dibaba 10000 m Lauf

አትሌቲክስ

47ኛው የስፓኝ ሣን-ሢልቬስትሬ፤ የዘመን መለወጫ የአሥር ኪሎሜትር ሩጫ ውድድር የኢትዮጵያ አትሌቶች ልዕልና የታየበት ሆኖ አልፏል። በውድድሩ በወንዶች ወጣቱ አትሌት ሃጎስ ገ/ሕይወት ሲያሸንፍ በሴቶች ደግሞ የኦሎምፒኳ ሻምፒዮን ጥሩነሽ ዲባባ ባለድል ሆናለች። በወንዶች የኤርትራው ተወዳዳሪ ተክለማርያም መድህን ሁለተኛ ሲወጣ ሶሥት የስፓኝ ተወዳዳሪዎች እስከ አምሥተኛው ቦታ በመከታተል ገብተዋል። በሴቶች ገለቴ ቡርቃ ጥሩነሽን ተከትላ ሁለተኛ ስትሆን ሩጫውን በሶሥተኝነት የፈጸመችው የብሪታኒያዋ አትሌት ሱዛን ፓርትሪጅ ነበረች። ባቲ ቡርቃ ስድሥተኛ!                                                    
በሣን-ሢልቬስሬው የ 15 ኪሎሜትር ሩጫ ደግሞ የኬንያ አትሌቶች ቀንቷቸዋል። የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና የማራቶን የብር ሜዳሊያ ተሸላሚ የነበረችው ፕሪስካ ጄፕቱ ውዴ አያሌውን ቀድማ ስታሸንፍ ሌላዋ ኬንያዊት ኤውኒስ ኪርዋም ሶሥተኛ ሆናለች። በወንዶች ያሸነፈው ታሪኩ በቀለ ነው። አዲሱ ዓመት ለኢትዮጵያ አትሌቶች ካለፈው የተሻለና ስኬት የሰመረበት እንደሚሆን ተሥፋ እናደርጋለን።

Flash-Galerie Andrea Petkovic

ቴኒስ

በአውስትራሊያ-ብሪስቤን ዓለምአቀፍ የቴኒስ ውድድር የመጀመሪያ ዙር ግጥሚያዎች ዛሬ የሚከተሉት ውጤቶች ተመዝግበዋል። በሴቶች የጀርመኗ አንድሬያ ፔትኮቪች የእሥራኤል ተጋጣሚዋን ሻሃር ፔርን 2-1 ስታሸንፍ አሜሪካዊቱ ሤሬና ዊሊያምስም ደቡብ አፍሪቃዊቱን ቻኔል ሺፐርስን በሁለት ምድብ ጨዋታ ረትታለች። ከዚሁ ሌላ የኤስቶኒያዋ ካያ ካኔፒ ሩሢያዊቱን አሌክሣንድራ ፓኖቫን፤ ቫኒያ ኪንግ ሜሊንዳ ሺንክን፤ አና ኢቫኖቫ ታማራ ፓሼክን፤ ጋሊና ቦስኮቦየቫ ቬራ ዱሼቪናን በማሸነፍ ለተከታዩ ዙር አልፈዋል። በወንዶች ደግሞ ዢል ሙለር ሪካርዶ ሜሎን፤ በርናርድ ቶሚክ ጁሊየን ባኔቱን፤ ዴኒስ ኢስቶሚን ፍሎሪያን ማየርን አሸንፈዋል።

አርጄንቲና ውስጥ በአትላንቲክ ጠረፍ አኳያ የሚካሄደው ውጣ-ውረድ የበዛው እሽቅድድም የዳካር ራሌይ ደግሞ በአዲሱ ዓመት ከባድ አደጋ በጋረደው ሁኔታ ተጀምሯል። ይሄውም የ 38 ዓመቱ ቢስክሌት ዘዋሪ ሆርሄ-ማርቲኔዝ-ቦኤሮ ትናንት ሕይወቱን ማጣቱ ነው። ቦኤሮን ለማዳን የተደረገው ጥረት ሁሉ ከጉዳቱ ከባድነት የተነሣ ሳይሣካ ቀርቷል። በጸጥታ ምክንያት ከአራት ዓመታት በፊት ከአፍሪቃ ወደ ደቡብ አሜሪካ የተሻገረው ራሌይ አደገኛና ቀድሞም ለብዙዎች ሞት ምክንያት መሆኑ የሚታወቅ ነው። የመጀመሪያው ከፓሪስ-ዳካር ራሌይ እ.ጎ.አ. በ 1979 ከተጀመረ ወዲህ ሕይወታቸውን ያጡት ተሳታፊዎች ከሃያ ይበልጣሉ። በአርጄንቲና ቦኤሮ ከፈረንሣዊው ከፓስካል ሄንሪ ተከትሎ ሁለተኛው መሆኑ ነው።  

መሥፍን መኮንን         

ተክሌ የኋላ                             

 

           

Audios and videos on the topic

 • ቀን 01.02.2012
 • አዘጋጅ
 • ያትሙ ገፁን ያትሙ
 • Permalink https://p.dw.com/p/13dAc
 • ቀን 01.02.2012
 • አዘጋጅ
 • ያትሙ ገፁን ያትሙ
 • Permalink https://p.dw.com/p/13dAc