የስፖርት ዘገባ፤ የካቲት 9 ቀን፣ 2007 ዓ.ም. | ስፖርት | DW | 16.02.2015
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ስፖርት

የስፖርት ዘገባ፤ የካቲት 9 ቀን፣ 2007 ዓ.ም.

ሊዮኔል ሜሲ ዳግም ሐትሪክ ሠርቷል፤ ቡድኑ ባርሴሎና ላቫንቴን 5 ለዜሮ በመርታት ከመሪው ሪያል ማድሪድ ጋር ትንቅንቁን አጠናቅሮታል። በቡንደስሊጋው ባየር ሙይንሽን ሐምቡርግን 8 ለባዶ አንኮታኩቷል። አርሰናል በእንግሊዝ FA Cup ድል ቀንቶታል። በጣሊያን ሴሪኣ ዝቅተኛ ነጥብ ያላቸው ኹለት ቡድኖች ኃያላኑን ቡድኖች ተፈታትነው ነጥብ አስጥለዋል።

በአጋጣሚው መሪው ጁቬንቱስ ከሮማ ጋር ያለውን የነጥብ ልዩነት ወደ 7 ከፍ አድርጎታል። ኢትዮጵያዊው አትሌት ሙክታር እድሪስ ጣሊያን ውስጥ አሸናፊ ሆኗል።

በጀርመን ቡንደስ ሊጋ እሁድ የካቲት 8ቀን 2007 ዓ.ም. ፓዴቦርን ሐኖቨርን 2 ለ1፣ ፍራይቡርግ ሔርታ ቤርሊንን 2 ለ 0 አሸንፈዋል። ሔርታ ቤርሊን 37 ሺህ 617 ተመልካቾች በታደሙበት እና የዘንድሮ የሻምፒዮንስ ሊግ የፍፃሜ ውድድር በሚከናወንበት በሜዳው ቤርሊነር ኦሎምፒያስታዲዮን ውስጥ ነበር የተቀጣው።

ቡድናቸው ቤርሊነር መሸነፉ ውስጣቸውን ያስቆጨው አዲሱ አሠልጣኝ ፓል ዳርዳይ «ከሽንፈታችን ተምረን ጠንክረን መሥራት ይገባናል»ብለዋል። የቀድሞው አሠልጣኝ ጆ ሉሑካይ ከተሰናበቱ ወዲህ ቤርሊንን ማሠልጠን የጀመሩት አዲሱ አሠልጣኝ እስካሁን አንድ ጨዋታ አሸንፈው አንድ ተሸንፈዋል። «አሁን መሸነፍ ምን አይነት ስሜት እንደሚፈጥር ይሰማኛል። ጠንከር ማለት ያሻል»ሲሉ 17 ነጥብ ይዞ ወራጅ ቃጣናው ግርጌ የሚገኘው ቡድናቸውን መንፈስ ለማፅናናት ሞክረዋል።

የቤርሊን ተጨዋቾች ግብ አካባቢ

የቤርሊን ተጨዋቾች ግብ አካባቢ

የአሸናፊው ፍራይቡርግ አሠልጣኝ ክርስቲያን ሽትራይሽ በበኩላቸው ቡድናቸው በስነ-ምግባርም ሆነ በአጨዋወት ብቃቱ ድንቅ እንደነበር ተናግረዋል።

«እጅግ በጣም ጥሩ ስነ-ምግባር እና አስተማማኝ ብቃት የታየበት ጨዋታ ነው። ከዶርትሙንድ ጋር ማሳካት ያልቻልነውን ዛሬ አሳክተነዋል። በርካታ ተጨዋቾቻችን በጉዳት እና በህመም ሳይገኙ በዚህ ሣምንት ያደረግነው ልምምድ አስደንጋጭ ነበር። እንዲያም ሆኖ በወሳኙ ቅፅበት ግብ አስቆጥረናል።»

ባለፈው ሣምንት ፍራይቡርግ ቀስ እያለ ከሽንፈት አዙሪት ውስጥ በወጣው ቦሩስያ ዶርትሙንድ 3 ለዜሮ መሸነፉ ይታወሳል። ዶርትሙንድ 22 ነጥብ ይዞ 15ኛ ደረጃ ላይ ነው የሚገኘው።

ኃያሉ ባየር ሙይንሽን የሐምቡርግ ቡድንን ከትናንት በስትያ እጅግ ሠፊ በሆነ የ8 ለባዶ ውጤት አንኮታኩቷል። ባየር ሙይንሽን ከኹለት ዓመት በፊትም ይህንኑ ሐምቡርግን 9 ለ2 ማሸነፉ ይታወቃል። ቲኬቱ ተሽጦ ባለቀበት እና 75 ሺህ ተመልካቾች በታደሙበት አሊያንስ አሬና ስታዲየም ሦስት ተጨዋቾች እያንዳንዳቸው ኹለት ግቦችን አስቆጥረዋል። ቶማስ ሙይለር በ21ኛው እና 55ኛው ደቂቃ ላይ፣ ማሪዮ ጎይትስ በ23ኛው እና 88ኛው እንዲሁም የዕለቱ ኮከብ የነበረው ሆላንዳዊው አሪየን ሮበን በ36ኛው እና 47ኛው ደቂቃ ሲያገቡ፤ አሪየን ሮበን ፍፁም ቅጣት ምት ማስገኘት ችሏል። ሮበርት ሌቫንዶቭስኪ እና ፍራንክ ሪቤሪ በ56ኛው እና 69ኛው ደቂቃ ላይ እያንዳንዳቸው አንድ ግብ አስቆጥረዋል።

አሪየን ሮበን እና ሌቫንዶቭስኪ

አሪየን ሮበን እና ሌቫንዶቭስኪ

ቡንደስ ሊጋውን ባየር ሙይንሽን በ52 ነጥብ እየመራ ይገገኛል። ዎልፍስቡርግ በ44 ይከተላል። ቦሩስያ ሞይንሽንግላድባኅ በ36 ነጥብ ይሰልሳል። በሌሎች ጨዋታዎች ሻልካ አይንትራኅት ፍራንክፉርትን 1 ለምንም ሲረታ፤ አውስቡርግ በቬርደር ብሬመን 3 ለ2 ተሸንፏል። በርካታ ግቦች በተቆጠሩበት ጨዋት ዎልፍስቡርግ ባየር ሌቨርኩሰንን 5 ለ4 አሸንፏል። የቦን ከተማ ተጎራባቹ የኮሎኝ ቡድን በቦሩስያ ሞይንሽንግላድባኅ 1 ለዜሮ በመሸነፍ ነጥብ ጥሏል። የቅዳሜው ድል በባየር ሙይንሽን የእግር ኳስ ታሪክ ከ31 ዓመት ወዲህ ታላቁ ድል ሆኖ ተመዝግቧል።

በቅዳሜው የ8 ለዜሮ ድል ታጅበው ከቡድናቸው ጋር ወደ ዩክሬይን የሚያቀኑትአሠልጣኝ ፔፕ ጋርዲዮላ ደስታቸውን ገልጠዋል።

«አሁን በዚህ ዓመት የመጀመሪያችን በሆነው የሻምፒዮንስ ሊግ ፍልሚያ ላይ ማተኮር እንችላለን። የአጨዋወት ስልታችን በመመለሱ ደስተኛ ነኝ።» ቡድናቸው ባየር ሙይንሽን በሻምፒዮንስ ሊግ ፍልሚያ ወደ ሩብ ፍፃሜ ለማለፍ ነገ ዩክሬይን ውስጥ ከሻካታር ዶኒዬትስክ ጋር ይጋጠማል።

አሠልጣኝ ፔፕ ጉዋርዲዮላ በትናንቱ ጨዋታ ረፍት ያደረገው አማካይ ተጨዋቻቸው ዣቪ አሎንሶን ለነገው ጨዋታ ይጠራሉ ተብሏል። የክንፍ ተጨዋቹ ፍራንክ ሪቤሪ እና ተከላካዩ ራፊናህ ከጉዳት አገግመው በተመለሱበት የትናንት ወዲያው ግጥሚያ የቀድሞ ብቃታቸውን ለማሳየት ጥረት አድርገዋል። ተከላካዩ ጄሮሜ ቦዋቴንግ ደግሞ ጀርመን ውስጥ የሚደረጉ ኹለት ጨዋታዎች ላይ እንዳይሳተፍ የተላለፈበት እገዳ በማክተሙ በነገው የዩክሬይኑ ጨዋታ ተሰላፊ ይሆናል ተብሏል። ፊሊፕ ላም፣ ዣቪ ማርቲኔዝ እና ቲያጎ አልካንታራ አይሰለፉም ተብሏል።

የባየር ሙይንሽን አሠልጣኝ ፔፕ ጉዋርዲዮላ

የባየር ሙይንሽን አሠልጣኝ ፔፕ ጉዋርዲዮላ

ሻካታር ዶኒዬትስክ የዓማፂያን እና የዩክሬን መንግሥት መድፎች በተደጋጋሚ የሚያጓሩበት ግዛት፣ ወታደራዊ ውጥረት የሰፈነበት ምድር ውስጥ ነው የሚገኘው። በምሥራቅ ዩክሬይን ግጭት የተነሳ የነገው ውድድር የሚደረገው ሌቪቭ ከተማ ውስጥ ነው። በደጋፊው ፊት ኃያሉ ባየር ሙይንሽንን የሚገጥመው ሻካታር ዶኒዬትስክ በሚያደርገው የመጀመሪያ ግጥሚያው ቀላል ተፋላሚ ቢደርሰው ምኞቱ ነበር። የሚገጥመው ግን ሌላ የእግር ኳስ መድፈኛ ነው።

ሆኖም በሻምፒዮንስ ሊግ የምድብ ጨዋታዎች ወቅት ዘጠኝ ኳሶችን ከመረብ ማሳረፍ የቻለው ብራዚሊያዊው አጥቂ ሉዊስ አድሪያኖ ባየርን ሙይንሽንን ለመፋለም ቡድኑ ሻካታር ዶኒዬትስክ በሚገባ መዘጋጀቱን ገልጧል። «ድክመታቸውን ነቅሰን ለማውጣት ያላሰለሰ ጥረት አድርገናል» አለ ከ8 ዓመታት በፊት በ3 ሚሊዮን ዩሮ ወደ ሻካታር ቡድን የመጣው ብራዚሊያዊው አጥቂ፤ ቀጠለ «ቀዳሚ ግባችን ማሸነፍ ነው። ከባየርን ሙይንሽ ጋርም ቢሆን እንኳን ነጥብ መጣሉ አያስደስተንም» ሲል አለመስጋታቸውን፤ እንደውም ዓላማቸው ማሸነፍ ብቻ እንደሆነ አስረግጧል። የጀርመን ቡድንን በደጋፊው ፊት የሚገጥመው ሻካታር ባለፈው ወር ልምምድ ሲያደርግ የነበረው ብራዚል ውስጥ ነበር።

በጉዳት ከጨዋታ ውጪ የቆዩ የባየር ሙይንሽን ተጨዋቾች በሚመለሱበት የነገው ግጥሚያ የዩክሬይኑ ተቀናቃኝ ቡድን ሻካታር ወሳኝ የመሀል ተከላካይ ታራስ ስቴፓኔንኮ በተጣለበት ገደብ አይሰለፍም። አጥቂው በርናርድ በበኩሉ መተጣጠፊያውን እየለበለበው መቸገሩን ጠቅሷል። እነዚህ ችግሮች በቡድኑ ውስጥ ቢከሰቱም ብራዚሊያዊው አጥቂ ሉዊስ አድሪያኖ ቡድናቸው የተሻለ መሆኑን ለማስረገጥ ሞክሯል። « እነሱ በየሦስት እና አራት ቀናቱ ተደጋጋሚ ጨዋታዎችን እያደረጉ በመሆኑ የተለየ እንቅስቃሴ ነው የሚኖራቸው»አለ አድሪያኖ። «ሆኖም እኛ በተሻለ የሰውነት አቋም ላይ ነው የምንገኘው።»ሲል የቡድኑ በራስ መተማመንን ለመገንባት ሞክሯል። የዩክሬይኑ ሻካታር ዶኒዬትስክ ቡድን የጀርመን ቡድንን በደጋፊው ፊት ካሸነፈ 35 ዓመታት ተቆጥረዋል።

የሻካታር ዶኒዬትስክ ደጋፊዎች

የሻካታር ዶኒዬትስክ ደጋፊዎች

ለሻምፒዮንስ ሊግ የእግር ኳስ ፍልሚያ ነገ ባየር ሙይንሽን እና ሻካታር ዶኒዬትስክ በሚጫወቱበት ተመሳሳይ ሠዓት የእንግሊዙ ኃያል ቸልሲ እና የፈረንሣዩ ፓሪስ ሴንት ጀርሜይን ይገናኛሉ። ከነገ በስተያም ኹለት የሻምፒዮንስ ሊግ ተጨዋቾች ይኖራሉ። የስፔኑ ሪያል ማድሪድ የጀርመኑ ሻልካን ሲገጥም፤ የስዊትዘርላንዱ ባዘል የፖርቹጊዙ ፖርቶን ይፋለማል። የፍጻሜ ጨዋታው ጀርመን ቤርሊን ከተማ፥ ቤርሊነር ኦሎምፒያስታዲዮን በተሰኘው ስታዲየም ውስጥ ግንቦት 29 ቀን ይከናወናል።

በስፔን ላሊጋ ትናንት ባርሴሎና ሌቫንቴን 5 ለባዶ ባሸነፈበት ጨዋታ ሊዮኔል ሜሲ ሐትሪክ ሠርቷል። እስካሁን 26 ኳሶችን ከመረብ በማሳረፍ በበርካታ ግቦች ከሚመራው ከሪያል ማድሪዱ ክሪስቲያኖ ሮናልዶ ጋር ያለውን የግብ ልዩነት ወደ ኹለት አጥብቦታል። ያም ብቻ አይደለም በደረጃ ሠንጠረዡ ቡድኑ ባርሳ ከሪያል ማድሪድ ጋር የነበረውን ልዩነት እጅግ በማጥበብ ወደ አንድ አድርሶታል።

በዚህም መሠረት ሪያል ማድሪድ 57 ነጥብ ሲኖረው፤ ተፎካካሪው ባርሴሎና 56 ነጥቦች መሰብሰብ ችሏል። ትናንት በሴልታቪጎ 2 ለባዶ በመረታት ነጥብ የጣለው አትሌቲኮ ማድሪድ በ50 ነጥቡ ተወስኗል። ራዮ ቫሌካኖ ትናንት ቪላሪያልን 2 ለባዶ አሸንፏል። ጌታፌ በቫሌንሺያ 1 ለዜሮ ተረትቷል።

በእንግሊዝ FA cupግጥሚያ ብራድፎርድ ፕሬሚየር ሊግ ውስጥ የሚገኘውን ሠንደርላንድን 2 ለዜሮ በማሰናበት በቡድኑ የ39 ዓመት ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ ሩብ ፍፃሜ ለማለፍ ችሏል። ብራድፎርድ ቀደም ሲል ቸልሲንም በማሸነፍ ጉድ ማሰኘቱ ይታወሳል። አርሰናል በተመሳሳይ ግብ ከፕሬሚየር ሊግ ውጪ የሚገኘውን ሚድልስቦሮውን ሸኝቷል። አስቶን ቪላ ላይስተርን 2 ለ1 ድል አድርጓል።

ፍሪትስ ዶፕፈር በረዶ ላይ ዚግዛግ ሲንሸራተት

ፍሪትስ ዶፕፈር በረዶ ላይ ዚግዛግ ሲንሸራተት

በጣሊያን ሴሪኣ የደረጃ ሠንጠረዡን በ54 ነጥብ የሚመራው ጁቬንቱስ ከወራጅ ቃጣናው ስር በ19 ደረጃ ላይ ከሚገኘው ሴሴና ጋር ኹለት እኩል አቻ በመውጣት ነጥብ ጥሏል። ሮማ ከፓርማ ጋር ያለምንም ግብ ተለያይተዋል። ዘንድሮ ውጤት የራቀው ኤሲሚላን ከኢምፖሊ እንዲሁም ቶሪኖ ከካግሊያሪ ጋር አንድ እኩል በመውጣት ከመሸነፍ ድነዋል። ኢንተር ሚላን አታላንታን 4 ለ 1፣ ጄኖዋ ሔላስ ቬሮናን 5 ለ2 በሆኑ ሰፊ ልዩነቶች ረትተዋል። ላትሲዮ ኡዲኒዜን 1 ለዜሮ፣ ሺዬቮ ቬሮና ሳምፕዶሪያን 2 ለ1 ድል አድርገዋል።

አትሌቲክስ

በጣሊያኑ ሳን ቪቶሬ ኦሎና 83ኛ የመስክ ሩጫ ውድድር ኢትዮጵያዊው አትሌት ሙክታር እድሪስ ትናንት የ10 ሺህ ሜትሩን የመስክ ላይ ሩጫ በ33 ደቂቃ ከ50 ሠከንድ በማጠናቀቅ አንደኛ ወጥቷል። La Gazetta dello Sport የተሰኘው በጣሊያንኛ ቋንቋ የሚታተመው የስፖርት ጋዜጣ ጭቃማ በሆነው መስክ ላይ በተከናወነው የሩጫ ውድድር አሸናፊ የሆነውን የ21 ዓመት ወጣት «ትንሹ ቀነኒሳ» ሲል ጠቅሶታል። አትሌት ሙክታር እድሪስ በመጀመሪያዎቹ ስድስት ዙሮች 30ኛ የነበረ ሲሆን፤ ውድድሩ ሊጠናቀቅ አንድ ከግማሽ ዙር ሲቀር ተፈትልኮ በመውጣት ማሸነፉን ጋዜጣው ዘግቧል።

የበረዶ ላይ መንሸራተት ውድድር

ዩናይትድ ስቴትስ ቢቨር ክሪክ ውስጥ ትናንት በተከናወነው በዘንጎች መሀል የበረዶ ዚግዛግ መንሸራተት ዓለም አቀፍ ውድድር ጀርመናዊው ፍሪትስ ዶፕፈር ኹለተኛ በመውጣት የብር ሜዳሊያ ተሸላሚ ለመሆን ችሏል። ፍሪትስ ካሸነፈ በኋላ ደስታውን እንዲህ ነበር የገለጠው።

«ምንጊዜም በዋናነት ደስታን በተደጋጋሚ ማደስ ይገባል። እናም ዛሬ በእውነቱ ደስታ ከእኔ ጋር ናት።»

ፍሪትስን በማሸነፍ የወርቅ ሜዳሊያ ያጠለቀው ፈረንሣዊው ዦን ባፕቲስት ነው። ፌሊክ ኖይሮይተር በበኩሉ ለጀርመን ነሐስ አስገኝቷል። የዓምናው የዓለም በዘንጎች መሀል የበረዶ ዚግዛግ መንሸራተት ውድድር ባለድሉ አውስትራሊያዊው ማርሴል ሒርሸር ከውድድሩ ጥቂት ቀደም ብሎ ራሱን ከፉክክሩ አግልሏል።

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ሸዋዬ ለገሠ

Audios and videos on the topic