የስፖርት ዘገባ ጥር 25 ቀን፥ 2007ዓ.ም. | ስፖርት | DW | 02.02.2015
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ስፖርት

የስፖርት ዘገባ ጥር 25 ቀን፥ 2007ዓ.ም.

በአፍሪቃ ዋንጫ ጨዋታዎች ጋና፣ ኮትዲቯር፣ ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ እና ኢኳቶሪያል ጊኒ ለግማሽ ፍፃሜ ደርሰዋል። አስተናጋጇ ያለፈችበት ጨዋታ ዳኝነት ውዝግብ አስነስቷል። ቡንደስ ሊጋው ጀምሯል፤ አስገራሚ ውጤቶች ተከስተዋል። የጀርመኑ ኃያል ባየር ሙንሽን በዎልፍስቡርግ የ4 ለ1 ከባድ ሽንፈት ቀምሷል። ተጨዋቾቹ አንዳች ብራቅ ወረደብን ብለዋል።

በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ የእግር ኳስ ግጥሚያ ትናንት አርሰናል አስቶን ቪላን 5 ለባዶ በሆነ ሰፊ ልዩነት በማሸነፍ ቀጥቶታል።ገና ጨዋታው ከተጀመረ ከ5ኛው ደቂቃ አንስቶ አስቶን ቪላን መቅጣት የጀመረው አርሰናል የመጀመሪያዋን ግብ ያስቆጠረው በኦሊቨር ጂሮድ ነው። በ8ኛው ደቂቃ ላይ ኹለተኛዋን ግብ የጀርመኑ ብሔራዊ ቡድን ተሰላፊ ሜሱት ኦሲል ማስቆጠር ችሏል። ሦስተኛዋን ግብ ከረፍት መልስ በ56ኛው ደቂቃ ላይ ከመረብ ያሳረፈው ቴዎ ዋልኮት ነው። 63ኛው ደቂቃ ላይ ሌላ ውርጅብኝ በሳንቲ ካርሎዝ የዘነበበት አስቶን ቪላ 5ኛዋ ግብ የተቆጠረችበት ፍጹም ቅጣት ምት ለሄክቶር ቤሌሪን በ92ኛው ደቂቃ ላይ ሲሰጥ አንገቱን ከመድፋት ውጪ ምንም ማድረግ አልቻለም።

በሌላ ጨዋታ ስዋንሲ ሲቲ ሳውዝሐምፕተንን 1 ለምንም አሸንፏል። ከትናንት በስትያ ሊቨርፑል ዌስትሐም ዩናይትድን 2 ለዜሮ በመርታት ሦስት ነጥብ ሰብስቧል። ማንቸስተር ዩናይትድ ሌስተር ሲቲን 3 ለ1 በማሰናበት በደረጃ ሠንጠረዡ 43 ነጥብ በመሰብሰብ ሦስተኛ ለመሆን ችሏል። መሪው ቸልሲ ከተከታዩ ማንቸስተር ሲቲ ጋር አንድ እኩል ተለያይቷል። ቸልሲ 53 ነጥብ በመያዝ በደረጃ ሠንጠረዡ በአንደኛነት ሲገኝ፤ 48 ነጥብ ያለው ማንቸስተር ሲቲን አስከትሏል። ማንቸስተር ዩናይትድ በ43 ነጥብ ይሰልሳል። ሳውዝሐምፕተን እና አርሰናል በ42 ነጥብ ሆኖም በግብ ክፍያ 4ኛ እና 5ኛ ደረጃ ላይ ይገኛሉ። ሊቨርፑል 40 ነጥብ ካለው ቶትንሀም በ2 ነጥብ ዝቅ ብሎ 7ኛ ደረጃ ይዟል።

ቴዎ ዋልኮት

ቴዎ ዋልኮት

በጀርመን ቡንደስ ሊጋ 18ኛ ዙር የመክፈቻ ጨዋታ ኃያሉ ባየር ሙይንሽን ዎልፍስቡርግ 4 ለ1 በሆነ ከባድ ሽንፈት ተቀጥቷል። የባየር ሙይንሽኑ አጥቂ ቶማስ ሙይለር ሽንፈቱን እንዲህ ገልጦታል።

«በእውነቱ ምናልባትም ለየት ባለ መልኩ ሊከናወን ይገባ ከነበረው የመክፈቻ ጨዋታችን በተቃራኒው አንዳች ብራቅ የወረደበት ጨዋታ ነበር። ሆኖም ምን ታደርገዋለህ? ይልቅ ይኽ ጨዋታ አሁን ልዩነታችንን የበለጠ ለማስፋት ጥሩ አጋጣሚ ነው ባይ ነኝ።»

ትናንት ብሬመን ሔርታ ቤርሊንን 2 ለባዶ አሸንፏል። አውስቡርግ ሆፈንሀይምን 3 ለ1 ሸኝቷል። የደረጃ ሠንጠረዡን ባየር ሙይንሽን በ45 ነጥብ ይመራል። ዎልፍስቡርግ በ37 ነጥብ ይከተላል። ሞይንሽንግላድባኅ በ30 ነጥብ ይሰልሳል። ሻልካ እና አውስቡርግም 30 ነጥብ ይዘው በግብ ክፍያ ልዩነት 4ኛ እና 5ኛ ደረጃ ላይ ይገኛሉ። የቀድሞው ኃያል ቦሩስያ ዶርትሙንድ አከርካሪው ተመትቶ በያዘው 16 ነጥብ የደረጃ ሠንጠረዡ ጠርዝ 18ኛ ላይ ተዘርግቶ እያጣጣረ ነው።

ትናንት በተከናወኑ የአፍሪቃ ዋንጫ ሩብ ፍፃሜ ግጥሚያዎች ጋና ጊኒን 3 ለባዶ በሆነ ሰፊ ልዩነት ድል አድርጋለች። በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ ለኤቨርተን ተሰልፎ የሚጫወተው ጋናዊው ክሪስትያን አፁ ኹለት ግቦችን ማስቆጠር ችሏል። ክዌሲ አፒያህ ሦስተኛዋን ግብ ከመረብ በማሳረፍ ጥቋቁር ከዋክብቱን ለድል አብቅቷል።

የጋና ቡድን ደጋፊዎች

የጋና ቡድን ደጋፊዎች

የጊኒው ያታራ በባከነ የጭማሪ ሠዓት አሳሞዋህ ጊያን ላይ ጥፋት በመፈፀሙ በቀይ ካርድ ከሜዳ ተሰናብቷል። በነገራችን ላይ ጊኒ በኢቦላ ተሐዋሲ እጅጉን ከተጠቁት ሦስቱ የምዕራብ አፍሪቃ ሃገራት አንደኛዋ በመሆኗ የማጣሪያ ጨዋታዎቿን በሙሉ ያከናወነችው ከሀገሯ ውጪ ነበር። ጊኒ ለአፍሪቃ ዋንጫ ሩብ ፍፃሜ አይደለም ማጣሪያውን ማለፏ በራሱ ብዙዎችን አስገርሞ ነበር። ሆኖም በጋና ተረትታ ከውድድሩ ተሰናብታለች። ጥቋቁር ከዋክብት በሚል የሚጠሩት የጋና ብሔራዊ የእግር ኳስ ቡድን ተጨዋቾች ደጋፊ የሆነው ፊፊ ባርቴል ጋና ለፍፃሜ ደርሳ አሸናፊ እንደምትሆን ከወዲሁ ተማምኗል።

«ከመጀመሪያው ጨዋታ በስተቀር በሁሉም ጨዋታዎች ተደምሜያለሁ። አሁን በጥቋቁር ከዋክብቱ እምነት ጥያለሁ። የዋንጫው አሸናፊ መሆን እንደምንችል እተማመናለሁ።»

ሌላኛው የጋና ቡድን ደጋፊ እስራኤል ባባናዋ በበኩሉ የጋናን ቡድንን አስመልክቶ ሙሉ ለሙሉ እርግጠኛ ከመሆን ይልቅ ምኞቱን መግለጥ የፈለገ ይመስላል።

«እስካሁን ጥሩ ነው። አስደስተውኛል። የዋንጫው አሸናፊ እንዲሆኑ እመኛለሁ።»

እርስዎስ በአፍሪቃ ዋንጫ ለፍጻሜ ማን እና ማን የሚደርሱ ይመስልዎታል? አሸናፊውስ?

የኮትዲቯር ተጨዋቾች ግብ አስቆጥረው ሲደሰቱ

የኮትዲቯር ተጨዋቾች ግብ አስቆጥረው ሲደሰቱ

ትናንት በተከናወነ ሌላ ጨዋታ አልጀሪያ በኮትዲቯር 3 ለ1 ሽንፈት ተሰናብታለች። የኮትዲቯሩ አጥቂ ዊልፍሬድ ቦኒ ሁለት ኳሶችን በጭንቅላት ገጭቶ ከመረብ ያሳረፈበት እንቅስቃሴው የሚደነቅ ነበር። ሁለተኛዋ ግብ እንድትቆጠር በእንግሊዙ ፕሬሚየር ሊግ ማንቸስተር ሲቲ አብሮት የሚጫወተው ያያ ቱሬ መጥኖ የላካት የቅጣት ምት በቀጥታ ያረፈችው የዊልፍሬድ ጭንቅላት ላይ ነበር። ልዩ ተሰጥዖውን ያስመሰከረው የኮትዲቯሩ አዲሱ አጥቂ ዊልፍሬድ ቦኒም ኳሷን በግሩም ሁናቴ ከመረብ ቀላቅሏታል። ኹለት ጨዋታዎችን ተቀጥቶ የነበረው በጣሊያን ሴሪኣ የሮማው አጥቂ ጄርቪንሆ ሦስተኛዋን የማሳረጊያ ግብ ሊያስቆጥር ችሏል።

የኮትዲቯር ቡድን ያለ ዲዲዬር ድሮግባ፤ በእነ ዊልፍሬድ ቦኒ፣ያያ ቱሬ እና ጄርቪንሆ በድል ጎዳና እየገሰገሰ ነው። ለአልጄሪያ በ51ኛው ደቂቃ ላይ ብቸኛዋን ግብ በድንቅ ሁናቴ ያስቆጠረው ሂላል ሶውዳኒ ነበር። የኮትዲቯር ተከላካዮች ድክመት ለግቧ አስተዋጽዖ አድርጓል።

ከትናንት በስትያ ቅዳሜ፤ ወደ ግማሽ ፍፃሜው ለማለፍ በመጀመሪያ የተገናኙት ኹለቱ ኮንጎዎች ነበሩ። ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ኮንጎን 4 ለ2 ቀጥቶ ለማለፍ ችሏል። አስተናጋጇ ኢኳቶሪያል ጊኒ ቱኒዚያን 2 ለ1 ለማሸነፍ ችላለች። በዚህ ጨዋታ የመሀል ዳኛው ቱኒዚያዎችን በሚመለከት ያስተላለፏቸው ውሳኔዎች ጥያቄ ሊያስነሱ የሚችሉ ናቸው። የቱኒዚያ ተጨዋቾች ላይ ጥፋት ሲሰራ ችላ የማለት እና የኢኳቶሪያል ጊኒ ተጨዋቾችን በተመለከተ እያንዳንዷ እንቅስቃሴ ላይ ፈጣን እና አሻሚ ውሳኔዎችን ሲያስተላልፉ ታይተዋል። መደበኛ የጨዋታ ጊዜው አንድ እኩል ተጠናቆ በተጨመረው ሠዓት ነበር አስተናጋጇ አገር ያገኘችውን አጨቃጫቂ የፍፁም ቅጣት ምት ለስፔኑ ሪያል ማድሪድ ይጫወት የነበረው ጸጉረ-ጉዱሩ ጃቪየር አንጄል ባልቦዋ በድንቅ ሁናቴ ከመረብ ያሳረፈው። ይኽ ውሳኔ እና ውጤት ቱኒዚያን ከውድድሩ ሊያስወጣ ችሏል። የመሀል ዳኛው ውሳኔ ጥያቄ ያስነሳል።

የኢኳቶሪያል ጊኒ ብሔራዊ የእግር ኳስ ቡድን

የኢኳቶሪያል ጊኒ ብሔራዊ የእግር ኳስ ቡድን

ከነገ በስትያ ኮትዲቯር ከዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ጋር ይጋጠማል። በነጋታው ሐሙስ አስተናጋጇ ኢኳቶሪያል ጊኒ ማላቦ ስታዲየም ውስጥ ጠንካራዋ ጋናን ትፋለማለች። ጋና በአፍሪቃ ዋንጫ ታሪክ ለአራት ጊዜ ድልን ተቀዳጅታለች። እጎአ በ2010 ለፍፃሜ ቀርባ በግብፅ በመሸነፍ በኹለተኛነት ማጠናቀቋ ይታወቃል። ጨዋታዎቹ በጉጉት ይጠበቃሉ።

በስፔን ላሊጋ ትናንት ባርሴሎና ከኋላ ተነስቶ ቪላሪያልን 3 ለ2 አሸንፏል። የማሸነፊያዋን ግብ በ55ኛው ደቂቃ ላይ ያስቆጠረው ሊዮኔል ሜሲ ነው። በ45ኛው እና 53ኛው ደቂቃ ላይ የተቆጠሩት ቀሪዎቹ ግቦች የኔይማር እና የራፊናህ ናቸው። ቪላሪያል መጀመሪያ ላይ እየመራ እንዲቆይ ያስቻለውን ግቦች በ30ኛው እና 51ኛው ደቂቃዎች ላይ አስቆጥረው የነበሩት ዴኒስ ቼሪሼቭ እና ሉሲያኖ ቬዬቶ ናቸው። ሴቪላ ኤስፓኞላን 3 ለ2፣ አትሌቲክ ክለብ ሌቫንቴን 2 ለባዶ እንዲሁም አልሜሪያ ጌታፌን 1 ለዜሮ አሸንፈዋል። ቅዳሜ መሪው ሪያል ማድሪድ ዘንድሮ የዓለማችን ኮከብ እግር ኳስ ሆኖ የተመረጠው ክርቲያኖ ሮናልዶ በሌለበት ሪያል ሶሲዬዳድን ገጥሞ 4 ለ1 ኩም አድርጎታል። ሮድሪጌዝ እና ራሞስ ኹለቱን ግቦች ሲያስቆጥሩ፤ የእለቱ ኮከብ የነበረው ፈረንሳዊው ካሪም ቤንዜማ ሁለት ተጨማሪ ግቦችን ከመረብ ማሳረፍ ችሏል። ብቸኛዋን ግብ ለሪያል ሶሲዬዳድ ያስቆጠረው አሪትስ ኤሉስቶንዶ ነው።

አትሌቲኮ ማድሪድ አይባርን 3 ለ1 ረትቷል። በደረጃ ሠንጠረዡ ወራጅ ቃጣና ውስጥ የሚገኘው ኤልሼ ዳግም በግራናዳ የ1 ለባዶ ሽንፈት ቀምሶ ግራ ተጋብቷል። ሴልታቪጎ ኮርዶባን 1 ለባዶ በማሸነፍ ወደ ወራጅ ቃጣናው ግርጌ 17ኛ ደረጃ ላይ ገፍቶታል።

የዓለም ኮከብ እግር ኳስ ተጨዋች ክሪስቲያኖ ሮናልዶ

የዓለም ኮከብ እግር ኳስ ተጨዋች ክሪስቲያኖ ሮናልዶ

በደረጃ ሠንጠረዡ ሪያል ማድሪድ 51 ነጥብ ሰብስቦ ቀዳሚነቱን እንዳስጠበቀ ነው። ባርሴሎና በ47 ነጥብ ይከተላል፤ ከአትሌቲኮ ማድሪድ ጋር ልዩነቱ የግብ ክፍያ ብቻ ነው። በዓለም እግር ኳስ ለ4 ጊዜያት ምርጥ ተብሎ የተመረጠው የባርሴሎናው ሊዮኔል ሜሲ ቡድኑ ዛሬ ባደረገው ልምምድ ላይ አለመገኘቱ ተዘግቧል። ሊዮኔል ሜሲ በአንድ ወር ጊዜው ውስጥ ለኹለተኛ ጊዜ ደጋፊዎቹ ከሚኙበት የልምምድ ሜዳ የቀረው በጨጓራ ኅመም ምክንያት መሆኑን ተናግሯል። አርጀንቲናዊው አጥቂ ሊዮኔል ሜሲ ከቡድኑ አሠልጣኝ ጋር ቅራኔ ገብቷል ተብሎ ቀደም ሲል መዘገቡ ይታወሳል።

በጣሊያን ሴሪኣ የእግር ኳስ ፍልሚያ መሪው ጁቬንቱስ በደረጃ ሠንጠረዡ 11ኛ ላይ ከሚገኘው ኡዲኔዜ ጋር ትናንት ባደረገው ጨዋታ ያለምንም ግብ ተለያይቷል። ሳሱዎሎ ኢንተር ሚላንን 3 ለ1 ረትቷል። አትላንታ ካግሊያሪን፣ ፓሌርሞ ቬሮናን፣ ሴሴና ላትሲዮን እንዲሁም ናፖሊ ቺዬቮን 2 ለ1 አሸንፈዋል። ሣምፕዶሪያ በቶሪኖ 5 ለ1 ተንኮታክቷል። ቅዳሜ ዕለት ፊዮሬንቲና ከጄኖዋ እንዲሁም ሮማ ከኢምፖሊ አንድ እኩል በመውጣት ነጥብ ተጋርተዋል።

የደረጃ ሠንጠረዡን ትናንት ነጥብ የጣለው ጁቬንቱስ በ50 ነጥብ እየመራ ይገገኛል። ሮማ በ43 ነጥብ ይከተላል። ናፖሊ 39 ነጥብ ይዞ ሦስተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል። 26 ነጥብ የያዙት ኤስ ሲ ሚላን እና ኢንተር ሚላን ቁልቁል 12ኛ እና 13ኛ ደረጃ ላይ በመገኘት እነ ጁቬንቱስን በርቀት ለመመልከት ተገደዋል። ፓርማ በ9 ነጥብ የደረጃ ሠንጠረዡ ግርጌ ላይ ይገኛል።

በአውስትራሊያ ግራንድ ስላም የሜዳ ቴኒስ ፍፃሜ ሠርቢያዊው ኖቫክ ጆኮቪች ትናንት ሜልቦርን ከተማ ውስጥ ለአምስተኛ ጊዜ አሸናፊ ለመሆን ችሏል። ኖቫክ ጆኮቪች ትናንት በተከታታይ ያሸነፈው ብሪታኒያዊው አንዲ ማሪን 6 ለ3 እና 6 ለ0 በሆኑ ሰፊ ልዩነቶች ነው። በ19ኛው የአውስትራሊያ ግራንድ ስላም የሜዳ ቴኒስ የሴቶች ውድድር ደግሞ የ33 ዓመቷ አሜሪካዊት ሴሬና ዊሊያምስ ሩሲያዊቷ ማሪያ ሻራፖቫን በመርታት ትናንት እንደ ኖቫክ ጆኮቪች የዋንጫ ተሸላሚ ለመሆን በቅታለች።

የአውስትራሊያ ግራንድ ስላም የሜዳ ቴኒስ አሸናፊ ኖቫክ ጆኮቪች

የአውስትራሊያ ግራንድ ስላም የሜዳ ቴኒስ አሸናፊ ኖቫክ ጆኮቪች

ትናንት በአፍሪቃ ዋንጫ የእግር ኳስ ጨዋታ ውድድር የቱኒዚያ እና የአዘጋጇ ኢኳቶሪያል ጊኒ ውድድር ማብቂያ ላይ ተጨዋቾች ለግብግብ ቡጢ ጨብጠው ሲገባበዙ ታይተዋል። የሞሪታኒያው የመሀል ዳኛ ሴሹርን ራጂንድራፓርሳድ በፀጥታ ኃይላት ታጅበው ከሜዳው በሚወጡበት ወቅት በተበሳጩ የቱኒዚያ ተጨዋቾች ድብደባ ተቃጥቶባቸዋል። ቱኒዚያ በዓለም የእግር ኳስ መስፈርት 22ኛ ደረጃ ላይ ስትገኝ በአወዛጋቢ ሁናቴ የተሸነፈችው 118ኛ ደረጃ ላይ በምትገኘው አስተናጋጇ ኢኳቶሪያል ጊኒ ነው። የቱኒዚያ ተጨዋቾች የዳኛ በደል ደርሶብናል ሲሉ ቅሬታ አሰምተዋል።

ውዝግቡ ተካሮ የቱኒዚያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት ዋዴ ጃሪ የትናንቱን ሽንፈት ተከትሎ ከአፍሪቃ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን በምኅፃሩ ካፍ መውጣታቸውን ይፋ አድርገዋል። ዳኛው ፍፁም ቅጣት ምት አለአግባብ ሰጥተውብናል ሲሉም ወቀሳ አሰምተዋል።

ለዓለም አቀፍ እግር ኳስ ፌዴሬሽን በምኅፃሩ ፊፋ ፕሬዚዳንትነት ከሚወዳደሩት አራት ሰዎች መካከል የፖርቹጋል ብሔራዊ ቡድን የቀድሞ ተጨዋች ሉዊስ ፊጎም እንደሚገኝበት ተገለጠ። ለውድድሩ የሚቀርቡት ሌሎቹ ሦስቱ ሰዎች የዮርዳኖዳኖሱ ልዑል አሊ ቢን አል ሑሴን፣ የደች እግር ኳስ ማኅበር ፕሬዚዳንት ሚሻኤል ፋን ፕራግ እና ሴፕ ብላተር መሆናቸው ተጠቅሷል። ፊፋ አራቱ ሰዎችን በተመለከተ በስነምግባር ኮሚቴው በኩል አጣርቶ ወደ ይፋዊ ውድድሩ ውስጥ እንደሚያስገባቸው ጠቅሷል።

አግዳሚ ወንበር ላይ ተቀምጠው የነበሩት የቱኒዚያ እና የአስተናጋጇ ኢኳቶሪያል ጊኒ ተቀያሪ ተጨዋቾች ተገቢ ባልሆነ መንገድ በቡጢ ሲቧቀሱ ነበር ሲል ሮይተርስ ዘግቧል። በእዚህን ወቅት ግን አንድም ተጨዋች ሆነ የቡድን አባል ቀይ ካርድ አላየም።

ማንተጋፍቶት ስለሺ

አርያም ተክሌ

Audios and videos on the topic