የስፖርት ዘገባ፤ የካቲት 30 ቀን፣ 2007 ዓ.ም | ስፖርት | DW | 09.03.2015
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ስፖርት

የስፖርት ዘገባ፤ የካቲት 30 ቀን፣ 2007 ዓ.ም

የባርሴሎናው ሊዮኔል ሜሲ ዳግም ሐትርቲክ በመስራት በላሊጋው ያስቆጠረው ግብ ከሪያል ማድሪዱ ክሪስትያኖ ሮናልዶ ተስተካክሏል። የስፔኑ ኃያሉ ሪያል ማድሪድ አሠልጣኝ ካርሎ አንቼሎቲ ለመጀመሪያ ጊዜ ሜዳ ውስጥ በደጋፊያቸው ዘለፋ እና ጩኸት ገጥሟቸዋል። ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ትናንት ፓሪስ ከተማ ውስጥ ፍፁም የበላይነታቸውን አስመስክረዋል።

አዲስ አበባ ውስጥ ትናንት በተጠናቀቀው 12ኛው የአፍሪቃ ወጣቶች አትሌቲክስ ሻምፒዮን ውድድርም ኢትዮጵያ ካገኘችው 6 ወርቅ መካከል 5ቱ የተገኘው በሴት አትሌቶች ነው። ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ትናንት ፓሪስ ከተማ ውስጥ በተከናወነው ግማሽ ማራቶን የሩጫ ውድድር ፍፁም የበላይነታቸውን አስመስክረዋል።

የሻምፒዮንስ ሊግ የነገ እና የከነገ ወዲያ ጨዋታዎች ድልድል እንዲሁም የአውሮጳ ታላላቅ ቡድኖች ውጤትን ወደ በኋላ ላይ እናሰማችኋለን። አሁን በቅድሚያ ኢትዮጵያውያን በአሌቲክስ ፉክክር በተለያዩ ቦታዎች የተቀዳጁትን ድል እንመልከት።

የ12ኛው የአፍሪቃ ወጣቶች አትሌቲክስ ሻምፒዮን ውድድር ከየካቲት 26 እስከ የካቲት 29 ድረስ በአዲስ አበባ ከተማ በመኪያሄድ ትናንት ተጠናቋል። ከተለያዩ የአፍሪቃ ሃገራት የተውጣጡ ወጣቶች በውድድሩ ተሳታፊ ሆነዋል። በውድድሩ 209 ሴቶች፣ 145 ወንዶች እና አሠልጣኞችን ጨምሮ 172 የቡድን አባላት በድምሩ ከ500 በላይ ሰዎች መሳተፋቸው ተጠቅሷል። ኢትዮጵያ ከተለመደው የረዥም ርቀት ባሻገር 100 ሜትርን ጨምሮ በአጭር ርቀት የሩጫ እና የርምጃ ውድድር፤ የአሎሎ፣ የጦር እና የዲስክ ውርወራ እንዲሁም የከፍታ ዝላይ ተሳታፊ ሆናለች። በውድድሩ ኢትዮጵያን ጨምሮ የሁሉም ሃገራት ሴቶች የበላይነት ይዘው ነው ያጠናቀቁት።

በአጭር ርቀት ፉክክር የምዕራብ አፍሪቃ ተወዳዳሪዎች በተለይ የናይጀሪያ አትሌቶች የበላይነታቸውን አሳይተዋል። በውድድሩ ተካፋይ ከሆኑት 39 ሃገራት መካከል ኢትዮጵያ አጠቃላይ በሰበሰበችው የሜዳሊያ ብዛት ቀዳሚ ሆና ጨርሳለች። ሆኖም በሰበሰበችው በርካታ የወርቅ ሜዳሊያ ናይጀሪያ የአጠቃላይ ውድድሩ የበላይ በመሆን በአንደኛነት ጨርሳለች። ናይጄሪያ 12 ወርቅ፣ 8 የብር እና 7 የነሐስ በጥቅሉ 27 ሜዳሊያዎችን ነው ያገኘችው። ደቡብ አፍሪቃ 9 ወርቅ፣ 7 ብር እንዲሁም 7 ነሐስ በጥቅሉ 23 ሜዳሊያዎችን በማግኘት ኹለተኛ ሆና አጠናቃለች። ኢትዮጵያ በ6 የወርቅ፣ በ12 የብር እና በ10 የነሐስ በአጠቃላይ 28 ሜዳዮችን በመሰብሰብ በአራተኛነት ጨርሳለች። ግብፅ በ13፣ ኬንያ በ12 ሜዳሊያዎች አራተኛ እና አምስተኛ ሆነው አጠናቀዋል።

የፓሪስ ግማሽ ማራቶን ባለድል ኢትዮጵያውያት

የፓሪስ ግማሽ ማራቶን ባለድል ኢትዮጵያውያት

ከፈረንሳይ ፓሪስ ወጣ ባለ ቦታ ላይ ትናንት በተከናወነው የፓሪስ ግማሽ ማራቶን ውድድርም ኢትዮጵያውያት ተፎካካሪዎች ከአንደኛ እስከ ሦስተኛ ተከታትለው በመግባት በውድድሩ የበላይነታቸውን አስመስክረዋል። የብርጓል መለሠ በአንደኛነት በ1:09:54 በመግባት የወርቅ ሜዳሊያ ተሸላሚ ሆናለች። በግማሽ ማራቶኑ ሩጫ ኹለተኛ የወጣችው አፈራ ጎድፋይ በፓሪስ ስትወዳደር ለመጀመሪያ ጊዜ ነው። የገባችበት ሠዓት 1:10:08 ነው። በቀለች ዳባ በበኩሏ በፓሪስ ግማሽ ማራቶን ስትወዳደር ለመጀመሪያ ጊዜ ነው። ሆኖም ግን የድሉ ተቋዳሽ ለመሆን ችላለች። ውድድሩን በ 1:10:13 ሦስተኛ በመውጣት የነሀስ ሜዳይ ተሸላሚ ሆናለች።

ነገ እና ከነገ በስተያ አራት ቡድኖች ለሻምፒዮንስ ሊግ የእግር ኳስ ፍልሚያ ይገናኛሉ። ነገ የፖርቺጊዙ ፖርቶ ከስዊዘርላንዱ ባዝል፤ እንዲሁም የስፔኑ ሪያል ማድሪድ ከጀርመኑ ሻልከ ጋር ይጋጠማሉ። ፖርቶ ስዊዘርላንድ ውስጥ ከእዚህ ቀደም ባከናወነው ግጥሚያ አንድ እኩል ነው የተለያየው። ሪያል ማድሪድ ሻልካን ቀደም ሲል 2 ለ0 አሸንፎ ነው ነገ በደጋፊው ፊት የሚገጥመው። በዓለማችን እጅግ ውድ ዋጋ የተከፈለባቸው ተጨዋቾችን ያሰባሰበው ሪያል ማድሪድ አሠልጣኝ ካርሎ አንቼሎቲ የተጠበቀውን ያህል ውጤት አላመጡም በሚል ተደጋጋሚ ነቀፌታ ሲሰነዘርባቸው ነበር።

ሻምፒዮንስ ሊግ ሻልከ ከሪያል ማድሪድ

ሻምፒዮንስ ሊግ ሻልከ ከሪያል ማድሪድ

ሪያል ማድሪድ ከስፔን ዋንጫ ውድድር በጎረቤት አትሌቲኮ መባረሩ እና በእዚሁ የከተማው ተቀናቃንኝ ቡድን በላሊጋው ፍልሚያ 4 ለባዶ መረታቱ እጎአ ከ1947 ወዲህ ታላቁ ሽንፈት ሆኖ ተመዝግቧል። ከትናንት በስትያ ሪያል ማድሪድ በአትሌቲኮ ቢልባዎ 1 ለዜሮ መረታቱ በእርግጥም ደጋፊዎቹን አስቆጥቷል። ከእዚህ ቀደም ማድሪድ ከቪላሪያል ጋር አንድ እኩል በመውጣት ነጥብ በመጣሉ ደጋፊዎች አሠልጣኝ ካርሎ አንቼሎቲ ላይ ለመጀመሪያ ጊዜ በተቃውሞ ሲጮኹ ተደምጠዋል።

ከነገ በስትያ ኹለት የሻምፒዮንስ ሊግ ግጥሚያዎች ይከናወናሉ። እጎአ በ2012 የሻምፒዮንስ ሊግ ባለድል የነበረው ቸልሲ ቀደም ሲል ከፓሪስ ሴንጀርሜይን ጋር 1 እኩል በመለያየት ነጥብ ተጋርቶ ወጥቷል። በሜዳው ነው የሚጫወተው። በ2013 ዋንጫውን በእጁ ያስገባው ኃያሉ ባየር ሙይንሽን በበኩሉ ከሻክታር ዶኒዬትስክ ጋር ዩክሬይን ለቪቭ ውስጥ ያደረጉት ጨዋታ ግብ አልባ ሆኖ ቢጠናቀቅም እዚህ ጀርመን በደጋፊው ፊት የሚጫወት ከመሆኑ አንፃር ዕድሉ ሰፊ ነው ተብሏል። የሚሆነው ግን አይታወቅም።

የኮሎኙ ማርሴል ሪሴ በአይንትራኅት ፍራንክፉርት ላይ ግብ አስቆጥሮ ደስታውን ሲገልጥ

የኮሎኙ ማርሴል ሪሴ በአይንትራኅት ፍራንክፉርት ላይ ግብ አስቆጥሮ ደስታውን ሲገልጥ

በጀርመን ቡንደስ ሊጋ ትናንት ኮሎኝ ባልተጠበቀ ሁናቴ አይንትራኅት ፍራንክፉርትን 4 ለ2 አሸንፏል። በባየር ሌቨርኩሰን 3 ለባዶ የተረታው ፓዴርቦርን በደረጃ ሠንጠረዡ ቁልቁል ወርዶ 16ኛ ላይ ነው የሚገኘው። ከትናት በስትያ ኃያሉ ባየር ሙይንሽን ሐኖቨርን 3 ለ 1 አሸንፏል። ከሽንፈት አዙሪት ወጣ የተባለው ቦሩስያ ዶርትሙንድ ከሐምቡርግ ጋር ያለምንም ግብ ተለያይቷል።

በእዚህም መሠረት የደረጃ ሠንጠረዡን ባየር ሙይንሽን በ61 ነጥብ ይመራል፤ የቡድኑ የቁርጥ ቀን ልጅ አርየን ሮበን 17 ኳሶችን ከመረብ በማሳረፍ በአይንትራኅት ፍራንክፉርቱ አሌክሳንደር ማየር በአንድ ግብ በመበለጥ ኹለተኛ ኮከብ ግብ አግቢነቱን እንደያዘ ነው። በቡንደስ ሊጋ ግጥሚያ በአጭር ጊዜ ውስጥ 100 ኳሶችን ከመረብ በማሳረፍ አሪየን ሮበን አዲስ ክብር ወሰን አስመዝግቧል። ቮልፍስቡርግ በ50 ነጥብ በደረጃ ሠንጠረዡ ኹለተኛ ነው። 41 ነጥብ ያለው ቦሩስያ ሞይንሽንግላድባኅ ሦስተኛ ደረጃ ይዟል።

ሻምፒዮንስ ሊግ ቸልሲ ከፓሪስ ሴንጄርሜይን

ሻምፒዮንስ ሊግ ቸልሲ ከፓሪስ ሴንጄርሜይን

በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ ከትናት በስትያ ቶትንሐም ኪው ፒ አርን 2 ለ አንድ አሸንፏል። ሌሎቹ ጨዋታዎች በአጠቃላይ ማክሰኞ እና ረቡዕ ነው የተከናወኑት። ዋነኞቹ ተፎካካሪዎች አሸናፊ ለመሆን ችለዋል። በእዚህም መሠረት የደረጃ ሠንጠረዡን ቸልሲ በ63 ነጥብ እየመራ ይገኛል። ቸልሲ ከነገ በስተያ ለሻምፒዮንስ ሊግ ፍልሚያ ከፈረንሣዩ ፓሪስ ሳንጀርሜይን ቡድን ጋር የሚገናኘው በፕሬሚየር ሊጉ ያለውን የበላይነት ስንቅ በማድረግ ነው። ማንቸስተር ሲቲ በፕሬሚየር ሊጉ ላይ በ58 ነጥብ በኹለተኛነት ይገኛል። አርሰናል በአንድ ነጥብ ልዩነት ከስሩ የሚገኘው 54 ነጥብ ይዞ ደረጃው ሦስተኛ ነው። ማንቸስተር ዩናይትድ በ53 ነጥብ አራተኛ እንዲሁም ከቅርብ ጊዜ አንስቶ በተደጋጋሚ ያሸነፈው ሊቨርፑል በ51 ነጥብ ከዋነኞቹ ተፎካካሪ ቡድኖች ተርታ በመሰለፍ 5ኛ ነው።

በስፔን ላሊጋ ትናንት እሁድ ባርሴሎና ራዮ ቫልካኖን ስድስት ለ አንድ አሸንፏል። አርጀንቲናዊው ሊዮኔል ሜሲ ሶስት ግቦች ባስቆጠረበት የካምፕ ኑ ጨዋታ ሊዊስ ሱአሬዝ ሁለት ተከላካዩ ጄራርድ ፒኬ አንድ አክለው ባርሴሎናን የስፔን ላሊጋን በቀዳሚነት እንዲመራ አስችለውታል። በእለቱ በተካሄዱ ሌሎች ጨዋታዎች አትሌሊኮ ማድሪድ እና ቫሌንሲያ አንድ እኩል አቻ ሲለያዩ ሪያል ሶሲዳድ ኤስፓኞልን አንድ ለባዶ፤ ቪላሪያል ሴልታ ቪጎን አራት ለአንድ አሸንፈዋል።

ክርስቲያኖ ሮናልዶ እና ሊዮኔል ሜሲ

ክርስቲያኖ ሮናልዶ እና ሊዮኔል ሜሲ

የስፔን ላሊጋን ባርሴሎና በ62 ነጥቦች በአንደኝነት ሲመራ ባለፉት ሁለት ጨዋታዎች ግብ ማስቆጠር የተሳነው እና ቅዳሜ እለት በአትሌቲክ ክለብ አንድ ለባዶ የተሸነፈው ሪያል ማድሪድ በ61 ነጥቦች ሁለተኛ፤ አትሌቲኮ ማድሪድ በሶስተኛ ደረጃ ላይ ይገኛሉ።

በእለተ እሁድ 24ኛ የላሊጋ ሃትሪክ ያስመዘገበው ሊዮኔል ሜሲ የኮከብ ጎል አግቢነቱን ከሪያል ማድሪዱ ክርስቲያኖ ሮናልዶ ጋር በ30 ጎሎች ተስተካክሏል።

በጣልያን ሴሪ አ ትናንት እሁድ በተካሄዱ ጨዋታዎች ቼይቮ ከሮማ ባዶ ለባዶ ፤ ኢንተር ሚላን ከናፖሊ ሁለት ለሁለት ተለያይተዋል። የደረጃ ሰንጠረዡን ጁቬንቱስ በ58 ነጥብ በቀዳሚነት ሲመራ ሮማ በስምንት ዝቅ ብሎ በ50 ነጥብ ሁለተኛ ናፖሊ በ46 ሶስኛ ደረጃ ላይ ይገኛል።

ላንስ አርምስትሮንግ

ላንስ አርምስትሮንግ

በዓለም አቀፍ የብስክሌት ማኅበር የተቋቋመው አጣሪ ኮሚሽን ባለሥልጣናት የቀድሞው የቱር ደ ፍራንስ የብስክሌት ሽቅድምድም ባለድል ላንስ አርምስትሮንግ የአደንዛዥ ዕጽ ተጠቅመሀል ክስን ባለሥልጣናቱ አድበስብሰዋል ሲል ተቸ። እጎአ ከ1999 እስከ 2005 ድረስ በተደረጉ የቱር ደ ፍሯንስ ብስክሌት ሽቅድምድም ለ7 ጊዜያት ያሸነፈው የ43 ዓመቱ ላንስ አርምስትሮንግ በውድድር ወቅት አደንዛዥ ዕጽ መጠቀሙን እንዳመነ ተዘግቧል።

የዓለማችን የአጭር ርቀት ባለድል ዩሴን ቦልት በ200 ሜትር ርቀት የሩጫ ውድድር የፊታችን ሐምሌ 2 ቀን የሚወዳደር መሆኑን ዛሬ አስታወቀ። ይኽ ውድድር የዓለማችን የአጭር ርቀት ኮከብ ዘንድሮ በአውሮጳውያኑ የበጋ ወራት የሚያከናውነው ኹለተኛው ጠንካራ ውድድር ነው ተብሏል።

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ዓርያም ተክሌ

Audios and videos on the topic