የስፖርት ዘገባ፤ የካቲት 16 ቀን፣ 2007 ዓ.ም. | ስፖርት | DW | 23.02.2015
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ስፖርት

የስፖርት ዘገባ፤ የካቲት 16 ቀን፣ 2007 ዓ.ም.

የኢትዮጵያውያን ድል እየተደጋገመ ነው። በወንድም በሴትም ኢትዮጵያውያን አትሌቶች አሸናፊ በመሆን በጃፓን የተኪያሄደውን የቶኪዮ ማራቶን ተቆጣጥረውታል። በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ የእግር ኳስ ፍልሚያ ትናንት ሊቨርፑል ሳውዝሐምፕተን ላይ ድል በመቀዳጀት ወደ ዋነኞቹ ተፎካካሪዎች ተርታ ተጠግቷል።

በጀርመን ቡንደስ ሊጋ ኃያሉ ባየርን ሙይንሽን እንደለመደው ኃያል በትሩን ፓዴርቦርን የተባለው ቡድን ላይ በማሳረፍ አይቀጡ ቅጣት ቀጥቶታል። በስፔን ላሊጋ መሪው ሪያል ማድሪድ ኤልሼን በማሸነፍ ከባርሴሎና በአራት ነጥብ ርቋል።በጣሊያን ሴሪኣ ሮማ ነጥብ በመጣሉ ከመሪው ጁቬንቱስ በዘጠኝ ነጥብ ርቀት ለመገደብ ተገዷል። የሻምፒዮንስ ሊግ የጥሎ ማለፍ ጨዋታዎች ማክሰኞች የካቲት 17 ቀን፣ 2007 ዓ.ም.እና ረቡዕ ይካሄዳሉ።

ወደ ሻምፒዮንስ ሊግ እና የአውሮፓ ሊጎች የእግር ኳስ ግጥሚያ ውጤቶች ከመሻገራችን በፊት ቀዳሚ ያደረግነው የአትሌቲክስ ዜናን ነው። ጃፓን ውስጥ ትናንት በተከናወነው የማራቶን ሩጫ ዓለም አቀፍ ውድድር ኢትዮጵያውያን በሴቶችም በወንዶችም አሸናፊ በመሆን የወርቅ ሜዳዮችን አጥልቀዋል። በወንዶች የሩጫ ውድድር አሸናፊ የሆነው እንደሻው ንጉሴሲሆን፤ ሩጫውን በአንደኛነት ለማጠናቀቅ የፈጀበት ጊዜ ሁለት ሰዓት ከስድስት ደቂቃ ነው። እንዳሸው ያስመዘገበው የትናንቱ ውጤት ከነሐሴ 16 ቀን እስከ ነሐሴ 24 2007 ዓም ቻይና ውስጥ በሚከናወነው የቤጂንግ ዓለም አቀፍ የአሸናፊዎች አሸናፊ የሩጫ ውድድር ላይ ለመሳተፍ ዕድሉን እንዳሰፋለት አሶሲየትድ ፕሬስ ዘግቧል።

በትናንቱ የጃፓን ማራቶን የወንዶች የሩጫ ፉክክር ሁለት ሰዓት ከስድስት ደቂቃ ከ33 ሰከንድ በመግባት 2ኛ የወጣው የለንደን ኦሎምፒክ አሸናፊ የነበረው ዩጋንዳዊው ስቴፈን ኪብሮች ነው። ኬንያዊው ዲክሰን ቹምባ ከዩጋንዳዊው በሦስት ሠከንዶች ብቻ ለጥቂት ተቀድሞ 3ኛ ወጥቷል።

በቶኪዮ ማራቶን በሴቶች አሸናፊ የሆነችው ኢትዮጵያዊቷ ብርሃኔ ዲባባ ውድድሩን ለማጠናቀቅ የፈጀባት ጊዜ 2 ሰዓት ከ23 ደቂቃ ከ14 ሰከንድ ነው። ኬንያዊቷ ሄላህ ኪፕሮፕ በ2 ሰዓት ከ24ደቂቃ ከ03ሰከንድ ውድድሯን በማጠናቀቅ 2ኛ ወጥታለች። በሦስተኛነት ያጠናቀቀችው ኢትዮጵያዊቷ ቲኪ ገላና ከኬኒያዊቷ ጋር ልዩነቷ 23 ሠከንድ ነበር። ከወንዶች አሸናፊ የሆነው እንደሻው « በነበረው ቀዝቃዛ አየር እና መጠነኛ ካፊያ ምክንያት ውድድሩ ትንሽ አድካሚ ነበር፤ ሆኖም ድንቅ ውጤት በመሆኑ በብሔራዊ ቡድኑ ውስጥ ቦታ እንዲኖረኝ ይፈቅድልኛል» ማለቱን የፈረንሣይ ዜና አገልግሎትዘግቧል። በቶኪዮው የማራቶን ዉድድር 36 000 የሚደርሱ ሯጮች ተካፍለዋል። የቶኪዮ ማራቶን ከዓለም ታላላቅ ስድስት የማራቶን ውድድሮች አንዱ ነው።

የጁዶ ትግል

የጁዶ ትግል

እዚህ ጀርመን ውስጥ ባሳለፍነው ዓርብ እና ቅዳሜ ዕለት በተከናወኑ የጁዶ እና ጂጂትሱ ፍልሚያዎች ደግሞ ኹለት ኢትዮጵያውያን ወጣቶች ተሳታፊ ሆነዋል። ወጣቶቹ ያሬድ ንጉሤ እና ሐና ኔሪ ይባላሉ። በኢትዮጵያ የጁዶ እና ጂጂትሱ ስፖርት እንዲያድግ ጥረት የሚያደርጉት ዶክተር ፀጋዬ ደግነህ ወጣቶቹ ጀርመን ለውድድር እንዴት እንደመጡ እና ተሳትፎዋቸው ምን ይመስል እንደነበር ገልፀውልናል።

ዶክተር ፀጋዬ ደግነህ በኢትዮጵያ አዲስ አበባን ጨምሮ በተለያዩ ከተሞች የጁዶ እና ጂጂትሱ ስፖርት ማኅበራት እንደሚገኙ ሆኖም በኦሎምፒክ ደረጃ ለመወዳደር ፌፌሬሽን ለመመስረት ጥረት እየተደረገ መሆኑን ጠቅሰዋል። ስፖርቱ ከሚፈልገው ልዩ አልባሳት አንስቶ፣ የመለማመጃ ምንጣፎች እና ሌሎች ተግዳሮቶች እንዳሉበት ፤ እንደውም ዱስልዶርፍ ውስጥ የተለያዩ ቡድኖች ያገለገሉ የጁዶ እና ጂጂትሱ ትጥቆችን እያመጡ እንደሰጧቸው ተናግረዋል። ወጣቶቹ በዓለም አቀፍ ደረጃ እንዲወዳደሩ የተደረገው ጥረት የሚበረታታ ሲሆን ወደፊት ስፖርቱ የበለጠ አድጎ ኢትዮጵያ በዚህ የስፖርት ዘርፍ በዓለም ተወዳዳሪ እንድትሆን የሚመለከታቸው አካላት በአጠቃላይ የበኩላቸውን ድጋፍ ሊያደርጉ ይገባል እንላለን።

ጁዶ፤ አትሌት ያሬድ እና ሐና

ጁዶ፤ አትሌት ያሬድ እና ሐና

የአውሮጳ ታላላቅ ቡድኖች ውጤቶችን እናቀርብላችኋለን። በመጀመሪያ ከእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ የትናንትና ግጥሚያ ነው የምንጀምረው። ትናንት ቶትንሐም ከዌስትሐም እንዲሁም ኤቨርተን ከሌስተር ሲቲ ጋር ኹለት እኩል በመውጣት ነጥብ ተጋርተዋል። ሊቨርፑል ሳውዝሐምፕተንን ኹለት ለባዶ ሲረታ፤ ማንቸስተር ሲቲ ኒውካስል ዩናይትድን 5 ለምንም አንኮታኩቷል። በዚህም መሠረት ከትናንት በስትያ ከበርንሌይ ጋር አንድ እኩል በመውጣት ነጥብ ከጣለው መሪው ቸልሲ ጋር ያለውን የነጥብ ልዩነት ወደ አምስት ዝቅ አድርጎታል። ቸልሲ 60 ነጥብ ነው ያለው።

አርሰናል ከትናንት በስትያ ክሪስታል ፓላስን 2 ለ1 በመርታቱ 48 ነጥብ ይዞ ከማንቸስተር ሲቲ በ7 ነጥብ ተበልጦ በደረጃ ሠንጠረዡ ሦስተኛ ነው። ከትናንት በስትያ በስዋንሲ ሲቲ 2 ለ1 የተሸነፈው ማንቸስተር ዩናይትድ 47 ነጥብ ሰብስቦ አራተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል። ሳውዝሀምፕተን ትናንት በሊቨርፑል 2 ለዜሮ በመሸነፉ 46 ነጥብ ላይ ሲወሰን፤ ደረጃው 5ኛ ነው። ሊቨርፑል 45 ነጥብ ይዞ ስድስተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል።

በጀርመን ቡንደስሊጋ ትናንት ዎልፍስቡርግ ሔርታ ቤርሊንን 2 ለ1 ረትቷል። ቅዳሜ ዕለት ሻልካ እና ብሬመን እንዲሁም ፍራይቡርግ ከሆፈንሃይም አንድ እኩል አቻ ተለያይተዋል። ማይንትስ አይንትራኅት ፍራንክፉርትን 3 ለ1 አሸንፏል። ኃያሉ ባየር ሙይንሽን ፓዴርቦርንን 6 ለዜሮ በሆነ ሽንፈት እንደማይሆን አድርጎታል።ባየር ሌቨርኩሰን እና አውስቡርግ 2 እኩል ሲለያዩ፤ ኮሎኝ ከሐኖቨር እንዲሁም ሐምቡርግ ከሞይንሽንግላድባኅ ጋር አንድ እኩል ተለያይተዋል።

የደረጃ ሠንጠረዡን አሁን ባየር ሙይንሽን በ55 ነጥብ እየመራ ይገኛል። ዎልፍስቡርግ በ47 ነጥብ እንዲሁምሞይንሽን ግላድባኅ በ37 ነጥብ ኹለተኛ እና ሦስተኛ ናቸው።

በስፔን ላሊጋ ትናንት መሪው ሪያል ማድሪድ ኤልሼን 2 ለባዶ ባሸነፈበት ጨዋታ ሰሞኑን ግብ የራቀው የነበረው ክሪስቲያኖ ሮናልዶ አንድ ግብ በማስቆጠር ኹለተኛዋንም አመቻችቷል። አትሌቲኮ ቢልባዎ ራዮ ቫሌካኖን እንዲሁም ቪላሪያል ኤስ ዲ አይበርን 1 ለምንም አሸንፈዋል። ሪያል ሶሴዳድ እና ሴቪላ ባደጉት ግብግብ ሴቪላ 4 ለ3 ተሸንፏል። የደረጃ ሠንጠረዡን ሪያል ማድሪድ በ60 ነጥብ ይመራል። ባርሴሎና በ56 ይከተላል። አትሌቲኮ ማድሪድ በ53 ይሰልሳል።

በጣሊያን ሴሪ ኣ ደግሞ ትናንት ሚላን ሴሴናን 2 ለዜሮ፣ ኢምፖሊ ቺዬቮ ቬሮናን 3 ለባዶ እንዲሁም ላትሲዮ ፓሌርሞን 2 ለ1 አሸንፈዋል። ሔላስ ቬሮና ከሮማ፣ ፊዮሬንቲና ከቶሪኖ አንድ እኩል አቻ በመውጣት ነጥብ ተጋርተዋል። 57 ነጥብ የሰበሰበው ጁቬንቱስ ሴሪኣውን እየመራ ይገኛል። ሮማ በ48 ነጥብ ይከተላል። ናፖሊ 42 ነጥብ ይዞ ሦስተኛ ነው።

የሻምፒዮንስ ሊግ የጥሎ ማለፍ ግጥሚያ ነገ እና ከነገ ወዲያም ይከናወናል። በነገው ውድድር የእንግሊዙ ማንቸስተር ዩናይትድ ከስፔኑ ባርሴሎና ጋር ይፋለማል። የጀርመኑ ቦሩስያ ዶርትሙንድም የጣሊያኑ ጁቬንቱስን ይገጥማል። ከነገ በስትያ ደግሞ የእንግሊዙ አርሰናል ከፈረንሳዩ ሞናኮ፣ እንዲሁም የጀርመኑ ባየር ሌቨርኩሰን ከስፔኑ አትሌቲኮ ማድሪድ ጋር ተቀጣጥረዋል። ውድድሩ የጥሎ ማለፍ በመሆኑ እጅግ በጉጉት ይጠበቃል።

ከኢትዮጵያዊ አባት እና ከቼክ ሪፐብሊካዊት እናት የተወለደው የእግር ኳስ ተጫዋቹ ቴዎዶር ገብረ ሥላሴ በጀርመኑ ቬርደር ብሬመን የእግር ኳስ ቡድን ውስጥ የነበረው ውል ለኹለት ተጨማሪ ዓመታት መራዘሙ ተነገረ። ቴዎዶር ከብሬመን ቡድን ጋር የገባው ውል የሚያበቃው ከአንድ ዓመት ግድም በኋላ ነበር። ቴዎዶር ውሉን ካደሰ በኋላ ለጋዜጠኞች በሰጠው ቃለምልልስ «እዚህ የሚሰማን እንደቤቴ ነው፤ ይሄ ደግሞ ገና ወደ ቡድኑ ከመጣሁበት ጊዜ አንስቶ የሚሰማኝ ስሜት ነው» ብሏል። ቴዎዶር ገብረ ሥላሴ ተወልዶ ያደገው ጀርመንን በስተምሥራቅ በምታዋስናት ቼክ ሪፐብሊክ ውስጥ ሲሆን፤ ወደ ብሬመን የተዘዋወረው እጎአ በ2012 ዓም ከቼኩ ስሎቫን ሊቤሬች ቡድን ነው። ቴዎዶር በቡንደስ ሊጋው ለ69 ጊዜ የተሰለፈ ሲሆን፤ 5 ግቦችን አስቆጥሯል። ከአውሮጳ ክረምት ወዲህ ዳግም በተጀመረው የቡድንደስ ሊጋ ፉክክር ቬርደር ብሬመን እስካሁን ሳይሸነፍ በስምንተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል። ቬርደር ብሬመን የፊታችን ቅዳሜ ከሻልካ ጋር ይጋጠማል።

ስዊድን ውስጥ እየተኪያሄደ በሚገኘው ሰሜናዊ የበረዶ መንሸራተት ፉክክር ላይ የጀርመን ቡድን ትናት ሦስተኛውን የወርቅ ሜዳይ አገኘ። ከከፍታማ የበረዶ ግግር በፍጥነት ቁልቁል በረዶ ላይ በመንሸራተት እና ዓየር ላይ በመንሳፈፍ የቡድን ውድድር ጀርመናውያኑ ትናንት ያገኙት ወርቅ በዚህ ዘርፍ ከ28 ዓመታት ወዲህ የመጀመሪያው ሆኖ ተመዝግቧል። የአንድ ጊዜ የዓለም ባለድሉ ዮሐንስ ራይጄክ፣ የኦሎሚክ አሸናፊው ኤሪክ ፍሬንስል፣ ቲኖ ኤደልማን እና ፋቢያን ሪይስለ ተራ በተራ ያደረጉት ውድድር ተደምሮ ነበር የጀርመን ቡድን ወርቅ ሊያገኝ የቻለው።

የናይጄሪያ እግር ኳስ ቡድን የመላው አፍሪቃ እግር ኳስ ጨዋታዎች የዘንድሮውድድሩን በተሳካ ሁናቴ ጀመረ። የናይጄሪያ ቡድን የሣምንቱ ማሳረጊያ ላይ ባደረገው ግጥሚያ የጋቦን አቻውን 4 ለ1 በሆነ ሰፊ ልዩነት ነው ያሸነፈው። የኢትዮጵያ ቡድን ሱዳንን ድሬዳዋ ውስጥ በሜዳው እና በደጋፊው ፊት አስተናግዶ 2 ለ1 ተሸንፏል። ቡሩንዲ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ኮንጎን ኪንሻሳ ውስጥ 1 ለባዶ ስታሸንፍ፤ ዩጋንዳ እና ሞዛምቢክ ያለምንም ግብ አቻ ተለያይተዋል። የኢትዮጵያ ቡድን ብቸናዋን ግብ ያስቆጠረው በባከነ ሠዓት በተገኘ ፍፁም ቅጣት ምት ነው። ግቧን ያስቆጠረውም ዳዋ ሁቴሳ ነው። ለሱዳን ቡድን በመጀመሪያው አጋማሽ ሁለቱን ግቦች ያስቆጠሩት ዓሊ ዖስማን እና አታር ኧል ጣሂር ናቸው። ግብጽ የፊታችን እሁድ ኬንያን ታስተናግዳለች።

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ኂሩት መለሰ

Audios and videos on the topic