የስፖርት ዘገባ፤ ግንቦት 3 ቀን፣ 2007 ዓ.ም | ስፖርት | DW | 11.05.2015
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ስፖርት

የስፖርት ዘገባ፤ ግንቦት 3 ቀን፣ 2007 ዓ.ም

አትሌት ኃይሌ ገብረሥላሴ በ42 ዓመቱ አንዳንዶች 45 ይላሉ ትናንት ከሩጫ ውድድር መሰናበቱን ይፋ አድርጓል። በሻምፒዮንስ ሊግ የግማሽ ፍፃሜ ወሳኝ ፍልሚያ ባየር ሙይንሽን ከስፔኑ ባርሴሎና ጋር ጀርመን ሙይንሽን ውስጥ ማክሰኞ ግንቦት 4 ቀን 2007 ዓ.ም ይገናኛል። የማለፍ ዕድሉ እጅግ ጠባብ ነው።

በፔፕ ጓርዲዮላ የሚሠለጥነው ባየር ሙይንሽን ለዋንጫ የማለፍ እጅግ የጠበበ እድል ይዞ ነው ወደ ሜዳ የሚገባው። ከዚህ ቀደም ለሩብ ፍፃሜ በፖርቶ ተረትቶ አለቀለት ሲባል በሜዳው አሊያንስ አሬና እንደ አዲስ ማንሰራራቱ ይታወሳል። ባርሴሎና ላይ ከ3 ግብ በላይ አስቆጥሮ ማለፉ ግን ብዙዎችን አጠራጥሯል። በመኪና ሽቅድምድም ጀርመናዊው ኒኮ ሮዝበርግ ትናንት አሸንፏል።

«ብቸኛው ንጉሥ» «የእግር ኳሶች ጣዖት» «ምጡቁ» «ከሌላ ዓለም የመጣው» ሲሉ ጽፈውለታል የዓለማችን ታላላቅ የስፖርት ጋዜጦች። «ሜሲ የበርሊኑን ግንብ አንኮታኮተው»ም ሲሉ አወድስውታል፤ ሌላም ሌላም። ባለፈው ሣምንት ሊዮኔል ሜሲ ቡድኑ ባርሴሎና የጀርመኑ ባየር ሙይንሽንን 3 ለባዶ በረታበት ጨዋታ በ3 ደቂቃዎች ልዩነት ኹለት ግቦችን በማግባት ልዩ ተጨዋች መሆኑን በማረጋገጡ ነበር ውዳሴው።

ሊዮኔል ሜሲ

ሊዮኔል ሜሲ

ለባየር ሙይንሽኑ አሠልጣኝ ፔፕ ጓርዲዮላ የቀን ቅዠት የሆነባቸው፣ በፊት በስራቸው የሠለጠነው ሊዮኔል ሜሲ ከነ ኔይማር ጋር ነገ ወደ ጀርመኑ አሌያንስ አሬና ያቀናል። ሰሞኑን ተደጋጋሚ ሽንፈት ያስተናገዱት ፔፕ ጓርዲዮላ ከልብ የሚወዱት ግና ባለፈው ሣምንት ጉድ የሠራቸው ሊዮኔል ሜሲ በነገው ጨዋታ ሌላ ምን አይነት ጉድ ሊፈጥርባቸው እንደሚችል የሚያውቁት ነገር የለም። ባርሴሎናን በሰፋ የግብ ልዩነት አሸንፈው ለዋንጫ በርሊን ላይ መሰየማቸው ግን አጠራጣሪነቱ እጅግ ጎልቷል።

ፔፕ ጓርዲዮላ «በአምስት ደቂቃዎች ውስጥ ሦስት ግቦችን ባስቆጥር ደስ ይለኛል» ሲሉ ምኞታቸውን ገልጠዋል። «በደንብ አጥቅተን ብዙ የግብ ዕድሎችን ማግኘት መቻል አለብን» ሲሉ አከሉ አሠልጣኙ የነገውን ጨዋታ በተመለከተ ሲናገሩ።

ባየር ሙይንሽን ከሦስት ሣምንት በኋላ በሀገሩ ጀርመን የሚከናወነው የፍፃሜው ጨዋታ ተመልካች ላለመሆን 4 ለ0 ማሸነፍ ይጠበቅበታል፤ አለበለዚያም 5 ለ1 ወይንም ደግሞ 6 ለ2። 3 ለ0 አሸንፎም በጭማሪ ሠዓት ሌላ ተጨማሪ ግብ ማስቆጠር። ይኽ ሁሉ ታዲያ የስፔኑ ኃያል ባርሴሎና ላይ ነው። አይታሰብም ማለት አይቻልም። በእርግጥም የኳስ ነገር አይታወቅም። የሚሆነውን ለማየት ግን ከአኹን ጀምሮ 26 ሠዓታት ግድም መጠበቅ የግድ ነው።

አሊያንስ አሬና ስታዲየም

አሊያንስ አሬና ስታዲየም

ባሳለፍነው ሣምንት የባየር ሙይንሽን በባርሴሎና 3 ለዜሮ ሽንፈት የበርካታ ጋዜጦች ዓብይ ርእስ ሆኖ ነበር የቆየው። ባየርን ሙይንሽን እንደማይሆን ሆኖ የተንኮታኮተው በ15 ደቂቃዎች ውስጥ ነበር።

የባየርን ሙይንሽን ሽንፈትን በተመለከተ ጋዜጦች እንዲህ ብለው ነበር። «ድንቁ፣ አስማተኛው ሜሲ። የባየርን ሙይንሽን አሠልጣኝ ፔፕ ጓርዲዮላ እንዲያ ኮትኩተው የዓለማችን ምርጥ ተጨዋች እንዳላደረጉት ሁሉ ሜሲ ቅዠት አስታቅፎ ላካቸው። ጨዋታዎች ፍፃሜያቸው በተጨዋቾች እንጂ በአሠልጣኞች እንደማይወሰን ያሳየ ጨዋታ» በማለት የሆላንዱ der Telegraf ጋዜጣ አስነብቧል።

«ከሌላ ዓለም የመጣው ሜሲ ባየርን ሙይንሽንን አጠፋው። ኹለት ግቦች በሌዮኔል ሜሲ፣ የኔይማር ሲደመር ሦስት ግቦች በ15 ደቂቃዎች ውስጥ። ባርሳ ለፍፃሜው መድረሱን አረጋግጧል። ፔፕ ጓርዲዮላ ሙከራ ለማድረግ ፈልገው ነበር ግን እንደማይሆን ተንኮታክተዋል» ሲል ሌላ አንድ ጋዜጣም አትቷል።

በጀርመኑ ቡንደስሊጋ አሸናፊነቱን ያረጋገጠው ባየር ሙይንሽን በእርግጥም ሰሞኑን አቅም ከድቶት ሰንብቷል። ባየርን ሙይንሽን በቡንደስ ሊጋው በደረጃ ሠንጠረዡ 5ኛ በሆነው በአውስቡርግ ቅዳሜ ዕለት 1 ለዜሮ ተረትቷል። ባየር ሙይንሽን ባለፈው ሣምንትም በባየር ሌቨርኩሰን 2 ለምንም ሽንፈት ቀምሶ ነበር።

ፔፕ ጓርዲዮላ

ፔፕ ጓርዲዮላ

የባየር ሙይንሽን አሠልጣኝ ፔፕ ጓርዲዮላ ከተደጋገመባቸው ሽንፈት አንፃር ቡድኑን ጥለው ሊሄዱ ነው የሚል ጭምጭምታ እየተሰማ ነው። እሳቸው ግን «እዚህ ደስተኛ ነኝ» ሲሉ ሊጠናቀቅ አንድ ዓመት በቀረው ውላቸው መሠረት በሚቀጥለው የውድድር ዘመንም የባየር ሙይሽይን አሠልጣኝ ሆነው እንደሚቀጥሉ ተናግረዋል።

በቡንደስ ሊጋው ቮልፍስቡርግ ከመሪው ባየር ሙይንሽን ጋር የነበረውን የ14 ነጥብ ልዩነት ወደ 11 በማውረድ 65 ነጥብ መሰብሰብ ችሏል። በደረጃ ሠንጠረዡ ኹለተኛ ነው። ቦሩስያ ሞይንሽን ግላድባኅ በማሸነፍ ነጥቡን ወደ 63 አሳድጓል በሦስተኛ ደረጃው ላይ ይገኛል። ባሳለፍነው ሣምንት ባየር ሙይንሽንን ድል የነሳው ባየር ሌቨርኩሰን ከትናንት በስትያ በቦሩስያ ሞይንሽንግላድባኅ 3 ለ0 ድል በመነሳቱ 58 ነጥቡ ላይ ተወስኖ አራተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል። ቦሩስያ ዶርትሙንድ ሔርታ ቤርሊንን ቅዳሜ ዕለት 2 ለ ምንም መርታት በመቻሉ ደረጃውን በኹለት አሻሽሎ 7ኛ መኾን ችሏል፤ 43 ነጥብ አለው።

ባለፈው ሣምንት ወራጅ ቃጣናው ላይ ከነበሩት ከሐኖቨር እና ከሽቱትጋርት አንደኛው ድል ሲቀናው ሌላኛው ነጥብ ተጋርቷል። ሐኖቨር ከቬርደር ብሬመን ጋር አንድ እኩል ተለያይቶ ነጥብ በመጋራቱ በ31 ነጥብ የወራጅ ቃጣናው ጠርዝ ላይ ይገኛል። ፍራይቡርግ ከሐምቡርግ ጋር አንድ እኩል አቻ በመውጣት ነጥብ በመጋራቱ እንደ ሐኖቨር 31 ነጥብ አለው በግብ ክፍያ ልዩነት ግን 15ኛ ደረጃ ላይ ነው የሚገኘው። ሽቱትጋርት ምንም እንኳን ማይንትስን 2 ለዜሮ በመርታት 30 ነጥብ ላይ መድረስ ቢችልም በ18ኛ ደረጃ ወደ መጨረሻው ወራጅ ቃጣና ከማሽቆልቆል ግን አልዳነም። በቮልፍስቡርግ ትናንት 2 ለባዶ የተቀጣው ፓዴርቦርን በ31 ነጥቡ ተወስኖ ወራጅ ቃጣናው ውስጥ ከመጨረሻ ኹለተኛ ከአጠቃላዩ 18ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል።

አትሌቲክስ

ከሩብ ምዕተ-ዓመት ዓለም አቀፍ የሩጫ ውድድር በኋላ ኃይሌ ገብረ ሥላሴ የመሮጫ ጫማውን መስቀሉን በማንቸስተር ታላቁ ሩጫ ትናንት ይፋ አድርጓል። ኃይሌ ገብረሥላሴ በ25 ዓመታት የሩጫ ዘመኑ 27 የዓለም፣ 2 የኦሎምፒክ ውድድሮችን አሸንፏል፣ ክብርወሰንም ሰብሯል። አትሌት ኃይሌ ገብረ ሥላሴን ከየትኛውም አትሌት ጋር ማወዳደር አይቻልም ሲል የሚጀምረው ጋዜጠኛ ምሥጋናው ታደሠ በfm 96.3 ፕላኔት ስፖርት የሬዲዮ ፕሮግራም ዋና አዘጋጅ እና አቅራቢ ነው። «ኃይሌ ለማንኛውም አትሌት ትልቅ ምሳሌ ሊሆን የሚችል ነው። ምናልባት እሱን ከሌሎች አትሌቶች ጋር እኩል ልታነጻፅረው አትችልም።»

ኃይሌ ገ/ሥላሴ በሲድኒ ኦሎምፒክ አሸንፎ

ኃይሌ ገ/ሥላሴ በሲድኒ ኦሎምፒክ አሸንፎ

በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ ትናንት ማንቸስተር ሲቲ ኩዊንስ ፓርክ ሬንጀርስን 6 ለዜሮ በኾነ ሰፊ ልዩነት አሸንፏል። 73 ነጥብ አለው። በ84 ነጥቡ የዋንጫው ባለቤት መሆኑን አስቀድሞ ያረጋገጠው ቸልሲ ከሊቨርፑል ጋር አንድ እኩል በመለያየት ነጥብ ተጋርቷል። 62 ነጥብ ላይ የደረሰው ሊቨርፑል ለአውሮፓ ሊግ ጨዋታ ለማለፍ የነበረው ተስፋ አራተኛ ደረጃ ላይ በሚገኘው ማንቸስተር ዩናይትድ እጅግ ተመናምኗል። ማንቸስተር ዩናይትድ ቅዳሜ ዕለት ክሪስታል ፓላስን 2 ለ1 በመርታት ነጥቡን 68 ማድረስ ችሏል። ኹለት ተስተካካይ ጨዋታዎች እየቀሩት በ70 ነጥብ ሦስተኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው አርሰናል ዛሬ ከሠዓታት በኋላ ከስዋንሲ ሲቲ ጋር ይጋጠማል። ኹለተኛ ደረጃ ላይ ከሚገኘው ማንቸስተር ሲቲ ጋር የነጥብ ልዩነቱ 3 ብቻ ነው።

ለሻምፒዮንስ ሊግ ፍልሚያ ሪያል ማድሪድ ከጁቬንቱስ ጋር ረቡዕ ይገናኛል። አሸናፊው ከባየር ሙይንሽን እና ባርሴሎና አሸናፊ ጋር ለዋንጫ ይጋጠማል።

በፎርሙላ አንድ የመኪና ሽቅድምድም ጀርመናዊው ኒኮ ሮዝበርግ ትናንት አሸናፊ ሆኗል። በስፔን ግራንድ ፕሪ ሽቅድምድም ድል የቀናው ጀርመናዊ በመርሴዲስ ተሽከርካሪ ተወዳዳሪ የነበረው ሌዊስ ሐሚልተንን ሲያሸንፍ በዚህ የውድድር ዘመን የመጀመሪያው ሆኖ ተመዝግቦለታል።

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ነጋሽ መሐመድ

Audios and videos on the topic