የስፖርት ዘገባ፤ የካቲት 23 ቀን፣ 2007 ዓ.ም. | ስፖርት | DW | 02.03.2015
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ስፖርት

የስፖርት ዘገባ፤ የካቲት 23 ቀን፣ 2007 ዓ.ም.

እጎአ በ2022 በረሃማዋ ቓታር ውስጥ ሊከናወን ዕቅድ የተያዘለት የዓለም ዋንጫ ውድድር ከወዲሁ ውዝግብ አስነስቷል። የአውሮጳ ቀዳሚ ሊጎች ያከናወኑዋቸውን ጨዋታዎች ከእንግሊዝ ተነስተን ጀርመን፣ ብሎም ስፔን እና ጣሊያን ደርሰን እንቃኛለን።

በአፍሪቃ የአሸናፊዎች አሸናፊ የእግር ኳስ የቡድኖች ውድድር ቅዱስ ጊዮርጊስ ትናንት ባህርዳር ከተማ ውስጥ የአልጄሪያውን ኤል ኦይላም ቡድን ለማሸነፍ ችሏል። ሆኖም ወደ ቀጣዩ ዙር ለማለፍ አልተሳካለትም። ምክንያት? አንድ የስፖርት ጋዜጠኛ ያብራራልናል። እዛው ባህር ዳር ከተማ ውስጥ ለአፍሪቃ የኮንፌዴሬሽን ጨዋታ ደደቢት ከትናንት በስትያ የኮትዲቯሩን ሲሸልስ ቡድን በመርታት 16 ቡድኖች ወደሚገኙበት ቀጣዩ ዙር ለማለፍ ተሳክቶለታል።

በጀርመን ቡንደስ ሊጋ ኃያሉ ባየር ሙይንሽን የኮሎኝ ቡድንን 4 ለ1 የረታበት ጨዋታ ተደምሮ አሪየን ሮበን በርካታ ግቦችን ከመረብ በማሳረፍ በቀዳሚነት እየገሰገሰ ነው። አሌክሳንደር ማየር እግር በእግር እየተከተለው ነው። የእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ፣ የጀርመን ቡንደስ ሊጋ ፣ የስፔን ላሊጋ እና የጣሊያን ሴሪኣ ውጤቶችን ወደ በኋላ ላይ እንቃኛለን።

በሳምንቱ መገባደጃ ባህር ዳር ከተማ ውስጥ የተከናወኑ ኹለት ዓበይት ጨዋታዎችን ቀዳሚ አድርገናል። ትናንት ባህር ዳር ስታዲየም ውስጥ ቅዱስ ጊዮርጊስ የአልጄሪያውን ኤል ኦይልማ ቡድን 2 ለ 1፣ ደደቢት ደግሞ የኮትዲቯሩን ሲሸልስ ቡድን 2 ለ 0 ማሸነፍ ችለዋል። በባህር ዳር ስታዲየም ታድሞ የነበረው የሐትሪክ ጋዜጣ ባለቤት እና ዋና አዘጋጅ ይሳቅ በላይ የጨዋታውን ይዘት እና ድባብ እንዲህ ይገልጣል።

ቅዱስ ጊዮርጊስ ቀደም ሲል በኤል ኦይልማ ቡድን አልጄሪያ ውስጥ 1 ለዜሮ በመሸነፉ ምንም እንኳን ትናንት 2 ለ1 አሸናፊ ቢሆንም ኤል ኦይልማ ከሀገሩ ውጪ ግብ በማስቆጠሩ ማለፍ ችሏል። ደደቢት ከቅዳሜው የ2 ለ0 ድል ባሻገር በመጀሪያው ጨዋታ ሲሸልስን ከሀገር ውጪ 3 ለ 2 በማሸነፉ አጠቃላይ ውጤቱ 5 ለ2 ነው። የቡድኑ አሠልጣኝ ዮሐንስ ሣህሌ ቡድናቸው በማለፉ ደስታቸውን ገልጠዋል።

ደደቢት ቡድን በአፍሪቃ ኮንፌዴሬሽን ውድድር ላይ ኢትዮጵያን ወክሎ የሚጫወት ቡድን ሲሆን፤ በመቀጠል የሚጋጠመው ከናይጀሪያው ዎሪ ዎልፍስ ቡድን ጋር ነው።

ወደ አውሮጳ የእግር ኳስ ቡድኖች ውጤት ነው የምናልፈው። በመጀመሪያ የጀርመኑ ቡንደስ ሊጋ። በቡንደስ ሊጋው ኃያሉ ባየር ሙይንሽን ኮሎኝን 4 ለ1 በመርታት የቡንደስ ሊጋውን ዋንጫ ለመውሰድ እየገሰገሰ ነው። የዓርብ እለቱ ድል ለባየር ሙይንሽን 115ኛው ሆኖ ተመዝግቧል። ባየር ሙይንሽን በ58 ነጥብ ቡንደስ ሊጋውን እየመራ ይገኛል።

ዎልፍስቡርግ ትናንት ቬርደር ብሬመንን 5 ለ3 በማሸነፉ በ50 ነጥብ ይከተላል። ትናንት ፓዴርቦርንን 2 ለዜሮ የረታው ቦሩስያ ሞይንሽንግላድባኅ 40 ነጥብ ይዞ ይሰልሳል። ፓዴርቦርን በትናንቱ ሽንፈት የደረጃ ሠንጠረዡ ጠርዝ ላይ 16ኛ ነው። ቅዳሜ እለት ሻልካን 3 ለ 0 መሸኘት የቻለው ቦሩስያ ዶርትሙንድ በተደጋጋሚ ማሸነፍ በመቻሉ አሁን ወደ 10ኛ ደረጃ ከፍ ብሏል። ቡንደስሊጋውን የባየር ሙይንሽኑ አሪየን ሮበን በ17 ግቦች ይመራል። የአይንትራኅት ፍራንክፉርቱ አሌክሳንደር ማየር 16 ኳሶችን ከመረብ በማሳረፍ በኹለተኛነት ይከተላል።

በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ ትናንት ሊቨርፑል በደረጃ ሠንጠረዡ ኹለተኛ የሆነው ማንቸስተር ሲቲን 2 ለ1 ለመርታት ችሏል። አርሰናል ኤቨርተንን 2 ለባዶ አሸንፏል።

ዋይኔ ሩኒ

ዋይኔ ሩኒ

ከትናንት በስትያ ማንቸስተር ዩናይትድ ሰንደርላንድን 2 ለምንም ሸኝቷል። በዚህ ጨዋታ ለማንቸስተር ዩናይትድ ኹለቱን ግቦች ከመረብ ያሳረፈው ዋይኔ ሩኒ አንጌል ዲማሪያ መሻሻል እያሳየ ነው ብሏል። «አጌል ዲ ማሪያ በማንቸስተር ዩናይትድ ውስጥ አስቸጋሪ ጊዜውን ተወጥቶ ብቃቱን ማሳየት የቻለ ተጨዋች ነው » ሲል ዋይኒ ሩኒ ተናግሯል። የ27 ዓመቱ አርጀንቲናዊ አጥቂ ዲ ማሪያ 92 ሚሊዮን ዶላር የተከፈለውን ያህል ብቃቱን ማሳየት አልቻለም እየተባለ ሲተች ነበር። ዲማሪያ በ19 የፕሬሚየር ሊግ ጨዋታዎች ግብ ማስቆጠር የቻለው ለ3 ጊዜ ብቻ ነው። ሆኖም የቡድኑ የቁርጥ ቀን ልጅ የሆነው ዋይኔ ሩኒ ኹለቱን ግቦች በማስቆጠሩ ማንቸስተር ዩናይትድ በ50 ነጥብ የደረጃ ሠንጠረዡ ላይ በ4ናነት ይገኛል። ቸልሲ አንድ ተስተካካይ ጨዋታ እየቀረው በ60 ነጥብ እየመራ ነው። ማንቸስተር ሲቲ በ55 ነጥብ ይከተላል። አርሰናል 51 ነጥብ ሰብስቦ 3ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል።

በስፔን ላሊጋ ትናንት ሪያል ማድሪድ ከቪላሪያል ጋር አንድ እኩል ተለያይቷል። ሆኖም የደረጃ ሠንጠረዡን በ61 ነጥብ እየመራ ይገኛል። ቫሌንሺያ ሪያል ሶሴዳድን 2 ለባዶ ሲረታ ሴቪላ ከአትሌቲኮ ማድሪድ ጋር ያለምንም ግብ ተለያይቷል። በዚህም መሠረት ባርሴሎና ከሪያል ማድሪድ በ2 ነጥብ ብቻ ዝቅ ብሎ በ59 ነጥብ በደረጃ ሠንጠረዡ ኹለተኛ ነው። አትሌቲኮ ማድሪድ 54 ነጥብ ይዞ ይሰልሳል።

የሪያል ማድሪድ ደጋፊዎች

የሪያል ማድሪድ ደጋፊዎች

በጣሊያን ሴሪኣ ጁቬንቱስ 57 ነጥብ ይዞ የደረጃ ሠንጠረዡን በአንደኛነት ይመራል። ሮማ በ48 ይከተላል። ናፖሊ 45 ነጥብ አለው፤ ሦስተኛ ነው።

እጎአ በ2022 ቓታር ውስጥ በክረምት ወቅት ይኪያሄዳል የተባለው የዓለም ዋንጫ የእግር ኳስ ፍልሚያ መርሃ-ግብር ከወዲሁ ውዝግብ አስነስቷል። እጅግ ከፍተኛ ወበቅና ሙቀት በሚኖርበት የበጋ ወቅት ውድድሩን ቓታር ውስጥ ማከናወን ከባድ በመሆኑ በክረምት ለማከናወን ተወስኗል። የእግር ኳስ ማኅበር ዓለም አቀፍ ፌዴሬሽን በእንግሊዘኛ ምኅፃሩ FIFA የየአህጉራቱ የእግር ኳስ ማኅበራት፣ እንዲሁም የገንዘብ አቅማቸው ከፍተኛ የሆኑ ቡድኖች እና የእግር ኳስ ማኅበራት ተወካዮች በተገኙበት ዶሃ ላይ ውሳኔ ሲሰጥ በርካቶች ተቃውሞ አሰምተዋል። የአውሮጳ ቡድን ማኅበር ምክትል ሊቀመንበር እና የባየር ሙይንሽን ቡድን ተቀዳሚ ምክትል ሊቀመንበር የቀድሞ የጀርመን ብሔራዊ ቡድን ተጨዋቹ ካር ሐይንስ ሩሜኒገ የቓታሩ የዓለም ዋንጫ ውድድር በርካታ የአውሮጳ እግር ኳስ ቡድኖች ፉክክር በሚያደርጉበት ወቅት ሊኪያሄድ መታቀዱን ችግር ሊፈጥር እንደሚችል ጠቁሟል።

ካርል ሐይንስ ሩሜኒገ

ካርል ሐይንስ ሩሜኒገ

«የዛሬው ውሳኔ በድንገት የመጣ አይደለም፤ ቀደም ሲል ዳር ዳር ሲባልበት የነበረ ነው። ለእግር ኳስ አፍቃሪያን ግን ይህ አዲሱ የ2022ቱ የዓለም እግር ኳስ መርሃ-ግብር አስቸጋሪ እና ፈታኝ ይሆናል። የዓለም ዋንጫ መርሃ ግብሩ ሲቀየስ ዓለም አቀፍ ቡድኖችን ግንዛቤ ያስገባ ሁሉንም ሊያግባባ የሚችል መሆን ነበረበት። የአውሮጳ ቡድኖች እና ማኅበራት ክረምት ወቅት ላይ ለሚካሄደው የ2022ቱ የዓለም እግር ኳስ ዋጋ መክፈል አይጠበቅባቸውም። ቡድኖቹ ላይ ለሚከሰተው ጉዳት ተገቢ የሆነ ካሳ ለመክፈል የምር ዝግጁነቱን እንጠብቃለን።»

አትሌቲክስ፤ ትናንትበደቡብ አሜሪካዋ ፖርቶ ሪኮ ዋና ከተማ ሳን ዩአን በተካሄደ የ10 ኪሎ ሜትር የሩጫ ውድድር ኢትዮጵያዊቷ በላይነሽ ኦልጂራ አሸናፊ ሆናለች። ንፋሳማውን ውድድር በ31 ደቂቃ ከ 57 ሰከንድ ያሸነፈችው በላይነሽ ሁለተኛ እና ሶስተኛ ደረጃ ካጠናቀቁት ኬንያውያኑ ሲንቲያ ሊሞ እና ቤትሲ ሳይና ከፍተኛ ፍክክር ገጥሟት እንደነበር የአለም አቀፉ አትሌቲክስ ፌዴሬሽኖች ማህበር በድረ-ገጹ አስፍሯል። ሌላዋ ኢትዮጵያዊት ስንታየሁ እጅጉ ውድድሩን በአራተኛነት አጠናቃለች።

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ነጋሽ መሐመድ

Audios and videos on the topic